Tuesday, 04 December 2018 12:01

“መንገድ የመዝጋት ቀን” ታወጀ? - የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጤና የጎደለው አመፅ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(5 votes)

• መንገድ መዝጋት? (ለዚያውም በብድር የተሰራ መንገድ? ከአፍሪካ አገራትም በታች፣በመንገድ እጦትና እጥረት የምትጠቀስ አገርውስጥ!)።
• በየወሩ፣ “ከተሽከርካሪ የፀዱ የመንገዶች ቀን እንደሚጀመር የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ” ይላል ዜናው - የምስራች ይመስል።
• መንገዶች በብድር የተሰሩትና በዶላር ወለድ የሚከፈልባቸው ለዚህ ነው? “ከመኪና ነፃ የወጡ ስፖርት መስሪያ አስፋልቶች”!
• “ኤሌክትሪክ የማጥፋት ቀን ተከበረ” የሚል ዜናም አስታውሱ - በዓመት አንድ ቀን ሳይሆን በቀን እየደጋገመ በሚጠፋበት አገር።
• በብድር መንገድ እገነባለሁ የሚል ዜናም ፕሮፖጋንዳም እንሰማ ነበር። ዛሬስ? ብድር የሚመጣው መንገድ ለመዝጋት! ለምሳሌ?
• ለታክሲዎች የተዘጉ መንገዶች - በአዲስ አበባ! ቢሊዮን ብሮችን የፈጁ መንገዶች ጥቂት አውቶቡሶች እንዲመላለሱበት!

  ከዓለም አገራት፣ በሕዝብ ብዛት 13ኛ፣... በስፋት 26ኛ የሆነች አገር፣ በመኪና ብዛት ስሟ በደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ያስቸግራል። የደረጃ ሰንጠረዡን ስንፈትሽ ከላይ ሳይሆን ከታች በኩል ከጀምርን ግን፣ በቀላሉ የኢትዮጵያን ስም እናገኘዋለን። በዓለም ውስጥ፣ መኪና ብርቅ የሆነባትና የመጨረሻው ደረጃ ላይ የተቀመጠች አገር፣ ኢትዮጵያ መሆኗን፣ ዘ-ኢኮኖሚስት ባለፈው ወር ባሳተመው የመረጃ መጽሐፍ ይገልፃል። (The Economist፣ POCKET WORLD IN FIGURES፣ 2019 Edition)።
ኢትዮጵያ ውስጥ፣ “አንድ መኪና ለ1000 ሰው” እንደሆነ መጽሐፉ ጠቅሶ፣ በመኪና እጦት 1ኛ ናት ብሏል። የእጦት 5ኛ ደረጃ ላይ የሰፈረችው ማላዊ ናት - “ሦስት መኪና ለ1000 ሰው”።
ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳና ላይቤሪያ ይሻላሉ - በእጦት ሰንጠረዥ ላይ እስከ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የመኪና ብዛታቸውና የየአገሮቹ የሕዝብ ቁጥር ሲነፃፀር፣ “አራት መኪና ለ1000 ሰው” ይሆናል። ከኢትዮጵያ አራት እጥፍ ማለት ነው።
23ኛ የእጦት ደረጃ ላይ ናት ኬንያ (17 መኪና ለ1000 ሰው)።
39ኛ የእጦት ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ግብፅ ደግሞ፣ 46 መኪና ለ1000 ሰው።
የእጦት አውራ ለመሆን እንደ ኢትዮጵያ፣ “ለ1000 ሰው፣ 1 መኪና ብቻ”። ይሄ እውነት ነው። ነገር ግን፣ የደካማነት ማረጋገጫ፣ የበታችነት ማሳያ፣ የጥፋተኝነት ማስረጃ አይደለም። ጥፋትና ድክመታችንማ ከዚህ የባሰ ነው።
የኢትዮጵያ አይነት እጦት፣ ችግር እና ድህነት፣... በዓመት ይቅርና በአስርና በሃያ ዓመታት፣ በሃምሳና ከዚያ በላይ በምዕተ ዓመታት ተደራራቢ ጥፋት ሳቢያ የሚከሰት እንጂ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ አይደለም። ይሄንን ወይም ያኛውን ሰውዬ ላይ የሚላከክና በጥፋተኝነት የሚያስፈርጅም አይደለም። በቃ፣ አገሪቱ ድሃ ናት። ይሄ ካለፉት አመታት ታሪክ የመጣ ውጤት ነው። ዋናው ጥያቄ፣ “ለወደፊትስ፣ ለመጪዎቹ ዓመታትስ?” የሚል ነው።
የእጦት ሰንጠረዥ ውስጥ 1ኛ መሆኗን አይተን፣... ለወደፊትስ ከእጦት ሰንጠረዥና ከውራ ደረጃ እንድትወጣና ኑሮ እየተሻሻ ወደ ብልፅግና ደረጃ እንድንሰግስ እንፈልጋለን ወይ? ከፈለግንስ ለግስጋሴ እንተጋለን ወይ? ወይስ...
በመኪና እጦት 1ኛ የሆነች አገር ውስጥ፣ መንገዶችን ከመኪና እንቅስቃሴ ማፅዳት በሚል መፈክር፣ እጦትን ወደሚያባባስ ቁልቁለት ለመንደርደር እንሽቀዳደማለን?
ለነገሩ፣... በመኪና እጦት ብቻ ሳይሆን፣ በመንገድ እጦትም ኢትዮጵያ የችግረኞች ሰንጠረዥ መደበኛ አባል ናት። ባለፉት ሃያ ዓመታት፣ በከፍተኛ የውጭ እርዳታና ብድር፣ በርካታ መንገዶች በፍጥነት የተሰሩ ቢሆንም፣ ገና ብዙም ፈቅ አላልንም።
በ1995 ዓ.ም የኢትዮጵያ የአስፋልት መንገዶች ርዝመት፣ ወደ 5ሺ ኪሎ ሜትር ነበር።
1995ዓ.ም    5ሺ ኪሎሜትር።
2000 ዓ.ም    6ሺ ኪሎሜትር።
2005 ዓ.ም    10ሺ ኪሎሜትር።
2010 ዓ.ም    15ሺ ኪሎሜትር።
እንግዲህ ተመልከቱ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ አስፋልት መንገድ በፍጥነት የተስፋፋ ይመስላል። በ15 ዓመታት ውስጥ ወደ ሦስት እጥፍ ማደግ፣ በእርግጥም ትልቅ ለውጥ ነው። ነገር ግን፣ መነሻው በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ ትልቁ ለውጥ፣ ከነባሩ የእጦት ሰንጠረዥ ለማላቀቅ የሚበቃ ለውጥ አይደለም።  
በሌላ አነጋገር፣ በአገር ስፋትና በሕዝብ ብዛት ሰንጠረዥ ላይ ከፍ ብላ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፣ በመንገዶች ስፋትና ርዝመት ዛሬም ድረስ ከዝቅተኛዎቹ ጋር የእጦት ወለል ላይ የምትቀመጥ ሆናለች።
መንገድ እጥረት፣ በተለይ በወጉ የተሰራ የአስፋልት መንገድ እጦትም የዚያኑ ያህል ከቀዳሚ ተጠቃሾች መካከል የምትመደብ ናት።
የኢትዮጵያ ስፋትና የሕዝብ ብዛት፣ በትንሽ ቢበልጥም፣ ከግብፅ ጋር ተቀራራቢ ነው። የአስፋልት መንገድ ርዝመታቸው ግን የሰማይና የምድር ያህል ይራራቃል። የኢትዮጵያ የአስፋልት መንገድ፣ 15 ሺ ኪ.ሜ ገደማ ነው። የግብፅ ከ125 ሺ ኪ.ሜ ይበልጣል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በታየው ፈጣን የአስፋልት መንገድ ግንባታ ብትቀጥል፣ እንዲያውም በእጥፍ ፍጥነት የአስፋልት ግንባታ ቢካሄድ እንኳ፣ የግብፅን ያህል ለመድረስ ከ50 ዓመት በላይ ይፈጅባታል።
የጋና የአገር ስፋት እና የሕዝብ ብዛት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር ሩብ ያህል ነው። የጋና የአስፋልት መንገድ ርዝመት ግን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሚስተካከል ነው። አጠገባችን ካለችው ኬንያ ጋር ማነፃፀር ይሻላል። በሕዝብ ብዛትና በስፋት የኢትዮጵያ ግማሽ ብትሆን ነው። በአስፋልት መንገድ ርዝመት ግን፣ ከኢትዮጵያ ትበልጣለች እንጂ አታንስም።
በሌላ አነጋገር፣ ከኬንያ በእጥፍ የባሰ የመንገድ ድህነት አለብን። ከጋና ደግሞ በአራት እጥፍ ይከፋል - የመንገድ እጦታችን።
ያ ሁሉ እርዳታና ብድር እየመጣም፣... ከፌደራል መንግስት በጀትም ሃያ በመቶ ያህሉ ለመንገድ ግንባታና ጥገና እየተመደበም፣... ባለፉት 15 ዓመታት የአገሪቱ የአስፋልት መንገድ ወደ ሦስት እጥፍ ቢያድግም፣... የእስከዛሬው ሁሉ ተደምሮም፣ በርዝመትና በስፋት የሚበልጡ አዳዲስ የአስፋልት መንገዶች እጥፍ ድርብ ብዙ ግንባታ ያስፈልገናል - ከድህነት የመላቀቅ፣ ከእጦት ሰንጠረዥ የመውጣት ጉዞ ለመጀመር።
ታዲያ፣ በተቃራኒው፣ አዝጋሚውን የመሻሻል ጅምር የሚያሳልጥ ሳይሆን የሚያሰናክል፣ አዳዲስ መንገዶችን የሚከፍት ሳይሆን የሚዘጋ፣ የመኪኖችንና የተሳፋሪ ዜጎችን ጉዞ የሚያቀላጥፍ ሳይሆን እንቅስቃሴያቸውን የሚያግድ ዘመቻ ማወጅ የጤና ነው? በጤና ሊሆን አይችልም።
ባለፉት ዓመታትና እስካሁን እንዳየነው ከሆነ፣ መንገዶች ተዘግተው ዜጎች የሚጉላሉት በሁለት ምክንያቶች ነው።
አንደኛ፣ በአመፅና በስርዓት አልበኝነት ዘመቻ ምክንያት ነው። ይሄ የተሟላ ጤንነትን አያሳይም። “መንግስት የዜጎች ነፃነት ይጥሳል” የሚል የተቃውሞ መፈክር ይዞ፣ “እኔም የዜጎችን ነፃነት እጥሳለሁ” ብሎ እንደመዝመት ነው። መንገድ መዝጋት፣ ሌላ ትርጉም የለውም። እንደ አፄ በጉልበቱ፣ አምባገነን መንግስት፣ “በማንአለብኘትና በጉልበት ዜጎችን ማንቀጥቀጥ እችላለሁ” እንደማለት ነው - የዜጎችን የእለት ተእለት ስራ ማናጋትና ኑሯቸውን የማመሳቀል የጉልበት ስልጣን። ይሄ ጤንነት አይደለም።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ በተቃወሰ መንግስትና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካኝነት መንገዶች ተዘጋግተው ዜጎች መንቀሳቀስ እንደሚያቅታቸው ታውቃላችሁ። የመንግስት መቃወስና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅስ የጤና ናቸው? አይደሉም።
የአስፋልት መንገዶችን ለመዝጋት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የታወጀው ዘመቻስ የጤና ነው? የዘመቻው ስያሜና በሚዲያ የተነገረበት ስሜት፣ ጤንነትን አያመለክትም። “ከተሸከርካሪ የፀዱ መንገዶች”? መንገዶች የተሰሩት ለተሽከርካሪዎችና ለእንቅስቃሴ እንደሆነ የተረስቶ፣... ተሽከርካሪዎች እንደ ቆሻሻና እንደ ብክለት የሚቆጠሩበት ጉደኛ ዘመን ላይ ነን።
ለመሆኑ፣ በብድር የተሰራና በዶላር ወለድ የሚከፈልበት የአስፋልት መንገድ ላይ፣... ለዚያውም በአንድ ከተማና በአንድ መንገድ ላይ ብቻ ሳይሆን በበርካታ መንገዶች ላይ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ ማገድ፣... ለዚያውም ለተወሰኑ ደቂቃዎች ወይም በአመት አንዴ ብቻ ሳይሆን፣  በየወሩ ቀኑን ሙሉ በርካታ መንገዶችን መዝጋት አስፈለገ? የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጤና የጎደለው ዘመቻ ለማወጅ፣ ሰበቡ ምንድ ነው?
“...ቦታውን የተለያዩ ጤናን ለሚያበለፅጉ የአካል እንቅስቃሴዎች ለመስራት፣ጤናማ የአኗኗር ዘዴ መልዕክቶችን ለማስተላለፍና ለተለያዩ የጤና ቅድመ ምርመራ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል “ከተሽከርካሪ ፍሰት የፀዱ መንገዶች ቀን”ይፋ አድጓል። (የፋናቢሲ ዘገባ ነው)።    
ኢዜአም፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለሙያ የሰጡትን መግለጫ በመጥቀስ ፅፏል።
“...ጤናማ  ባልሆነ አመጋገብ፣ በቂ እንቅስቃሴ ካለማድርግ፣ ሲጋራ ከማጨስ፣ አልኮል አብዝቶ ከመጠቀምና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዘው ሰው ቁጥር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።” (በኢዜአ የተዘገበ የባለስልጣን ገለፃ ነው። በዚህ አላበቃም።)።
በበሽታ የተያዘ ሰው ቁጥር እየጨመረ ነው? እና ምን ተሻለ?
“...መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ የጤናና አካል ብቃት ስፖርቶች የሚከናወኑ ይሆናል።” (ኢዜአ)።
አሃ፣... ለካ፣ እንዲህ አይነት “የምስራች ዜና” ለአዲስ አበባ ብቻ የተደገሰላት አይደለም።
“ይህ ስራ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ በሌሎች የክልል ከተሞች ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የተነገረው።” ሲል ኢዜአ ዜናውን ይጨርሳል።
መንገድ ካልተዘጋ፣ ስፖርት መስራት የማይቻል፣ የጤና ምርመራም የማይሞከር ጉዳይ ይመስልም?

Read 4612 times