Monday, 03 December 2018 00:00

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገው ውይይት ተስፋ ፈንጣቂ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

     ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ በአገሪቱ ላይ 5 አገራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል - ከአንዱ ምርጫ በስተቀር የተቀሩት በአብላጫዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅቡልነት ያላገኙ መሆናቸው ከተደጋጋሚ ንግግራቸውና እሳቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡
በዚህም ረገድ የሚበዙት የፖለቲካ ተንታኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከፓርቲዎቹ ጐን ነው የሚቆሙት፡፡  
ባለፉት 27 ዓመታት ገዢው ፓርቲና ተፎካካሪዎች ለ4 ጊዜያት ያህል ለድርድር መቀመጣቸውን ፓርቲዎቹ ያስታውሳሉ፡፡ አብዛኞቹ ድርድሮች በቅድመ - ምርጫ እንደ ዝግጅት የተካሄዱ ነበሩ፡፡ በ2008 ተጀምሮ የተቋረጠው ድርድር ግን በሃገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የሚያጠነጥን ነበር፡፡
እንደምርጫው ሁሉ የፓርቲዎቹ ያለፉት ዓመታት ውይይቶችና ድርድሮችም የከሸፉ እንደነበሩ ተፎካካሪዎቹ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡
ከ20 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩትን ኦፌኮ እና ኢዴፓ የሚመሩት ፕ/ር መረራ ጉዲና እና ዶ/ር ጫኔ ከበደ እንዲሁም ከተመሰረተ አመት ያልሞላውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ክርስቲያን ታደለ ሰሞኑን ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ከተሳተፉት መካከል ይገኙበታል፡፡  
ከዚህ ቀደም ከኢህአዴግ ጋር ለበርካታ ጊዜያት ለድርድር መቀመጣቸውን የሚያስታውሱት የኦፌኮ ሊቀ መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ውይይቶቹና ድርድሮቹ እርባና ቢስ ነበሩ ይላሉ። አብዛኞቹ ፈረንጆችን ለማታለል የተደረጉ ነበሩ ባይ ናቸው፡፡ የኢዴፓው ዶ/ር ጫኔ ከበደ ከዚህ ሃሳብ ጋር በከፊል ይስማማሉ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከፓርቲዎች ጋር በሚያደርገው ውይይት ምን እንደሚፈለግ፣ ሃገሪቱ በቀጣይ ምን አይነት የፖለቲካ ሁኔታ እንደምትሻ ፍኖተ ካርታ አስቀምጠው ተቃዋሚዎችን ለውይይት መጥራታቸው፣ ከዚህ ቀደም ከተካሄደው የተሻለ ያደርገዋል የሚሉት
ፕ/ር መረራ፤ ምርጫ ቦርድ እንደ ገለልተኛ አካል ውይይቱን እንዲመራ ሃሳብ ማቅረባቸውም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ያደርገዋል ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ የውይይቱ ማካሄጃ ስነ ስርአት ደንብ በምርጫ ቦርድ እንዲወጣ መደረጉም አዲስ ነገር ነው ብለዋል - ፕ/ር መረራ ጉዲና፡፡
ውይይቱ በዚህ መልኩ እንዲካሄድ ፍኖተ ካርታ መቀመጡ ጥሩ ጅማሮ ነው ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ፤ ከሞላ ጎደል ከዚህ በፊት ከነበረው ግልፅና ሁሉንም አሳታፊ ለማድረግ የተሞከረበት ሂደት ነው በማለት ጅምሩን አድንቀዋል፡፡ ኢህአዴግ ለ27 ዓመቱ የምርጫ ችግር አንድ እልባት ለማበጀት እንደፈለገም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁርጠኝነት አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የተካሄዱት ድርድሮች የሃገሪቱን ዲሞክራሲ የሚያሳድጉ ሳይሆን የበለጠ የሚገድሉ እንደነበሩ የሚገልፁት የኢዴፓ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ በበኩላቸው፤ በእነዚያ ድርድሮች የወጡ አዋጆችና ህጎች በባህሪያቸው አፋኞች ነበሩ ይላሉ፡፡ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው ውይይት ከአነሳሱ ብዙ ተስፋ የሚሰጡ ፍንጮች የተስተዋለበት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ጫኔ፤ ጠ/ሚኒስትሩ ራሳቸው ከዚህ ቀደም ለተደረጉ ድርድሮች እውቅና አለመሰጠታቸው፣ የሃገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ለማሻሻል ቁርጠኛ መሆናቸውን ያረጋግጣል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ ድርድሮች የይስሙላ ነበሩ፤ ሁሉንም አካታች አልነበሩም” የሚለው የ32 ዓመቱ ፖለቲከኛ ክርስቲያን ታደለ በበኩሉ፤ “አሁን አደራዳሪውም ተደራዳሪውም ኢህአዴግ አይደለም ቢያንስ አደራዳሪው  ምርጫ ቦርድ መሆኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው ድርድር ለየት ያደርገዋል ብሏል። የውይይቱ ጅማሮ የሃሳብ ገደብ የተጣለበት አለመሆኑን የጠቆመው ክርስቲያን፤ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ውይይቱ የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ ለማሻሻል ተስፋ የሚጣልበት ይሆናል፤ ብሏል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በቁርጠኝነት አሁን የያዙትን ሃሳብ ሳይሸራረፉ ወደፊት የሚገፋ ከሆነ የሁላችንንም ትብብር ሊያገኑ ይችላሉ ያሉት ፕ/ር መረራ፤ የዶ/ር ዐቢይ የመጨረሻው ነብይነትና ቁርጠኝነት የሚፈተነውም ምርጫውን እንዳሰቡት ነፃና ዲሞክራሲያዊ በማድረጉ ላይ ነው ይላሉ። አቶ ክርስቲያን በበኩሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻቸውን ምርጫውን የተሳካ ያደርጉታል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ ምርጫው እንደታሰበው ስኬታማ እንዲሆን ከወዲሁ በሀገሪቱ ተፈጥረው የነበሩ ቅራኔዎች በእርቅና በድርድር እልባት ማግኘት አለባቸው፤ ይህ ባልተደረገበት ሁኔታ ወደ ምርጫ ዘሎ መግባት ሃገሪቱን የበለጠ ወደ ቀውስ ሊከታት ይችላል የሚል ስጋትም አለው፡፡ ለዚህ መፍትሔው ደግሞ በቅራኔ ውስጥ ያሉ አካላት በሙሉ ወደ እርቅና ብሔራዊ መግባባት የሚመጡበትን አማራጭ ማፈላለግ ነው - እርምጃው በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫም ሆነ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጠቃሚ ነው ይላል - ወጣቱ የአብን አመራር፡፡
የሃገሪቱ የተቃርኖ ፖለቲካ ሳይፈታ፣ የኢህአዴግ ቁርጠኝነት በአግባቡ ሳይፈተሽ፣ ወደ ምርጫ የሚገባ ከሆነ ሃገሪቱን ወደ ሌላ ቀውስ ያሸጋግራል ሲሉ ፕ/ር መረራ የክርስቲያንን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡
“ተቃዋሚዎች የሚፈልጉት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ ጨዋታ ነው” የሚሉት ፕ/ር መረራ፤ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁንም ቡዳውን አላገኘው፤ ቡዳው እስኪገኝ ድረስ ጥንቃቄ መደረግ አለበት” በማለት ከዚህ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የበሠለ ፖለቲከኛም ፖለቲካም የለም ባሉት እስማማለሁ ብለዋል፡፡ “የሀገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች ዋነኛውን የዲሞክራሲ ፈተና እንዳላለፉ ግልጽ” ነው ብለዋል ፕ/ር መረራ።
አሁንም ለውጡ ምንድን ነው የሚፈልገው? የሚለውን አብዛኞቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አያውቁትም የሚሉት ዶ/ር ጫኔ፤  በዚህ በኩል ጠ/ሚኒስትሩ የሚመሩት ኢህአዴግ ብዙ ርቀት ሄዷል” ይላሉ፡፡
ከተቃዋሚዎች አንፃር የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሄድ ብዙ ቀናነት የሚታይበት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ጫኔ፤ ሆኖም የሚጠቅመው  ቀጣዩ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀናነት ሳይሆን በውይይትና ድርድሩ የሚወጡ የመጫወቻ ህጐችና ጠንካራ አፈፃፀማቸው ነው ለምርጫው የሚጠቅመው ብለዋል፡፡ ይህ ቁርጠኝነት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል እንዳለ ያስታውቃል ብለዋል - ዶ/ር ጫኔ፡፡
በሃሳብ ላይ ተመስርተው ለእውነት የቀረበ ፖለቲካ የሚያካሂዱ የፖለቲካ ድርጅቶች ከ10 አይበልጡም ይላሉ - ዶ/ር መረራ፡፡ ሌላው በፖለቲካ የሚቀልድ እንጂ ትክክለኛ ፖለቲካ የሚያካሄድ ፓርቲ አይደለም፤ እነዚህ ደግሞ ወይ በህዝብ ይገፋሉ ወይም አቅም ባላቸው ፓርቲዎች ይዋጣሉ ባይ ናቸው፡፡
በአሜሪካም ከዲሞክራቶቹና በሪፐብሊካን በተጨማሪ በርካታ ፓርቲዎች መኖራቸውን የጠቆሙት አንጋፋው ፖለቲከኛ፤ ዋናው ቁም ነገር የትኛው ፓርቲ በሃሳቡ የህዝብን ልብ ያሸንፋል የሚለው ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ለኔ የመዋሃድ ነገር ብዙም አያሳስበኝም፤ ሁሉንም ቀጣዩ ምርጫ ያስተካክለዋል - ብለዋል፡፡
ብዙ ፓርቲዎች ሃሳብ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደማያደርጉ የሚገልፁት ዶ/ር ጫኔ በበኩላቸው፤ ሃሳብ ያላቸው ጥቂቶች የሊቀ መንበርነት ቦታ ሳያስጨንቃቸው ለሃሳብ ልዕልና ሲሉ በጋራ ሊሠባሰቡ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡
ኢዴፓም ከውጭ ከመጡና ሀገር ውስጥ ከነበሩ ፓርቲዎች ጋር ለመዋሃድ ወይም ግንባር ለመፍጠር እየተወያየ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ጫኔ፤ አሁን በሀገሪቱ ከሚገኙ በሃሳብ በሚታገሉ ፓርቲዎች መካከል ውህደትና ግንባር መፍጠር የሚቻልበት ሠፊ እድል አለ ይላሉ፡፡
ነገር ግን ይህ ሂደት፣ በ2011 መጠናቀቅ እንዳለበት ያሳስባሉ፤ ምክንያቱም ለቀጣይ አመት ከተሻገረ፣ ውህደቱም ግንባሩም “የእነቶሎ ቶሎ ቤት…” ይሆንና ነገሮች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊያመሩ ይችላሉ ሲሉ ይሰጋሉ ዶ/ር ጫኔ፡፡
በሀገሪቱ በርካታ የፖለቲካ ተቃርኖዎች፣ የታሪክ አለመግባባቶች፣ ያልተሻሩ በደሎች አሉ የሚለው ደግሞ ወጣት ክርስቲያን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርቲዎች በቀላሉ ወደ ውህደት ይመጣሉ ማለት የማይታሰብ ነው ይላል ፖለቲከኛው - እርስ በእርስ የሚጣረሱ ሃሳቦች አብሮ መስራት የሚችሉት እርቅ ሲፈጽሙ ብቻ ነው ሲል ሃሳቡን ያጠናክራል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባደረጉት የመጀመሪያ ውይይት ብዙዎች እርካታ ተሰምቷቸዋል፡፡ ጅምሩ አዲስ ተስፋ ፈንጣቂ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሀገሪቱም የፖለቲካ ሂደት አዲስ ጅማሮ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግላቸው ጭምር እየወሰዷቸው ያሉ ተራማጅ እርምጃዎች፤ በውይይቱ ተሳታፊዎች አድናቆት ተቸሯቸዋል። በሰሞኑ ውይይት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ውህደት ከመጡ በግላቸውም ጭምር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡Read 7027 times