Print this page
Monday, 10 December 2018 00:00

“አዬ ያ አስተማሪ ያለበት አባዜ አስተዋይ ተማሪ የጠየቀው ጊዜ!” የጥንት ግጥም

Written by 
Rate this item
(11 votes)

 የዛሬውን ርዕሰ - አንቀፅ ለየት ከሚያደርጉት አንዱና መልኩንም ይሁን ገበሩን ልዩ የሚያደርገው ተረቱ በትርክት ዓይነት አለመቅረቡ ነው፡፡ ታዲያ በምን ሊቀርብልን ነው መባሉ አይቀርም፡፡ መልሱ በግጥም፣ የሚል ነው! በማን ግጥም? በፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ መንግሥቱ ለማ፡፡ የመንግሥቱ ለማ ግጥምን የመረጥነው ተራኪ በመሆኑ ነው፡፡ እንደሚመች አቅርበነዋል፡፡
የአንበርብር ጐሹ ሞት
እስቲ ላነሳሳው አንበርብር ጐሹን
በደራ አደባባይ የወደቀውን
እሱስ ሆኖ አይደለም ታሪከ - ቅዱስ
መጽደቋንም እንጃ ያች የአምበርብር ነብስ!
የሚያዘወትራት የአንበርብር ወዳጅ
ነበረችው አንዲት ጠይም ቆንጆ ልጅ፡፡
አንድ ቀን በምሽት፣ ደጃፉን ቢመታ
ወይ የሚለው አጣ፣ ገጠመው ዝምታ
ደጋግሞ ቢጥርም አሊያም ቢለምን
ሌላ ሰው ወስዶታል የሱን ቦታውን
በንጉሡ ብትለው ሥራዬን ልሥራበት
ለንጉሡ ተመኛት ለዚያን ቀን ሌሊት!
ይሄውም ሆነና ዋነኛ ጥፋቱ
አርባ ጅራፍ ሆነ ህገኛ ቅጣቱ!
እየተገረፈ እዚያው ግጥም አለ
ጅራፉም እድሜውም ሠላሳን ሳይሞላ!
ከተሰበሰቡት ከተመልካቾቹ
የልብ ድካም ነው አሉ ከፊሎቹ
ዓለም እንደዚህ ናት፤ አሉ ፈላስፎቹ፡፡
    ኧረ ስንቱ ስንቱ፣ ናቸው የሞቱቱ
    ለንጉሣቸው ክብር፣ ለባንዲራይቱ!!  
                (መንግሥቱ ለማ)

***
ለንጉሣቸው፣ ለባንዲራቸው፣ ለሀገራቸው፣ ለራሳቸውም የሞቱ እልፍ አዕላፋት ናቸው፡፡ ሆኖም ዕውቅና የሚሰጣቸው ቀርቶ የሚናገርላቸው፣ የሚዘምርላቸው የለም፡፡ አስከፊው ነገር ይህ በመሆኑ የሚሳቀቅም፣ የሚፀፀትም፣ የሚዘገንነውም የለም፡፡ በእኛ አገር ከቀደሰው ጋር ለመቀደስ፣ ማረስ ከጀመረው ጋር ለማረስ፣ ከተኮሰው ጋር ለመተኮስ ዝግጁ ያልሆነ ማንም የለም፡፡ ችግሩ ማን ይጀምርለት? ነው! “እድመቱ አንገት ላይ ማን የማትጊያውን ቃጭል ይሠር?” ነው፡፡
ለአንድ አገር፤
አንድ ቀዳሽ
አንድ አራሽ
አንድ ተኳሽ
ያስፈልጋል ይላሉ አበው፡፡ ጠቢቡ በሃይማኖትም በተሐድሶም ጠቃሚ ነው!! ቀዳሹ ውስጥ ምሁር አለ፡፡
አራሽ በምግብ ራሳችንን እንድንችል ዋስትና የሚሆነን አምራቻችን ነው!! የምርት ጀግና ነው፡፡
ተኳሹ፤ አገር ድንበር ጠባቂያችን፣ ጀግናችን ነው!
ያለነዚህ ሶስት አውታሮች በሰላም፣ በመረጋጋትና በልበ - ሙሉነት መጓዝ አዳጋች ነው፡፡
በሰላም ውስጥ ዕርቀ - ሰላም አለ፡፡ ብሔራዊ መግባባት አለ፡፡ በመግባባት ውስጥ ልማትና ዕድገት አለ፡፡ የጤና ልማት፣ የትምህርት ልማት፣ የፍትሕ ልማት፣ የዲሞክራሲ ልማት፣ የማህበራዊ ልማት ወዘተ የመግባባት ልጅ ልጆች ናቸው፡፡
ማናቸውም ዕድገትና እንቅስቃሴ የየራሱ እንቅፋት አለው፡፡
“…የጓሮ ጐመን ሲፈላ
አጥፊ ትሉን እንዲያፈላ!”
እንዳለው ነው ሎሬት ፀጋዬ፡፡ እንቅፋቶቹ፤ በጐሣ ግጭትም፣ በሙስናም ይምጡ፣ በመማር ማስተማርም ሆነ በነዳጅ እጥረት ወይም በሥርዓተ- አልበኝነት፤ መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ህብረተሰቡ ሊጋተራቸው ይገባል፡፡ ተጠያቂው መጠየቅ አለበት፡፡ አዋቂና በሳሉ መጠየቅ አለበት፡፡
“አዬ ያ አስተማሪ፣ ያለበት አባዜ
አስተዋይ ተማሪ በጠየቀው ጊዜ” የሚለው የጥንት ግጥም ትርጉምና ፋይዳ የሚኖረው እዚህ ላይ ነው!!

Read 8134 times
Administrator

Latest from Administrator