Saturday, 08 December 2018 14:11

የበሽታውን ምንነት ማንም ሳያውቅላቸው የሞቱ ብዙ ናቸው

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው ሳምንት እትም ሴቶች ስለመሃጸን በር ካንሰር ምን ያህል ግንዛቤ አላቸው? ዝንባሌያ ቸው እንዲሁም አስቀድሞ በመከላከሉ ረገድ ምን ያህል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ? የሚለውን በደቡብ አካባቢ ከተደረገ ጥናት የተወሰነ ነገር አስነብበናል፡፡ ሴቶች በተለይም በኢት ዮጵያ ለሞት የሚዳርጋቸው የካንሰር አይነት የተለያየ ቢሆንም የማህጸን በር ካንሰር በገዳይነቱ በሁለተኛነት ደረጃ መመዝገቡን ጥናቱ ይፋ አድርጎአል፡፡
ሴቶችን ይጎዳሉ ተብለው የሚታወቁት የማህጸን ካንሰር አይነቶች ሶስት ናቸው፡፡
የማህጽን በር ካንሰር… (cervical cancer)፣ ይህ በተለይም በታዳጊ አገሮች (80%) ሰማንያ በመቶ ያህል የሚከሰት ሕመም ነው፡፡
ከሴት የዘር ፍሬ የሚነሳው (Ovary) ሌላው የካንሰር አይነት ሲሆን ይሄ ግን ባደጉ ባላደጉ አገሮች ተብሎ የማይለይ ሁሉም አካባቢ የሚከሰት ነው፡፡
ሌላው (Endometrial cancer) ኢንዶሜትሪያል ካንሰር የሚባለው ነው፡፡
የማህጸን በር ማለት ልጅ የሚወለድበት ወይንም የታችኛውንና የላይኛውን የማህጸን ከፈል የሚያገናኝ ነው። ይህ አካል ቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ ሊከሰት ያሰበውን የካንሰር ሴል አስቀድሞ ህመም ሳይከሰት እና ሕመሙም ወደ ካንሰር ሳይለወጥ ማከም ይቻላል፡፡ በእርግጥ ሕመሙ ገና ሲጀምር ምንም ስሜት ስለማይኖር ወይንም ሊታወቅ የሚችልበት መንገድ ስለማይኖር ማንኛዋም ሴት በተለይም እድሜዋ ከ25-30/አመት ከደረሰ በተወሰነው የጊዜ ገደብ ቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባታል። ይኼውም …በየአመቱ፤በሁለት አመት፤ ወይንም ከአምስት አመት በፊት ምርመራ እያደረጉ እራሳቸውን አስቀድመው ማወቅ ይገባቸዋል፡፡  
የማህጸን በር ካንሰር ወደካንሰር ከተለወጠ በሁዋላ ሴትየዋ በአካልዋ ላይ የምታያቸው ምልክ ቶች ይኖራሉ። አንዲት ሴት በብልት አካባቢ ፈሳሽ፤ ቁስል የመሳሰሉት ነገሮችን ካየች ሕመሙ ወደካንሰር ደረጃ ተለውጦአል ማለት ነው፡፡ የማህጸን በር ካንሰር በጊዜው ተደርሶበት ሕክምና ከተደረገለት የሚድን ሕመም ስለሆነ ሴቶች በእድሜያቸው 60 አመት እስኪሞላቸው ድረስ ጊዜውን ጠብቀው ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ነጻነት አበራ አሰፋ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እንደሰሩት ጥናት ለማህጸን በር ካንሰር የሚያጋልጡ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነሱም ከዚህ እንደሚከተለው ናቸው፡፡
የመጀመሪያው Human papilloma virus (HPV) ነው። ይህ ቫይረስ በመላው አለም ለሕመሙ መንስኤ እንደሚሆን የታመነ ሲሆን ይኼውም ከ11-12% ሲሆን ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ግን በከፍተኛ ደረጃ ማለትም ወደ 24% ይደርሳል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል ግልጽ ያለ የተመዘገበ መረጃ ባይኖርም በህብረተሰቡ ውስጥ ወደ 35.8/% የሚሆኑ ሴቶች በምስራቅ አፍሪካ በቫይ ረሱ ምክንያት ከሚከሰት ኢንፌክሽን ለህመም እንደተጋለጡ የሚያሳይ ሲሆን ይህ ኢትዮጵያንም የሚጨምር መረጃ ነው።
ሌላው ከባህላዊ ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ወደካንሰር እንዲያድግ በር የሚከፍቱ ባህላዊ ድርጊቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የልጅነት ጋብቻ ተጠቃሽ ነው፡፡ የልጅነት ጋብቻ በተለይም በገጠር አካባቢ የተለመደ ድርጊት ሲሆን በስፋት የሚስተዋለ ውም በኢትዮጵያ ሰሜናዊ አካባቢ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሴት ህጻናት ካለእድሜያቸው ካገቡ በሁዋላ በመጀመሪያ ልጅ ሲወልዱ የማህጸን በር ካንሰር የመታየት እድሉ ሰፊ ይሆናል። ጥናቶች እንዳረጋገጡትም በ16 አመት ወይንም ከዚያ በታች ባለ እድሜ የመጀመሪያ ልጅ ከወለዱ ሴቶች የተገኘው 2.5% ያህል ሲሆን ከዚያ በላይ እስከ ሀያ አመት እና ከዚያ በላይ ባሉት ሴቶች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ለማህጸን በር ካንሰር የመጋለጣቸው እድል 2.2/% በመሆን ዝቅ ያለ ነው፡፡ አልፎ አልፎም ከአንድ በላይ ጋብቻ በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ለቫይረሱ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ይሆናል፡፡  
ከብዙ ሴቶች ወይንም ወንዶች ጋር የወሲብ ግንኙነት መፈጸም ሌላው ለማህጸን በር ካንሰር የሚያጋልጥ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ግንኙነት ምክንያት በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ለሚተላለፉ በሽታዎች የመጋለጥ እድልም ይኖራል።
ከኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ በተለይም ከኤችአይቪ ኤይድስ ጋር በተገናኘ Human papilloma virus (HPV) የማህጸን በር ካንሰር እንዲከሰት የማድረግ እድል አለው፡፡ ፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት እንዳወጣው መረጃ ከሆነ 534.000/የሚሆኑት የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ያለ ሴቶች አብዛኞቹ በማህጸን በር ካንሰር ለመያዝ  የተጋለጡ ነበሩ፡፡
ድህነት፤ ከሰሀራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት እስከአሁን ባለው ሁኔታ ድህነት መገለጫቸው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የማህጸን በር ካንሰር እና ድህነት የሚያያዙበትን ምክንያት ሲያብራራ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ባላቸው ቤተሰቦች አስቀድሞ ሕመሙን ለመከላከልም ይሁን ህመሙን ካወቁት በሁዋላ እራሳቸውን ሙሉ በሙሉ የሚፈለገውን ወጪ ሸፍነው ለመታከም ዝግጁ ስለማይሆኑ የካንሰር ህመሙ ሲበረታ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህም የማህጸን በር ካንሰር የዝቅተኛው ማህበራዊና ኢኮኖሚ አካባቢዎች በሚል ይታወቃል፡፡
ንቃተ ሕሊና አለመኖር፤ የማህጸን በር ካንሰር በቅድሚያ ጥንቃቄ ከተደረገ መቶ በመቶ ሊድን የሚችል ሕመም ነው፡፡ በእርግጥ የአገልግሎቱ ብቃትና የሴቶቹ ንቃተ ሕሊና ሁኔታውን ይወ ስነዋል፡፡ በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ሰዎች ነገሮችን በግልጽ ከመ ናገር ወይንም ወደሕክምናው ከመሄድ እራስን ማቀብን እንደሚያወግዙና በግልጽ ከቤተሰ ብም ሆነ ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር መወያየት እንደሚገባ እንደሚያምኑ ያሳያል፡፡ በህብረ ተሰቡ ዘንድ ያለው የማህጸን በር ካንሰር እውቀት የተወሰነ እንደሆነም ጥናቱ አሳይቶ አል፡፡ በተለይም ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ የመጡ የጥናቱ አካላት ስለማህጸን በር ካንሰር እውቀቱም የላቸ ውም …ሰምተውም አያውቁም፡፡ ስለሕመሙ ሁኔታ ሲነገራቸው የተገኘው አሳዛኙ ምላሽ….ብዙ ሴቶች በተገለጸው ሕመም ሲሰቃዩ እንደነበርና የበሽታውን ምንነት ግን ማንም ሳያውቅላቸው መሞታቸውን  ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በዋና ከተማዋም በተደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደታየው ከሆነ በኤችአይቪ ቫይረስ ከተያዙ ሴቶች ውስጥ 1/3ኛ የሚሆኑት ብቻ ስለ ማጸን በር ካንሰር እንደሚ ያውቁ ተናግረዋል፡፡ ብዙዎቹም የማህጸን በር ካንሰር የማይድን በሽታ መሆኑን እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
የማህጸን በር ካንሰርን መከላከልና መኖር አለመኖሩን አስቀድሞ ማወቅ ለሴቶች ጤና እና ሕይወት ማዳን መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ ሴቶች የስነተዋልዶ ጤናን በሚመለከት በማህጸን በር ምክንያት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንዲችሉ እውቀታቸውን ማጎልበት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ጥናት አቅራቢዋ ነጻነት እንደሚገልጹት በኢትዮጵያ የማህጸን በር ካንሰርን በሚመለከት የተለያዩ ቅድመሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ ፕሮግራሞችን መዘርጋት አስፈላጊ ነው፡፡ በእርግጥ ስልጠና ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት እንዲሁም ፊት ለፊት እለት በእለት የሚያጋጥሙ ለሕሙማን ልዩ ትኩረት እንዲሰት የሚያስገድዱ ሁኔታዎች መኖራቸውና የተለያዩ የጤና ፍላጎቶችን ማሟላት ግድ ስለሚሆን ሊያስቸግር ይችላል፡፡
ይታገሱ ሀብታሙ አወቀ፤ ሳሙኤል ዮሀንስ አያንቶ እና ታሪኩ ላላጎ ኤርሳዶ ከማህጸን በር ካንሰር ጋር በተያያዘ ያለውን እውቀት ዝንባሌ እና ድርጊት በፈተሹበት ጥናታቸው እንዳመ ለከቱት ከሆነ ሴቶች በስነተዋልዶ ጤናቸው ጉዳይ የተሸለ እውቀት እንዲኖራቸው ፤ንቃተ ህሊናቸው እንዲዳብር ማድረግ እና መረጃ በቀላሉ እንዲያገኙ ማስቻል ያስፈልጋል። ይህንን የማህጸን በር ካንሰርን ምንነትና የመከላከሉን ተግባር በሚመለከት ከሌሎች ለእናቶች ከሚሰጡ መረጃዎች ጋር በማያያዝ በሆስፒታሎችም ይሁን በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካኝነት ለእናቶች መስጠት ይቻላል፡፡ ለምሳሌም በእርግዝና ክትትል ወቅት ወይንም ከቤተሰብ እቅድ ዘዴ ፕሮግራም ከመሳሰሉት ጋር አዛምዶ በማንሳት ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ይጠቅማል፡፡ በማህጸን በር ካንሰር ዙሪያ ሰፋ ያለ ጥናት ቢደረግም ጠቃሚ ስለሚሆን በዚህ ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ ሁሉ ቢያስቡበት መልካም ነው፡፡

Read 2324 times