Monday, 10 December 2018 00:00

ለአገራዊ ሰላምና ብልጽግና አገራዊ ምህረትና እርቅ

Written by  በግዛቸው መንግሥቱ (ከባሕር ዳር)
Rate this item
(0 votes)

(ከዘመነ ጥፋት ወደ ዘመነ ምህረት እንመለስ)
                 በግዛቸው መንግሥቱ (ከባሕር ዳር)


     ዘመነ ጥፋት
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በምድር ላይ ሊከሰት ወይም ሊፈፀም የሚችለው ማንኛውም ወንጀል በሃይማኖታዊ ትርጉሙ ደግሞ ኃጢያት ምንም ሳይቀርና ሳይጎድል በአሰቃቂ ሁኔታ በአገራችን ኢትዮጵያ  ተፈጽሟል፡፡ የግፍና በደል ጽዋ በአገሪቱ ምድር ሞልቶ በገፍ ፈሷል፣ ኑሮው እንደ እሬት መሯል፣ እንደ መርግ ከብዷል፣ ብዙ ባለስልጣናት እንደ ጊንጥ ይናደፉ፣ እንደ ሽፍታ ይዘርፉ ነበር፡፡ ከትንሽ ስርቆት እስከ ትልልቅ የአገር ዘረፋ፣ ከትንሽ ግርፋት እስከ አካል መጉደልና ሕይወት መጥፋት በዜጎች ላይ በቃል ሊገልጽ በማይችል ደረጃ ግፍ ተፈጽሟል። ደረጃው ይለያይ እንጂ ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር ያሉ ብዙ ሰራተኞች፣ ከቀበሌ ሊቀመንበር እስከ ፌደራል ያሉ ብዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት በአገር ዘረፋና ጥፋት ተሳትፈዋል ወይም ደግፈዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ከጣቢያ ፖሊስ እስከ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር፣ ከቀበሌ ሚሊሻ እስከ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና ጀነራሎች፣ ከቀበሌ ደህንነት እስከ ፌደራል ደህንነት ኃላፊ ድረስ ያሉ አካላት ህዝብን ገርፈዋል፣ ገድለዋል፣ አንገላተዋል፣ አንገት አስደፍተዋል፣ ከአገር አሰድደዋል፤ ፍትህንና ነፃነትን አድራሻውን አጥፍተው ቀብረዋል ወይም ወንጀሉን በመደገፍ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጂ ከሰፈር ሱቅ እስከ አስመጭና ላኪ ያሉ በርካታ ነጋዴዎች የንግድ ስርዓቱን አዛብተዋል፣ ግብር አጭበርብረዋል፣ ሰርቀዋል፣ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ አድርገዋል፡፡ በርካታ የሃይማኖት መሪዎች ከታች እስከ ላይ ባላቸው መዋቅር የህዝብና የአገር ሀብት ዘርፈዋል፣ በዝብዘዋል፣ ፍትሐዊነት በጎደለው አሰራር አማኙን አንገላተዋል፣ አሰቃይተዋል፣ አሳደዋል፡፡
በዚህ የጥፋት ዘመን ሞራልና ስነ ምግባር በመረሳቱ፣ እምነት በመላላቱና በመዘንጋቱ ፣ ከሀሳብና ከዕውቀት ይልቅ ለቁሳዊ ነገር ትኩረት በመደረጉ ሌብነት በአገሪቱ ነግሶ ዙፋን ላይ ወጥቷል፤ ሰርቆ ሀብት ማካበት እንደ ትልቅነት፣ ክብርና ዘመናዊነት ሲታይ ሐቀኝነትና ታማኝነት እንደ ኋላ ቀርነትና ጅልነት በመታሰቡና በመቆጠሩ ሌብነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየሰፋ መጥቶ በርካታ ሰው መርህ የለቀቀ፣ ህግና ስርዓት የጣሰ፣ ከአገሩና ከወገኑ ይልቅ እራስ ወዳድ ሆኖ ህዝቡንና አገሩን ሲዘርፍና ሲያስለቅስ ኖሯል፡፡ የዘረፋው መጠን መለያየት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ የሌብነት ዘመን ያልተደፈረ ተቋም፣ ያልተነቀነቀ በር፣ ያልተጣሰ ህግ፣ ያልተደፈረ የሃይማኖት ተቋም ማግኘት ያስቸግራል። ዘረፋውና ሌብነቱ ጭካኔ የተሞላበት በመሆኑ አገር ይለውጣሉ የተባሉ የልማት ድርጅቶች ግንባታ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፤ አገሪቱ በብድር እዳ በእዳ ሆና ለመውደቅ ስትንገዳገድ ቆይታለች፤ ዘመን ያለፈባቸውና በሕይወት ላይ አደጋ የሚያደርሱ የግብርና ግብዓቶች ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የማር ምርት ግብዓት ለአርሶ አደሩ ተሰራጭተዋል ወይም የአገር ኢኮኖሚን አድቅቀው ጥቅም ላይ ሳይውሉ ቀርተዋል፤ የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈበት መድኃኒት ለህዝብ ተሰራጭቷል ወይም ገበያ ላይ ውሏል፤ ድሃው ህዝብ ጎጆ መቀለሻ አጥቶ መሬት ያለ አግባብ ለሌቦች ሲሸጥና ሲለወጥ፣ በነጻ ሲሰጥና ሲታጠር ኖሯል፤ በመንግስት የተገነቡ ቤቶች በቤተ ዘመድና በገንዘብ ለተወሰነ ቡድን ሲተላለፉ ኖረዋል፣ ጠፍተዋል፤ ከፍተኛ የግንባታ ገንዘብና ቁሳቁስ ባክኗል፣ በድሃው ስም ተለምኖ የሚመጣ የእርዳታ ገንዘብ ተዘርፏል፣ በድሃው ስም ተነግዷል፣ የብድር ገንዘብ አገሪቱን እዳ ውስጥ ዘፍቆ የጥቂቶች ማድመቂያ ሆኗል፤ ህጻናት የወተትና የሻይ መጠጫ አጥተው በችግር እየተሰቃዩ ስኳር በኮንትሮ ባንድ ተዘዋውሯል፣ ተሰውሯል፤ ድሆች እየተቸገሩ ዘይት ሲደበቅና በስውር ሲሸጥ ኖሯል፤ ጉቦ የማይከፍሉ ዜጎች አንድ መታወቂያ ማግኘት ሲቸገሩ መታወቂያና መሸኛ በቀበሌ አጭበርባሪዎችና ደላላዎች በገንዘብ በመቸብቸቡ ሌቦቹ እስከ 10 እና 12 መታወቂያ ይዘው አገር ሲዘርፉ ኖረዋል፤ ከህጋዊ ነጋዴዎች ይልቅ ብዙ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ተጠቃሚና ሀብት ያካበቱ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ መንግስት ለስራ ማስኬጃ የሚመድበው ገንዘብ በራሱ አመራሮችና ቡችላ ባለሙያዎች ተመዝብሯል፤ የታቀዱ ስራዎች በተግባር ሳይከናወኑ በሪፖርት ብቻ ተሰርተዋል፤ የልማት ድርጅቶች አገርንና አካባቢን ከማልማት ይልቅ የግለሰቦችን ሆድ ሲሞሉና የልማት ስራዎችን ሲያጓትቱ ቆይተዋል፤ የህዝብ ሀብት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ፣ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በማንአለኝበት ተወስዷል፣ የአገር ሀብት ወደ ውጭ ሸሽቷል፣ ተዘርፏል፣ በየወደቡ ባክኗል፤ የልማትና የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊነት የጎደለው በመሆኑ አገር ለማፍረስ እንደ ንፋስ ሲወዘውዛት ቆይቷል፤ የልማት ድርጅቶች በግለሰቦች ፈቃድ ተሰርዘዋል ወይም ከታሰቡበት ክልል ይልቅ ወደ ሌላ ክልል ሂደው እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡
የሚገርመው ሌብነት ስር ከመስደዱ የተነሳ በዚህ ዘመን በብዙ ሌባ ነጋዴዎችና ሰራተኞች የመስሪያ ቤቶች ተፈላጊነትና ተወዳጅነት እንኳ የሚለካው በስራቸው ባህርይና አገራዊ ጠቀሜታ ሳይሆን በነበራቸው የዘረፋ አመችነትና የመዘረፍ አቅም ሆኗል፡፡ በዚህ አገር የመዝረፍ ሂደት የሰሞኑ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በርከት ያሉ የህወሓት አባላት የአንበሳውን ድርሻ ወስደው ሲዘፈቁበትና ሲዋኙበት የኖሩ ሲሆን የኦዴፓ፣ የአዴፓ፣ የደሕዲንና የአጋር ድርጅቶች ብዙ አባላትም ከደሙ ነጻ ሊሆኑ አይችሉም፤ አብረው ተነክረዋል፣ ለሌብነት ሥርዓቱ አጨብጭበዋል፡፡ የሚመሩትን ክልልና ህዝብ በአርአያነት ከመምራት ይልቅ ሞራሉና ልዕልናው የወረደ ሆኖ የሌብነት አስተሳሰብ እንዲዳብር መንገድ መርተዋል፤ ድሃ እያለቀና እየተሰቃየ ለባለሀብት ሲሰግዱና የአገር ሀብትን በህገ ወጥ መንገድ ለተወሰኑ ግለሰቦች ሲያስረክቡ ኖረዋል፤ እነርሱ በሀብት ደልበዋል፣ የአገርና ህዝብ ሀብት አባክነዋል። ብዙ ነጋዴዎችና ባለሙያዎች፣ ደላላዎች የዘረፋ ኔትወርክ ዘርግተው፣ በሐቅ መስራት ወንጀል እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ከተመሰረቱበት ዓላማ በተቃራኒው ቆመው ህዝብ አስለቅሰዋል፤ አገር በድለዋል፡፡  በዘመኑ ሌብነት በአገሪቱ ውስጥ ትልልቅ ስር ሰዶ ተንሰራፍቷል፣ ቅርንጫፉ አድጎ ቅጠሎቹ ለምልመዋል፣ ግንዱ ወፍሯል፣ ዘሩ ተባዝቶ በአገሪቱ ተሰራጭቷል፤ መስረቅ ክብር ሆኖ በአደባባይ ተመርቋል፤ እንደ ጀብድና ጀግንነት ታይቶ ለብዙዎች የውርደት ሳይሆን የክብር ካባ አልብሷል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት እንደ እባብ መርዙ በሚናደፈው ስመ ዲሞክራሲ፣ በአገራችን ኢትዮጵያ የደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግፍ በቃል ተዘርዝሮ የማያልቅ ሲሆን አእምሮ ሊያስበውና ሊሸከመው ይከብዳል። የገዥውን ፓርቲ እድሜ ለማራዘም በጨለማ ቤት የተገረፈውና የታሰረው፣ ብልቱ የተኮላሸው፣ ዘሩን እንዳይተካ የተደረገው፣ የማምከኛ ክትባት የተወጋው፣ ጥፍሩ የተነቀለው፣ እግሩና እጁ የተቆረጠው፣ ምላሱና ብልቱ በፒንሳ የተጎተተው፣ ተዘቅዝቆ የተገረፈው፣ ግብረ ሶዶም የተፈጸመበት፣ በሴት ልጅ ክብር ገላ ላይ በእንስሳዊ ስሜት ወንድ የተፈራረቀው፣ ክብር የሆነው ገላው እርቃኑን ሆኖ የተሳቀበትና ቆሻሻ የተጨመረበት፣ የተገረፈውና በአካሉ ላይ ግፍ የተፈፀመበት፣ ከአውሬ ጋር እንዲታገል የተደረገው፣ በዓላትን ሲያከብር በታቦትና በመስጊድ ፊት የተረሸነው፣ በአደባባይ የተጨፈጨፈው፣ ተናገር ተብሎ ስብሰባ ተጠርቶ በተናገረው በስውር ሲገደል የኖረው፣ ሀብትና ንብረቱን የተቀማው፣ እንዲሰደድ የተደረገው፣ ከስራው የተባረረው---- በዚሁ ዲሞክራሲ በሚቀነቀንበት የጨለማ ዘመን ነበር፡፡   
በዚህ ክፉና መራራ የበደል ዘመን የአማራ ገበሬ ቢሮክራት በሚል መሬቱን ተነጥቆ ቤተሰቡን እንዲበትንና እንዲሰደድ ተደርጓል፣ ያለውም የሌለውም የጦር መሳሪያ አምጣ እየተባለ ተገርፏል፤ ከእነ ቤተሰቡ ተሰቃይቷል፤ ሰርቶ የገዛውንና በባህሉ የክብሩና የዝናው መገለጫ የሆነውን መሳሪያ ተነጥቋል፡፡ ይህም የሆነው እንወክለዋለን ብለው በስሙ በተቀመጡት የስርዓቱ አስፈጻሚ የብአዴን አመራሮች ትዕዛዝ ነው፡፡ በአገሪቱ በተዘረጋው የስለላ ሰንሰለት መረብ የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነቱን አጥቶ፣ አገቱን ደፍቶ፣ ስሜቱን ገቶ እንዲኖርና እንዲሸማቀቅ ተደርጓል። በተለይ የመንግስት ሰራተኛው በቅርብ የስራ ኃላፊውና የህዋስ ተጠሪዎች ሳይቀር በሚደረግበት የማሸማቀቅና አንገት የማስደፋት ሂደት ማንነቱን አጥቷል፡፡
በዚህ የጥፋት ዘመን የተዛባና የልብ ወለድ ታሪክ ተደርሶና ተሰብኮ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ቂም ቋጥሯል፣ በመለያየትና መከፋፈል እስትራቴጂ በብሔር ግጭት በተደጋጋሚ ብዙ ሕይወት  ጠፍቷል፤ ህዝብ ከሚኖርበት ተፈናቅሏል፤ ብሔሮችን የሚያጋጩ ሰነዶች ተዘጋጅተው ተሰራጭተዋል፣ ጥላቻን የሚፈጥሩና የሚያባብሱ ሐውልቶች ቆመዋል፤ በሃይማኖቶች መካከል ግጭቶች እንዲፈጠሩ ተደርጓል፣ ሃይማኖቶች ተደፍረዋል፤ የምሁራን መፍለቂያ በሚባሉት ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀር ተማሪዎች በብሔራቸው እንዲጋጩና አንድነት እንዳይኖራቸው ሰፊ ስራ ተሰርቷል፤ የገዥውን ወገን የበላይነት የሚያንጸባርቁ ሙዚቃዎች ሲቀነቀኑ ኖረዋል፤ የብሔርተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራቸው ውስጥ የሚኖርን ህዝብና ብሔር በጠላትነት ፈርጀው፣ ማኒፌስቶ ቀርጸው በህዝብ ላይ በደል አድርሰዋል፡፡  
በመጨረሻም የበደልና የግፍ ጽዋው ሞልቶ በመፍሰሱ፣ የህዝብ ተቃውሞ ማዕበል አገሪቱን አጥለቅልቆ ወጥቷል፣ የተቃውሞ ሞገዱ አይሎ ጨቋኞችን ከስልጣን አስወግዷል፡፡ የህዝቡ እንባ እንደ ራሔል እንባ ከፈጣሪ ደርሶ ፈጣሪ በጥበቡ ከዘንዶው መካከል ዶ/ር ዐቢይንና መሰሎቻቸውን አስነስቶ ወደ ምህረት ዘመን መርቶናል፡፡

ዘመነ ምህረት
ዘመነ ምህረት ከተጀመረ ገና የ7 ወር ጨቅላና ጅምር ሲሆን በህዝብ ተጋድሎና እንባ፣ በአባቶችና እናቶች ጸሎትና ልመና፣ በፈጣሪ ረቂቅ ጥበብ፣ ፊት ለፊት በሚታዩት በዶ/ር ዐቢይና ስማቸው በማይነገርላቸው ከመጋረጃ በስተጀርባ ባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች፣ ፖለቲከኞችና ምሁራን ጥረት የተፈጠረ ነው። የተጀመረው ዘመነ ምህረት፤ የጥፋት ዘመን ቁርሾ ባይለቀውም፣ በጥፋት ዘመን እስር ቤቶችን ያጥለቀለቁ እስረኞች ተፈተዋል፣ የተሰደዱ ተመልሰዋል፣ የተጣሉ መታረቅ ጀምረዋል። ኢትዮጵያ ጎጆ ካወጣቻት ልጇ ኤርትራ ጋር ታርቃለች፣ የነጻት ነፋስ ነፍሷል፣ ፍትህ በፍትህ መንገድ ላይ መጓዝ ጀምራለች፤ ህዝብ ከስጋትና ተዐቅቦ ወጥቶ ለአገራዊ ለውጥ ድምፁን ማሰማት ጀምሯል፤ ወታደሩ መንገድ ላይ ዜጎችን ከመግደል ወጥቶ ሰላም ወደ ማስከበር ገብቷል፤ ፖሊስ መንገድ ላይ ያገኘውን ሁሉ ከመደብደብ ታቅቦ ፍትህ የማስከበሩን ስራ ጀምሯል። የፍትህ ተቋማት በጨለማ ቤት ንፁህን ዜጎችን ከማሰቃየት ወጥተው ለፍትህ ዘብ መቆም ጀምረዋል፣ ምህረትና ሰላም በአገሪቱ መሽተት ጀምሯል፤ የብሩህ ተስፋ ጭላንጭል ይታያል፡፡
በሌላ መልኩ ባለፉት 27 ዓመታት ስልጣናቸውን ተጠቅመው ከፍተኛ በደልና ግፍ ፈጽመዋል የተባሉ፣ በአገር ላይ ከፍተኛ ስርቆት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው፡፡ ወንጀለኞችን በህግ ቁጥጥር ስር የማዋሉ ሂደት የሚቀጥል ይመስላል፤ መቀጠልም አለበት፡፡ ይህ ተግባር ፍትህ የተጠማውን ህዝብ በጣም ሲያስደስት፣ ሌቦችና ጨካኞችን ግን በእጅጉ አስከፍቷል፡፡ ስለዚህ ይህ የምህረት ዘመን እንዲቀጥል፣ አገራዊ እድገትና ብልጽግና እንዲመጣ ፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ አገራዊ አስተሳሰብ በህዝቡ ዘንድ እንዲያድግ፣ ፍትህ እንዲረጋገጥ ምን ይደረግ? ለሚለው፤ የጥፋት ዘመንን በምህረት ዘመን መተካት፣ ጥፋትን በምህረትና ይቅርታ መደመስስ እንዲሁም አገራዊ እርቅ መፈጸም ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ከጥፋት ዘመን እንዴት ወደ ምህረት ዘመን እንመለስ?
1ኛ. ለወንጀሎች ምህረት ማድረግ   
ባለፉት ዓመታት ሞራልና ስነ ምግባር በመዝቀጡ የአገርና ህዝብ ሀብት ትስስር ፈጥሮ ሲዘርፍ የኖረን፣ የገዥውን ድርጅት እድሜ ለማራዘም ሲባል እንደ ስርዓት ተይዞ ከላይ እስከ ታች በተዘጋ ሰንሰለት የሰው መብት ሲረግጥና ሲያሰቃይ የኖረን የተጠራቀመና የደለበ በርካታ ወንጀለኛን በአንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋል፣ ፍትሐዊ ቅጣት መስጠት፣ በገፍ አስሮ መቀጠል፣ መመርመርና አገራዊ መግባባት መፍጠር አንደ ሀገር የሚከብድና የሚያስጨንቅ ጉዳይ በመሆኑ በተጠናና በተደራጀ መንገድ በጥንቃቄ በመመርመርና በመፈተሽ የምህረት አሰጣጥ ሂደቶችን ጠብቆ ምህረት ወደ ማድረግ ተግባር ቢገባ የተሻለ አገራዊ ጠቀሜታ ያስገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ምህረት ማድረግ ለኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃይማኖተኛ በመሆኑና እያንዳንዱ ሃይማኖት ምህረትና ይቅርታን የሚሰብክ፣ አንድነትና ፍቅርን የሚያስተምር በመሆኑ ለወንጀለኞች ወይም ኃጢያተኞች ምህረት ማድረግና የኋላውን ትቶ ወደ ፊት ለመራመድ የሚቸገር አይሆንም፡፡ ምህረት ማድረግ የህሊና ፈዋሽ መድኃኒት፣ የሰላም በር መክፈቻ ቁልፍ፣ የፍቅርና የይቅርታ ምንጭ፣ የጥላቻና መለያየት ማርከሻ መድኃኒት፣ የጽድቅ መንገድ፣ የፀፀት ማምከኛ ፈንጂ፣ የአንድነትና የልማት ገመድ፣ የሃይማኖት ማገር ነው። ስለዚህ በእኔ እምነት፤ ሃይማኖተኛ ለሆነውና ንስሃንና ምህረትን ለሚያምነው ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለወንጀለኞች ይቅርታ አድርጎ አገሩን ወደ ማሳደግ ዘመቻ ማስገባት ያን ያህል አስፈሪና ከባድ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም የምህረት አሰጣጥ ሂደቱን  እንደሚከተለው መፈጸም ይቻላል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ፣ ሀብት የዘረፉና ግጭት እንዲፈጠር ያደረጉ ግለሰቦችን ከቀበሌ እስከ ፌደራል ድረስ በህግ በቁጥጥር ስር ማዋል፤
የኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ እንደሚያውቀው በዘመነ ጥፋት ከቀበሌ እስከ ፌደራል፣ ከከተማ እስከ ገጠር ያሉና የነበሩ ብዙ አመራሮች፣ ብዙ ነጋዴዎች፣ ብዙ ሰራተኞች በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ህዝብን በማሰቃየትና ግጭት በመፍጠር፣ በመዝረፍና በመሳሰሉት ተሳትፈዋል፣ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ የተሳተፈውን ሁሉ በህግ ቁጥጥር ስር ማዋል ከባድ ከመሆኑም በላይ የወንጀለኛው ብዛት ሌላ የአንድ ትልቅ ሐገር ህዝብ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ጥንቃቄ በተመላበት መንገድ በማጣራትና በመመርመር፣ ከፍተኛና ከባድ በደል የፈጸሙና የሰብዓዊ መብጥት ጥሰት ያደረሱ፣ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ሕይወት እንዲጠፋና ህዝብ እንዲፈናቀል ያደረጉ፣ ከፍተኛ ዘረፋ የፈጸሙ የትኛውም ብሔር ወይም የፖለቲካ ድርጅት፣ የትኛውም ሃይማኖት ወይም ተቋም አባል የሆኑ ወንጀለኞች በየደረጃው ባሉ የፍትህና የፀጥታ አካላት ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ በቁጥጥር ስር ውለው፣ በህግ ፊት ሊቀርቡ ይገባል፡፡ ህዝቡም ከብሔርተኝነትና ወገንተኝነት ወጥቶ በእውነት ላይ ተመስርቶ፣ ወንጀለኞችን በመጠቆም ለህግ አሳልፎ መስጠት ይኖርበታል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ዋና ዋናዎቹ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሂደት በትኩረትና በጥበብ ተመርቶ ወንጀለኞች በጥፋታቸው እንዲቀጡ፣ ህዝብና አገር እንዲካስ፣ ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን ማድረግ ይገባል። ከተቻለ በሃይማኖት ስም ከፍተኛ ዘረፋ የሚፈጽሙ ሌቦችም በህግ ቁጥጥር ስር ቢውሉ በአገሪቱ ላይ ሙሉ የሰላም ነፋስ እንዲነፍስ ያድርጋል፡፡ ይህ ሲሆን ምህረት ለማድረግና የተዘረፈውን ሀብት ለማስመለስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡  
ህዝቡ ለወንጀለኞች ምህረት እንዲያደርግ፣ ወንጀለኞች ተፀፅተው ህዝብንና አገራቸውን ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድረግ የሚያስችል የተደራጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ  ስራ መስራት፤
አገራችን ከነበረችበት የመበቃቀል ታሪክ ለመውጣት እየተውተረተረችና ዳዴ እያለች ጉዞ ጀምራለች፡፡ ምህረት ማድረግ በተለያዩ የዓለም ሀገሮች የተለመደና የሚዘወተር ተግባር ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ህዝብ ላላት ሀገር ደግሞ ዘርፈ ብዙ የሆነ  ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው። የኢትዮጵያ ህዝብ መሐሪና ሩህሩህ፣ መሪዎቹን አክባሪና የሚሉትን የሚሰማ ቅን ህዝብ ሲሆን በ27 ዓመታት የጥፋት ዘመን ውስጥ በደል የፈጸሙ ወንጀለኞችን በእስር ቤት ከማሰቃየትና በፍርድ ቤት ከማመላለስ በላይ ሂደቱን ጠብቆ ምህረት ማድረግ ለአገራዊ ልማት፣ ለመግባባት፣ የዲሞክራሲ ባህልን ለማዳበር፣ ማህበራዊ ትስስራችን ለማጠናከር፤ በባህል፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ የሚኖረውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ አጎልቶ በማሳየት ከበቀል መንፈስ ወደ ምህረት መንፈስ መመለስ በጣም አስፈላጊ ነው። ባለፉት ዓመት በኢትዮጵያ በተፈጸመው በደል፣ ግፍና የአገር ዘረፋ ሂደት መጠኑና ደረጃው ቢለያይም ያልተሳተፈ የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ድርጅት አባል ማግኘት አይቻልም። ለወንጀለኞች ምህረት ማድረግ የትኛውንም ብሔር ወይም የፖለቲካ ድርጅት ለማስደሰት ወይም ለማስከፋት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ስለዚህም የምህረቱን አስፈላጊነትና የኋላ ቆሻሻ የበቀል ታሪክን ቅርጫት ውስጥ ጨምሮ ወደ ልማትና አገራዊ አንድነት ማምራቱ በመንግስት፣ በሃይማኖት መሪዎችና አማኞች፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በምሁራን ትኩረት በመስጠት፣ በሰለጠነ መንገድ መሰራት ይኖርበታል። በአፈጻጸሙ ዙሪያ መንግስት በተለይም የፍትህ ተቋማት በበሰለ መንገድ ተወያይተው ከፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከምሁራን ጋር በመሆን የተለያዩ ሚዲያዎችንና ልዩ ልዩ መድረኮችን በመጠቀም፣ የህዝቡን አመለካከት ወደ ምህረት ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የግንዛቤ ፈጠራውም ለወንጀለኞች ምህረት በመደረጉ በጊዜያዊና በዘላቂነት የሚያስገኘውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ በማሳየት ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡
በሌላ መልኩ ከትንሽ እስከ ትልቅ ወንጀል የፈጸሙ በህግ ቁጥጥር የዋሉም ይሁን ያልዋሉ ዜጎች ከልቦናቸው  ተፀፅተው ለህዝባቸውና ለፈጣሪያቸው ይቅርታ የሚጠይቁ፣ ንስሐ የሚገቡ፣ የዘረፉትን ሀብት የሚመልሱ እንዲሆኑ የሚያስችል ስራ መሰራት ይገባዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ዐቢይ አህመድም የተለመደውን መሐሪና ሩህሩህነታቸውን አስቀጥለው በአገሪቱ ምህረት የማድረጉን ጅማሮ መሰረት ጠንካራ እንዲሆንና ወንጀለኞችም ሆነ ህዝቡ ከልቦናው ተቀብሎ አገር ወደ ማበልጸግ ጉዞ እንዲገባ በሰላውና በተሳለው አንደበታቸው ቢሰብኩና አደራቸውን ቢያስተላልፉ፣ ለአስፈጻሚው አካል መመሪያ ቢሰጡና በትኩረት ቢከታተሉ የጀመሩትን ሁለገብ የዲሞክራሲና የፍትህ ማስፈን ሂደት እንዲሁም አገር የማልማት እንቅስቃሴ  የተሳካ  ያደርግላቸዋል፡፡
ፈቃደኛ ያልሆኑንትን ወንጀለኞች በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሂደቱን ማስቀጠል
በቁጥጥር ስር የዋሉ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ያሉ ወንጀለኞች የተሰጣቸውን ምህረት ተጠቅመው፣ ጥፋታቸውን አምነው፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በይፋ ይቅርታ ካልጠየቁ፣ የዘረፉትን አምነው ለአገሪቱ ካልመለሱ በተያዙበት አግባብ በፍርድ ቤት ቅጣት እንዲያገኙ ማድረጉ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ግፍና በደል የደረሰባቸውን ዜጎች መካስ
ባለፉት ዓመታት ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ መስፋት፣ ለፍትህና ነጻነት የታገሉ የተለያዩ ግለሰቦች ብዙ ግፍና በደል ደርሶባቸዋል፤ ሀብታቸው ተዘርፏል፡፡ ይህን ደግሞ መንግስት አምኗል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ዜጎች ተለይተው፣ በመንግስት በይፋ ይቅርታ ተጠይቀው፣ ካሣ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡
ማጠቃለያ
 በዚህ የምህረት አሰጣጥ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች እንደሚነሱና ተግዳሮቶች እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል ምህረት ማድረጉ ወደፊት ወንጀለኞችን ያበረታታል፣ ወንጀለኞችን አያስተምርም፣ በህዝብ ላይ ግፍ የፈጸሙ እንዴት ምህረት ይደረግላቸዋል የሚሉ እንደሚሆኑ ስገምት፣ የብሔርተኝነት አስተሳሰብና ወንጀለኞች የዘረፉትን ለመመለስና ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ያለመሆን ዋና ዋና ተግዳሮቶች እንደሚሆኑ አስባለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በ27 ዓመት በዘርፈ ብዙ ወንጀሎች የተጨማለቁ  በርካታ የደለቡ ወንጀለኞችን ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ በአንድ ወቅት ተደራሽ አድርጎ፣ ፍትሐዊ ፍርድ ማሰጠቱ ከዚህ በላይ ከባድ ሆኖ ይታየኛል፤ ለታሰበው አገራዊ ዕርቅና ለተጀመረው ምህረትም መሰናክል ይሆናል፤ በአገራዊ ዕድገትና ስራ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ የተዘረፈው ሀብት እንዳይመለስ በር ይዘጋል፡፡ ስለዚህ ምህረት የማድረጉ ሂደት በአገራዊ ንቅናቄና ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ  ስራ ታግዞ ሂደቱን ጠብቆ ከተፈጸመ፣ ለወደፊቱ ህግን የሚያስከብሩ ጠንካራ ተቋማት ከተደራጁና ፍትህ የማስከበሩ ስራ በትኩረት ከተጀመረ፣ በ27 ዓመት የተጠራቀመንና የደለበን ወንጀለኛ በቁጥጥር ስር አድርጎ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ ከመጠበቅና ፍትህ ከማግኘት ይልቅ ምህረት ማድረጉ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚል ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡ እነዚህ ወንጀለኞችም የዘረፉትን ሀብት ከመለሱልንና ይቅርታ ከጠየቁን ሌላውን በቀልን ለእኔ ተውት የሚለው ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ዋጋቸውን እንደሚከፍላቸው አልጠራጠርም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብና ወንጀለኞችም ከልብ የመነጨ ይቅርታና ምህረት አድርገው ተስፋ ወደምናደርገው አገራዊ ዕድገትና ብልፅግና እንድንገባ፣ የራሱን የመሰረት ጡብ ያስቀምጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  (ይቀጥላል)


Read 385 times