Print this page
Monday, 03 December 2018 00:00

12 የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ ፃፉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ሂውማን ራይትስዎች” እና “አርቲክል 19”ኝን ጨምሮ 12 ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አዲሱን የበጐ አድራጐት እና ሲቪክ ተቋማት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ደብዳቤ ፃፉ፡፡
ተቋማቱ በሀገሪቱ የማህበራትንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ነፃነት ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፣ አዲስ የተረቀቀው አዋጅ አለማቀፍ የሠብአዊ መብት አጠባበቅ ህግጋትን ጠንቅቆ ያሟላ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
“አዲስ የተረቀቀው አዋጅ በዋናነት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሲቪል ማህበራት ስለሚኖራቸው የፋይናንስ ምንጭ፣ ያለ ውጣ ውረድ በቀላሉ ምዝገባ ስለማያከናውኑበት ሁኔታ አብዝቶ የተጨነቀ ነው” ያሉት ተቋማቱ፤ “ለሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር አይደለም የሚል ስጋት አለን” ብለዋል፡፡
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በተለይ የአፍሪካ ህብረት የሰብአዊ መብት አጠባበቅ በነፃነት የመሰብሰብና ማህበር የመመስረት መብቶችን በተመለከተ የደነገጋቸውን ማሟላቱን የሚኒስትሮች ም/ቤት እንዲያረጋግጥ ተቋማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
“ረቂቅ ህጉ፤ ሁሉ ማህበራትና ተቋማት እንደ አዲስ ሊመዘገቡ ይገባል ማለቱም ተገቢ አይደለም” ያለው ደብዳቤው በተለይ የሰብአዊ መብት ተቋማትን እንቅስቃሴ የሚገድብ ድንጋጌ በመሆኑ ሊሻር ይገባዋል ብሏል፡፡ አዲስ እየተረቀቀ ያለው አዋጅ፤ ሃገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ እንቅስቃሴ ሙሉ የሚያደርግና በእጅጉ ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች መቀረፍ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሆኖ እንዲዘጋጅም ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ያሉም አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሀገሪቱ ያለምንም ገደብ ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር አዋጅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያረጋግጡ በደብዳቤው ተጠይቋል፡፡
ደብዳቤውን የፃፉት12 ድርጅቶች፡- አርቲክል 19፣ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማህበር፣ ሲቪክስ፣ የሲቪል መብት ተሟጋቾች፣ የኢትዮጵያ መብት ድርጅቶች ቡድን፣ ሂዩማን ራይትስዎች፣ ኬኔዲ ሂውማን ራይትስ፣ ዎርልድ ኦርጋናይዜሽን አጌኒስት ቶርቸር እና ዲፌንድ ዲፌንደርስ የተሰኙ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ናቸው፡፡ 

Read 7259 times
Administrator

Latest from Administrator