Monday, 10 December 2018 00:00

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሊቋቋም ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 - “ኢህአዴግ አገራዊ እርቅና መግባባት አያስፈልግም ብሎ ጽንፍ ይዞ ሲከራከር ነበር”
    - “በሁሉም ዜጐች የሚከበሩና ስማቸው በመጥፎ የማይነሱ ዜጐች በኮሚሽኑ ውስጥ በአባልነት ይታቀፋሉ”
          
    ለግጭትና ቁርሾ ምክንያት የሆኑ ችግሮች፣ ምክንያቶችና የስፋት መጠናቸውን አጣርቶ እውነታውን በማውጣት ተመልሰው እንዳይመጡ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ፣ ተግባራዊ እርምጃዎችን የሚወስድና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመነጭ ገለልተኛና ነፃ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሊቋቋም ነው፡፡
የእርቀ ሰላም ኮሚሽኑን ማቋቋም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት የሚዘረዝረውና ለምክር ቤቱ የቀረበው መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ ኢህአዴግ አገራዊ እርቅና ይቅርታ አስፈላጊ አይደለም የሚል ጽንፍ ይዞ ሲከራከር መቆየቱን ይጠቁማል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ግለሰብ ፖለቲከኞች አገራዊ እርቅ ለአገራዊ ችግሮቻችን እንደቁልፍ መፍትሔ የሚታዩ ጉዳዮች እንደሆኑና ኢትዮጵያ ከገባችበት ፖለቲካዊ ችግር መሰረታዊ በሆነ መልኩ እንድትወጣ አገራዊ እርቅና መግባባት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በመጥቀስ ሲሟገቱ ቆይተዋል፡፡
ላለፉት በርካታ አመታት እርስ በርሳችን ስንዋጋ፣ አንዱ ሌላውን ሲበድልና ሲያቆስል በመቆየታችን የውጪ ወራሪዎች ካደረሱብን ሰብአዊና ቁሳዊ ጥቃት ይልቅ እርስ በርሳችን አንዱ በሌላው ላይ ያደረሰው ጉዳት በብዙ እጥፍ ይበልጣል ያለው መግለጫው፤ በሃሳብ ልዩነትና በብሔር ስም ተቧድነን ተገድለናል፤ ቂምን ተቋጥረናል፤ አንዱ ሲያሸንፍ ሌላው ቂም ይዞ ለበቀል ቀኑን ይጠብቃል፡፡ ይህንን የመረቀዘ የልብ ላይ ቁስል እንዲሽር ልናደርግ የምንችለው በአገራዊ የእርቅና የይቅርታ መንገድ ብቻ ነው ይላል፡፡
ባለፉት በርካታ ዓመታት ተበደልኩ የማይልና ያልተቀየመ የህብረተሰብ ክፍል አለመኖሩን የጠቀሰው መግለጫው፤ ሁሉም ተበደልኩ የሚል ስሜት ባለበት ሁኔታ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን በማቋቋም ወደ ሌላ ንትርክ ሳንገባ፣ አገራዊ የእርቅና የይቅርታ ፕሮግራም አውጀ፣ መርዛማውን ስሜት ማስወገድ አለብን ሲል አትቷል፡፡
ይህንን አገራዊ ፕሮግራም ለማከናወን የሚችሉ በሁሉም ዜጐች ዘንድ ክብርና ተቀባይነት ያላቸውና እስከ አሁን ስማቸው በየትኛውም ብሔር ወይም አካባቢ በመጥፎ የማይነሱ የተከበሩ ዜጐችን ስብስብ በአባልነት ያቀፈና እስከ ሶስት ዓመት የሚቆይ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ለማቋቋም መታቀዱም ተገልጿል። ኮሚሽኑ ከፍ ያለ ክብርና ተቀባይነት ያላቸው የሃይማኖት አባቶችን፣ የጐሳ መሪዎችን፣ ምሁራንንና የሀገር ሽማግሌዎችን የሚያካትትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወሰን በቂ ቁጥር ባላቸው ዜጐች የተዋቀረ ይሆናል ተብሏል፡፡
በዕርቀ ሰላም ኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደተመለከተው፤ በተለያዩ ጊዜያቶችና በታሪክ አጋጣሚዎች የሰብአዊ መብት ጥሰትና ሌላ በደል ተጠቂዎች የሆኑ ወይንም ተጠቂዎች ነን ብለው የሚያምኑ ዜጐች በደላቸውን የሚናገሩበት፣ በደል ያደረሱ ዜጐች ላደረሱት በደል በግልጽ የሚፀፀቱበትና ይቅርታ የሚጠይቁበትን ሁኔታ በማመቻቸት እርቀሰላም እንዲወርድ ያደርጋል፡፡ የተጠቂነት ስሜት ያላቸውን አካላት ልዩ ልዩ የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት ፊት ለፊት እየተገናኙ እንዲወያዩ የሚያደርግ ሲሆን ለልዩነቱ ምክንያት የሆነው ጉዳይ የሚወገድ መሆን አለመሆኑ፣ ድርጊቱ የተቋጨ ወይም አሁንም የቀጠለ መሆኑን ያጣራል፤ በአጠቃላይ ኮሚሽኑ በአገሪቱ ያለውን ችግር ምንነት፣ የበደሉን ሁኔታና የበዳዩን ማንነት፣ በደሉ የተፈፀመበትን አካል የሚያመላክቱ ጉዳዮች ላይ ምርመራ በማካሄድ እርቀሰላም እንዲፈፀምና በዳይም ይቅርታ ጠይቆ፣ ተበዳይም እውነታውን አውቆ፣ በእርቀሰላም ይቅር የሚባባሉበትንና በአንድነት አብረው የሚኖሩበትን ሁኔታ ያመቻቻል ተብሏል፡፡
ይኸው የኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ከተደረገበት በኋላ ጉዳዩ ለውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቷል፡፡  

Read 4931 times