Print this page
Sunday, 25 November 2018 00:00

የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች አሿሿም አሁንም ሊጤን ይገባዋል!!

Written by  ከአብዱራህማን አህመዲን (የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)


ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት “ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይስ ከፍተኛ የዝርፊያ ተቋማት?” በሚል ርእስ አንድ መጣጥፍ አዘጋጅቼ ነበር፡፡ የዚያ ጽሁፍ ዋነኛ ትኩረት በዩኒቨርስቲዎቻችን እየተፈጸመ ባለው “ምሁራዊ ምዝበራ” ላይ ቢሆንም፤ ምዝበራውን ስለሚዘውሩት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች አሿሿምም ጥቂት ነጥቦችን ጠቅሼ ነበር፡፡
ያንን ጽሑፍ ባዘጋጀሁበት “ዘመነ ኃ/ማሪያም”፣ ኢህአዴግ ጆሮውን በጥጥ ደፍኖ ስለነበር፣ አይሰማንም ወይም በዘመኑ ቋንቋ “ባላየ” ያልፈን ነበር፡፡ ዛሬ የ“መደመር”ን መፈክር (Motto) በማስተጋባት ላይ የሚገኘው “ቄሮ ተከል ኢህአዴግ” የሚሰማ ስለመሆኑ መቶ በመቶ እርግጠኞች ባንሆንም፤ በአሳሳቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጩኸት ማሰማታችንን እንቀጥላለን፡፡
በዚሁ አግባብ ነው ባለፈው ሰሞን በዚችው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ስለ አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ አንዳንድ ነጥቦችን ለማመላከት የሞከርኩት፡፡ በዚህኛው መጣጥፍ ደግሞ ስለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች አሿሿም የምለው ነገር ስላለኝ ነው ዳግም በአዲስ አድማስ በኩል ብቅ ያልኩት፡፡
ብዙውን ጊዜ በፖለቲካና በኢኮኖሚው ጉዳይ ላይ ስናተኩር፣ የዚህ ሁሉ መሰረት የሆነውን ማህበራዊ ጉዳይ እየዘነጋነው እንደሆነ ያሳሰበኝ አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር ወንድሜ ነው፡፡ ባህል፣ ትምህርትና ጤናን የመሳሰሉት ማህበራዊ ጉዳዮቻችን ጤናማ ካልሆኑ፤ ጤናማ ፖለቲካም ሆነ ጤናማ ኢኮኖሚ ሊኖረንም፤ ልንገነባም አንችልም፡፡
ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስለሚመሩበት ሁኔታ በአዋጅ ቁጥር 650/2001 በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ ስለ መንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት አሿሿምም በዚሁ አዋጅ ላይ ተገልጿል፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 16 ላይ ስለ አካዳሚያዊ ነጻነት በሦስት ንዑስ አንቀፆች ሰፍሯል። ማንኛውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም፣ በተቋሙ ተልእኮና በአለም አቀፍ መልካም ልምድ መሰረት፣ አካዳሚያዊ ነጻነት እንደሚኖረውም ተጠቅሷል፡፡ በአንቀጽ 17 ላይ ደግሞ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነፃነት ምን መሆን እንዳለበት ተገልጿል። በአንቀጽ 52 ላይ የመንግስት የትምህርት ተቋም ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት አሿሿምና የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ምን መምሰል እንዳለበት በዝርዝር ተቀምጧል፡፡
አዋጁ ለዓመታት የወረቀት ላይ ነብር ሆኖ መዝለቁ አሌ የማይባል ሀቅ ነው፡፡ የአዋጁን መንፈስ በተጻረረ መልኩ ዩኒቨርሲቲዎች ብቃትን ሳይሆን ፖለቲካዊና ዘውጋዊ ማንነትን ባማከለ መልኩ በተሾሙ የገዥው ፓርቲ እንደራሴዎች እንዲመሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይህ የተሳሳተ አሰራር በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መተቸቱን ተከትሎ፣ የትምሕርት ሚኒስቴር ከሁለት ዓመት በፊት “በመንግሥት የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት የአመራሮችና አስተዳዳሪዎችን ምርጫ ሹመት/ምደባ ለመደንገግ የወጣ መመሪያ 002/2009” የተሰኘ ደንብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ፤ የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት አሿሿም የአፈጻጸም መመሪያ፣ የአዋጁን መንፈስ ተከትሎ የተዘጋጀ ነው ወይ? የሚል ነው፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው በዩኒቨርሲቲ ለረዥም ጊዜ ያስተማሩ ወዳጆቼ እንደነገሩኝ ከሆነ፣ በደንቡ ውስጥ በመስፈርትነት የተቀመጡት አንዳንዶቹ መመዘኛዎች ከአዋጁ መንፈስ ጋር የሚቃረኑ ናቸው። የአዋጁ መንፈስ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ማህበረሰብ ውስጥ ለዩኒቨርስቲዎቹ የላቀ አመራር (Strategic Learship) ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎችን በመምረጥ መሾም ነው፡፡ ይህ የአዋጁ መንፈስ ግን በደንቡ አተገባበር የተጣሰ መሆኑ ይስተዋላል፡፡
ለአብነት ያክል “የዩኒቨርሲቲ አመራሮች አመራረጥና አሰያየም” የሚል ርዕስ ያለው የዚሁ ደምብ አንቀጽ 6/3/ለ፤ ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደር እጩን የስራ ልምድ አስመልክቶ “በከፍተኛ ትምሕርት ወይም ከዚህ ውጭ ባለ መስክ በከፍተኛ አመራርነት የተረጋገጠ የሥራ ልምድ ያለው...” ይላል::
እንዲህ ያለው “ሊበሏት ያሰቧትን ዥግራ ዶሮ ናት ይሏታል” ዓይነት አካሄድ፣ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነት እየሰሩ ያሉ ካድሬዎችን ወደ ፕሬዝዳንትነት እናሳድግ ከማለት የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርኳቸው የዩኒቨርስቲ ሊቃውንት፤ “በዩኒቨርስቲው ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አዳዲስ አመራሮች ወደፊት እንዲመጡ ከተፈለገ በዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ኃላፊነት ስልጣን ሳይሰጣቸው በየዩኒቨርስቲው የሚያስተምሩ ልምድም እውቀትም ያላቸው ወጣትና አንጋፋ ተመራማሪዎች የመወዳደር እድል ሊሰጣቸው ይገባል። እነዚህ ሙስናም ሌብነትም ያልተጠናወታቸው፣ ራሳቸውን በማስተማርና በመመራመር ሥራ የጠመዱ፣ እድል ከተሰጣቸው አዳዲስ አሰራር ማመንጨት የሚችሉ፣ የእውቀትና የልምድ ልሂቃን በውድድር ወደ አመራርነት ቢመጡ ዩኒቨርስቲዎችን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር እድል ሊፈጠር ይችላል” ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ በአሁኑ ወቅት የዲያስፖራው ማኅበረሰብና መንግሥት ጥሩ መቀራረብ መፍጠራቸው ይስተዋላል፡፡ በውጪ ሀገር ደግሞ በርካታ ዓለም አቀፍ እውቅናን ያተረፉ ኢትዮጵያዊ ምሁራን አሉ፡፡ እነዚህ ምሁራንና ሊቃውንት በየሰባት ዓመቱ የሚሰጣቸውን እረፍት (Sabbatical Leave) ተጠቅመው  ወደ ሀገር ቤት በመምጣት፣ እውቀታቸውንና ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትና በከፍተኛ ትምሕርት አስተዳደርና አመራር ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት የድርሻቸውን የሚወጡበት እድል ቢመቻች፣ በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ራሱን የቻለ  አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
በአንድ ወቅት መቀሌ ዩኒቨርስቲና አዳማ ዩኒቨርስቲ ከውጪ ሀገር “ፈረንጅ” የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶችን ቀጥረው ሞክረውታል፡፡ የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት የቻሉ ግን አይመስለኝም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የአገሩን ሰርዶ ለአገሩ በሬ የሚለውን ብሂል ግምት ውስጥ ማስገባቱ አስፈላጊ ነው፡፡ አካታች መስፈርቶችን በማውጣት የራሳችንን ሰዎች ከአገር ውስጥም ከዲያስፖራም በባትሪ መፈለጉ ቅድሚያ ቢሰጠው ይሻላል ባይ ነኝ፡፡
ወደ ሌላ ተያያዥ ጉዳይ እንለፍ! የቀድሞው ትምህርት ሚኒስቴር (የአሁኑ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር) ቀደም ሲል ተዘፍቆበት ከነበረው የአሰራር ስህተት የወጣ አይመስልም፡፡ ለዚህ አባባል ማሳያ የሚሆኑኝ ሰሞኑን እጄ ውስጥ የገቡ ሁለት ደብዳቤዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም ደብዳቤዎች የተፈረሙት በአንድ ኃላፊ - በሚንስትሯ በዶ/ር ሂሩት ወልደማሪያም ነው፡፡ ሁለቱም ደብዳቤዎች የተጻፉት በተመሳሳይ ቀን - ጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ነው፡፡
አንደኛው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡- “በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን የአመራር ምልመላ ቅጥር ሹመት መመሪያ ወጥቶ እየተተገበረ መሆኑ ይታወቃል። በቅርቡ በተለያዩ አካላት እየቀረቡ ያሉትን የመመሪያውን ክፍተት በቅርብ አስተካክለን እስክንልክ ድረስ በሂደት ላይ ያሉትን ጨምሮ በመመሪያ ቁጥር 02/2009 መሰረት የአመራር ምልመላ፣ መረጣና ሹመት ለጊዜው እንዲቆም የተወሰነ መሆኑን አስታውቃለሁ” ይላል፡፡
መመሪያው ላይ የታዩ ጉድለቶችን ለማረምና ለማስተካከል እንዲህ ያለ ደብዳቤ መጻፍ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ አይሆንም፡፡ እኔን የገረመኝ ግን ከላይ የተገለጸውን ሃሳብ ጽፈው የፈረሙት ሚኒስትር ራሳቸው በዚያው እለት (በሁለተኛው ደብዳቤ ላይ እንደተመለከተው) “ለ…… ከህዳር 1 ቀን 2011 ጀምሮ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙ መሆኑን [አስታውቃለሁ]” በማለት ጽፈው መፈረማቸው ነው፡፡
እንዲህ ያለው ሁኔታ ትምህርት ሚኒስቴር (የአሁኑ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር) ግልጽነት ከጎደለው፣ ለአንድ ጉዳይ ሁለት መስፈርት ከመጠቀም (Double Standard) የአሰራር አዙሪት አለመውጣቱን ብቻ ሳይሆን፤ ክብርት ሚንስትሯን ምን ነካቸው? የሚያሰኝ አስደማሚ ክስተት ነው፡፡ ሁለቱን ደብዳቤዎች በሁለቱ እጆቻቸው ጎን ለጎን አድርገው የፈረሟቸው ካልሆነ በስተቀር “… በሂደት ላይ ያሉትን ጨምሮ … የአመራር … ሹመት ለጊዜው እንዲቆም” ያለ ሰው፤ በዚያው እለት የሹመት ደብዳቤ መፈረም ምን ይባላል?
ቀደም ባሉት ጊዜያት የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች ይሾሙ የነበሩት የፖለቲካ ታማኝነትንና ዘርን መሰረት አድርጎ ነበር፡፡ ይህ አሿሿም ሙስናንና ዝርፊያን አላስቀረም፡፡ የትምህርት ጥራትን አላመጣም፡፡ የመምህራንን ችግር አልፈታም፡፡ ሕዝብንና ሀገርን ተጠቃሚ አላደረገም፡፡ በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል ይሰራበት የነበረው የአመራር ምልመላ፣ መረጣና ሹመት መመሪያ ቁጥር 002/2009 እንዲፈተሽ መደረጉ ጥሩ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች የምረጡኝ ዘመቻ አድርገው በቀጥተኛ የምርጫ ሂደት (Direct Democracy) በዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እንዲመረጡ ቢደረግ መልካም ነው፡፡
ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ሹመት ጋር በተያያዝ አንድ ነገር ልጨምር… ባለፉት 9 ዓመታት በዲላ ዩኒቨርሲቲ 6 ፕሬዚዳንቶችና ከግማሽ ደርዘን በላይ ምክትል ፕሬዝዳንቶች (የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ከግምት ዉስጥ ባላስገባ መልኩ የበቁ የነቁ ናቸው በሚል የዘር መስፈርት) በትምሕርት ሚኒስቴር አማካኝነት ተሹመዋል:: ሁሉንም ፕሬዚዳንቶች ማለት ይቻላል የብቃት ማነስና ብልሹ አሰራር ችግር ይታይባቸዋል በሚል ምክንያት  ከኃላፊነት ያሰናበታቸውም ይሄው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ነው፡፡ ይህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አሁንስ ከስህተቱ ተምሯል? አይመስለኝም!
የአንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የሹመት ዘመን ስድስት ዓመት እንደሆነ በአዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በዘጠኝ ዓመት 6 ሰው ተቀያየረ ማለት የእያንዳንዱ ፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመን ቢበዛ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ነው ማለት ነው፡፡ ፕሬዝዳንቶቹ ለምን ተቀያየሩ? ጥፋታቸው ምን ነበር?… በዝርዝር የሚታወቅ ነገር የለም! ግን… በዚህ የፕሬዝዳንት መቀያየር ውስጥ አንድ እውነት ፈልጎ ማግኘት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ይኸውም በእውቀትና በልምድ ሳይሆን በፖለቲካ አመለካከትና በዘር ማንነት ላይ የተመሰረተ ሹመት የተሻለ ውጤት ማስገኘት      አለመቻሉን ነው፡፡
ከዚህ በፊት ደጋግሜ እንዳልኩት፤ ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ተቋማት ናቸው ካልን፣ ሐጎስ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ፣ ገመቹ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ወለተ-ማሪያም የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ ፋጡማ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ ቲመርጋ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ፣… ፕሬዝዳንት ሆነው ቢሾሙ ምንድነው ችግሩ? ሌላው ቀርቶ ፈረንጅስ እየተሾመ አይደለም እንዴ? ሁሉን ነገር  በዘር፣ በጎሣ፣ ብሔር፣… መስፈርት መለካት ትርጉምም ፋይዳም  የለውም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በአካዳሚክ ተቋማት እንኳ ከእንዲህ ዓይነት ዘውግ ተኮር አሰራር ብንወጣ ምናለበት?!
ፌዴራሊዝማችን ሊጠነክርና አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ መፍጠር የምንችለው ከተለያዩ ብሔር/ብሔረሰቦች የተገኘን ኢትዮጵያውያን በጋራ የምንመራቸው የጋራ ተቋማትን እየገነባን ስንሄድ እንጂ በመንደርና በጎጥ ሚዛን እየተለካንና እየተሰፈርን በመሾማችን ሊሆን አይችልም፡፡ “ዶክተር” ትብለፅ ትግራይ ተወልዳ፣ ሐረር ከተማ ያሉ ወገኖችዋን ብታክም፤ ጎንደር የተወለደው “ኢንጅነር” አላምረው፣ ኦጋዴን ወርዶ ግድብ ሰርቶ መስኖ ቢዘረጋ፤ የአፋሩ አይዳሒስ ወደ ጋምቤላ÷ የጋምቤላው ዑጁሉ ወደ መቀሌ÷ የሶማሌው አብዱላሂ ወደ ሻሸመኔ÷ የአምቦው መገርሳ ወደ ደብረ ማርቆስ÷… ወዘተ. ሄደው በሙያቸው እንዲያገለግሉ ቢደረግ፣ ፌዴራሊዝማችን በደምና በአጥንት፤ በላብና በፍቅር ተሳስሮ፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ከመፍጠር ውጪ ምን ጉዳት ይከሰታል?
ስለ ዩኒቨርስቲ ቦርድ አባላት አመራረጥ አንዲት ነጥብ ልጨምር፡፡ ክብርት ሚኒስትሯ ደንቡ ላይ ክፍተቶች ይታያሉ ባሉት መሰረት ማሻሻያ የሚደረግ ከሆነ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚመሩ የአስተዳደር ቦርድ አባላት አመራረጥንም ቢመረምሩት መልካም ነው፡፡ እስከ አሁን ባለው አሰራር፣ በማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የሚቋቋሙ ቦርዶች አባላት የሚመረጡበት መስፈርት አንድም የገዢውን ፓርቲ የአባልነት መታወቂያ መያዝ አሊያም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን መሆን እንጂ እውቀት፣ ብቃትና ልምድን ማዕከል በማድረግ አልነበረም፡፡ የነበረው አሰራር፤ አካታች መስፈርትን መሰረት ካደረገ ምልመላና መረጣ ይልቅ በድርጅታዊ ኮታ የሚደረግ ምደባ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
የዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ቦርድ አባላትም በተመሳሳይ ሁኔታ በዚህ መልኩ እንዲመደቡ በመደረጉ ምክንያት ለሀገራቸው አስተዋጽዖ ማበርከት የሚችሉ፣ የኢህአዴግ አባል ያልሆኑ ዜጎች እድሉን የሚያገኙበት ሁኔታ ዝግ ነበር፡፡ ስለሆነም፤ ይህ ዓይነቱ ዘርንና የፓርቲ አባልነትን ብቻ መስፈርት ያደረገ የቦርድ አባላትን የመመደብ አሰራር ቀርቶ ለዩኒቨርሲቲው እድገት አስተዋጽዖ ለሚያደርጉ ዜጎች ሁሉ እድሉ ክፍት ሊሆን ይገባልና ክብርት ሚስትሯ ቢያስቡበት መልካም ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ… በአዋጁ አንቀጽ 52 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ “የዩኒቨርሲቲ እጩ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንቶች… ህገ መንግስቱንና የመንግስት ፖሊሲዎችን የተቀበሉ መሆን ይኖርባቸዋል” የሚለው መስፈርትም አስፈላጊነቱ አይታየኝም፡፡ ዩኒቨርስቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤የሣይንስና የምርምር ተቋማት እንጂ የካድሬ ማሰልጠኛ ባለመሆናቸው እንዲህ ያለው መስፈርት ጠቃሚ አይደለም፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ፣ የተለያየ እምነትና ህልም ያላቸው ወጣቶች የሳይንስ እውቀት የሚቀስሙባቸውና ምርምር የሚያደርጉባቸው የእውቀት መቅደሶች እንጂ የፓርቲ ርእዮተ-ዓለም የሚጋቱባቸው መድረኮች አይደሉም፡፡ እናም፤ የእውቀት መቅደሶችን የሚመሩ ሰዎች የሳይንስ እውቀት፣ የአስተዳደር ጥበብና ልምድ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ እንጂ ህገ መንግስትንና የመንግስት ፖሊሲን ከመቀበል አለመቀበል ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው አይገባም፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፣ ጽሁፌን ከመቋጨቴ በፊት፣ ህገ መንግስትንና የመንግስት ፖሊሲን ከመቀበል አለመቀበል ጋር የተያያዘ አንድ ነገር ላንሳ። ከላይ በጨረፍታ እንደገለጽኩት፤ በአንድ ወቅት የአዳማ ዩኒቨርሲቲና  የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች “ፈረንጆች” (የውጪ ሀገር ሰዎች) ነበሩ፡፡  ታዲያ እነዚያ “ፈረንጆች” ፕሬዝዳንት የሆኑት የኢትዮጵያን ህገ መንግስትና የመንግስትን ፖሊሲዎች አምነው ስለተቀበሉ ነበር? እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያ ህገ መንግስትም ሆነ የመንግስት ፖሊሲዎች ቀይ ይሁኑ ቢጫ የሚያውቋቸው አይመስለኝም፡፡ ይልቁኑ እነዚያን ፈረንጆች በፕሬዝዳንትነት እንዲሾሙ ያደረጋቸው ያላቸው አካዳሚያዊ እውቀትና ልምድ ነበር የሚል ግምት አለኝ፡፡ በዚሁ መንገድ ብንሄድስ?!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡






Read 2761 times