Sunday, 25 November 2018 00:00

በየመን ከ85 ሺህ በላይ ህጻናት በርሃብ እንደሞቱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


      በአመት ከ3 ሚ. በላይ አፍሪካውያን ህጻናት ያለዕድሜያቸው ያገባሉ

ላለፉት ሶስት አመታት በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰዋ የመን፤ ከ85 ሺህ በላይ የሚገመቱ የአገሪቱ ህጻናት በረሃብ ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውን ሴቭ ዘ ችልድረን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የእርስ በርስ ጦርነቱ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና ተቋማት፣ ለዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብና የመድሃኒት ድጋፍ ለማድረግ እንዳይችሉ እንቅፋት መፍጠሩንና በዚህም በርካታ የአገሪቱ ህጻናት ለርሃብና ለሞት እየተዳረጉ እንደሚገኙ ያስታወቀው  ድርጅቱ፤ ባለፉት ሶስት አመታት ጊዜ ውስጥ በርሃብ ምክንያት ለሞት የተዳረጉት የአገሪቱ ህጻናት ቁጥር ከተጠቀሰው በእጅጉ የበለጠ ሊሆን እንደሚችልም አመልክቷል፡፡
የአለም የምግብ ድርጅት በበኩሉ፤ ከሰሞኑ በየመን የምግብ ዋጋ በእጥፍ  መጨመሩንና የምግብ እጥረት በርካታ ዜጎችን ለህመምና ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል ያለውን ስጋት ገልጧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደግሞ በየመን 8.4 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በከፋ የምግብ እጥረት ችግር ውስጥ እንደሚገኙና በቅርብ ጊዜያት ውስጥም ተጨማሪ 14 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለረሃብ ይጋለጣሉ ተብሎ እንደሚገመት አስታውቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፤ በየአመቱ ከ3 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን፣ 18 አመት እድሜ ሳይሞላቸው በግዳጅ ወደ ትዳር እንደሚገቡ አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡ የአለም ባንክ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የጥናት ሪፖርት እንደሚለው፣ አፍሪካ ያለ እድሜያቸው በሚዳሩ ህጻናት ሳቢያ በየአመቱ 63 ቢሊዮን ዶላር ያህል ታጣለች፡፡ አፍሪካውያን እድሜያቸው ሳይደርስ ወደ ትዳር በመግባታቸው ትምህርታቸውን እንደሚያቋርጡ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ይህም የአህጉሪቱን ህጻናት ለከፋ ችግር እያጋለጣቸው እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡

Read 1021 times