Monday, 10 December 2018 00:00

ጠ/አቃቤ ህግ ህይወት እየቀጠፉ ያሉ ግጭቶችን እመረምራለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ግጭቶች በጊዜ አልባት እንዲበጅላቸው ተጠይቋል

   በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ህይወት እየቀጠፉና በርካቶችን እያፈናቀሉ ያሉ ግጭቶችን በጥልቀት እንደሚመረምር የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያስታወቀ ሲሆን ግጭቶች ለሃገሪቱ ስጋት ከመሆናቸው በፊት መቋጫ እንዲያገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችና አለማቀፍ ተቋማት አሳስበዋል፡፡
በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከሰሞኑ በተፈጠሩ ብሄር ተኮር ግጭቶች የሰው ህይወት መጥፋቱና መፈናቀል ማጋጠሙ የተገለፀ ሲሆን በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ (ምዕራብ ወለጋ) አዋሳኝ በተፈጠሩ ተመሳሳይ ግጭቶችም ሰዎች ሞተዋል፤ በርካቶችም ተፈናቅለዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የረድኤት ድርጅቶች ከፀጥታው አስተማማኝ አለመሆን ጋር ተያይዞ ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ እንዳልቻሉም አስታውቀዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ የተፈጠሩ ግጭቶችን ተከትሎም በዋና ዋና የኦሮሚያ ከተሞች መንግስት ፀጥታ እንዲያስከብር፣ ዜጎችን ከሞትና መፈናቀል እንዲታደግ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
የአለማቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በተለይ በምዕራብ ወለጋና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ብዛት በውል አውቆ ዕለታዊ ሰብአዊ ድጋፍም ማድረስ እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡
መንግስት በየአካባቢው እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን እንዲያስቆምና ሰብአዊ ድጋፍ የሚደርስበትን መንገድ እንዲያመቻች ድርጅቶቹ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ ከዚህ በኋላ መንግስት ግጭት ደርሶ ዜጎች ከተጎዱ በኋላ እርምጃ መውሰዱ ጥቅም የለውም፤ ግጭቶችን አስቀድሞ የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ ሲል አሳስቧል፡፡
በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በቅማንት የአስተዳደር ጥያቄ ምክንያት በተፈጠረ ግጭት የሰዉ ህይወት መጥፋቱን፣ የንግድ መደብሮችን ጨምሮ በርካታ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ያስታወቁት የክልሉ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ብ/ጀነራል አሳምነው ፅጌ የክልሉ መንግስት ሰላም የማስከበር ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል፡፡
ግጭቱ ባየለባቸው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሶስት ቀበሌዎች ማለትም ጉባይ ጀጀቢት ሌጫ እና ጮቃ ላይ ላለፉት ሶስት ዓመታት ድብቅ ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጥ እንደነበር የገለፁት የፀጥታ ቢሮ ኃላፊው፤ በአካባቢው ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ አራት አመታት መቆየቱን አስረድተዋል፡፡
ከሰሞኑ በአካባቢው ለተፈጠረው ግጭት መነሻ ምክንያት የሆነው ከዚህ ቀደም የአማራ ክልል ምክር ቤት 69 ቀበሌዎች በቅማንት አስተዳደርነት እንዲካተቱ ያፀደቀው ውሳኔን በመቃወም ተጨማሪ ሶስት ቀበሌዎች ሊሰጡን ይገባል በሚል መሆኑንም ብ/ጀነራል አሳምነው ፅጌ አስታውቀዋል፡፡
ግጭቱ እስከ ሐሙስ ሙሉ ለሙሉ አለመረጋጋቱን የጠቆሙት ምንጮች፤ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀል ወደ አዋሳኝ የትግራይ ክልል መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ችግሩን የፈጠሩት በቅማንት ስም የተደራጁ ቡድኖችና በገንዘብ ተደልለውና ከሌላ አካል ገንዘብ ተቀብለው ነው ያሉት የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው፤ በተለይ በጭልጋ አካባቢ ሰባት ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ የንብረት ውድመትና ሰብአዊ ቀውስ መፈጠሩን አልሸሸጉም፡፡
በአሁኑ ወቅትም የክልሉ ፀጥታ ቢሮ ከፌደራል መከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በመቀናጀት ፀጥታ የማስከበር ተግባር እያከናወነ መሆኑን እንዲሁም ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቀደም ሲል ለሶስት አመታት የድብቅ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ሆነው የቆዩትን ቀበሌዎች ወደ መንግስት መዋቅር ውስጥ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ብ/ጀነራል አሳምነው ፅጌ አስታውቀዋል፡፡
ግጭት ከጀመረ ከወር በላይ በሆነው በምዕራብ ወለጋ አካባቢም የመከላከያ ሰራዊት ተሰማርቶ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ያስታወቀ ሲሆን በዚህም ከ3 መቶ በላይ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አምስት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚገኙበት ሲሆን ከእነዚህም መካከል የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አንዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ አካባቢውን አረጋግቶ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ መንግስት እየገለፀ ሲሆን የረድኤት ድርጅቶች በበኩላቸው፤ ከትናንት በስቲያ (ሐሙስ) ባወጡት መግለጫ፤ አካባቢው እንዳልተረጋጋና ሰብአዊ ድጋፍ እንኳ ለማድረስ እንደተቸገሩ አስታውቀዋል፡፡
ሁኔታውን በትኩረት እየተከታተለ እንደሚገኝ የገለፀው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፤ በተለይ ወደ ምዕራብ ወለጋ ስለ ግጭቱ ምርመራ የሚያደርግ ቡድን ማሰማራቱን አስታውቋል፡፡
የተሰማራው ቡድን የወንጀል ድርጊቶችንና አይነቶችን እንዲሁም ፈፃሚዎች ላይ ማጣራት ያከናውናል፣ በቀጣይም ተጠርጣሪዎች ለህግ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
በሃገሪቱ እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች ዙሪያ የአቋም መግለጫ ያወጡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በበኩላቸው፤ መንግስት ከግጭቶቹ ጀርባ ያለውን ሴራ በትኩረት እንዲመረምር ጠይቀዋል። መንግስት ግጭት ከማጋጠሙ በፊት የቅድመ መከላከል ተግባር እንዲያከናውንም አሳስበዋል - ፓርቲዎቹ፡፡
በየጊዜው በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እና አቶ አስራት ጣሴ፤ በየጊዜው የሰው ህይወት እየቀጠፉ ያሉ ግጭቶች በጊዜ መቋጫ ካልተበጀላቸው፣ ለሀገሪቱ መፃኢ እድል ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ፡፡
ከዚህ አንፃር መንግስት የግጭቱን መነሻ በማጥናት፣ አፋጣኝ መፍትሄ ማበጀት እንዳለበትም አሳስበዋል - ፖለቲከኞቹ፡፡

Read 5750 times