Monday, 10 December 2018 00:00

ቤቲ ጂ ከ “አፍሪማ” ታላቅ ስኬት ማግስት …

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)


      በአማርኛ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ የምታቀነቅነው ድምፃዊት ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ.)፤ ለየት ባለ የአዘፋፈን ዘይቤዋና ጥልቅ ትርጉም ባላቸው የዘፈን ግጥሞቿ ትታወቃለች፡፡ በኮክ ስቱዲዮ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ሙዚቀኞች ጋር ተጣምራ በመስራትም ብቃቷን አሳይታለች፡፡ ከወራት በፊት ያወጣችው ሁለተኛው “ወገግታ” የተሰኘ አልበሟም ተወዳጅነትን አትርፎላታል፡፡
ድምፃዊቷ በቅርቡ ከኖቬምበር 21 -24 ቀን 2018 በጋና ዋና ከተማ አክራ በተካሄደው የመላው አፍሪካ የሙዚቃ ሽልማት “All African Music Award (AFRIMA)” በሶስት ዘርፎች ማለትም፡- በ “ምርጥ የአመቱ የሙዚቃ አልበም”፣ በ “የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ሴት ዘፋኝ” እና በ”ተስፋ የተጣለባት ሙዚቀኛ” ዘርፎች በማሸነፍ ስኬትን ተቀዳጅታ የአገሯንም ስም አስጠርታለች፡፡ በሦስት ሽልማቶች ከተንበሸበሸች በኋላ ምን አዳዲስ ዕድሎች ተከፈቱላት?  ተደማጭነቷ ምን ያህል ጨመረ? ወደፊትስ ምን አቅዳለች በሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከድምፃዊት ቤቲ ጂ ጋር አጭር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡
በመጀመሪያ በ”አፍሪማ” ለተቀዳጀሽው ታላቅ ስኬት በራሴና በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ሥም እንኳን ደስ አለሽ እላለሁ…
እኔም እንኳን አብሮ ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ፡፡ ውጤቱ የኔ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው፡፡


    ስኬትሽን እንዴት እያጣጣምሽው ነው ታዲያ?
ደስታው መቼም ወደር የለውም፤ በጣም ያስደስታል። ከደስታው ጐን ለጐን ደግሞ ከዚህ የበለጠ ውጤታማ ስራ እንዴት ልስራ፣ በምን መልኩ ሥራዬን ላሳድግ የሚለውንም ማሰብ ተገቢ ስለሆነ፣ ደስታውንም ሀላፊነቱንም ጐን ለጐን እያጣጣምኩ እገኛለሁ፡፡
“ወገግታ” የተሰኘው ሁለተኛ አልበምሽ ገና ለአድማጭ ሳይደርስ ፍሬንድሺፕ ሆቴል በሚገኘው ኤቪ ክለብ ማስመረቅሽ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የወቅቱ የአገሪቱ ሁኔታ ብዙ ትኩረትን የሚረብሹ ሁነቶች የተከሰቱበት ስለነበር፣ አልበሙን እንደገና የማስመረቅ እቅድ እንደነበረሽ ገልፀሽ ነበር፡፡ አሁንስ ምን አስበሻል?
አልበሙን እንደገና ለማስመረቅ አላሰብንም፤ ነገር ግን ራሱን አልበሙን ምክንያት በማድረግ፤ የተለያዩ ኮንሰርቶችን በተለያዩ ቦታዎች ለመስራት፣ ከ“ይሳቃል ኢንተርቴይንመንት” ጋር እያሰብን ነው ያለነው፡፡ እንግዲህ ጊዜው ሲደርስ የምንገልጽ ይሆናል፡፡
በመላው አፍሪካ የሙዚቃ ሽልማት (አፍሪማ) አስደናቂ ውጤት ካስመዘገብሽ በኋላ ሙዚቃዎችሽን በኦንላይን ገበያ ለዓለም ለማቅረብ የሚያስችል ያየሽው ፍንጭ ወይም ምልክት የለም?
ከሽልማቱ በኋላ ከተለያዩ የሌላ አገር አርቲስቶች ጋር በትብብር ለመስራት በስፋት ለማቀድ አስችሎኛል። እርግጥ ያሸነፍኩበት ጊዜ አጭር ስለሆነ የኦንላይን ገበያው ምን ይመስላል የሚለውን አላየሁትም፡፡ እስኪ ወደፊት እመለከተዋለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቃን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እንደምትፈልጊ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ስትገልጪ ነበር፡፡ በ“አፍሪማ” የተቀዳጀሽው ውጤት ያለምሽውን ለማሳካት ምን ያህል ጉልበት ይሆንሻል?
ቢያንስ በተለያዩ አገራት ሰዎች የመታየት፣ ሥራዎቼ የመደመጥና ትኩረት የማግኘት አጋጣሚውን ይፈጥራል። አፍሪካ መድረክ ላይ ወጥቶ መጫወት መቻል በራሱም እኮ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ሙዚቃ ብዙ ስለማያውቁ፣ ከማሸነፉ ባሻገር እዛ መድረክ ላይ መጫወቱ ትልቅ ሚና አለው የሚል እምነት አለኝ። የሽልማት ሥነ ሥርዓቱን እንደተመለከታችሁት፤ መድረኩ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ከመላው አፍሪካ ማለትም ከደቡብ፣ ከሰሜን፣ ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ እንዲሁም ከመካከለኛው አፍሪካ የተውጣጡ ትልልቅ ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ትልቅ መድረክ ነበር፡፡ እናም እነዚያ ሁሉ የኢትዮጵያን ሙዚቃ የመስማት እድል አግኝተዋል፡፡ ከመስማታቸው በተጨማሪ የእኛን ሙዚቃ የማድነቅና የመውደድ ሥሜታቸውን ሲገልፁ ስለነበር፣ ቀስ በቀስ ከአፍሪካ ወደ ዓለም ሙዚቃችንን ለማሳደግ ትልቅ አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ሽልማቱ የሚሰጠው ብርታትና ጉልበት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ከሽልማቱ በኋላ ዘፈኖችሽ በተለይም በዩቲዩብ ተደማጭነታቸው የጨመረበት ሁኔታና የተነቃቃ ነገር አለ?
በጣም ልዩ የሆነ መነቃቃት አለ፤ ይሄንን ታዝቤያለሁ። ዩቲዩብ ላይ ኦዲዮ ለቅቆ ማሰማት ልክ አይደለም፤ ግን “ገርዬ” የተሰኘው ቪዲዮ በ “ምነው ሸዋ ኢንተርቴይንመንት” ከተለቀቀ በኋላ በዚህ በአጭር ጊዜ እንኳን ከ140ሺህ ሰው በላይ ተመልክቶታል፡፡ በጣም ጥሩ የሆነ መነቃቃት አለ ብዬ መግለጽ እችላለሁ፡፡   
ከሌሎች የአፍሪካ ሙዚቀኞች፣ ፕሮዲዩሰሮችና አቀናባሪዎች ጋር የአብረን እንስራ ግብዣስ ቀርቦልሻል?
አዎ! የተለያዩ የአብረን እንሰራ ጥያቄዎች ቀርበውልኛል፤ እየቀረቡልኝም ይገኛል፡፡ እነዚህን ግብዣዎች በማናጀሬ አማካኝነት… የትኞቹ ይቅደሙ፤ የትኞቹ ይከተሉ የሚለውን ቅደም ተከተል እያስያዝናቸው ነው፡፡ ከሌሎች ጋር የመስራቱን ጉዳይ ስራዬ ብለን ይዘን እንቀጥልበታለን፡፡
በአንድ ወቅት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚወጣና ለአለም ገበያ የሚቀርብ አልበም መስራት መጀመርሽን ተናግረሽ ነበር፡፡ እሱ ሥራ ከምን ደረሰ?
ሥራው እየተሰራ በመንገድ ላይ ነው፡፡ በመጀመሪያ ለኢትዮጵያዊያን አድናቂዎቼ በአማርኛ የተሰናዳ አልበም ማቅረብ አለብኝ የሚል ሃሳብ ስለነበረን ነው “ወገግታ”ን ያስቀደምኩት፡፡ እንግሊዝኛ አልበሙ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
“ወገግታ” የተሰኘው የሁለተኛው አልበምሽ ግጥም፣ ዜማና ቅንብሩ የተሰራው በአንድ ወጣት ባለሙያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለመሆኑ ይህ ባለሙያ ማን ነው? በሙያው ላይ ቆይቷል ወይስ አዲስ ነው? አዲስ ከሆነስ እንዴት ተዋውቃችሁ?
ይህ ወጣት ባለሙያ ያምሉ ሞላ ይባላል፡፡ በእኔ ስራ ነው ሙዚቃ “ሀ” ብሎ የጀመረው፡፡ ዘሩባቤል ሞላ የሚባል ጊታር ተጫዋች አለ፡፡ ይህ ልጅ የ“መሃሪ ብራዘርስ” ባንድ አባል ሲሆን የያምሉ ሞላ (የኔን ስራ የሰራው ልጅ)  ወንድም ነው፡፡ የጃኖ ባንዱ አባል የሆነው ሚካኤል ሀይሉ፤ “ያምሉ የሚባል አንድ አቀናባሪ አለ፤ ብታገኚው ጥሩ ነው” ብሎ ጠቆመኝና አገኘሁት፡፡ በጣም ጐበዝ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ አመንኩበትና ሥራን ውጤታማም ሆንን፡፡
ያምሉ ግጥምና ዜማውን እሱ ከጠበቀው በላይ አሳምረሽ ስለሰራሽለት፣ በጣም አመስግኖሻል ይባላል?
እንግዲህ ሥራውን በጋራ ሆነን ስለሰራነው በጥሩ መንፈስና ሀይል ነው ስንሰራ የነበረው፡፡ ስለዚህ አንተ ሰራህልኝ፣ አንቺ ሰራሽልኝ የሚባል ነገር አልነበረንም። የመተጋገዝና የመደጋገፍ ሥራ ነው የሰራነው። የስቱዲዮ ቆይታችንም እጅግ አስደሳች ነበር። አልበሙ ከመውጣቱም ሽልማቱ ከመምጣቱም በፊት በስራችን አንዳችን በአንዳችን ደስተኞች ነበርን። አልበሙ ሲወደድና ሲደነቅ ደግሞ ደስታችን ወደር አልነበረውም፡፡ እሱ ያመሰገነኝና ጥሩ አድርጋ ሰርታለች ያለኝ አሁን ሳይሆን፣ ገና ስቱዲዮ እያለን ነበር ለማለት ነው፡፡ ገና ከቀረፃ ጀምሮ ነበር ይህ ጥሩ መንፈስ የመጣው፡፡ ሁለታችንም በውጤታችን ደስተኞች ነን፡፡
በአዲስ አድማስ ላይ ስለ አልበምሽ የተሰራውን ዳሰሳ (Review) አይተሽው ነበር…?
አዎ አንብቤው ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ አዲስ አድማስንም መላውን የኢትዮጵያን ህዝብም አድናቂዎቼንም በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ይህ ውጤት የሚዲያውም የአድናቂዎቼም ድምጽ ተጨምሮበት፣ ጉልበት ሆኖኝ የመጣ እንጂ የኔ የብቻዬ ድካም አይደለምና… በጣም በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የተገኘው ውጤት የመላው ኢትዮጵያ ነውና እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን እላለሁ፡፡ 

Read 1322 times