Saturday, 24 November 2018 12:23

3 ታዳጊዎች ለ”አፍሪካ ስፔሊንግ ቢ” ውድድር በሞምባሳ ይገኛሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 ”ተማሪዎቹ በአፍሪካ ደረጃም አኩሪ ውጤት ያመጣሉ” የስፔሊንግ ቢ ባለቤትና መሥራች
* 1ኛ የወጣ አሸናፊ 280 ሺ ብር፣ 2ኛ የወጣ ደግሞ 140 ሺ ብር ይሸለማሉ ተብሏል


የሁለተኛ ደረጃን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በአሜሪካ የተከታተሉት አቶ ዐቢይ በቀለ፤ በአገራችን የዛሬ 6 ዓመት የተጀመረው የ”ኢትዮጵያ ስፔሊንግ ቢ” ውድድር መሥራችና ባለቤት ናቸው፡፡ በአሜሪካ ሳሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከሆኑ ቤተሰብ ለተወለዱ አሜሪካዊ ተማሪዎች የስፔሊንግ ቢ ውድድር ጀምረው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ውድድሩ ለአገራችን የሚኖረውን ትልቅ ፋይዳ በመገንዘብም፣ በ2005 ዓ.ም በአዲስ አበባና በደብረ ዘይት ከሚገኙ 400 ት/ቤቶች፣ 212 ሺህ ያህል ተማሪዎችን በማሳተፍ፣ ውድድሩ መጀመሩን  አቶ ዐቢይ ያስታውሳሉ። የማታ ማታም ውድድሩን ያሸነፉት ሁለት ሴት ህጻናት ነበሩ፤ የ9 ዓመቷ ሊዲያ ብርሃኑ እና የ13 ዓመቷ ፌበን በየነ፡፡ ሁለቱ ህጻናትም ቃል በተገባላቸው መሠረት፣ ወደ አሜሪካ ተጉዘው፣ በዋሺንግተን የተካሄደውን ዓመታዊ፣ አገር አቀፍ የስፔሊንግ ቢ ውድድር ለመታደም መቻላቸውን አቶ ዐቢይ ይገልጻሉ፡፡ የ3ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው ሊዲያ ብርሃኑ፤ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝታ፣ እዚያው አሜሪካ መቅረቷን ጠቁመዋል፡፡   
በ2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ 16 ከተሞች ከ500 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በስፔሊንግ ቢ ውድድር ማሳተፍ የተቻለበት ትልቅ ስራ መሰራቱን የጠቆሙት አቶ ዐቢይ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውድድሩ እየተለመደና እየተወደደ በመምጣቱ ከኢትዮጵያ ባሻገር ከሌሎች ዘጠኝ የአፍሪካ አገራት ጋር የ”አፍሪካ ስፔሊንግ ቢ”ን መመስረታቸውን ተናግረዋል - የዛሬ 3 ዓመት፡፡ በመጀመሪያው ዓመት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ውድድር ላይ ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ ከሄዱት ሶስት ተማሪዎች ውስጥ አንዷ 2ኛ፣ ሁለቱ ደግሞ 5ኛ እና 11ኛ ወጥተው መመለሳቸውን ገልጸል - መሥራቹ። ባለፈው ዓመት ግን ስፖንሰር በማጣታቸው ተወዳዳሪ ሳይልኩ መቅረታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው “ስፔሊንግ ቢ” ተወዳድረው፣ ምርጥ ሦስት ውስጥ የገቡት አሸናፊዎች፡- ከአዲስ አበባ ተማሪ ምስጋና ዳምጠውና ተማሪ ህያብ አለማየሁ እንዲሁም ከባህር ዳር ተማሪ ቅዱስ ፍስሃ ለ”አፍሪካ ስፔሊንግ ቢ” ውድድር፣ ከትላንት በስቲያ ወደ ኬንያ ሞምባሳ ያቀኑ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ውድድሩ ተጀምሯል ተብሏል፡፡ የውድድሩ አሸናፊዎችም ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት እንደሚያገኙ አቶ ዐቢይ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ 1ኛ የወጣ ተወዳዳሪ 1ሚ. ሽልንግ (280 ሺህ ብር)፣ ለት/ቤቱ 52 ሰው የሚጭን የት/ቤት ባስና ለተማሪው የቅርብ መምህር 500 ሺህ ሽልንግ (140 ሺህ ብር) የሚያገኝ ሲሆን 2ኛ የወጣ ተወዳዳሪ 500 ሺህ ሽልንግ (140 ሺህ ብር) እንዲሁም የቅርብ መምህሩ የተማሪውን ግማሽ ያህል ክፍያ እንደሚያገኝ የጠቆሙት አቶ ዐቢይ፤ “ተማሪዎቹ በአፍሪካ ደረጃም አኩሪ ውጤት እንደሚያመጡ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል፡፡
ሦስቱ የ”አፍሪካ ስፔሊንግ ቢ” ተወዳዳሪ ታዳጊዎች፣ ከትላንት በስቲያ ወደ ኬንያ ሞምባሳ ከመጓዛቸው በፊት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ አግኝታ  አነጋግራቸዋለች፡፡ እንደሚከተለውም  ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡-  


“በአፍሪካ ደረጃ አሸንፋለሁ የሚል ትልቅ ተስፋ አለኝ”
ህያብ ዓለማየሁ እባላለሁ፡፡ የስኩል ኦፍ ኔሽን የ7ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፡፡ ት/ቤቴን ወክዬ በስፔሊንግ ቢ ስወዳደር ቆይቻለሁ፡፡ ታላቅ ወንድሜ አማን ዓለማየሁም በስፔሊንግ ቢ ሲወዳደር ቆይቶ ምርጥ 13 ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው በዚህ ውድድር፣ የመጨረሻው ምርጥ ሶስት ውስጥ ገብቼ ሁለተኛ በመውጣቴና በአፍሪካ ደረጃ ለመወዳደር ወደ ኬንያ ሞምባሳ መሄዴ አስደስቶኛል። በት/ቤቴ፣ በወላጆቼና በጓደኞቼ በኩል የተሰጠኝ አድናቆትና ክብር ይበልጥ እንድበረታ አድርጎኛል፡፡
በአፍሪካ ደረጃ አሸንፌ ለመምጣት ከፍተኛ ዝግጅት አድርጌያለሁ፡፡ አሸንፋለሁ የሚል ትልቅ ተስፋም አለኝ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ እናትና አባቴን እንዲሁም ያበረታቱኝ የቅርብ መምህሮቼንና ጓደኞቼን አመሰግናለሁ፡፡ ሌሎች ተማሪዎችም ስፔሊንግ ቢ ውድድርን ቢወዳደሩ፣ በተለይ የእንግሊዝኛ ችሎታቸውን ስለሚያዳብርላቸው ይጠቅማቸዋል የሚል መልዕክት አለኝ፡፡ እኔም በመበርታቴ ይሄው ከአባቴ ጋር ወደ ኬንያ ሞምባሳ ለመሄድና ለመወዳደር እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ ለዚህ በመብቃቴ የተሰማኝን ደስታ ለመግለፅ ያዳግተኛል፡፡  
“7ኛ ክፍል ሆኜ በኢትዮጵያ ደረጃ አሸንፌአለሁ”
ምስጋና ዳምጠው እባላለሁ፡፡ 15 ዓመቴ ነው፡፡ በኢትዮ ብሔራዊ ት/ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፡፡ የኢትዮጵያ “ስፔሊንግ ቢ” ውድድርን መወዳደር የጀመርኩት ገና የ3ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ፣ በዘጠኝ ዓመቴ ነበር። ውድድሩን እንደ ቀልድ ነበር የጀመርኩት። ያሸነፈ አሜሪካ የመሄድ ዕድል አለው ሲባል ሁሉ እውነት አይመስለኝም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ውድድሩ የምር መሆኑንና በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚካሄድ  አወቅሁኝ፡፡ አንድ የክፍል ጓደኛዬ በውድድሩ አሸንፋ አሜሪካ ሄዳ፣ እዛው ነፃ የትምህርት እድል ስታገኝ፣ ትኩረት ሰጥቼ መወዳደር ጀመርኩኝ፡፡
በቀጣዩ ዓመት በእልህና በጥንካሬ ውድድሩን ለማሸነፍ አቅጄ መወዳደር ጀመርኩኝ፤እያሻሻልኩ እያሻሻልኩ በአምስተኛው ሙከራዬ፣ 7ኛ ክፍል እያለሁ፣ በኢትዮጵያ ደረጃ አሸነፍኩና የዋንጫና የ25 ሺህ ብር ሽልማት አገኘሁ፡፡ ይህ ሽልማት ይበልጥ አበረታታኝ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ይሄው በአፍሪካ ደረጃ ለመወዳደር  እድል አገኘሁ፡፡ ከሶስቱ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች አንደኛ ነው የወጣሁት፡፡
ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጠንካራ ተፎካካሪዎች ይጠብቁናል፡፡ እኔም ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የምችለውን ዝግጅት አድርጌያለሁ፡፡ እንግዲህ ከእግዚአብሔር ጋር ጥሩ ውጤት የማመጣ ይመስለኛል፡፡ ከአባቴ ጋር ለጉዞ በዝግጅት ላይ እያለሁ ነው ያገኘሽኝ። መልካም ዕድል ተመኙልኝ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
“ውድድሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋዬን በሚገባ አዳብሮልኛል”
ተማሪ ቅዱስ ፍስሃ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከባህር ዳር ሲሆን በባህር ዳር አካዳሚ የ10ኛ ክፍል ተማሪና የ17 ዓመት ወጣት ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ “ስፔሊንግ ቢ” ውድድር ላይ መሳተፍ የጀመርኩት በ2008 ዓ.ም፣ የ7ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው፡፡ ያን ጊዜ ከክፍሌና ከምማርበት ት/ቤት አንደኛ ነበር የወጣሁት፡፡ ከዚያ ባህር ዳርን ወክዬ አዲስ አበባ መጣሁ፤ ከዚያም ምርጥ 13 ውስጥ ገብቼ ተመለስኩኝ፡፡ በ2009 ዓ.ም በት/ቤትና በባህር ዳር ደረጃ ተወዳደርን። ከት/ቤትም ከባህር ዳርም ሁለቱንም አንደኛ ወጥቼ፣ በግንቦቱ አገር አቀፍ ውድድር፣ ምርጥ አስር ውስጥ ገባሁ፡፡ በማጣሪያው ደግሞ ሶስተኛ ወጣሁ ማለት ነው፡፡
ውድድሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዬን በእጅጉ አዳብሮልኛል፡፡ ሌሎች ተማሪዎችም በውድድሩ ተሳታፊ ቢሆኑና ቢሞክሩት፣የግድ አሸናፊ ባይሆኑ እንኳን የእንግሊዝኛ ችሎታቸውን ለማዳበር በእጅጉ ያግዛቸዋል። እኔ በአፍሪካ ደረጃ በሚደረገው ውድድር፣ በጣም ጥሩ ውጤት አመጣለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁላችንም ጥሩ ውጤት አምጥተን፣ የአገራችንን ስም እናስጠራለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ለውድድር መቅረባችን በራሱ ለእኔ ትልቅ ውጤት ነው፡፡
ለዚህ በመብቃቴ ቤተሰቤም ደስተኛ ነው። ከእናቴ ጋር ነው ወደ ሞምባሳ የምጓዘው፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡     
 

Read 2308 times