Wednesday, 05 December 2018 00:00

ሶርያ በርካታ ዜጎች የተሰደዱባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ሆናለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመሰዋና 6.3 ሚሊዮን ያህል ዜጎቿ የተሰደዱባት ሶርያ፤በአለማችን እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች አገራቸውን ጥለው የተሰደዱባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን ዩኤስኤ ቱዴይ ዘግቧል፡፡በሶርያ የእርስ በእርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት እ.ኤ.አ ከ2011 አንስቶ 6.3 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች ድንበር አቋርጠው ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ከእነዚህም መካከል 3.3 ሚሊዮን ያህሉ በቱርክ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡ ከአለማችን አገራት በርካታ ዜጎችን በማሰደድ የሁለተኛ ደረጃን የያዘቺው አፍጋኒስታን ናት ያለው ዘገባው፣ 2.6 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች መሰደዳቸውንና ከእነዚህም መካከል 1.4 ሚሊዮን ወይም 74 በመቶ ያህሉ በጎረቤት አገር ፓኪስታን የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ ገልጧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ነጻነቷን ያወጀቺውና እንደ አገር መቆም ተስኗት፣ በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ የኖረቺዋ ደቡብ ሱዳን፤ በ2.4 ሚሊዮን ስደተኞች የሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም ዘገባው አመልክቷል።
ሌላዋ አፍሪካዊት አገር ሶማሊያ፤ በ806 ሺህ ያህል ስደተኞች የአራተኛ ደረጃን ይዛለች ያለው ዘገባው፤ 723 ሺህ ያህል የሮሂንጋ ሙስሊሞች ወደ ጎረቤት አገር ባንግላዴሽ የተሰደዱባት ማይንማር፣ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል፡፡

Read 4768 times