Saturday, 24 November 2018 12:24

“ዝንቧን እሽ ብያት አላውቅም”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንዲ ሩኒ የሚባል አሜሪካዊ ጋዜጠኛ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ ሀኪሞች ከሥልጠና በኋላ ወደ ሥራ በሚሰማሩበት ጊዜ መሀላ አላቸው፡፡ እናማ…  ጋዜጠኞችም ቢኖራቸው ጥሩ ነበር ይላል፡፡ ለምሳሌ…
“ጋዜጠኛ የሆንኩት የሰው ልጅ ሁሉንም መረጃ ካገኘ ዓለም የተሻለች ስፍራ ትሆናለች ብዬ  ነው፡፡” አሪፍ አይደል? በአሁኑ ጊዜ መረጃን በተመለከተ አንዱ ችግር ብዙ ሰው ሚዲያው አሁንም ትክክለኛና የተሟላ መረጃ እየሰጠን አይደለም ብለው ማመናቸው ነው፡፡ መረጃዎች ተበጣጥሰውና ተቆራርጠው ነው ሚደርሱን ይላል፡፡ እንዲህ ሆኖ ታዲያ ‘ያለፈ’ የሚባለውን አሁንም ‘አናት አናቱን’ ከማለት በቀር ምን የተሻለ ነገር አገኘን ይላል፡፡
በቀደም አንድ ሚኒባስ ላይ ሬድዮ ተከፍቶ በሆነ የአገራችን ክፍል ስለደረሱ ችግሮች ዜና እየተላለፈ ነበር፡፡ ጉዳቶቹ በቁጥር እየገለጹ ነበር፡፡ ይሄን ጊዜ ባለታክሲው “ውሸታሞች!” ይላል፡፡ እናማ…ለካስ ከስፍራው የመጡ ሰዎች ያወሩለትና በዜና እየሰማ የነበረው አልገጠሙለትም፡፡ እዚህ ላይ ለእሱ የነገሩት ሰዎች እውነተኛ መሆን ያለመሆናቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ባለታክሲው በሚዲያው መረጃ ላይ እምነት ማጣቱ ነው። በእርግጥ እሱ በጠቀሰው ቁጥርና በዜናው በተጠቀሰው ቁጥር መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ በሚዲያው እምነት መታጣቱ መልካም ምልክት አይደለም፡፡ የሚዲያ ሰዎቻችን መረጃዎችን በመግለጫና በኦፊሴላዊ ማብራሪያ ብቻ ሳይሆን ራሳቸው ማጣራት የሚችሉባቸውን ዘዴዎች ሊፈልጉ የሚገባበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
አንዲ ሩኒ ይቀጥላል…
“ለሰዎች መስማት የሚፈልጉትን ሳይሆን መስማት ያለባቸውን ለመንገር እጥራለሁ፡፡” ይህ የሚያዲችን አንድ ችግር ነው፡፡ ሰዉ ቢሰማ ይወደዋል በሚል መረጃዎች ግማሽ ልጩ፣ ግማሽ ጎፈሬ እየሆኑ ይመስላል፡፡ የምር ግን ነገሬ ብላችሁ እንደሁ “ሰዉ መስማት የሚፈልገው ይህን ነው፣” አይነት ነገር ጥቂት የማይባሉ ቃለ መጠይቆች ላይ የምናየው ነው፡፡ አለ አይደል… ተጠያቂውን ሰው በመረጃና በማስረጃ ሞግቶ የተሟላ ስእል ከማቅረብ ይልቅ ማፋጠጥ፣ ወይም አውጫጪኝ  አይነት የሚመስሉ ነገሮች አሉ፡፡
የምር ግን…አለ አይደል …ለምሳሌ ተጠያቂውን… “ሚስትዎን ይደበድባሉ ይባላል…፣” ሲባል ሰውየው.. “እንኳን ልደበድባት ዝንቧን እሽ ብያት አላውቅም፤” ሊል ይችላል፡፡ ይሄኔ እኛ ምን ብናደርግ ጥሩ ነው…ወደ ሌላው ጥያቄ እንሄዳለን። እንዴት ነው ነገሩ…የሚስትየዋስ ጉዳይ! መሆን የነበረበት… “ዝንቧን እሽ ብያት አላውቅም፤” ሲል.. “ለምሳሌ ባለን መረጃ መሠረት፤ በዚህ ቀን፣ በዚህ ሰዓት ሲደበድቧቸው ጎረቤት ደርሶ ነው ያስጣላቸው፣” አይነት ነገር አያስፈልግም እንዴ! አለበለዛ መጀመሪያም ሚስቱን እንደሚደበድብ የተጠየቀው ‘የማሳጣት’ አይነት ነገር ይመስላል። እናማ… መሞገት የሚቻለው፣ የተደበቀ እውነት ማውጣት የሚቻለው በ“ይባላል”ና በ“ይወራል” ብቻ ሳይሆን የሚዲያ ሰዎች አንድ፣ ሁለት እርምጃ ቀደም ብለው በሚይዟቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች ቢሆን አሪፍ ነው፡፡ ያኔ የህዝቡም እምነት የተሻለ ይሆናል ለማለት ነው፡፡
“ዝንቧን እሽ ብያት አላውቅም፤” ያለውን በማስረጃና በመረጃ መሞገት ነው እንጂ!
አንዲ ሩኒ ይቀጥላል…
“ለራሱ በሚጠቅም መልኩ ብቻ መረጃ የሚሰጠኝን ሁልጊዜም እጠራጠራለሁ፡፡”
ይቺ በጣም አሪፍ ናት… ለዚህ ነው መረጃዎች የአንድ ወገን ብቻ የሚሆኑት፡፡ አብዛኞቻችን ወይም ሁላችን  ሊባል በሚችል ሁኔታ ዋናው ጥረት ራስን መከላከል ላይ ነው እንጂ የራስን ጥፋት ማመን ላይ አይደለም፡፡ ብዙዎች ዜናዎች ላይ በመረጃ  ሰጪነት የሚጠቀሱ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ ወይም ተቋማት ‘ያኛው ግለሰብ’ ‘ያኛው ቡድን’ ‘ያኛው ተቋም’ ስላጠፋው ይናገራሉ እንጂ አራቱ ጣቶቻቸው ወደ እነሱ እንደሚያመለክቱ ይረሱታል፡፡ ጥፋቱ ወይም ጉድለቱ ላይ የእነሱን ድርሻ ሲናገሩ መስማት የተለመደ አይደለም። ለዚህም ነው የሚዲያ ሰዎች ከአንድ ወገን ብቻ የሚደርሳቸውን መረጃ የተሟላ ስለመሆኑ መጠራጠር ያለባቸው፡፡ “አተረማመሰው” ለመባባል ሚጢጢ ሰበቦች በምንፈለግበት በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት፤ መረጃዎች ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ ለአንዱ ብቻ መወገናቸው በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት በአጅጉ ይጎዳዋል፡፡   
“ዝንቧን እሽ ብያት አላውቅም፤” ያለውን በማስረጃና በመረጃ መሞገት ነው አንጂ!
ስሙኛማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ነው፡፡ ምንም እንኳን ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ከማሳሰብ አልፎ አስጊ የሚባል ደረጃ ላይ እየደረሰ ቢሆንም በመሀል ማንንማ ያልወገኑ፣ ባላቸው አቅም መረጃዎችን የተሟሉ ለማድረግ የሚጥሩ የሉም ማለት አይደለም፡፡
 የሚዲያ ሰዎች በሙያው ላይ ያሉት፣ በሌሎች ሙያዎች ላይ ካሉ ሰዎች በተሻለ ሀቀኛና የሙያ ስነምግባር አጥባቂ ሆነው አይደለም፡፡ እንደ ማንኛውም የአፕል ቅርጫት፤ እዚህኛው ቅርጫት ውስጥም የተበላሹ አፕሎች አሉ፡፡ ሰዋችን “ፈጥረው ነው እኮ የሚያወሩት፣” ማለት ከደጋገመ እምነቱ በእጅጉ እየተሸረሸረ ነው ማለት ነው። የምር ግን…ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም አልፎ፣ አልፎ ‘ፈጠራ’ እውነታውን የሚጫንባቸው ጊዜ አይኖርም አይባልም፡፡
“ዩ.ኤስ.ኤ ቱዴይ” ከአሜሪካ ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት አንዱ ነው፡፡ ጆን ኬሊ የሚባል የጦር ሜዳ ዘጋቢ ነበራቸው፡፡ ጆን ኬሊ በአገሪቱ ‘ስታር’ ወይም ኮከብ ከሚባሉት ዘጋቢዎች አንዱ ነው፡፡ ለዓመታት ከጦር ሜዳዎች የሚልካቸውን ዘገባዎች በርካቶች የሚከታተሏቸው ከመሆናቸው በላይ ሲያወድሱትም ኖረዋል፡፡ “ጋዜጠኛ ማለት እንዲህ ነው፣” አስብለውታል፡፡ በስተኋላ ግን በዘገባዎቹ ላይ ጥርጣሬ የገባቸው ክትትል ያደርጋሉ፣ ይሄኔ ነው ጉዱ የወጣው፡፡ ለእነኛ ሁሉ ዓመታት ይልካቸው የነበሩ ዘገባዎች እውነተኞች ሳይሆኑ በአመዛኙ ፈጠራዎች መሆናቸው ተደረሰበት፡፡
“ዝንቧን እሽ ብያት አላውቅም፤” ያለውን በማስረጃና በመረጃ መሞገት ነው አንጂ!
ይቺን ስሙኝማ… አንድ አሜሪካዊ የሬድዮ ጋዜጠኛን አንድ የመድሀኒት ፋብሪካ ማስታወቂያ እንዲሠራለት ይጠይቀዋል፡፡ ጋዜጠኛውም፤ “ለምን እኔን መረጣችሁኝ?” ይላቸዋል፡፡ ምን ቢሉት ጥሩ ነው… “ድምጽህ ሀይለኛ ራስ ምታት የያዘው ሰው ድምጽ ስለሚመሰል ነው” አሉትና አረፉት፡፡
የምር ግን እዚህ እኛም ዘንድ እኮ ይሄ የማስታወቂያ ነገር…አንዳንዱ ሀራራው እያዛጋው “ኸረ በለጬውን ቶሎ በሉ!” የሚል ይመስላል። አንዳን ከሚስቱ ጋር ተጣልቶ ቂሙን እኛ ላይ የሚወጣ ይመስላል፡፡ የምር ግን ምን መሰላችሁ…አንዳንዴ ‘ኖርማል’ በሚባል ድምጽ ቢነገሩ ይበልጥ ትርጉም መሰጠት የሚችሉ ነገሮችን የቴሌቪዥን ስክሪን በሚነቀንቅ ድምጽ ሲሉት የሆነ ሲኖትራክ ምናማን የስቴዲየም ግንብ ጥሶ የገባ ነው የሚመስሉት፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… አንዳንድ እህቶቻችን ደግሞ ትኩረታቸው የሚያስተዋውቀት ምርት ላይ ሳይሆን፣ የሆነ ሰው የኮረኮራቸውና “ተው እንጂ  ሼም ይያዝህ!” የሚሉት ሰው ያለ ነው የሚመስለው፡፡
አሁን ትልቅ ችግር ያለብን ነው የሚመስለው፤ በትክክለኛው መረጃና በዘገባ አቅራቢው  የግል አስተያየት መካከል ያለው መስመር ሲጠፋ በተደጋጋሚ እያየን መሆኑ ነው፡፡
እንደውም ሰዋችን አሁንም ቢሆን ቁጥራቸው እየተበራከተ ያሉት መገናኛ ብዙሀን፤ ልንሰማቸው የሚገቡንን መረጃዎች፣ ከእነ ሙሉ ማስረጃዎች እየነገሩን አይደለም እያለ ነው፡፡ አንድ የማይካደው ነገር በተለይ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ላይ ብዙ መልካም ነገሮች ያሉትን ያህል፤ ‘ዘ ሴም ኦልድ ሰቶሪ’ የሚባሉ አይነት ነገሮችም አሉ፡፡ ከ‘ስሞች’ መለዋወጥ በስተቀር ቃናቸው ያልተለወጡ ነገሮች ያሉ ይመሰላል፡፡ አንድ አልፎ፣ አልፎ የሚሰማ ነገር አለ… “እነሱ እንዲህ ያደርጉ አልነበር እንዴ!” ይባላል፡፡ ‘እነሱ’ የተባሉት ሲያደርጉት ትክክል ያልነበረ ነገር፤ እኛ ስናደርገው እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል! ያለፉት ስህተቶች፣ ያለፉት ጉደለቶች፣ ያለፉት  የማዳላትና ዜጋንና ዜጋን የማበላለጥ አሠራሮች ይቅሩ እየተባለ አይደል እንዴ!
ተመልካችና አድማጭ ለመሳብ የሚደረገው ፉክክር ጥሩ ነው፡፡  ምክንያቱም የሚዲያ ተቋማቱ የንግድ ተቋማት እንጂ የበጎ አድራጎት ማህበራት ወይም ቤተ መቅደሶች አይደሉምና ነው፡፡ ግን ደግሞ ሀላፊነት ሊጨመርበት ይገባል፡፡
“ዝንቧን እሽ ብያት አላውቅም፤” ያለውን በማስረጃና በመረጃ መሞገት ነው እንጂ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 9030 times