Saturday, 24 November 2018 12:12

“ክልሎች የፌደራል መንግስቱን አካሄድ የመቃወም መብት አላቸው” ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ከህግ ማስከበር እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የክልል መንግስታት የፌደራል መንግስቱን አካሄድ መቃወማቸው መብት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አስታወቁ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከትላንት በስቲያ በፓርላማ ተገኝተው የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ሹመት በም/ቤቱ አባላት ባፀደቁበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ሰሞኑን የፌደራል መንግስት በሙስናና የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ፣ የክልል መንግስታት መቃወማቸው መብታቸው መሆኑን ጠቁመው ይሄን መብታቸውን መቃወምና አለመቀበል ስህተት መሆኑን አስረግጠው ገልፀዋል - ለውጡ የመጣው ሰዎች ያልመሰላቸውንና ያላመኑትን በግልጽ እንዲቃወሙ መሆኑን በመጠቆም፡፡
“ክልሎች ማንኛውንም የፌደራል መንግስት ውሳኔ እጃቸውን አውጥተው አጨብጭበው እንዲቀበሉ አንጠብቅም” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ያልመሰላቸውን የመቃወም፤ መቃወማቸውንም በሚዲያ በይፋ የመግለፅ መብት አላቸው” ብለዋል፡፡
“የኛን ንግግር የሚደግም ሳይሆን ትክክል አይደለም ብሎ ሲያስብ ተቃውሞውን በይፋ መግለፅ የሚችል ክልል፣ ምክር ቤትና የምክር ቤት አባል ነው የምንፈልገው” ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ “በዚህ መሃል ግን ባለን ስልጣን ልክ ህግን ማስከበር ግዴታችን ነው፤ እየተናገርን ነገር ግን ህግን የማናስከብር ከሆነ ነው ግጭት የሚፈጠረው በማለት አብራርተዋል፡፡
“ባለፉት 30 ዓመታት የተፈፀሙ ወንጀሎችን በሙሉ ቆጥረን ሰዎችን ወደ ህግ እናቅርብ ቢባል ያለን እስር ቤት አይበቃም፤ ራሱን የቻለ ከተማ መገንባት ያስፈልገናል” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ከጥቃቅን ነገሮች አንስቶ ያልተነካካ የለም፤ አሁን በዋና ዋና ጉዳይ ላይ የተኩረን ነው እርምጃ እየወሰድን ያለነው፤ ቀሪዎቹ በቅርቡ በተቋቋመው የእርቅና የብሔራዊ የመግባባት ኮሚሽን በኩል የሚታዩ ይሆናል” ብለዋል፡፡
የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ በሰብአዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ በፌደራል መንግስቱ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ፖለቲካዊ መልክ እየያዘ መምጣቱንና የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ያለው መሆኑን በመግለፅ፤ የፌደራል መንግስቱን አካሄድ እንደማይቀበሉት መናገራቸው ይታወሳል፡፡


Read 10290 times