Saturday, 24 November 2018 12:40

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

“በቅንነትና በጥበብ ማሰብ አለመቻል አለመኖር ነው”

አንድ ሰውዬ ነበር … ደስተኛና ባለ ጊዜ፡፡ ባልና ሚስቱ ትዳራቸው የተቃና፣ ቤታቸው የተሟላ ቢሆንም ውስጥ ውስጡን የምትቀና ሚስት ነበረችው፡፡ አቶ ባል ፆምና ፀሎት ቢያበዛም ምንም የጎደለበት ነገር እንደሌለ ያስታውቃል። ሰውየው በጓደኞቻቸውና በጎረቤቶቻቸውም የተከበረና የተወደደ ነው፡፡
ሴትየዋ ግን የባል ወግ መነፈግን ጨምሮ ያልተመቻት ነገር ያለባት ይመስላል፡፡ ቢቸግራት ለምትቀርባት ጓደኛዋ ሚስጥሯን አጫወተቻት፡፡ ጓደኛዋ አንድ ቀን ድንገትና በአጋጣሚ እንደሆነ አስመስላ ከሌላ ሰው ጋር አስተዋወቀቻት፡፡ …
ሰውየው ይኸ ቀረው የማይባል በመሆኑ ከህይወት የተረፈች መሰላት፡፡ አንድ ቀን በቤቷ ውስጥ ከአዲሱ ሰውዬ ጋር ሲዝናኑ፣ ለመስክ ሥራ ሄጃለሁ ያለው ባሏ ድንገት ከች አለ። .. ባለቤቷና አብሮት ያለው ጓደኛው፤ ምንም እንዳልተፈጠረ አድርገው አረጓጓት፡፡ ኑሮ ቀጠለ፡፡ ነገር ግን ባለቤቷ ችግሩ በተፈጠረበት ቀን ወዳጇ ትቶት የሸሸውን ጃኬት በነበረበት እንዲቆይ አሳሰባት። በኪሱ የነበረውን መታወቂያ፣ ገንዘብና ቁልፎች በሳሎኑ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ ማንም እንዳይነካቸው ከለከለ፡፡ እሱ ግን ሲወጣና ሲገባ በእጁ እየነካካ ይዝናናባቸዋል፡፡ ሚስቱ ይህን ስታይ ሃፍረቷን እያስታወሰች ትሸማቀቃለች፡፡ እያደርም ውስጧ እየተጎዳ ብቻዋን መለፍለፍና ማልቀስ ስራዋ ሆነ፡፡ በመጨረሻም ቀውሳ እንደወጣች አልተመለሰችም። ከባለቤቷ ጋር የተገናኘችው ከ13 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ .. ህግ ፊት!! … ከዚያስ?
***
መኖርና ማሰብ አይነጣጠሉም፡፡ በቅንነትና በጥበብ ማሰብ አለመቻል ግን አለመኖር ነው፡፡ ስለምንበላውና ስለምንጠጣው ስናስብ፣ ሌሎች እንዳይበሉና እንዳይጠጡ እያደረግን ከሆነ፤ ስለ ቤትና ስለ መኖሪያ ስናስብ፣ ሌሎችን መጠለያ እያሳጣን ከሆነ፤ ንብረት ስለ ማፍራት ስናስብ፣ ከሌሎች ጉቦ እየተቀበልን፣ እየሰረቅንና እያታለልን ከሆነ አልኖርንም፡፡ ስለ ጤና እያሰብን፣ ሌሎችን ህመምተኛ ካደረግን፤ ስለ ሰላም እያሰብን፣ ለሌሎች ሰላም ከነሳን፤ ስለ ነፃነት እያሰብን፣ የሌሎችን ነፃነት ከገፈፍን፤ ስለ ፍትህ እያወራን፣ ኢ ፍትሃዊ ከሆንን፤ አልኖርንም፡፡ ትልቅ ነን እያልን ሌሎችን ካሳነስን፣ አውቀናል እያልን ሌሎችን ካደናቆርን አልኖርም፡፡ ራሳችንን እንደ ጀግና፣ ሌሎችን እንደ ፈሪ ከቆጠርን፤ ታታሪ ነን ብለን፣ ሌሎችን እንዳይሰሩ ካደረግን አልኖርንም። ብሔር ብሔረሰብ እያልን፣ የሌሎች ማንነት ካልተዋጠልን፤ ስለ ሐገር እያወራን፣ ሌሎችን ከከፋፈልንና ካጋጨን፤ ስለ ስልጣኔና ሰብዓዊነት እየሰበክን፣ በተግባር ጨካኝ ከሆንን አልኖርንም። መኖርን ገድለነዋል፡፡ እኛም በገዛ እጃችን፣ በገዛ ሃሳባችን ሞተናል፡፡ ከሌሎች በላይ ነን እያልን፣ እርቃናችንን ወደ መቃብራችን እየወረድን ነው። “ዘበኞቹን ማን ይጠብቃቸው?” (Who shall stand guard for the guard themselves?) ሲባል፣ ያለ ነገር አይደለም፡፡
ወዳጄ፡- አንድን የሂሳብ ፕሮብሌም (equation) የተለያየ ፎርሙላ ተጠቅመን ልንፈታው (solve ልናደርገው) እንሞክራለን፡፡ ለምሳሌ 4 ቁጥርን ለማግኘት የግድ ሁለትና ሁለትን ብቻ መደመር የለብንም፡፡ ከፈለግን አንድ ሺ አንድ መንገዶች አሉ፡፡ ከለመድነው ባህላዊ፣ ሎጂካዊ፣ ብዙሃኑን መከተል ከሚያስመስለው መንጋዊ አስተሳሰብ ውጪ፣ እውነትን የምንፈልግበት የአስተሳሰብ ጥበቦች አሉ - የትኛው ቦታ ላይ ትክክል እንደሆንን፣ የትኛው ላይ ደግሞ እንደተሳሳትን ለማወቅ የሚያግዙ፡፡ ህይወት እንደ ሂሳብ ሁሉም የሚስማማባት ዕውነት ባለመሆኗ፣ ላንተ ለወዳጄ ልክ የመሰለህ፣ ለኔ ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ … ወይም የተገላቢጦሽ!! … ሁላችንን የሚያስጨበጭብ ዕውነት የሚገኘው ኤዲሰን እንዳደረገው፣ አስተሳሰባችንን በአዳዲስ ሙከራዎች መፈተሽ ስንችል ነው፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት (369-286) የኖረው የታላቁ ላዖ ፁ ደቀ-መዝሙርና ተተኪው ቹዋንግ ፁ፤ ፍልስፍናና ጥበብን፣ ተፈጥሯዊ እምነትና ሳይንስን ባዋሃደው የጣኦኢዝም አስተሳሰብ አባት ነበር፡፡ ቹዋንግ፡- አንድ ቀን በህልሙ ነፃና ደስተኛ ቢራቢሮ ሆነ፡፡ በቢራቢሮነት ዕድሜው ሰው እንደነበር አላወቀም፡፡ ከእንቅልፉ ሲነቃ … ቢራቢሮ እንደነበረ ወይም ቢራቢሮው እሱን እንደነበር ማለሙን እንደማያስታውስ ፅፏል፡፡ ቹዋንግና ቢራቢሮው ሁለት መሆናቸውን የምናውቅ እኛ ነን፡፡ ፊቸር ፊልም ቢሆን ስለምናያቸው፣ ታሪኩ ይበልጥ ስሜት ይሰጠናል፡፡ ለቹዋንግ ወይም ለቢራቢሮው ግን እንግዳ ይሆንባቸዋል፡፡ አንዳቸው፣ አንዳቸው ውስጥ ስለሌሉ፡፡ ለቹዋንግ በቢራቢሮው ፋንታ ወፍ፣ ዝሆን ወይም ሌላ ሰው ቢሆን፣ ለቢራቢሮው ደግሞ በቹዋንግ ፋንታ ሌላ ሰው ወይም እንስሳ ቢሆንም ሃሳቡ ያው ነው። በዚህ አንድና ሁለት፣ ሶስትና አራት የመሆን፣ በዚህ የ‹ማለም› ልዩነት ውስጥ እርግጠኛው ነገር አንድ ብቻ ነው፡፡ … ፀሐፊው ቹዋንግ!! … ሌላው የአስተሳሰብ ጥበብ ማሳያ ቀለማት ናቸው፡፡ ቹዋንግ የሚሰናበተን ከጠፋብን እኛነታችን ጋር የምናገኘው አስተሳሰባችን ጥበባዊ ሲሆን እንደሆነ ይመክረናል፡፡ ኑሯችን አስተሳሰባችንን  ከመራው እንሳሳታለን፡፡ አስተሳሰባችን ኑሯችንን ሲመራው ግን ‹ልክ› እንሆናለን ብሏል፡፡ ሊቃውንት፤ አገርም ‹አገር› የምትሆነው፣ እንደ አገር ስታስብ ነው ይላሉ። በነገራችን ላይ ወዳጃችን ቮልቴር፤ “አገር ማሰብ ከጀመረች ማንም አያቆማትም።” (When once a nation begins to think, it is impossible to stop it) ብሎ ነበር፡፡ … እንዳለውም ሆኗል፡፡
***
ወደ ታሪካችን እንመለስ፡- ባልና ሚስቱ ከ13 ዓመታት በኋላ ህግ ፊት እንደተገናኙ ጠቅሰን ነበር ያቋረጥነው፡፡ ምክንያቱ ባጭሩ፡- ሰውየው ሴቲቱን ያገባት ሚስጢራዊ ተልዕኮ ስለነበረው ነው፡፡ በረቀቀ መንገድ የሚያበሳጫት፣ የውሸት ጓደኛ ወዳጅና የመሳሰሉትን በማዘጋጀት ለአሳፋሪ ስራ አመቻችቶ እንድትዋረድ፣ ራሷን እንድትጠላና ከአባቷ የወረሰችውን ቤት ጥላ እንድትሄድ ወይም እንድትሞት ለማድረግ ደክሟል፡፡ የሚኖሩበት ቤት አባቷ ከአርበኝነት እንደተመለሱ ለውለታቸው የተሰጣቸው ዳረጎት ሲሆን ከሳቸው በፊት የፋሽስት ወታደር መኖሪያ ቤት ነበር፡፡ ጠላት አገሩን ሲለቅና ባንዲራ ሲመለስ፣ በቤቱ ውስጥ ይኖር የነበረው ጣሊያን ወዳገሩ ለመሄድ ሲዘጋጅ፣ በትንሽ ሳጥን የሞላውን የተዘረፈ ጌጣ ጌጥና ገንዘብ ከሳሎኑ ውስጥ ቆፍሮ ቀብሯል። ይህንን ተደብቆ ያየው የጣሊያኑ አሽከር፣ ጊዜ ሲጠብቅ ቢኖርም አቅም በማጣቱና ሁኔታዎች ባለመፍቀዳቸው፣ ሚስጢሩን ለሁለት ባለ ጊዜዎች በመናገር በተደራጀ መልክ ሲዘጋጁበት ቆዩ፡፡ ልጅቱ አባቷ እንደሞቱ በሰርግ ያገባችው ሰውም፣ በጥናት የተመደበ ነበር። ጨዋና የተከበረ፣ ጿሚና ፀሎተኛ መስሎ የባልነት ወጉን እየነፈጋት፣ እሱ ግን በድብቅ እየማገጠና እያቆሰላት ህመምተኛ አደረጋት። በመጨረሻም እብስ ብላ ጠፋችለት፡፡ ባለቤቱ ከጠፋች ከጥቂት ወራት በኋላ አንድ ሌሊት ከግብር አበሮቹ ጋር በመሆን፣ የተቀበረውን ሃብት ለማውጣት ሲቆፍሩ፣ ያልተጠበቀ ነገር ሆነ፡፡ የጣሊያኑ አሽከር ልብ ያላለው ነገር፣ ሳጥኑ ውስጥ ከነበረው ሃብት ጋር ፈንጂም አብሮ መቀበሩን ነበር፡፡ … እናም ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ የሴትየዋ ባል ሁለት ዓይኑ ሲጠፋ፣አንደኛው እጁ ተቆረጠ፡፡ አንደኛው ሰው ሲሞት፣ ሌላኛው ዘመዱ መጠነኛ ጉዳት ደረሰበት፡፡ ይኸ የሰውየው ዘመድ ነው፣ በድርጊቱ ተፀፅቶ፣ ገዳም ወደገቡት የነፍስ አባቱ ዘንድ በመሄድ፣ ታሪኩን ከስር ጀምሮ የተናዘዘው፡፡ በአንድ ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብለው ሲያወራላቸው፣ አጠገባቸው የነበሩ የቤተ ዕምነቱን መገበሪያ የሚያዘጋጁ መነኩሲት እያዳመጧቸው ነበር። መነኩሲቷ ከነበረባቸው ህመም በፀበል ኃይል ስለተፈወሱ፣ ባለውለታቸው የሆነውን መልአክ ለማገልገል፣ በቅጥር ግቢው የሚኖሩ ናቸው። መነኩሲቷ፣ ዛሬ ህግ ፊት የቆመችው፣ ራሷን ጥፋተኛ አድርጋ ከቤቷ የተሰደደችው፣ የሰውየው ሚስት ነበረች፡፡
ወዳጄ፡- በትክክል አለማሰብ፣ ‹አለመኖር› ነው።
ሠላም!!


Read 1371 times