Monday, 10 December 2018 00:00

“ሀበሻ የገና ኤክስፖ” የዛሬ ሳምንት ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ለገናና ለፋሲካ ኤክስፖ 65 ሚ. ብር በጀት ተይዟል
              
    የተለያዩ ትልልቅ ኤክስፖዎችንና የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ያዘጋጀው “ሀበሻ የገና ኤክስፖ” የዛሬ ሳምንት በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚከፈት የሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ኃላፊዎች አስታወቁ፡፡
የኩባንያው ኃላፊዎች በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሳፋየር አዲስ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የገናና የፋሲካ በዓል ኤክስፖን ለማዘጋጀት የኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት ባወጣው ጨረታ ሀበሻ ዊክሊ በ47 ሚ. ብር ጨረታውን ማሸነፉን ተናግረዋል፡፡
ለሁለቱ ኤክስፖዎች ጨረታና ዝግጅት 65 ሚሊዮን ብር ማስፈለጉንና በጀቱ መያዙን የገለፁት የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዶኒክ ወርቁ፤ ለ23 ቀናት በሚዘልቀው በዚህ ኤክስፖ ከ500 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበትና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይጎበኘዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
ለመዝናኛው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቻለሁ ያለው ሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን፤ በ23 ቀናት 23 የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ለታዳሚ የሚያቀርብ ሲሆን 100 ወጣትና አንጋፋ ድምፃዊያን፣ 7 የተመረጡ ተወዳጅ ባንዶች፣ 13 ያህል ዲጄዎች፣ አራት እውቅ ኮሜዲያኖችና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ሶስት የሰርከስ ቡድኖች ዝግጅቱን ያደምቁታል ተብሏል፡፡
ለህፃናት መዝናኛ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠ የገለፁት ኃላፊዎቹ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚቀርብ 9D ሲኒማ፣ የዳይኖሰሮች ትርኢትና በርካታ የህፃናት መዝናኛዎች የተሰናዱ ሲሆን ቁመቱ 12 ሜትር ሆኖ የሚፈጀው የሻማ ሰም 500 ኪ.ግ የሆነ የሻማ የገና ዛፍ በመስራትና ለእይታ በማቅረብ ኤክስፖውን የተለየ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡ በ23 ቀናት የተለያዩ አይነት ሽልማቶች ለታዳሚው እንደሚቀርቡና ተሳታፊ ድርጀቶች በፋብሪካ ምርት ዋጋ እቃዎችን ለሽያጭ እንደሚያቀርቡም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1593 times