Monday, 10 December 2018 00:00

“ኦዴፓ የለውጥ ኃይል ስለሆነ ለመዋሃድ ወስነናል” አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ (የኦብኮ ሊቀ መንበር)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ቀደም ሲል በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ከኦሮሚያ ክልል ገዥ ፓርቲ ኦዴፓ ጋር ውህደት የፈፀመ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ ከተመሰረተ 22 ዓመታት ያስቆጠረው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) በተመሳሳይ ከኦዴፓ ጋር ውህደት ለመፈፀም ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ፓርቲው እንዴት እዚህ ውሳኔ ላይ ደረሰ? የኦብኮ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? ከኦዴፓ ጋር ምን አይነት ግንኙነት ይኖረዋል? በሚሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የፓርቲውን ሊቀመንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው በአጭሩ አነጋግሯቸዋል፡፡

    ከገዥው ፓርቲ ኦህዴድ/ኦዴፓ ጋር ለመዋሃድ እንዴት ውሳኔ ላይ ደረሳችሁ?
እንደሚታወቀው ላለፉት 22 ዓመታት ኦህዴድ/ኦዴፓን ስንቃወም ቆይተናል፡፡ በተለይም እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ የህዝብን ጥያቄ ሳይቀበል የቀረ ድርጅት በመሆኑ አምርረን ስንቃወመው የነበረ ድርጅት ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኦሮሞ ህዝብ ባደረገው ያላሰለሰ ትግል፣ በከፍተኛ መስዋዕትነት በኦህዴድ ውስጥ ለውጥ መጥቷል፡፡ ይሄን ለውጥ ያመጡት ደግሞ የ“ቲም ለማ” አባላት ናቸው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል ከኦሮሞ ህዝብ ጎን በመቆም የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እነ ዶ/ር ዐቢይ የሄዱበት ቆራጥነት የተሞላበት የመስዋዕትነት ጉዞ ለውጥ በመምጣቱ፣ ይሄ ለውጥም ወደ አማራ ክልልም ተሻግሮ ወደ ህዝቡ ልብ ውስጥ በመግባቱ፣ በአጠቃላይ በሃገሪቱ የምንፈልገው ለውጥ መጥቷል ብለን እናምናለን። ስለዚህ ኦዴፓን መቃወም አላስፈለገንም፡፡ ስለዚህ ተቀላቅለን አብረን ቀጣዩን ትግል መግፋት እንችላለን በማለት ነው ውሳኔውን ያሳለፍነው፡፡ አሁን የቲም ለማ አመራር የህዝብ ጥያቄ ይመልሳል የሚል ሙሉ እምነት አለን፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ በመሃከላችን ያለው ልዩነት ጠቧል ብለን ባሰብን ሰአት ከኦዴፓ ጋር ለመዋሃድ በጉባኤ ወስነናል፡፡ ከኦዴፓ ጋር ለመቀላቀል የሚያግደን የመስመርም የአቋምም ልዩነት የለንም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡
ኦዴፓ ተለውጧል ሲሉ መገለጫው ምንድን ነው?
እኛ ያየነው የግለሰቦቹን ለውጥ አይደለም። እነ አቶ ለማ የሚመሩት ኦዴፓ በጅማ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለውጡን ወደፊት ያስኬዳሉ ያላቸውን የአመራርና የአቅጣጫ ለውጥ አድርጓል፤ ስለዚህ እኛን እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰን በውስጡ እየፈጠረ ያለው ተጨባጭ ለውጥ ነው፡፡ አዲስ የመጡት አመራሮችም ዲሞክራሲን ወደፊት ለማስኬድ ጠንካራ አቋምና ቁርጠኝነት አላቸው የሚል ሙሉ እምነት በማሳደራችን ነው የመዋሃድ ውሳኔ ላይ የደረስነው፡፡ በኦዴፓ ውስጥ የመጣው ለውጥ መገለጫው የድርጅቱ የዲሞክራሲ ለውጥ ቁርጠኝነቱና ለዚህ ቁርጠኝነት ዝግጁ የሆነ አመራር መፈጠሩ ነው፡፡ የሃሳብ ልዩነታችን ስለተፈታ መቃወም ጥቅም የለውም፤ ብንደግፋቸው ለህዝባችን ይጠቅማል ብለን ነው የወሰንነው፡፡
ከዚህ ቀደም በእናንተና በኦህዴድ መካከል የነበረው  ልዩነት ምንድን ነው?
ሰፊ ልዩነት ነበረን፡፡ ኢህአዴግ የሚባለው ድርጅት የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር የማይሰማ፣ ጆሮ የለሽ ድርጅት ነው፡፡ ኦህዴድ ደግሞ የዚህ አካል ነበር፡፡ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እስረኛ ነበር፡፡ በዚህ የእዝ ሰንሰለት ውስጥ የህዝብን ድምፅ የሚሰማ አመራር አልነበረም፡፡ ይሄን ስንቃወም ነበር። በፖሊሲ ደረጃ ግን እኛ የተለየ ሃሳብ የለንም፡፡ ጥያቄው የመስመርና ለህዝብ ውግንና የመቆም ጉዳይ ነበር፡፡ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነበር፡፡ አሁን ግን ይሄ ለውጥ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር ያስችላል የሚል ፅኑ እምነት አለን፡፡
ለውጡ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብላችሁ ታምናላችሁ?
ለውጡ ከስር አልደረሰም፡፡ ገና ይቀረዋል፡፡ አሁንም ከላይ ያለውን ለውጥ ተቀብሎ ወደ ህዝቡ የሚያሸጋግር ኃይል ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን። ይሄን ለማድረግ ደግሞ ፓርቲ ከማብዛት የለውጥ ኃይሉን ማጠናከሩ ይበጃል፡፡ በሌላ በኩል፤ ህዝቡም 14 ሆናችሁ አትምጡብኝ፣ አንድ ሁኑ ብሎናል፡፡ ከዚህ በኋላ 14 ሆነን ህዝብ ዘንድ መቅረብ አንችልም፤ ይሄን ገፍቶ መቅረብ የህዝብን ጥያቄ አለመቀበል ነው፡፡ ስለዚህ ለውጡን ማገዝ አለብን፡፡
አብኮን ቀደም ሲል ፕ/ር መረራ ጉዲና ይመሩት የነበረ ድርጅት ነው፡፡ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ነው በምርጫ 97 ማግስት ወደ እናንተ የዞረው፤ ከዚያ በኋላም “የኢህአዴግ ተለጣፊ ናቸው” ስትባሉ ነው የቆያችሁት፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ምን ያህል በህዝቡ እንታመናለን ብላችሁ ታስባላችሁ?
ይሄ በአባባል ደረጃ ያለ ነው፡፡ በወቅቱ ፓርቲው በእኔ እንዲመራ የተደረገበት የራሱ ህጋዊ መሰረት አለው፡፡ በኦብኮ 2ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ፍትሃዊ ያልሆነ ምርጫ ተካሂዶ ነበር። በወቅቱ ምርጫ አይደለም የተካሄደው፤ የእርስ በእርስ መመዳደብ ነበር፡፡ ያንን ተቃውመን ነው ድምፃችንን ያሰማነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ አካሄድን ነው በወቅቱ የተቃወምነው፡፡ በኋላም ወደ ምርጫ ቦርድ ሄድን፡፡ በወቅቱ “ከእነዚህ ጋር አንነጋገርም፤ ተላላኪዎች ናቸው” ብለውን ነው፣ እነ ዶ/ር መረራ ከውይይቱ የሸሹት፡፡ በኋላ ጉዳዩ ወደ ህግ ሄዶ፣ በፍ/ቤት ነው ፓርቲውን እንድንመራ የተወሰነው። ለጉዳዩ ውሳኔ የሰጠው ህግ ነው፡፡
ውሳኔውም ቢሆን ጠንካራ ፓርቲዎችን ለማዳከም በገዥው ፓርቲ የተሸረበ ሴራ ነው ተብሎ ነበር--
እኛ ከሁሉም ጋር በኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ ተቀራርበን ስንሰራ ነበር፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄን ከሚቀበሉም ከማይቀበሉም ጋር ነበር የምንሰራው፡፡ አንድም ቀን ከኢህአዴግ ጋር በልዩ ሁኔታ የሰራንበት ቀን የለም፡፡ ከምርጫ በኋላ ለሃሜት የተዳረገው ምርጫ ቦርድና ፍ/ቤት ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ለኢህአዴግ ታማኝ ስለሆነ ፓርቲውን ነጥቆ ለእነ ቶሎሣ ሠጠ፣ ፍ/ቤቱም ነፃ ስላልሆነ ለእነ ቶሎሣ ሰጠ ሲባል ነው የከረመው፡፡ እኛ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብን ጥያቄ ይዘን፣ የፖለቲካ ስራችንን ነው ስንሰራ የኖርነው፡፡
ለምን ታዲያ እንደ ሌሎቹ የኦሮሞ ድርጅቶች የህዝብ ድጋፍና ተቀባይነት አላገኛችሁም?
እኛ የምንከተለው አካሄድ መንግስት ጥሩ ሲሰራ ጥሩ ሠርተሃል፣ ሲያጠፋ አጥፍተሃል የሚለውን ነው። በግልጽ የምናያቸውን ልማቶች ስንደግፍ ወያኔን ይደግፋሉ የሚል ነቀፋ ነው የተሰነዘረብን። እኛ ጭፍን ጥላቻና አስተሳሰብ አንፈልግም። የተሰራን ነገር ተሠርቷል ብለን፣ የጐደለውን እንዲሟላ እየጠየቅን ነበር የተጓዝነው። እነሱ መንገድ ሲሰራ “ወያኔ ጫካ ስለነበረ አሁን መንገድ አምሮት ነው የሠራው” ብለው ነው የሚመልሱት። እነሱ ለልማት፣ ለፀጥታ፣ ለደህንነት እውቅና ስለማይሰጡ “የወያኔ ተለጣፊዎች” የሚል ስም ተሰጥቶን ነበር፡፡ ይሄ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ራሱ መንግስትም ያውቃል፡፡ እኛ ወያኔ ሲያጠፋ፣ አንድም ቀን በቸልታ ያለፍነው ነገር የለም፡፡
ግን  ኦብኮ ለናንተ ከተሰጠ በኋላ በህዝብ ዘንድ የነበራችሁን ተቀባይነት አጥታችኋል?
አዎ ግን እኛ ብቻ አይደለንም ከ97 በኋላ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያጣነው፡፡ የተከፋፈለውም የኛ ድርጅት ብቻ አይደለም፡፡ ኦነግ እኮ በርካታ ቦታ ተከፋፍሎ የመጣው አንድ ሆኖ ወጥቶ ነው፡፡ ለምን ተከፋፈለ? አንድም የፖለቲካ ፓርቲ በህዝብ ዘንድ አመኔታ አልነበረውም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ዶ/ር መረራ ሊከበሩ ይችላሉ፤አቶ ዳውድ ሊከበሩ ይችላሉ፡፡ እኔም የትም ስሄድ “ሌባ መጣ” ብሎ ሠላማዊ ሠልፍ የወጣብኝ የለም፡፡ በሀገሬ አምቦ፣ በጥቁር ኢንጪኒ ተከብሬ ነው የምኖረው፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥም ተከብሬ ነው የምኖረው፡፡ የኦሮሞ ህዝብና ቄሮ ነው ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ነፃነቱን ያመጣው። ኦነግንም ከበረሃ ያመጣው የእነ አቶ ለማ መገርሣ ትግል ነው፤ ግንቦት 7ንም ከበረሃ ያመጣው የእነ አቶ ለማ መገርሣ ትግል ነው፡፡ እነ ዶ/ር መረራንም ከእስር ቤት ያስወጣው የኦዴፓ ትግል ነው፡፡ አሁን የኦሮሞ ህዝብ እየጠየቀ ያለው አንድነትን ነው እንጂ ኦፌኮን ወይም ኦነግን አሊያም ኦዴፓን አላለም፡፡ አንድ ሁኑ ነው ጥሪው፡፡ ይሄን ጥሪ ተቀብለን ነው፣ እኛም ኦዴፓን ለመቀላቀል የወሰንነው፡፡
ብዙ ጊዜ ፓርቲዎችን ከመዋሃድ የሚገታቸው የሊቀ መንበርነት ጉዳይ ነው፤ እናንተ ከኦዴፓ ጋር ስትዋሃዱ የስልጣን ድርሻችሁ ምንድን ነው?
እውነቱን ለመናገር እኛ የሊቀ መንበርነት ሱስ የለብንም፡፡ የሊቀ መንበርነት ሱስ ያላቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለ30 እና 40 ዓመት በሊቀ መንበርነት የመሩ ናቸው፡፡ እኛ የሚያሳስበን  የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ እንጂ የስልጣን ጉዳይ አያሳስበንም፡፡ በፖለቲካ ውስጥ አታስፈልግም ከተባልኩም ወደ ቤቴ ተመልሼ፣ ልጆቼን በሀገሬ ላይ በነፃነት አሳድጋለሁ፡፡ ስልጣን አልፈልግም። ስራ አስፈፃሚ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን የእነ “ቲም ለማ”ን የለውጥ እንቅስቃሴ ወታደርም ሆኜ ማገዝና መስዋዕትነት መክፈል እፈልጋለሁ፡፡ በእኔ ዙሪያ የተሠባሰቡ አመራሮችም ፍላጐታቸው ይኸው ነው፡፡   


Read 3783 times