Tuesday, 04 December 2018 10:19

የአንዳንድ ምሁራን አድርባይነት!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(13 votes)

(ሪፎርሙን በምክንያት የሚቃወሙትን አይመለከትም!!)
በቅርቡ የሙከራ ሥርጭቱን በጀመረው “ድምፂ ወያኔ” የቴሌቪዥን ቻናል ላይ አንድ ቃለ ምልልስ ተላልፏል፡፡ ለእኔ አስገራሚ ቃለ-ምልልስ ነበር፡፡

(አንዳንዶች ደግሞ ሳይበሽቁበት አይቀርም!) ቃለ ምልልሱ በወቅቱ አገራዊ ሪፎርም ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ (የአዲሱ አመራር የለውጥ እርምጃ ማለቴ

ነው!) ጣቢያው ቃለ ምልልሱን ያደረገው ከሁለት እንግዶች ጋር ነበር፡፡ ሁለቱም ምሁራን ናቸው፡፡ በተለይ አንደኛው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሌክቸረር

መሆናቸውን የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ (100 ፐርሰንት እርግጠኛ ባልሆንም!) ሁለቱም እንግዶች የሪፎርሙ ደጋፊ አለመሆናቸውን (ቀልባሽ አልወጣኝም!)

የተገነዘብኩት በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ነበር፡፡
ሁለቱ ምሁራን ዓለምን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያስደመመው የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የለውጥ እርምጃ ጨርሶ የተዋጠላቸው አይመስሉም፡፡ (የውጭ

ዲፕሎማቶች ሪፎርሙን "ፓራዳይም ሺፍት" ብለውታል!) እናላችሁ----ሁለቱ ምሁራን የዐቢይ አመራር የሚያከናውናቸው ሥራዎች ሁሉ አገሪቱን

አደጋ ላይ እንደጣላት ነው የሚያምኑት፡፡ አዲሱ አመራር ቅቡልነት ("ሌጂትሜሲ") የለውም ግን አላሉም፡፡ (ማን ሊሰማቸው!)
ኢትዮጵያ በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ድፍረትና ቅንነት ከኤርትራ ጋር በፈጠረችው አዲስ ሰላማዊ ግንኙነት እንኳን ሙሉ ለሙሉ ደስተኛ አይመስሉም፡፡

(ዓለምን ግን አጃይብ አሰኝቷል!) በተለይ ከሶማሌና ኤርትራ ጋር የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት…እንደ ጣልቃ ገብነት ነው

የሚቆጥሩት፡፡ (ውርደትም ጭምር!) ምክንያታቸው ደግሞ ሱማሌ "የፈረሰች አገር" ስትሆን፣ኤርትራ "አሸባሪ የምትደግፍ" ተብላ የተከሰሰች ናት የሚል

ነው፡፡ (ውሃ የማያነሳ ምክንያት ነው!)
እንደሚመስለኝ እነዚህ ምሁራን ከኤርትራ ህዝብ ጋር ሰላም መውረዱን ባይጠሉትም---የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ወደ ኢትዮጵያ መመላለስ

አልወደዱትም፡፡ (ግማሽ እርቅ አለ እንዴ?) ከህዝቡ ጋር እርቅ አውርዶ ፕሬዚዳንቱን ዞር በል ማለት አይቻልም እኮ!! እንደዚያ የሚቻል ቢሆንማ  

ኖሮ … የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ሁለቱ መሪዎች በተጣሉ ጊዜ … ህዝቡ ከኤርትራም ከኢትዮጵያም ባልተባረረ ነበር፡፡  
 በነገራችን ላይ ለውጡ ያልተዋጠላቸው አንዳንድ ወገኖች፣ “ባልታደሰው” የኢህአዴግ መንግስት፣ ወህኒ ተወርውረው የነበሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች

ከእስር መፈታታቸውን አይደግፉትም፡፡ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ፍረጃው ተነስቶላቸው፣ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው፤ የተለየ

ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በመያዛቸው የተነሳ ወህኒ የተወረወሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች በምህረት መፈታታቸውን እንደ በረከት ሳይሆን እንደ

መርገምት ነው የቆጠሩት፡፡ (ጠ/ሚኒስትሩ “ሰው ሲፈታ ዓይናችን ይቀላል” ነው ያሉት?!) በዚህ የይቅርታና የምህረት እርምጃ የተነሳ … “የህግ

የበላይነት ተጥሷል" ማለት ለእኔ እንቆቅልሽ ነው፡፡ (የህግ የበላይነት ተከብሮ ያውቃል እንዴ?)
ለውጡን የማይደግፉ አንዳንድ "አፍቃሬ ኢህአዴጎች" ያልገባቸው… አንድ ሃቅ አለ፡፡ ምን መሰላችሁ---ጦቢያም ሆነች ኢህአዴግ ከመፈራረስ የዳኑት

በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር አመራርና ቀናነት የተሞላበት አስተሳሰብ መሆኑ አልገባቸውም፡፡ (እንዲገባቸውም አይፈልጉም!)
ወደ ሰሞነኛ ጉዳይ እንሂድ፡፡ በቅርቡ የፌደራል መንግሥቱ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የቀድሞ ከፍተኛ  አመራሮችን  

ለህግ ማቅረቡን ተከትሎ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ እርምጃውን በመቃወም የሰጡት መግለጫ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ (ግራ

አጋብቷልም!) በይፋ የተቃወሙም ነበሩ፡፡
 “ነገሩ ከሰብዓዊ መብትና ሙስና ጥያቄዎች ወጥቶ ይህንን ህዝብ ወደ መምታት የፖለቲካ እርምጃ ሄዷል፤ ለዚህም ነው አንቀበለውም ያልነው” ብለዋል

- ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው፡፡ (የቱን ህዝብ ማለታቸው ነው?) እንዴት ነው በከፍተኛ ሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦች አንድን ሙሉ

ብሔር የሚወክሉት? የቀድሞው የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው  በቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ በካቴና ታስረው በቴሌቪዥን

መታየታቸውንም፣ ዶ/ር ደብረፅዮን - “የፖለቲካ ድራማ ነው” ብለውታል፡፡ (ሊያመልጡ ሲሉ እኮ ነው የተያዙት!) እኔ የምለው ግን ---

ተጠርጣሪ ወንጀለኛ በካቴና ታስሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉ አዲስ ነገር ነው እንዴ? (ዶ/ር መረራ እኮ ከአውሮፓ ስብሰባ መልስ በካቴና ታስረው

በሚዲያ ታይተዋል!) የአሜሪካ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችም እኮ በካቴና ታስረው በሚዲያ ይታያሉ፡፡ (በህግ ጥላ ሥር የመዋል ምልክት መስሎኝ!?)
 ከፖለቲከኞቹ የባሰ የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ምሁራን በጭፍን የሚሰጡት ድምዳሜ ነው፡፡ (ዕውቀትና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ገደል ገቡ!!) በመቀሌ

ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር መሆናቸው የተጠቀሰው አቶ የማነ ዘርዓይ የተባሉ ግለሰብ ለአንድ ሚዲያ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ "የፀረ

ሙስና ዘመቻው የትግራይ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው" - ብለዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተሰሩትን ነገሮች ሁሉ መጥፎ እንደነበሩ አድርጎ ማቅረብ ሌላው

ትልቅ ችግር ነው ብለው ያምናሉ - ምሁሩ፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበረ ሁላችንም የምናውቀው ነገር ሆና

ሳለ፤ ኢኮኖሚው፣ መከላከያውና የደህንነት ቢሮው ጥሩ ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው” ብለዋል - ምሁሩ በሰጡት አስተያየት፡፡
በእኔ በኩል፤ ተቋማቱ መጥፎ እንደነበሩ ተደርጎ ሲቀርብ አልሰማሁም፡፡ (ሪፎርም ላይ መሆናቸውን እንጂ!) በሁለት ዲጂት ሲያድግ እንደነበር ሲነገርለት

የቆየውን ኢኮኖሚያችንንም (እነ IMF ጭምር የመሰከሩለትን ማለቴ ነው!) የካደ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ (የኢኮኖሚ ኢ-ፍትሃዊነት አለመኖሩ ግን

ሃቅ ነው!) ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመጣ ግን ሰሞኑን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ምሁሩ እንደሚሉት፤ በ“ዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር

ችግር” አይደለም፡፡ (ይሄማ ለኛ ቅንጦት ነው!) ተጠርጣሪዎቹ በከፍተኛ የሙስናና የሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ናቸው፡፡ እደግመዋለሁ -

"በከፍተኛ የሙስናና የሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ናቸው!!"
እናም ምሁሩና አንዳንድ ለውጡ ያልተዋጠላቸው የአውራው ፓርቲ አመራሮች እንደሚያቀሉት … ነገሩ “የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግር”

አይደለም፡፡ በሰው ልጅ ላይ የተፈፀሙ ከባድና አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ናቸው!! (በዓይነታቸው የተለዩና ዘግናኝ ጥሰቶች!) ስንቱ ዜጋ ነው

በምርመራ ማዕከሎችና ማረሚያ ቤቶች በተፈፀመበት ድብደባ … ግርፋት … ቶርቸር … ጥፍር በፒንሳ መንቀል--- ብልት ላይ ውሃ ማንጠልጠል

---- ሰውነትን ጉንዳን ማስበላት ወዘተ---- ማሰቃያዎች ህይወቱን ያጣው … አካሉ የጎደለው … የመውለድ ፀጋውን የተነጠቀው … የሥነ ልቦና

ጉዳት የደረሰበት!! ኑሮና መተዳደርያው የፈረሰበት!!… ከአገር የተሰደደው!! (በሶማሌ ክልል ተገኘ የተባለውን የጅምላ መቃብር አስቡት!!) የሰው

ልጅ ከአውሬ ጋር ይታሰር ነበርም ተብሏል፡፡ ኧረ ምን ያልተደረገ አለ? (ገና ብዙ ይሰማል!!)
አብዛኞቹ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባዎች ደግሞ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች … ነበሩ፡፡ ለምን? እንዴት? የተባለ እንደሆነ --- ለመንግስት

ሥልጣን ስጋት በመሆናቸው ነው!! (ኢህአዴግ በ97 ምርጫ … እንዴት ከናዳው እንደዳነ አሳምረን እናውቃለን!)
እናላችሁ … በዜጎች ላይ እኒህን አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲያስፈፅሙ የነበሩና የፈፀሙ የመንግስት ባለሥልጣናት ናቸው ተጠርጥረው የተያዙት፡፡

(ከትግሬ ይሁን ከአማራ፣ ከኦሮሞ ይሁን ከሶማሊያ … ወዘተ ለውጥ የለውም!) እንኳንስ ጥብቅና ሊቆምላቸው የአገር ማፈሪያዎች ናቸው፡፡(“ሌብነት

ብሔር የለውም”! የሚለው ወቅታዊ አገላለጽ ተመችቶኛል!!) እናም አንዳንድ ምሁራን እርምጃውን ከብሄር ጋር በማያያዝ የሚሰጡት ጭፍን አስተያየት

አሳፋሪ ነው፡፡
በነገራችን ላይ በከፍተኛ ሙስናና በሰብአዊ መብት ጥሰት በተጠረጠሩ ላይ የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ያወጣውን

መግለጫ አንዳንድ ወገኖች መቃወማቸውን ጠ/ሚኒስትሩ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ የክልል መንግስታት ትክክል ያልመሰላቸውን መቃወም መብታቸው ነው

ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ግጭት የሚፈጠረው ህግ ለማስከበር ተባባሪ ሳይሆኑ ከቀሩ ብቻ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
በዚህ የጠ/ሚኒስትሩ ምላሽ እራሳቸው እርምጃውን የሚቃወሙት ጭምር ሳይገረሙ አይቀርም፡፡ በኢህአዴግ 27 ዓመት የሥልጣን ዘመን፤ የፌደራል

መንግሥቱን እርምጃ በመቃወም አንድ የክልል መንግስት (ህውሓት) መግለጫ ሲያወጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በተለያዩ የትግራይ ከተሞችም ህዝባዊ

ሰልፎች ተደርገዋል - የተቃውሞ! በ93 ዓ.ም የህውሓት ክፍፍል ጊዜ አንጋፋ የፓርቲው አመራሮች  ከሥልጣን መባረራቸውን አንዘነጋውም፡፡
በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትሩ፤ የክልሉ መንግስትና አንዳንድ ወገኖች “ህግ የማስከበር እርምጃው አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው” እያሉ የሚያቀርቡት

ውንጀላ ትክክል አለመሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል - ሰሞኑን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ በሰጡት ማብራሪያ፡፡
እናም ምን ለማለት ነው --- በሃገሪቱ ላይ የሚደረገውን ሪፎርም መቃወም መብት ቢሆንም ሃቁን መካድ ግን ያስተዛዝባል፡፡ በተለይ ምሁራንም እንደ

ፖለቲከኞች አድርባይ ሲሆኑ ማየት ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ወንጀልን ከዘርና ጎሳ ጋር ማያያዝ ህዝብንም አገርንም በእጅጉ ይጎዳል፡፡ የጠቀስኳቸው ወገኖች ግን

እንደማይሰሙኝ  አውቀዋለሁ፡፡ (አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ነው የሚባለው!)

Read 4595 times