Saturday, 24 November 2018 12:13

“የመጀመሪያ ግባችን ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(22 votes)

በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የመንግሥታቸው የመጀመሪያው ግብ ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ሲሆን በምርጫው ማሸነፍ ሁለተኛ ግባቸው እንደሆነ ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
 “ዲሞክራሲንና የዲሞክራሲ ባህልን ለመገንባት የጀመርነውን ለውጥ ተቋማዊ መሠረት ማስያዝ ይገባል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዲሞክራሲ ዋነኛው ተቋም ምርጫ ቦርድ በገለልተኛ ሰዎች መደራጀቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
“በመንግሥትና በህዝብ መካከል ያለው ውል በነፃ ሊመሠረት የሚችለው ዲሞክራሲያዊ የምርጫ ተቋም ሲኖር ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ዲሞክራሲን ለመገንባት ቀጣዩ ምርጫ ትልቁ ምሰሶ ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም፤ “ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድን እንደ መጀመሪያ ግብ ወስደን፣ ማሸነፍን ሁለተኛ ግብ እናደርጋለን፣ ማሸነፍን የመጀመሪያ ግብ ካደረግን ምርጫውን ፍፁም ዲሞክራሲያዊ የማድረግ ቁርጠኝነት አይኖረንም” ብለዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲን የተራበ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ሁላችንም ቀጣዩ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን በጋራ መቆም ይኖርብናል” ብለዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ተሿሚዋን ወ/ት ብርቱካንን እጩ አድርጐ ለማቅረብም ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከፖለቲካ ምሁራን ጋር ምክክር ማድረጋቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወ/ሪት ብርቱካን ለመንግስትም ቢሆን እጅ የማይሠጡ፣ ለፍትህ፣ ለህግ የበላይነትና ለዲሞክራሲ ዋጋ ለመክፈል የማይፈሩ፤ ይሄንንም በተግባር ያስመሰከሩ ጠንካራ ሴት መሆናቸውን ገልፀዋል -  ተሿሚዋ በኢትዮጵያ ህዝብ የሚታመኑ መሆናቸውንም በመጠቆም፡፡
በወ/ት ብርቱካን እጩነት ላይ በተለይ የዜግነታቸውንና ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ነፃ የመሆናቸውን ጉዳይ አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፤ ጠ/ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያም ተሿሚዋ ከፓርቲ አባልነት ከጥቂት ዓመታት በፊት መልቀቃቸውንና  በአሁኑ ወቅት በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆናቸው መረጋገጡን ገልፀዋል፡፡
ዜግነታቸውን አስመልክቶም ሲመልሱ፤ “ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ ነው፤ ተረጋግጧል” ብለዋል፡፡ “ዜግነትን በተመለከተ በየተቋማቱ እየተሾሙ ባሉ ግለሰቦች ላይ በሚነሳ ጥያቄ ለሃገራቸው ማገልገል የሚችሉ ሰዎችን ማራቅ እንደማይገባ የገለፁት ዶ/ር ዐቢይ፤ የውጭ ዜግነታቸውን ሠርዘው ሀገራቸውን ለማገልገል የሚመጡትን መቀበል አለብን ብለዋል - የማይፈቀደው ጥምር ዜግነት  መሆኑን በመጠቆም።
አዲሷ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው፤ በፖለቲካ ፓርቲ አመራርነት ውስጥ በማለፋቸው ምርጫ ቦርድ ያለበትን ተቋማዊ እጥረት እንደሚያውቁ ጠቁመው፤ ያላቸው ተሞክሮና ልምድ ተቋሙን ለመምራት አቅም እንደሚፈጥርላቸው ገልፀዋል፡፡
“በፓርቲ ውስጥ የነበረኝ ቆይታ መልካም ልምድ ነው፤ እስከ ዛሬ ትክክለኛ ምርጫ እንዳይኖረን ያደረጉ ችግሮች ምንድን ናቸው? ያሉት የህግ ክፍተቶችስ? በፓርቲዎች በኩል ያለው ችግር ምንድን ነው? የሚሉትን ጉዳዮች ለማየት እድል ሰጥቶኛል” ብለዋል ወ/ሪት ብርቱካን፡፡
ወገንተኛ ሆነው ፖለቲካን መከወን ቢፈልጉ በፓርቲ ውስጥ ሆነው መስራት ይችሉ እንደነበር የተናገሩት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ “ወገንተኝነትን ይዤ የአንድን ፓርቲ ጥቅም ለማስከበር ይሄን ተቋም ከተጠቀምኩበት ከማንም በላይ ራሴን ይቅር የምል ሰው አይደለሁም” ብለዋል፡፡ በህይወታቸው ሁሉ ዋጋ ሲከፍሉ የኖሩት እውነተኛ ዲሞክራሲ ለማምጣት መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሪት ብርቱካን፤ “እኔ የፖለቲካ ሽቀጣ ለማድረግ ትራፊ ህይወት የለኝም”፤ ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ወደ ፖለቲካ እንዲገቡ ያስገደዳቸው ጉዳይም የህግ የበላይነት አለመስፈን መሆኑን የገለፁት ተሿሟዋ፤ ከፓርቲ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ነፃ ካደረጉ 10 አመት እንደሆናቸው ጠቁመው፤ እንዴት ነው ወደ ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት የሠፈነበት ስርአት መሻገር ያለብን የሚለውን ሳብላላ ነው የቆየሁት” ብለዋል፡፡
በቅድሚያ የሚያከናውኑትን ጉዳይ ሲያብራሩም፤ የተጀመረውን የምርጫ ህግ ማሻሻያ ከፍፃሜ ማድረስና ቦርዱን በገለልተኝነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችን መመልመል መሆኑን ገልፀው፤ በፍጥነት ለቀጣዩ ምርጫ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
በ97 ምርጫ የአንጋፋው ተቃዋሚ ፓርቲ “ቅንጅት” ተ/ምክትል ሊቀመንበር፣ በኋላም ራሳቸው ያቋቋሙት “አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ” ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት የህግ ባለሙያዋ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ሁለት ጊዜ ለእስር መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን በዚያው ባሰራቸው የኢህአዴግ መንግስት መሾማቸው ለአንዳንዶች ግርምት መፍጠሩ አልቀረም፡፡
“ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በመመረጧ ደስታውን አልችለውም” ያሉት የመላ ኢትዮጵያውያን አንድት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ፤ “ለዲሞክራሲ፣ ለሰላማዊ ትግልና ለህግ የበላይነት የተገረፈች፣ የተሰቃየችና የታሰረች ጠንካራ ሴት ነች” ብለዋል፡፡
“ወ/ሪት ብርቱካን ማንም ቢመርጣት የምትታገለው ለዲሞክራሲ ማበብ ነው” ያሉት ዶ/ር በዛብህ፤ ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ ግን ተነጋግረው ቀጣዩን የምርጫ ቦርድ አደረጃጀትና አዋጪውን የምርጫ ህግና ስርአት ማበጀት አለባቸው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ሊከናወን የሚገባው ዋነኛ ተግባር ምርጫ ቦርድን እንደገና ማዋቀር ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለዚህም ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ በጉዳዩ ላይ ተደራድረው ወደ አንድ ስምምነት መምጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉአላዊነት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ በበኩላቸው፤ ወ/ሪት ብርቱካን ጠንካራ ስብዕና ያላት መሆኑን ገልፀው፤ “በዋናነት ለተሿሚዋ የስራ አመቺነት፤ የምርጫ ቦርድ አወቃቀር በድርድር መስተካከል አለበት” ብለዋል፡፡
አዲሷ ተሿሚ ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ የሚገባውም የምርጫ ቦርድ መዋቅርን ሙሉ ለሙሉ መቀየር መሆን እንዳለበት አቶ ጎይቶም አስገንዝበዋል፡፡
የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደም የሌሎቹን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ “ወ/ት ብርቱካን ለቦታው የሚመጥኑ የመርህ ሰው ናቸው፤ የተደረገው ሹመትም በህብረተሰቡ ዘንድ ምርጫ ቦርድ እየተቀየረ ነው የሚል ግንዛቤን የሚፈጥር መልካም ጅምር ነው” ብለዋል፡፡
ሆኖም ወ/ሪት ብርቱካን የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊገጥማቸው እንደሚችል ዶ/ር ጫኔ ይናገራሉ። ለዚያም የሚያስችል ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ተግባራትን ሲዘረዝሩም፤ የምርጫ ህጉን በፍጥነት ማሻሻል፣ የሰው ኃይል አመዳደብና አደረጃጀቱን ማሻሻል የሚሉትን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ምርጫዎችም ከመጪው ብሔራዊ  ምርጫ ጋር እኩል መካሄድ እንዳለባቸው፤ ዶ/ር ጫኔ ገልፀዋል፡፡ ወ/ት ብርቱካን በምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት የመሾም ጉዳይ በማህበራዊ ሚዲያዎችም መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
በፌስቡክ ደፋር ፖለቲካዊ ትንታኔዎችንና አስተያየቶችን በመስጠት የሚታወቀው የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመ፤ “እነሆ! ፍትህና ምርጫ በሃቀኛ ሰዎች እጅ ላይ ወደቀ” ሲል ጽፏል፡፡ “ወ/ት ብርቱካን የፍትህን ትርጉም፣ የምርጫ ፋይዳን ከማንም በላይ ጠንቅቃ ታውቃለች” ብሏል ስዩም፡፡  ፖለቲከኛውና መምህሩ አቶ ወንደሰን ተሾመ በበኩሉ፤ “የአገረ ኢትዮጵያ ከፍታ እውን የሚሆንበትን መንገድ የጠረገ እርምጃ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እየተወሰደ በመሆኑ የልብ ኩራት ተሰምቶናል” ሲል አስተያየቱን አስፍሯል፡፡ ታሪክ እንደ አባይ ወንዝ በአይኔ ስር ሲያልፍ አየሁ” ያሉት ደግሞ በጦማሪነታቸው የሚታወቁት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ናቸው፡፡
“ለእውነት መቆም በሞገስ አቁሟታል፣ የህይወት ጉዞዋ ምሳሌ ነው” ያለው ወጣቱ ፖለቲከኛና  ጦማሪ ዮናታን ተስፋዬ፤ “እንደ ዳኛ አምባገነንነትን ተጋፍጣለች፤ እንደ ነፃነት ታጋይ ለነፃነት ትልቁን ዋጋ ከፍላለች፤ እንደ የእውቀት ሰው የላቀ እውቀት ባለቤት ናት፤ እንደ ሰው አስደናቂ ቅን ነፍስ ያላት ነች” ሲል በአድናቆት ጽፏል፡፡
ቢቢሲን ጨምሮ አሶሴትድ ፕሬስና ሌሎች አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን “የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩ ግለሰብ የኢትዮጵያን ምርጫ ቦርድ ሊመሩ ነው” በማለት የዘገቡ ሲሆን፤ ወ/ት ብርቲካን በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የሚታመኑ ግለሰብ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ማን ናቸው?
አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ተወለዱ። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚሁ አዲስ አበባ ተማሩ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ተከታተሉ፡፡ በህግ ተመረቁ፡፡ ዳኛ ሆነው ሰሩ፡፡ ዳኛ ሆነው ሲሰሩ የገጠማቸውን የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ተቃውመው ስራቸውን አቆሙ፡፡ በኋላም በፖለቲካ ታግሎ ኢህአዴግን ለመለወጥ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኑ፡፡ በአመራርነትም አገልግለዋል። ራሳቸው የመሰረቱት የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲም ሊቀመንበርም ነበሩ፡፡ በፖለቲካ ትግላቸው ወቅት ሁለት ጊዜ ታስረዋል፡፡ ከአራት አመታት ያላነሰ እድሜያቸውንም በእስር አሳልፈዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ከታሰሩበት ሲፈቱ ወደ አሜሪካ በስደት አቀኑ፡፡ በአሜሪካ በሃርቫርድ ኬኔዲ ስኩል ኦፍ ገቨርናንስ በህዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡ በዚያው በአሜሪካን ሃገር “ናሽናል ኢንዶውመንትስ ፎር ዲሞክራሲ” በተባለ ድርጅት በተመራማሪነት ሰርተዋል፡፡ የመንግስት ጥያቄ ተከትሎ በቅርቡ ወደአገራቸው ተመልሰው መጡ፡፡ ከትናንት በስቲያም በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አቅራቢነትና በም/ቤቱ አጽዳቂነት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስነውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲመሩ ተሾሙ፡፡

Read 11896 times