Print this page
Saturday, 24 November 2018 12:54

ጓቲማላዊው ወታደር የ5130 አመታት እስር ተፈረደበት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የጓቲማላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ በ1982 በተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ 171 ሰዎችን ገድሏል ባለው የቀድሞ የአገሪቱ ወታደር ላይ የ5130 አመታት እስር ቅጣት ማስተላለፉ ተዘግቧል፡፡
ሳንቶስ ሎፔዝ አሎንዞ የተባለው የ66 አመቱ ጓቲማላዊ፤ አገሪቱ በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በነበረችባቸው ጊዜያት ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደልና የጭካኔ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በመፈጸም ክስ እንደተመሰረተበት የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ የአገሪቱ መንግስት ተጠርጣሪውን ከአሜሪካ በማስመጣት ክስ እንደመሰረተበት አመልክቷል፡፡
ተከሳሹ 171 ሰዎችን በጭካኔ መግደሉን በምርመራ ያረጋገጠው የአገሪቱ ፍርድ ቤት፤ በገደላቸው በእያንዳንዳቸው ሰዎች የ30 አመታት እስር እንደፈረደበትና በድምሩም በ5130 አመት እስር እንደተቀጣ ገልጧል፡፡
ፍርድ ቤቱ በግለሰቡ ላይ ያስተላለፈው የ5130 አመታት እስር ከአገሪቱ ህግ ጋር የሚጣረስ ነው በሚል መተቸቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በአገሪቱ ህግ መሰረት አንድ ወንጀለኛ ሊተላለፍበት የሚችለው ከፍተኛው የእስር ጊዜ 50 አመታት ብቻ እንደሆነም አስታውሷል።
እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 1996 በተካሄደው የጓቲማላ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ከ200 ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎች ተገድለዋል ወይም የደረሱበት ጠፍቷል ተብሎ እንደሚገመትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1796 times
Administrator

Latest from Administrator