Monday, 10 December 2018 00:00

ስለ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ከተነገረው የማልስማማበት!

Written by  በጫሊ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 “ጥልቅ ተሐድሶ በሚድሮክ መንደር!”   በሚልር ዕስኩርኩራ ዋፎ የተባሉ ጸሐፊ - ከለገጣፎ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ያሰፈሩትን አስተያየት አነበብኩት፡፡ በተለይ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕን በተመለከተ ያነሱት ሀሳብ በገንቢነቱ የምቀበለው ቢሆንም የቴክኖሎጂ ግሩፑን ዋና ሥራ አስፈጻሚ (ሲኢኦ) ዶ/ር አረጋ ይርዳው አመራርን በተመለከተ በድክመት መልክ ያሰፈሩት ሀሳብ ሚዛኑን የሳተ ሆኖ ተሰምቶኛል፡፡
እንደ ድክመት የተነሱ ነጥቦች ላይ
ያለኝ የግል አስተያየት
ጸሐፊው ዶ/ር አረጋ ይርዳው 26 ኩባንያዎችን በጥሩ ሁኔታ እየመሩ መሆኑን ባሰፈሩት ምስክርነት እስማማለሁ፡፡ ለእኔ ይህ ሥራ አገር ከመምራት እኩል ይሆንብኛል፡፡ አንድ ቤተሰብ መምራት ምን ያህል ከባድ መሆኑን ለምንገነዘብ ሰዎች፣ የዶክተር አረጋ ጥንካሬው ሃልኩ የቱ ድረስ እንደሆነ ይገባናል፡፡
“ዶክተር አረጋ እገሌን ቀጥረዋል፣ እንዲህ ብለዋል ይባላል” ለሚሉ አሉባልታ መሰል የጸሐፊው ሀሳቦች መልስ መስጠት አይገባም ነበር። ግን ጥቂት ሀሳቦችን መሰንዘር ለግልጽነት ሊረዳ ይችላል፡፡ በግሌ ግን ጠንካራ የሥራ መሪ ለመሆን የግድ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪና ዲፕሎማ አስፈላጊ ነው የሚለው አስተሳሰብ በከፊል የተሳሳተ ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በሥራቸው ስኬታማ ናቸው ማለትም ስለማይቻል ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ብዙ ምክንያቶችን ማንሳት ቢቻልም የጹሑፌ ትኩረት ባለመሆኑ እዘለዋለሁ፡፡
ዋናውና መርሳት የሌለብን ነጥብ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የረባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሳይኖራቸው፣ ዓለምን ያስደነቁ ታላላቅ ሥራዎች የከወኑ እጅግ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ነው። ከእነዚህ መካከል ቢሊየነሩ ሮክ ፌለር፣ ገጣሚና የቲያትር ደራሲው ዊሊያም ሼክስፒር፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እስከመሆን የደረሰው አብርሃም ሊንከን፣ የፊዚክስ ሊቁ አልበርት አንስታይን መጠቃቀስ ይቻላል፡፡
ከዚህ እውነታ አንጻር ሲታይ “12ኛ ክፍል በአግባቡ ያላጠናቀቀ” በማለት ጸሐፊው የጠቀሱት ግለሰብ መሾም ትክክል መሆን ወይም አለመሆኑ በሥራ አፈጻጸሙ የሚለካ ነው፡፡ ግለሰቡ ወረቀት የላቸውም  በሚል መነሻ ብቻ ለማሳነስና ለማጣጣል ጸሐፊው የሄዱበት ርቀት ተገቢ  ነው ብዬ አላምንም፡፡
ዶ/ር አረጋ የሚተካቸው ሰው አላዘጋጁም፣ በየደረጃው የሚገኙ ስራ አስኪያጆች ራሳቸውን ችለው እየሰሩ አይደለም በሚል በጥቅል ያነሱት ትችት ምናልባት ጸሐፊው ከመረጃ እጥረት የሰነቀሩት ሀሳብ ሳይሆን አይቀርም ብዬ ጠርጥሬያለሁ፡፡ ዶ/ር አረጋ በቅርብ ርቀት ሳውቃቸው፣ በተለይ ለወጣቶችና ለሴቶች ልዩ ስሜት ያላቸው መሪ ናቸው፡፡ ምናልባት ይህን በማድረጋቸው ካልተወቀሱ በስተቀር ወጣቶችን ለማብቃት ጥቂት እንኳን የማያንገራግሩ ብቻ ሳይሆን ”እኛ አርጅተናል” የምትለዋን አባባል በየመድረኩም በቀልድ መልክ ጣል የሚያደርጉት መሆኑ ለመለወጥ ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው የሚጠቁም ነው፡፡ ወጣቶች ወደ አመራር ቦታ እንዲመጡ ከታች ጀምሮ ልዩ ክትትል በማድረግ፣ ብቁ ሆነው ያዩዋቸውን ወጣቶች ወደፊት እንዲመጡ በማድረግ ረገድ ተቆጥሮ ሊጠቀስ የሚችል ሥራን አከናውነዋል። በአሁን ሰዓት ካሉት 26 ኩባንያዎች ጸሐፊው የጠቀሱትን ኤልፎራ ጨምሮ በወጣት የማኔጅመንት አመራሮች የተያዙት ኩባንያዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ በመርህ ደረጃ ዕድሜ ጠገብ አመራሮችን በወጣቶች እየተኩ የመሄዱ ጉዳይ የምስማማበት ሀሳብ ቢሆንም፣ ጨርሶ አንያቸው ዓይነት  አዝማሚያ፣ “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” የሚለውን አባባል የዘነጋ ስሜታዊ አስተያየት ሆኖብኛል፡፡
ዶ/ር አረጋ ሴቶች ወደ አመራር እንዲመጡ ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርጉ መሪ መሆናቸው ማንም የሚያውቀው ሐቅ ነው፡፡ የሴቶች ወይም የእናቶች ልጅ የማሳደግ ቤተሰባዊ ሀላፊነት ሸክምን ለማቃለልና ምቹ የስራ ቦታ ለማመቻቸት ከማንም ቀድመው ደረጃውን የጠበቀ የሕጻናት ማቆያ ከፍተዋል፡፡ በዚህም እናቶች ልጆቻቸውን የሚያሳርፉበትና በየሰዓቱ የሚያጠቡበት ምቹ አሰራርን ፈጥረዋል፡፡ ይህ ለአንድ የቢዝነስ ድርጅት ከትርፍ አኳያ ሲሰላ ኪሳራ መስሎ ላይ ላዩን ቢታይም የሴቶችን ሸክም በማቃለል፣ ምቹ የስራ ምህዳር በመፍጠር፣ ጤናው የተጠበቀ ትውልድ እንዲገነባ በማድረግ ረገድ በገንዘብ ሊለካ የማይችል ትርፍ ያለው ትልቅ እርምጃ መሆኑን እርስዎም ይስቱታል ብዬ አላምንም፡፡
ሌላው የዶ/ር አረጋ የአመራር ብቃት ማሳያ አመታዊ የኩባንያዎች የስፖርት ውድድርና የቤተሰብ ቀን እንዲኖር የሰጡት ልዩ ትኩረት ነው። በስፖርታዊ ውድድሩ አለቃና ምንዝር ሳይለይ ሁሉንም ማሳተፉ፣ የኢንዱስትሪ ሠላምን በዘላቂነት ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በሠራተኞች መካከል እውነተኛ መቀራረብ ወይም ጓደኝነት እንዲጎለብት በማድረግና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ያለው አስተዋጽኦ በቃላት የሚገለጽ አይደለም። የቤተሰብ በዓሉ፤ የሠራተኞች ቤተሰቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና የሚሰሩበትንም ተቋም ቀረብ ብለው እንዲያውቁ ጠቃሚ ዕድልን የፈጠረ ነው።
የውጭ ዜጎች ቅጥርን በተመለከተ
የውጭ ዜጎች ቅጥርን አስመልክቶ ጸሐፊው፤ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ኩባንያው አለአግባብ ወጪ እንዲያወጣ አስበው ያደርጉታል በሚል ያቀረቡትን ትችት በግሌ አልስማማበትም፡፡ ምናልባት ጸሐፊው ለኤልፎራ ቅርብ እንደመሆናቸው መጠን ፈረንጆቹ ይህን ያህል እየተከፈላቸው ሌሎቻችን ያነሰ ይከፈለናል ከሚል የቅናት ስሜት ተነሳስተው ያሉት ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። ዶ/ር አረጋ ቀደም ሲል በሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ውስጥ የነበሩ ፈረንጆችን ያሰናበቱት፣ ኢትዮጵያውያን ፈረንጆቹ የሚሰሩትን ያለችግር ተክተው መስራት እንደሚችሉ እርግጠኛ ስለነበሩ ነው። በዚህም ውሳኔ አተረፉ እንጂ አልከሰሩም። ወደ ኤልፎራ ሲመጣ ግን ፈረንጆቹ የያዙት ቦታ በኢትዮጵያውያን የሚሰራ ባለመሆኑ እንጂ ፈረንጅን ከፍሎ ለማምለክ አለመሆኑ ጸሐፊውም ይጠፋቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ ግን ኢትዮጽያውያን ጠጋ ብለው ስራውን እንዲቀስሙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ጸሐፊው በአዎንታ ማየት ለምን እንዳልፈለጉ በግሌ አልገባኝም፡፡ በአጭሩ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እንዲመጣ እየሰሩ ስለመሆናቸው በቅርብ ርቀት የማውቀው ነው። ይህ አሰራር ኤልፎራ ስር ባለው አልፋ አልፋ ፕሮጀክትም ሲተገበር የቆየ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በትክክል ዕውቀቱን መቅሰማቸው ሲረጋገጥ፣ የፈረንጆቹ ኮንትራት የሚቋረጥ ስለመሆኑ በግሌ አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም ዶ/ር አረጋ የሚያስተዳድሩት የቢዝነስ ኩባንያ ነውና፡፡ በአጭሩ ነጋዴ ናቸው፡፡ አንድን ሥራ ከቢዝነስ አኳያ አዋጪነቱን ማየትና መመርመር የዘውትር ተግባራቸው ነውና የውጭ ዜጎችን ያለ በቂ ምክንያት አስቀምጠው የሚቀልቡበት ሁኔታ እንደማይኖር ግልጽ ነው፡፡
በመጨረሻም፤ የጸሐፊው ትችት አዘል አስተያየት፤ ትንሽ ሚዛኑን ከመሳቱ በስተቀር መለመድ ያለበትና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ሕገ መንግስታዊ መብት አካል በመሆኑ በግሌ የማከብረው ነው፡፡

Read 4045 times