Saturday, 24 November 2018 12:08

4 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊዎች በገዛ ፈቃዳቸው ከሥራ ለቀቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

አራት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማኔጅመንት አባላት በገዛ ፍቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ባንኩ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫው አረጋግጧል፡፡
በራሳቸው ፍቃድ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት በባንክ ዋና የብድር መኮንን አቶ አባይ መሃሪ፣ የባንኩ የሰው ሃብት መኮንን አቶ ሰይፉ ቦጋለ፤ የባንኩ ዋና የኦፕሬሽን መኮንን አቶ አታክልቲ ኪዳነማሪያም እንዲሁም የባንኩ የጠቅላላ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሠረት አስፋው መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ቀደም ብሎም የባንኩ ዋና የቢዝነስ መኮንን የነበሩት አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ በራሣቸው ፍቃድ ከስራ መልቀቃቸውን ባንኩ አስታውቋል፡፡
በራሳቸው ፍቃድ ከስራ የለቀቁት የማኔጅመንት አባላት አቶ አባይና አቶ አታክልቲ ኪዳነማሪያም እያንዳንዳቸው ከ30 አመት በላይ በባንኩ ያገለገሉ ሲሆን አቶ ሰይፈ ቦጋለና ወ/ሮ መሠረት አስፋው ደግሞ ለ18 አመት መስራታቸው በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
የማኔጅመንት አባላቱ ለምን በፍቃዳቸው ከስራ እንደለቀቁ ያለው ነገር የለም፡፡ አባላቱ የለቀቁበትን ምክንያት ራሳቸው ተጠይቀው ቢገልፁ የተሻለ መሆኑን የባንኩ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ በልሁ ታከለ አስረድተዋል።
የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን ያስገቡትም ሁሉም በተለያየ ቀን መሆኑን አቶ በልሁ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ 

Read 9412 times