Monday, 03 December 2018 00:00

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት 50 መገናኛ ብዙኃን ተመረጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት 50 የሀገር ውስጥ እና የውጭ መገናኛ ብዙሀንን በኮሮስፖንዳንትነት የመረጠ ሲሆን ከዚህ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በሚመለከታቸው ባለስልጣናት የሚሠጡ መግለጫዎች የቀጥታ ስርጭት ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ትናንት በኮሮስፖንዳንትነት ለተመረጡ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው ማብራሪያ፤ በሃገሪቱ ያሉ መገናኛ ብዙኃንን በተለያዩ መስፈርቶች በመመዘን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ተከታታይ ዘጋቢነት መምረጡን አስታውቋል።
የብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን በዋናነት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮችን በዜና እና ወቅታዊ ሁነቶች በመዘገብ፣ በወጥነት መስራትን በመስፈርትነት መጠቀሙ የተጠቆመ ሲሆን ለህትመት መገናኛ ብዙኃን ደግሞ የጋዜጣው ስርጭት ከ5 ሺህ ኮፒ በላይ መሆኑና ከአንድ ዓመት በላይ በስርጭት መቆየቱ እንዲሁም በስርጭት ቆይታው 1 ዓመት ባይሞላው እንኳ ከ8 ሺህ ኮፒ በላይ እያሳተመ መሆኑ መስፈርት ሆኖ ተቀምጧል፡፡
በዚህ መስፈርት መሰረት ከግልና ከመንግስት ህትመቶች ስምንት የተመረጡ ሲሆን አዲስ አድማስ ጋዜጣ አንዱ ነው፡፡
በኮሮስፖንዳንትነት የተመረጡ መገናኛ ብዙኃን፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በሚሰጡ መግለጫዎች ላይ በመገኘት ጥያቄ የማቅረብ እድል ያገኛሉ፡፡ የሚሰጡ ዋና ዋና መግለጫዎችም በተለያዩ ቴሌቪዥኖች የቀጥታ ስርጭት ያገኛሉ ተብሏል፡፡   


Read 8173 times