Monday, 10 December 2018 00:00

ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የሚገፈትረው የህወሓት ፖለቲካ

Written by  ሚለር ተሾመ (በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር)
Rate this item
(3 votes)

 ይህን በወቅታዊ የአገራችን ማህበረ-ፖለቲካ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን መጣጥፍ እንዳዘጋጅ መነሻ የሆኑኝ ሦስት አበይት ምክንያቶች ናቸው፤ እነሱም በቅርቡ በህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የተሰጠው መግለጫ፣ የህወሓቱ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ከኤልቲቪ (LTV) ሾው አዘጋጅ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስና ከቀድሞ የስራ ባልደረባዬ (የህወሃት ደጋፊ የሆነ) ጋር በማህበራዊ ሚዲያ (Facebook) የነበረኝ ውይይት ናቸው፡፡ በእኔ አረዳድ፤ ሦስቱም በአመለካከታቸው በሚከተሉት ነጥቦች ከሞላ ጎደል ይስማማሉ፡-
በዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመራውና እንደ አዲስ የተዋቀረው መንግሥት፤ ህግን ለማስከበር የሚወስደው እርምጃ የትግራይ ህዝብን ለማዳከም እንደሆነ፣ እንዲሁም
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ከአማራ ክልል የሆኑት እና በማህበራዊ ሚዲያ ህወሓትን በመተቸት ሀሳባቸውን የሚከትቡ አክቲቪስቶችና ግለሰቦች፣ ሀቅ/እውነት ሳይኖራቸው በትግራይ ህዝብ ጥላቻ ብቻ የሚነዱ ናቸው።
በግሌ ሀሳቦቹ በአመክንዮ ሲፈተሹ ውሃ የማይቋጥሩ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ድምዳሜዎቹ መሬት ላይ ያለ ሀቅን ክዶ፣ የፖለቲካ ትርፍ ከማግኘት ባለፈ ታሪክን፣ ተፈጥሮንና ኢትዮጵያዊ ባህልን አውቆ በመዘንጋትና በመሸሽ የተቋጠሩ ይመስሉኛል፡፡

የኢትዮጵያዊ ሰብዕና ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሥነ ልቦናዊ መሠረቶች
ኢትዮጵያዊ ባህል(ማንነት) አለ ወይም የለም የሚለው አከራካሪ ቢሆንም፣ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ባህል(ማንነት) አለ ከሚሉት ጋራ ሀሳብ እጋራለሁ፤ ለዚህ መሠረቱ ደግሞ የረጅም ዘመን የሥነ መንግስት ታሪክ አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ዋናው ነው።
በርካታ ጸሐፍትና የታሪክ ሊቃውንት እንደጻፉት፤ የኢትዮጵያ የጥንት ስልጣኔ የመንፈሳዊ ስልጣኔ ነው፤ የቁሳዊ ስልጣኔ አልነበረም። የመንፈሳዊ ስልጣኔው አሻራ የሆኑት ደግሞ ፈሪሃ እግዚአብሄር፣ የፈጣሪ መንገድ የሆኑትን ሃይማኖቶችን አለመዳፈር፣ ለህግ መገዛት፣ ሥርዓተ መንግስትን ማክበር፣ ውለታ አለመርሳት፣ ለይቅርታና እርቅ ዋጋ መስጠት፣ ይቅር ባይንና አስታራቂን ማክበር፣ በራስህ ላይ እንዲሆን የማትፈልገውን ሌላው ላይ አለማድረግ፣ አለመስረቅ -- ከብዙ በጥቂቱ ናቸው። የተጠቀሱት መልካም እሴቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ የታሪኩ፣ የባህሉ፣ ትውፊቱ፣ እምነቱ፣ መሠረት የሆኑ በአጠቃላይ የኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና ወይም ተክለ ሰብዕና መገለጫዎች ናቸው።
ዛሬ ላይ የጀመርነው የለውጥ ሂደት ማጠንጠኛው እነዚህ እየተሸረሸሩ ያሉ ኢትዮጵያዊ ማንነቶችን በመጠበቅ ነው፤ ከተጀመረው አገራዊ ለውጥ አንጻር የህወሃት አመራሮችና ደጋፊዎች ሚና ምን መሆን እንዳለበት ለመረዳት ይረዳን ዘንድ፣ በፖለቲካው ምህዳር ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አላቸው ያልኳቸውን ሶስት ባህላዊ እሴቶች ያወያየን ዘንድ በወፍ በረር ለመዳሰስ እሞክራለሁ። እነሱም፡- የይቅርታና በቀል ጉዳይ ከባሕላችን አኳያ፣ ልጆች በማህበራዊ ግንኙነት ያላቸውን ሚና እንዲሁም አብሮ የመኖር ጥበብ እሴቶች ከፖለቲካችን አንጻር የሚሉ ናቸው፡፡

የይቅርታና በቀል ባህላችን.....
ሁለንተናዊ ኑሯችን ከባህል ተጽእኖ ነፃ ሊሆን አይችልም፤ ፖለቲካችን፣ ማህበራዊ እሴቶቻችን፣ ስነ-ልቦናዊ ውቅራችን በባህላችን የታነፀ እንደሆነ እንረዳለን። ኢትዮጵያውያን ለፍትህና ለክብራቸው አብዝተው እንደሚጨነቁ አያሌ የውጭ አገራዊ ጸሐፍት ይገልጻሉ፡፡ ፍትህ ለማግኘትና ክብርን ለማስጠበቅ ደግሞ የይቅርታና በቀል ክዋኔ ይጠቀሳል። በተለያዩ ብሔረሰቦች ሥነ ሥርዓቱ ቢለያይም የሚከወንበት አላማና ሂደት ከሞላ ጎደል ተመሳስሎሽ አለው፤ አላማው በሰላም ለመኖርና አጥቂና ተጠቂ እንዳይኖር እንደሆነ ይታመናል፤ እስቲ በየዐውዱ እንመልከተው፡-
ዐውድ 1፡-  አንድ ግለሰብ ሌላውን አውቆም ይሁን ሳያውቅ ቢገድል የይቅርታና በቀል አንኳር ሂደቶች እንደሚከተለው ይሆናል፡-
ገዳይ በሰራው ስራ ተፀፅቶ ከሟች ቤተሰብ ዓይንና አካባቢ ይሰወራል፤ ድሮ ድሮ ጫካ ይደበቃል....
የገዳይ ቤተሰብ ጉዳዩን እንደሰማ፣ በፀፀትና ከበቀል ጣጣ ስጋት ለመላቀቅ ሽማግሌ ወደ ሟች ቤተሰብ ይልካል....
ሽማግሌዎች ከብዙ መመላለስ በኋላ በሟችና ገዳይ ቤተሰብ መሀል ዕርቅ እንዲወርድ፣ ካሳ አስከፍለው ያስታርቃሉ.....
ከዚህ በኋላ ገዳይ ካሳ ጭኖ፣ በሽማግሌ ፊት ከሟች ቤተሰብ እግር ስር ወድቆ ይለምናል...
ይቅርታ በዚህ መልኩ ይጠይቃል፤ ይቅርታም ይደረግለታል፤ ይቅርታ ሳይጠይቅ በማን አለብኝነት የሚኖር ከሆነ ግን የሟች ቤተሰብ ወደ በቀል፣ ህብረተሰቡም ወደ ማህበራዊ ማግለል ቅጣት ይሄዳል፡፡
 ዐውድ 2፡- ልጅ የሰው ከብት ነድቶ ቤት ያመጣ እንደሆነ ቤተሰቡ ከብቱን ለባለቤቱ መልሰው፣ ልጃቸውን ቀጥተው፣ ይቅርታ እንዲጠየቅ ያደርጋሉ፡፡ ቤተሰቡ ይህን ካላደረገ ግን የነሱም ንብረት ነገ ይዘረፋል፤ ታዲያ ሌባ ልጃቸውን አሳልፈው ሰጥተው ከብቱን ካልመለሱ ለሌላ ውርደት ይዳርጋቸዋል፡፡ "የሌባ አባት፣ እናት፣ እህት..ጓደኛ" ወዘተ-- እየተባለ በየለቅሶ ቤቱ፣ በየሰርግ ቤቱ፣ በየገበያው በአሽሙር ይዘለፋሉ፤ ለዚህም አይደል “ባለጌን ካሳደገ የገደለ ፀደቀ” የተባለው፡፡
ከነዚህ ዐውዶች የምንረዳው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የይቅርታ ሥነ ስርዓት ሁለት መሠረቶች፡- ከልብ ተጸጽቶ ለይቅርታ መቅረብና የሰረቀውን ቆጥሮ ለተበዳይ (ለተዘራፊው) ካሳ መክፈል መሆኑን ነው፡፡ ታዲያ ይቅርታው ከዘገየ ወደ በቀል ምዕራፍ መታለፉ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይሄ ህዝብ መሬት፣ ጥሪት ብቻ አይደለም የሚያወርሰው፣ ደም፣ ሀቅንና ምንሽር ጭምር እንጂ!

ልጆች በማህበራዊ ግንኙነት ያላቸውን ሚና….
ልጆች በሁለንተናዊ ማህበራዊ ግንኙነት የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ሲባረኩ ቤተሰብ ከቤተሰብ ፣ ወዳጅ ከወዳጅ ያቀራርባሉ፤ ከፍ ሲል ደሞ በሞት የሚፈላለጉ ባላንጣዎችን ያስታርቃሉ። ባለጌ ልጅ ጎረቤት ከጎረቤት፣ ቤተሰብ ከቤተሰብ ያጣላል፣ እናቱን ከአባቱ ያጋጫል፣ ያፋታል። በግሌ የልጆች ፀብ ወደ ቤተሰብ ግጭት ከፍ ሲል ታዝቤአለሁ፡፡ ጎረቤት ከጎረቤት፣ ወንድም ከወንድሙ “ልጄን እንዲህ አልሽው/አልከው” በሚል ይኳረፋል፤ ይጋጫል፤ አልፎ ተርፎ ይቆራረጣል፡፡ ስለዚህ የልጆች ሁለንተናዊ ሰብዕናን ወላጆች ከስሜት ነፃ በሆነ መልኩ መመልከት ይገባቸዋል፡፡ ሀሳቤን ያጠናክርልኝ ዘንድ፣ አንድ ወዳጄ ያወጋኝን አስተማሪ ታሪክ ላጋራችሁ፡-
ልጁ ድብድብ አይሰለቸውም፤ እሱ ባለበት መንገድ ሴት አታልፍም፣ ገንዘብ፣ ጌጥ፣ ንብረት በጠራራ ፀሃይ ይነጥቃል፣ ፖሊስ ይደበድባል፣ ብቻ የማይሰራው ወንጀል የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ፖሊስ ጣቢያውን ቤቱ አድርጎታል፡፡ ታዲያ አባት ተደብድቦ ሲመጣ ሆስፒታል መውሰድ፣ ሲታሰር ፖሊስ ጣቢያ መመላለስ፣ ጉዳት ሲያደርስ ካሳ መክፈል ጥሪታቸውን አሟጦ፣ ስማቸውንም ካለቦታው አዋለ፡፡ በሚኖሩበት ከተማ አንቱ የተባሉ መምህር ናቸው እና ህብረተሰቡ “እሳት አመድ ወለደ”  እያለ ይተርትባቸው ጀመር። በእርግጥ የልጅ ስም ሲነሳ ያባት ስም መች ይቀራል። አባት ቢመክሩት፣ አባታዊ ቅጣት ቢቀጡትም አልመለስ አለ፣ ይልቁኑ ከባድ ወንጀሎች ላይ ይሳተፍ ጀመር። ስሞታው በዛ፣ አባት ታከታቸው። “ይሄ ልጅ ቀባሪ ሊያሳጣኝ ነው” ብለው ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ፣ “ከዚህ በኋላ ልጄ አይደለም” አሉ። ወደ ፍርድ ቤት ዘልቀው በቁማቸው ንብረታቸውን ለሌሎች ልጆቻቸው አወረሱ፡፡ በዚህም ስራቸው ከማህበረሰቡ ሳይነጠሉ በክብር ይኖራሉ፡፡ እናት ግን ሁሌም “ልጄ እንዲህ አያደርግም፣ ልጄ ደመ መራራ ስለሆነ እንጂ....” እያሉ የልጃቸው ተጠቂ የሆኑ ከሳሾችን ይራገማሉ፣ ይሳደባሉ፡፡ ልጁ ከሰው ቀምቶ የገዛላቸውን ልብስ አመስግነውና መርቀውት ይለብሳሉ፤ ከየት አመጣህ ብለው አይጠይቁም፡፡ ......በአጠቃላይ ስለ ልጃቸው ክፉ መስማት አይፈልጉም፤ የእናት አጀንት ሆኖ!.....ከዕለታት አንድ ቀን አመሻሽ ላይ፣ ከልጅነት እስከ እውቀት እየደበደበው፣ የያዘውን መጫወቻም ይሁን የሚበላ እየነጠቀው ያስቸገረውን አብሮ አደግ፣ እንደለመደው ፍቅረኛውን ሊነጥቀው ሲያስፈራራው፣ አብሮ አደጉ ከአባቱ ቤት በራፍ ላይ ገድሎ ጣለው፡፡ ታዲያ ሀገሬው እናቱን ወቀሰ፣ “ለዚህ የዳረገችው እሷ ነች”  እያለ ተሳለቀባቸው፡፡
ፖለቲካችንም ከዚህ የተለየ አይደለም። በብሔራችንም ይሁን በአስተሳሰባችን የሚመስሉን ፖለቲከኞች ልጆቻችን ናቸው። ሲያጠፉ እንደ አስቸጋሪው ልጅ አባት መጨከን ካቃተንና እንደ እናቱ ከሆንን፣ ፖለቲከኛ ልጆቻችን በቁማቸው ሞተው ይጣላሉ፡፡ ሀገሬው አይናችሁን ላፈር፣ በወንጀላችሁ ለህግና እጃችሁን ለካቴና ይላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ አብሮ የመኖር ጥበብና ፖለቲካችን........
የሰው ዘር ሁሉ መሠረቱ አዳም (አደም) እና ሄዋን (ሃዋ) ናቸው፤ ሁላችንም የአንድ አባትና እናት ልጆች ነን። በአንድ መንግሥት ሥር ለመኖር ግን የአዳምና ሄዋን ልጆች መሆናችን ብቻ በቂ አልነበረም፤ እናም አሁን ያለንበት ላይ ደርሰናል፤ አብሮነት ሁሌም እንደ አበባ እንክብካቤ ይፈልጋል። ካልተኮተኮተ፣ ካልታረመ፣ በቂ ውሃ ካላገኘ ይደርቃል። ስለዚህ አብሮ ለመኖር ጥበብ ያስፈልጋል።
ዛሬ ዛሬ ምንም ቢመናመንም እንኳን፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ሰፊ አብሮ የመኖር ጥበብ ዕሴቶች ባለቤት ነን፡፡ ለዚህም እንደ ዕድር፣ ዕቁብ፣ የጡት ልጅ፣ ሞጋሳ ወዘተ-- እድሜ ጠገብ ተቋማት አሉን፤ የትስስሮቻችን መርህ ደግሞ መከባበር፣ ሀቀኝነት፣ ፍትሀዊነት፣ መቻቻል ሆኖ ዛሬ ደርሰናል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የዘራኸውን ፍሬ አብዝቶ የሚያስታቅፍህ፣ ታጋሽ፣ የትናንቱን ደግ ጊዜ የሚያስታውስ፣ ይቅርታ ጠይቆ የመጣ ጠላትን የልብ ወዳጅ የሚያደርግ ህዝብ ነው። ይሄ ታላቅ ህዝብ፤ ለቅሶ ያልደረሰ ጎረቤቱ ጋር ለቅሶ አይሄድም። ለቅሶ ሄደህ ቀብር ብትቀር፣ ለለቅሶ መጥቶ ቀብር አይሄድልህም፤ ቤት ሲሰራ ደቦ ካላወጣህ ደቦ አያወጣልህም፤ ወልዶ ካልመረቅከው፣ አይመርቅልህም፤ “ብድር በምድር” የሚጫወት “ቁማርተኛ ህዝብ” ነው። ታዲያ ብድርህን የሚሚልሰው ስስታም፣ ጨካኝ፣ መጥፎ ሆኖ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም ማህበራዊ ዋስትናውን ማስጠበቂያ ዘዴው ስለሆነ እንጂ፤ “ፍቅር የጋራ ነው” የሚለውን እሳቤ ማሳያ መንገዱም ነው፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ይኸው ህዝብ፣5 እንጀራ እዝን ብታመጣለት፣ 500 እንጀራ የሚያመጣልህ፤ ትንሽ ዘርተህ ብዙ የምታጭድበት ቸር ህዝብ ነው። በዚህ መሀል እንከኖች ሲኖሩ በይቅርታ ይፈታል፣ ለቅሶ የበላ ሰው “ማሩኝ አጥፍቻለሁ” ቢል ይቅርታ አይከለከልም። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሰው ለቅሶ የበላ ሰው፣ ሰውዬው የእርሱን ለቅሶ ቢበላ “ለምን በላብኝ?“ ብሎ አይናደድም፣ መውቀስም አይችልም፡፡ ያሳፍረዋልና!!
አንዳንድ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች
 ልብ እንዲሉት የምሻው.....
እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያኮራ ከ3000 ዘመን ያለፈ የጋራ ታሪክ፣ በደምና ስጋ የተሳሰረ ወንድማማችነት፣ የቋንቋ፣ የኃይማኖትና የባህል ምስስሎሽ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ በመስዋዕትነት የተገነባች ሀገር ልጆች ነን፡፡ እንደ አንድ ታላቅ ታሪክና ታላቅ ህዝብ እንዳላት ሀገር፣ ብዙ ደግና ክፉ ጊዜያትን አልፈናል፡፡ ኢትዮጽያዊ ወንድማማችነትን ጠብቀን ለመኖር ዋጋ ተከፍሏል። አፄ ዮሐንስ በመተማ አንገታቸው ተቀልቷል፡፡ በአድዋና በባድመ ጦርነት አማራው፣ ኦሮሞው፣ ጉራጌው፣ ከምባታው ወዘተ--- ከትግራይ ወንድሙ ጋር ደሙን አፍስሷል፤ አጥንቱን ከስክሷል፡፡ ለዶ/ር ደብረፅዮን፣ ለአቶ ጌታቸው ረዳ እና ለቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ በልቤ ሙሉነት ማሳወቅ የምፈልገው፣ ማንም ኢትዮጵያዊ፣ የትግራይ ህዝብን አይጠላም፣ ያፈቅረዋል እንጂ፡፡ መውደዱንም በደም ዋጋ ከፍሎ አሳይቷል፡፡
በቀል ጎጂ ባህል ነውና መቅረት አለበት፡፡ በበቀል ፈንታ መንግስት ወንጀለኛን ለህግ ያቀርባል። አሁን ባለው የለውጥ መንገድ፣ ከልባቸው ተጸጽተው ይቅርታ ላልጠየቁ፣ የሰረቁትን ቆጥረው ላልመለሱ፣ ይልቁንም ሌላ ጥፋት ለማድረስ ለሚተጉ ግለሰቦች/ቡድኖች፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ያልሰጠው ከባህሉ የተነሳ ይመስለኛል። ታዲያ ይቅርታው በመዘግየቱ፣ የመንግስት ዋነኛ ተግባሩ ህግ ማስከበር ነውና ተጀምሯል፡፡ ወንጀለኛ ግለሰቦችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ግን፤ “ይሄ በቀል/የብሔር ጥቃት ነው” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በመጨረሻም.....
ከቅርብ ትውስታችን ብንጨልፍ እንኳ የአብሮነት ባህላችን አሻራ አልከሰመም፤ የጋሞ አባቶች ተንበርክከው ክፉዎች የወጠኑትን ሸፍጥ አከሸፉ፤ አባ ገዳዎች ለምስጋና አርባ ምንጭ ሄዱ። ወንድምነት በዋጋና ክብር አበበ፡፡ ነገር ግን አብሮ ለመኖር እነኚህ ሁሉ ዕሴቶቻችን፣ ነገን በጋራ ለመስራት መልካም ዕድል እንጂ ዋስትና አይደሉም፡፡
ኢትዮጵያዊው የፖለቲካ አክቲቪስት ጃዋር መሃመድ በአንድ ወቅት እንዳለው፤ የአዲሱ መንግስታችን ባህሪ በህወሓት መራሹ መንግስት አወዳደቅ ላይ የሚመሰረት ነው። ህወሓት ጊዜው ሳይመሽበት የሀገራችን እሴት የሆነውን ይቅርታ ሊጠቀም ይገባል፡፡ አንዳንድ የህወሓት ደጋፊዎችም ሆኑ የትግራይ ህዝብ፤ የአብሮ መኖር እሴቶችንና የልጆችን ሚና በመለየት፣ ነባራዊ ሀቁን መረዳት አለባቸው፡፡
ሃሳቤን ከመቋጨቴ በፊት ....ያባዘነኝ ጥያቄ ምን ነበር..?! ‘“የህወሓት ፖለቲካ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ገፍቶ የት ይደርሳል?!.” .....ከመድረሻው ፈጣሪ ይጠብቀን!!
ፈጣሪ ፍቅር፣ ማስተዋልና አንድነት ይስጠን!!
ከአዘጋጁ፡- ሚለር ተሾመ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር ሲሆኑ በመጣጥፉ  የተንጸባረቀው ሃሳብ ጸሃፊውን ብቻ የሚወክል መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2142 times