Saturday, 24 November 2018 12:45

ቃልም ስጋ ሆነ!!

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(5 votes)

ዘርዓያዕቆብ- ‹‹ረቂቁን እግዚአብሔር ማንም አላየውም፤ ማንም አልተላከውም--”
ስፒኖዛ - “እግዚአብሔርና ተፈጥሮ ሁለት የተለያዩ ነገሮች አይደሉም፤--”
አርስቶትል - ‹‹እግዚአብሔር ንፁህ እሳቦትና ንፁህ ኃይል ነው--››

  የቃልና የስጋ ሚስጥራዊ ግንኙነት እጅግ አስገራሚ ነው!! ሚስጥራዊነቱና አስገራሚነቱንም ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ ፅፎታል፣
በመጀመሪያ ቃል ነበር፣
… ቃልም እግዚአብሔር ነበር፤
ሁሉ በእሱ ሆነ፤
ከሆነውም አንዳችስ እንኳ ካለ እሱ (ካለ ቃል) አልሆነም፡፡

ቃል መለኮታዊ እሳቦት ነው፡፡ መጀመሪያ ይህ እሳቦት ብቻ ነበር፡፡ በእሱ ውስጥ ግን ሁሉም ህይወት፣ ሁሉም ሐሳብ፣ ሁሉም ባህሪ  ነበር፤ ሁሉም በአንድነት ቃል ነበር፡፡ ስጋ ምውት ነው፤ ህይወትን ግን ከቃል ያገኛል፡፡ ስጋ በድን ነው፤ እስትንፋሱን ግን ከቃል ያገኛል፡፡ ስጋ በቦታና በጊዜ የተዘረጋ ቁስ አካል ነው፤ እሳቤውን ግን ከቃል ያገኛል፡፡
ቃልም እግዚአብሔር ነው፤ ‹‹ብርሃን ይሁን›› ማለት ቃል ነው፡፡ እንደ ቃሉም ትዕዛዝ ፀሐይና ከዋክብት ተሰሩ፤ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍም ብርሃን ሆነ፡፡ ቃል ረቂቅ መለኮት ነው፤ በስጋ ውስጥ ግን ተጨባጭ ይሆናል፡፡ ጠፈርና ከዋክብት ስጋ ናቸው፤ በእነሱ ውስጥ ግን ቃል ተጨባጭ ሆነ፤ በእንቅስቃሴያቸው ውስጥም ይህ እሳቦት ሁልጊዜ አብሯቸው አለ፡፡ ሁሉ በቃሉ ሆኗልና በሰማይና በምድር ፍጥረታት ውስጥ ሁሉ ቃል ተጨባጭ ሆነ፡፡ ቃል አንድ ነው፤ ፍጥረታትን ግን በየወገናቸው አድርጎ በእነሱ ውስጥ ብዙ መሰለ፡፡
ስለዚህ ፈላስፋው ስፒኖዛ ትክክል ነበር፤ ‹‹እግዚአብሔርና ተፈጥሮ ሁለት የተለያዩ ነገሮች አይደሉም፤ እግዚአብሔር የተፈጥሮ ክስተቶች ውስጣዊ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው›› - ቃል ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ብቻ አይደለም፤ ‹‹ቃልም ስጋ ሆነ››፤ ‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን አለ፣ ብርሃንም ሆነ›› በሚሉት የወንጌል ትምህርቶች ውስጥ ቃል ከስጋ፣ መንፈስም ከቁስ ጋር ተዋህዷል፡፡
በመሆኑም፣ እግዚአብሔር መንፈስ ብቻ ሳይሆን ቁስ አካልም ሆኗል፡፡ መንፈስ የእግዚአብሔር አንደኛው መልክ ነው፤ ቁስም ሌላኛው፡፡ እናም ዓለሙ ሌላኛው የእግዚአብሔር መልክ ሆኖ ተገለጠ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ሁሉም ተፈጥሯዊ ህግ፣ ሁሉም ባህሪ፣ ሁሉም ቅድስናዎች፣ ሁሉም ጊዜ፣ ሁሉም ስፍራና ሁሉም ህልውና ሆነ፡፡ ሁሉ ከእርሱ ነው፤ ዓለሙን ሁሉ ከራሱ አመንጭቶ፣ ተመልሶ በእርሱ በኩል ይገለፃል፡፡ እናም ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ሁሉም የእሱ ነው፤ ሁሉም እሱ ነው፤ እሱም ሁሉም ነው፤
ልክ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው፤ ‹‹ሁሉ ከእሱና በእሱ፣ ለእሱም ነውና፡፡›› ስለዚህ፣ ከሐዋርያው ዮሐንስ በፊት የነበረው ሔራክላይተስም ትክክል ነበር፤ ‹‹ሁሉም በሎጎስ ሆነ››፡፡ ሎጎስ ቃል ነው - የፍጥረታት ሁሉ መለኮታዊ ህብረት፡፡ ይህ ቃል የፍጥረታት ሁሉ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው፡፡ ሁሉም ነገር በእሱ ውስጥ ተካትቷል፤ ከእሱ የተገኘ ነውና። ከእሱ ውጭ የሆነ አንዳች ነገር የለም፡፡
እሱ አንድ ነው፤ መልኩ ግን ብዙ ነው፤ መገለጫውም እልፍ አእላፍ፡፡ ማንም ከእሱ አይቀድምም፤ በእሱ ብቻ በኩል ግን ሁሉም ሆነ፡፡ ሁሉም የመጡት በእሱ ነው፤ የሚያንቀሳቅሳቸውም እሱ ነው፡፡ በእሱና ስለ እሱ እየኖሩ ብዙዎቹ ግን አያውቁትም፡፡ ጥቂት ብልሆች ብቻ ያውቁታል፡፡ ሐዋርያው እንዳለው፤ ‹‹እሱ በዓለሙ ውስጥ ሁሉ ነበር፤ ዓለሙም በእሱ ሆነ፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም፡፡›› ዓለሙ ሁሉ እሱን አይወቀው እንጂ፣ እሱ ግን ዓለሙን ከራሱ አመንጭቶ፣ በዓለሙ ኩነቶች በኩል ይገለፃል። እናም እግዚአብሔር ሁሉም ህጎች፣ ሁሉም ስሜቶች፣ ሁሉም አእምሮዎች፣ ሁሉም ዓይኖች፣ ሁሉም ጆሮዎች፣ ሁሉም ወቅቶችና ሁሉም ክስተቶች ሆኖ ይገለፃል፡፡
ስለዚህ፣ አርስቶትልም ትክክል ነበር፤ ‹‹እግዚአብሔር ንፁህ እሳቦትና ንፁህ ኃይል ነው››፡፡ ቃል እሳቦት ነው - መለኮታዊ ኃይል ያለው እሳቦት፡፡ እሳቦትም በመጀመሪያ ነበር፤ አሁን የምናየው ነገር ሁሉ አስቀድሞ በእሳቦት ውስጥ ነበር፤ አሁንም በነገሮች ውስጥ ሁሉ አለ፡፡ ነገሮች በራሳቸው ሐሳብና ዓላማ፣ መነሻና መድረሻ የላቸውም፡፡ ስለዚህም፣ በራሳቸው፣ ስለ ራሳቸው በዓላማ አይንቀሳቀሱም፡፡
እሳቦት ግን ሁሉን ያንቀሳቅሳል፤ ሁሉን ያደራጃል፤ በመላ አካላቸው ውስጥም የነገሮች ውስጣዊ ምንነት ሆኖ ይሰራል፤ ይሄም ምንነት እግዚአብሔር ነው፡፡ እሱ የሁሉም መነሻ፣ የሁሉም ሂደት፣ የሁሉም ግብና መድረሻ ነው፡፡
ስለዚህ፣ ፈላስፋው ሔግልም ትክክል ነበር፤ ‹‹በመጀመሪያ መንፈስ ነበር፤ በዓለም ላይ ሁሉ ከእሱ በስተቀር ምንም አልነበረም፤ መንፈስ ግን ዓለሙን ሁሉ ጠልሎበት ነበር፡፡ መንፈስም በውስጡ ህይወትን ጨምሮ ሌሎች ‹‹የመሆን›› እሳቤዎችን ሁሉ ይዞ ነበር፡፡ ከዚህ እሳቤም ቁስ ተገኝቷል፤ ቁስ ከመንፈስ ተገኘ››፤ልክ ጳውሎስ ‹‹የሚታየው ከማይታየው መጣ›› እንዳለው። እናም ከመንፈስ ቁስ አካል ወጣ፡፡ በዚህም መንፈስ በቁስ አካል ውስጥ ሁሉ ሰረፀ፡፡ ሆኖም ግን፣ መንፈስ በቁስ አካል ውስጥ ሁሉ ሰረፀ እንጂ ጭራሹኑ አልጠፋም፤ ይልቅስ በውስጣቸው ሆኖ ያንቀሳቅሳቸዋል እንጂ፡፡ በእንቅስቃሴያቸው ውስጥም ይበልጥ ለዓለሙ ሁሉ እየተገለጠና ተጨባጭም እየሆነ ሄደ፡፡ እናም ቁስ አካልን ከመንፈስ በማስገኘት፣ እግዚአብሔር ከረቂቅ ባህሪነት ወደ ተጨባጭ ነባራዊ እውነትነት ተቀየረ፡፡
ስለዚህ ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብም ትክክል ነው፤ ‹‹ረቂቁን እግዚአብሔር ማንም አላየውም፤ ደግሞም ማንም አልተላከውም፤ ተፈጥሮ ግን በመላ አካሏ ተሸከመችው እንጂ፤ እናም ተፈጥሮ በጠባዩዋና በህግጋቷ እግዚአብሔርን ገለፀችው።›› በዚህም ረቂቁ ቃል፤ በተፈጥሮ ህግና ስርዓት በኩል ተጨባጭ ሆነ፡፡
ቃል ረቂቅ ነው፤ ስጋ ሲለብስ ግን ተጨባጭ ይሆናል፤ ‹‹ቃልም ስጋ ሆነ›› እንደተባለው። እግዚአብሔር ፍትሕ ነው፤ ሆኖም ግን ፍትሕ ረቂቅ ባህሪ ነው፤ በፍርድ ቤቶች በኩል ግን ስጋ ለብሶ ተጨባጭ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ነፃነት ነው፤ ሆኖም ግን ነፃነት ረቂቅ ባህሪ ነው፤ በዲሞክራሲያዊ መንግስት ግን ተጨባጭ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ሆኖም ግን ፍቅር ረቂቅ ባህሪ ነው፤ በክርስቶስ፣ በመሐመድ፣ በቡድሐ … ግን ተጨባጭ ሆነ፡፡ ሰውም ረቂቅ ነው - የመለኮት ፍንጣቂ፤ ‹‹ቃል ስጋ ለብሶ፣ ፀጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ ውስጥ ሲያድር›› ግን ሰው ተጨባጭ ሆነ፡፡
እናም በሰብዓዊ ፍጡራን መገኘት መንፈስ አካላዊ ንቃተ ህሊናን ተቀዳጀ፡፡ ሆኖም ግን፣ በሰው ልጅ ላይ የተገኘው ይሄ ንቃተ ህሊና፤ የመንፈስ የመጨረሻ ግቡ አልነበረም፡፡ መንፈስ በሰው ውስጥ አካላዊ ንቃተ ህሊና ላይ ደረሰ እንጂ ራሱን የማወቅ ንቃት ላይ ግን አልደረሰም ነበር። በሰው ልጅ ውስጥ የሰረፀው መንፈስም ራሱን የማወቅ ሂደት በሰው ልጅ የታሪክ ሂደት ውስጥ እየተገለጠ እንዲሄድ አደረገ፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥም መንፈስ በሰው ልጅ በኩል ራስን የማወቅና ራስን አሟልቶ የመግለፅ ንቃተ ህሊና ላይ ደረሰ፤ ክርስቶስ ሆነ፤ እግዚአብሔር ሰው ሆነ፤ ሰውም እግዚአብሔር፡፡
‹‹እግዚአብሔር ሰው የመሆኑ ነገር፣ በሰው አእምሮ በፍፁም የማይመረመር ታላቅ ሚስጥር ነው›› ይላል፤ ዴንማርካዊው ፈላስፋ ኬርኩጋርድ (Kierkegaard)፡፡ የሚስጢራዊነቱ ምንጭ ደግሞ እግዚአብሔር ሁለቱንም መሆኑ ነው - ሰውም ነው፣ ሰውም አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለቱ ነገሮች በፍፁም የሚታረቁ አይደሉም፤ መለኮት ከስጋ ጋር፣ ዘላለማዊነት ከጊዜ ጋር ህብር የላቸውም። እግዚአብሔር ግን ራሱን ለዓለሙ መግለፅ ሲፈልግ ለአመክንዮም ረቂቅ የሆነውን መንገድ መረጠ፤ የማይለወጠው ተለውጦ፣ ታሪክ አልባው በታሪክ ውስጥ ታስሮ፣ ዘላለማዊው በዘመን ውስጥ ተቀንብቦ፣ ቃልም ስጋ ሆኖ ራሱን በእኛ ውስጥ ሊተርክ በክርስቶስ በኩል ሰው ሆነ፤ ዮሐንስ እንዳለው፣
‹‹መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድስ እንኳ የለም፤
በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እሱ ተረከው፡፡››


Read 895 times