Monday, 10 December 2018 00:00

“ዛሬ የሚከበረው የኢትዮጵያዊነት በዓል ነው” ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች በአል አስመልክቶ ለኢትዮጵያውያን መልዕክት ያስተላለፉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ “ቀኑ የኢትዮጵያዊነት በዓል ነው” ብለዋል፡፡  
“ውድ የሀገሬ ህዝቦች፤ይህ ቀን የኢትዮጵያዊነት ቀን ነው፤ ይህ ቀን የኃብራዊ አንድነታችን ማክበሪያ ቀን ነው፤ ይህ ቀን ሀገራችን አንድ፤ጸጋዎቿ ግን ብዙ መሆናቸውን የምንገልጽበት ቀን ነው፡፡” በማለት ነው ጠ/ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን የከፈቱት፡፡
በዓሉ ለይስሙላ የምናከብረው ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የምናደርግበት ትርጉም ያለው በአል ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ሁላችንም “ሆ” ብለን ወጥተን የኢትዮጵያዊነትን ልዩ ልዩ ጸጋዎች እያሳየን፣ እያከበርንና እየጠበቅን የምናከብረው የህብራዊ አንድነታችን መገለጫ፣ እንዲሁም ልዩነቶቻችን የአንድነታችን ፀጋ፣ አንድነታችንም የልዩነቶቻችን ተደማሪ ዋጋ መሆኑን የምንገልጥበት ታላቅ በአል ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያችን ከሰጠችን ፀጋዎች አንዱ ብዙም አንድም ሆነን ለመኖር መቻላችን ነው፤ ብዙውነታችን ሳይነጣጥለን፣ አንድነታችን ሳይጠቀልለንና ሳይውጠን በዝተን ኖረናል ብለዋል - ዶ/ር ዐቢይ በመልዕክታቸው፡፡
“ኢትዮጵያዊነት እንደ ኩሬ ውሃ ፀጥ ብሎ የተኛ አይደለም” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤በብሔረሰቦች መስተጋብር እንደ ባህሪ የሚታደስ እያደገ፣ እየዳበረና እየጠነከረ የሚሄድ የህዝቦች እሴት ነው ብለዋል፡፡
“በኢትዮጵያውያን መሃከል ያለው የቋንቋ ልዩነት ውበት መሆኑን ያወሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያን በጋራ ነው የመሰረትናት፣ በጋራ ነው ያቆየናት፣ በጋራ ነው የሞትንላት፣በጋራ ነው ያስከበርናት፣ በጋራ ነው እዚህ ያደረስናት” ሲሉ የእርስ በእርስ ጥላቻ፣ መገፋፋትና መራራቅ ቦታ እንዳይኖራቸው ተማፅነዋል፡፡ “መገፋፋትና መራራቅን የሚዘሩብንን ኩሩው ባህላችን አይታገሳቸውም፤ የዘሩትን እንነቅላባቸዋለን እንጂ እንዲያበቅሉት አንፈቅድላቸውም” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤”የሚለያዩን ሲመስላቸው ይበልጥ እንደመራለን፣ የተቃረንን ሲመስላቸው ይበልጥ እንደ ድርና ማግ ተሳስረን አንድ ሻማ እንሆናለን” ብለዋል፡፡
 በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በበአሉ ዋዜማ፣ ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 140 የ6ኛ ክፍል ተማሪዎችን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ መሪዎች የሚሆኑት የዛሬ ታዳጊዎች፤በልቦናቸው ቅንነትና ሰብአዊነትን እንዲያበለፅጉ መክረዋል። ከታዳጊዎች ጋርም በቤተ መንግሥቱ የተለያዩ ክፍሎች ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የማስታወሻ ፎቶግራፍም ተነስተዋል፡፡

Read 5711 times