Print this page
Monday, 03 December 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


     ቀደም ባለ ጊዜ ነው፡፡ ትልቅና የተደራጀ ጦር ያለው አገር፣ አንዲት ሰላማዊና ሃብታም የሆነችን ትንሽ ሀገር ለመውረር ዘመቻ ጀመረ፡፡ የወራሪዎቹ አራጣ ዘረፋ ነበርና ምንም ዓይነት ሽምግልና ሊያቆማቸው አልቻለም፡፡ ጦርነት ግድ የሆነባቸው የትንሺቱ አገር ህዝቦችም በበኩላቸው ተዘጋጁ፡፡ ወራሪዎቹ እየፎከሩ ሲደርሱ አገሪቷ በረዥም አጥር ተከልላ ጠበቀቻቸው፡፡ ዘማቾቹ መከለያውን ቃኝተው ከተጠጋን እንጠቃለን፣ የሚሻለው መግቢያና መውጫቸውን ዘግተን ስንቃቸውን ማስጨረስ ነው፡፡ ያኔ ሳይወዱ በግድ እጅ ይሰጣሉ በማለት አሰቡ፡፡ ከበቧቸውናም መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ ዛሬ፣ ነገ እያሉ ብዙ ጊዜ አለፈ፡፡
ብቅ የሚል አልታይ አለ፡፡ የራሳቸው ስንቅ አለቀ፡፡ መራብ ሲጀምሩ “ወደ አገራችን ተመልሰን ከምንዋረድ፣ የሞተው ሞቶ እናስገብራቸው” በማለት ተማከሩ። ዝናብ በሚዘንብበት አንድ ሌሊት ድምፃቸውን አጥፍተው ወደ አጥሩ ተጠጉ፡፡
በሩን በሃይል በርግደው ወደ ከተማው ሲዘልቁ፣ ከእንስሶች በስተቀር ማንም አልነበረም፡፡ ከተማዋን በረበሩ፡፡ ከከብቶች መኖ በስተቀር የእህል ዘር አላገኙም፡፡ ረሃብ ጠናባቸው፡፡ መጨረሻቸው ምን ይሆን?
***
ወዳጄ ያለንበት ዘመን የፉከራና የጀብደኝነት አይደለም፡፡ “ከፈለግን ጦርነት መስራት እንችላለን” የሚባለው ለ “ኔሽን” ሳይሆን ለ”ፕሌይ ስቴሽን” ሆኗል - ለልጆች መጫወቻ፡፡ ጉራና ተደፈርኩኝ ባይነት እንደ አኪለስና ሔክቶር፣ እንደ ሙሶሎኒና ሂትለር ተረትና ታሪክ ማዳመቂያ ነው፡፡ “ጠብ የፈለገ ሰበብ አያጣም” እንደሚሉት፤ ላሟ ሳትገዛ በጥጃ መጣላት፣ አፋፍ ላይ ሆኖ የቁልቁለቱን ምስኪን ውሃውን አደፈረስሽብኝ ማለት ጊዜው አልፎበታል፡፡ የልብን ሰርቶ “ይቅር በሉኝ፣ እንደገና ላሞኛችሁ” ማለት… የዘፈን ግጥም እንደሆነ ይቀራል እንጂ ማንም አይታለልም፡፡
ወዳጄ፡- ከሰበብ ጀርባ ምክንያት ካለ፣ ጥቅም የማስከበር ግጭትና ጦርነት ሊያስከትል ይችላል፡፡ “ጥቅም” ሲባል የስነልቦና ወይም የማቴሪያል ወይም የሁለቱም ሊሆን ይችላል፡፡ የባድመና የሁለቱ ፊደላት “ሸ” እና “ቸ” ጉዳይ ለኛ ምሳሌ ነው፡፡
ታላቁ ፓስካል፤ “የክሌዖፓትራ አፍንጫ አንድ ኢንች ቢረዝም ወይም ቢያጥር ኖሮ፣ የዓለም ታሪክ የተለየ ይሆን ነበር” (If Cleaopatra’s nose, had been an inch longer or shorter world’s histoy would have been changed) በማለት ጽፏል፡፡
በትንሽ ሰበብ ትላልቅ ጦርነቶች፣ ትላልቅ አብዮቶች ፈንድተዋል፡፡ በቱኒዝያ፣ ኢትዮጵያና… በሌሎች ብዙ አገራት አይተናል፡፡ ሰበብ የብዙ ድብቅ ምክንያቶች መገለጫ ነው፡፡ አንዳንዱ ግን ራሱን ችሎ ምክንያት ይሆናል፡፡ የአገር መዳከምና መመሳቀል ለጥቂት ራስ ወዳዶች መነገጃና የሃብት መሰብሰቢያ ሰበብ ይሆናል። በአሜሪካ የርስበርስ ጦርነት ወቅት ስለነበረው ምስቅልቅል የሚተርከው “ነገም ሌላ ቀን ነው” (Gone with the wind) የተባለው መጽሐፍ ገፀ ባህርይ ሬት በትለር… “ሰው የሚከብረው ወይ ሀገር ሲለማ ወይ አገር ሲመሳቀል ነው” ይላል -  ራሱን ምሳሌ አድርጐ፡፡
ወዳጄ፡- አገር የሚለማውና የህዝብ ኑሮ የሚሻሻለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ኢንዱስትሪ የሚስፋፋው፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት የሚያድጉት፤ በንግድ፣ በግብርናና በትራንስፖርት ዘርፍ ለውጥ ማምጣት ስንችል ነው የተረጋጋ ኑሮ የምንኖረው፡፡ አገር ከተመሳቀለች፤ ግብር በአግባቡ አይሰበሰብም፣ የፋብሪካና የግንባታ ጥሬ ዕቃዎች ይወደዳሉ፣ ምግብና መድሃኒትን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዕጥረት ይከሰታል፡፡ ይኸ ደግሞ ለህገወጥ ነጋዴዎች፣ ለደላሎችና ለአንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች የምድር ገነት፣ ለብዙሃኑ ሲኦል ስለሚሆን ለእርስበርስ መቃቃርና በሰበብ አስባብ ለመጣላት፣ አንድ የጀርባ ምክንያት ይሆናል፡፡
ዛሬ ትልቅና ሃብታም የሆኑ አገራት፤ ባለፉት ዘመናት ትናንሽ፣ ድሆችና እርስበርሳቸው የሚጋጩ ነበሩ፡፡ የዛሬዋ ዩኤስ አሜሪካ፤ ትናንትና ቦትሰንና ፊላዴልፊያ ነበረች፡፡ ግሪክ፤ ፈረንሳይና ጣሊያንን ጨምሮ ብዙ የአውሮፓ አገራት፤ በትናንሽ መንግሥታት የተከፋፈሉ ነበሩ፡፡ የአፍሪካና የሌሎች አህጉራት አገሮችም እንዲሁ። አገር ትልቅ የምትሆነው፣ የበለፀገ ማህበረሰብ የሚፈጠረው፣ የስልጣኔ መስኮት የሚከፈተው… የጋራ ኢኮኖሚ በመገንባት፣ በመተጋገዝና በመደጋገፍ… የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋን መቋቋም ሲቻል ነው፡፡
በሃቅ የሚነግዱ አገር ወዳዶችን እየገፉና ከስራቸው እያፈናቀሉ፣ የወታደሮችና ፖለቲከኞች ንብረት የሆኑ የንግድ ኩባንያዎችን እንቅስቃሴ ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ጋር በማሰናሰል “አድገናል” ማለት… ብዙሃኑን ህዝብ በመጫኛ እንደተጣለችው ዶሮ መቁጠር ነው፡፡
“መጥፎ መንግሥትና ፓርቲ በሚመራው አገር፤ በጦርነት ማሸነፍና መሸነፍ ለዜጐች ለውጥ የለውም፡፡ ሲቪሉ ሕዝብ በሁለቱም ጊዜ በከፍተኛ የግብር ጫናና በተለያዩ ችግሮች አበሳውን ማየቱ አይቀርም” በማለት የሚያረጋግጥልን ጆርጅ ሳንታያና ነው፡፡ (መጋዝ ሲሄድም ሲመለስም ይቆርጣል እንደማለት፡፡)
ወዳጄ፡- ጠብ ለፈለገ… ሰበብ አይታጣም ስንል በየዩኒቨርስቲዎቻችንና በአንዳንድ ቦታዎች በትንንሽ ሰበቦች በሚፈጠር አለመግባባት ሁከት እየተነሳ፣ የሰው ህይወት የሚቀጠፍበት የጀርባ ምክንያት ሲመረመር ስር የሰደደው የዘር ፖለቲካ ይመስለኛል፡፡ እንደ ዐቢይ ጉዳይ መንግሥትና ተፎካካሪዎቹ መክረው፣ የመፍትሔ አቅጣጫ ካልተለሙለትና መስመር ካላሲያዙት፣ በየጊዜው ብልጭ ድርግም እያለ፣ የለውጥ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡
በነገራችን ላይ ስለዘር ፖለቲካ ሳስብ፣ ፒተር ኡስታኖቭን አስታወስኩ፡፡
ሀ. ቂሎች በዘር ፖለቲካ ሲታለሉ ይገርመኛል፡፡ ለምሳሌ እኔ ሩሲያዊም፣ እንግሊዛዊም አሜካዊም እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ነኝ” ይላል - “Dear me” በሚል ርዕስ ባሳተመው የህይወት ታሪክ መጽሐፉ፡፡ ኡስታኖቭ የብዙ እውቀቶች ባለቤት (a man of many knowledges) በመባል ይታወቃል፡፡ ሴት አያቱ፤ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ከነበሩ እንግሊዛውያን ጋር ተጋብተው ከሄዱ ኢትዮጵያውያን አንዱ ናቸው፡፡ ፎቶግራፋቸው መጽሐፍ ውስጥ አለ፡፡
ፒተር ኡስታኖቭን ማየት ከፈለግህ፣ ታላቁን ፊልም “ስፓርታካስ”ን ተመልከት፡፡ ታግሎ የጣለውን ጓደኛውን “ግደለው” ሲሉት ባሪያ ሆኜ ባሪያ አልገድልም ብሎ ጦሩን ኔሮ ላይ ወርውሮ የሞተ ሌላ ኢትዮጵያዊ ገፀባህሪም ታያለህ፡፡ ኔሮን ሆኖ የተጫወተው ኡስታኖቭ ነው፡፡
ወደ ትረካችን ስንመለስ፡- የትንሺቱ አገር ህዝቦች ጠላት እንደሚዘምትባቸው እንዳወቁ አጥራቸውን አጠናክረው፣ ለከብቶቻቸው መኖና ውሃ አዘጋጅተው፣ በሩን ከውስጥ ቆልፈው፣ ከአካባቢው ጋር የተመሳሰለ ምሽግ ውስጥ ተደብቀው ጠበቁት፡፡ ወራሪው ገብቶ እንዳለቀ፣ በፍጥነት በሩን ከበቡ፡፡ የገባው አልወጣም፡፡ የወጣውም በር ላይ ቀረ፡፡
“ጦርነትን የምታሸንፈው ጭንቅላትህ ውስጥ ነው” ያለው ማን ነበር? ጥያቄው፤ “ጠብ ለፈለገ… ሰበብ አይጠፋም” እንዳይሆን አስብበት!! አስብበት!! እናስብበት!!
ሠላም!!  


Read 1147 times