Monday, 10 December 2018 00:00

ውሉን የሳተው የ“ቃልም ሥጋ ሆነ” ፍታቴ

Written by  ጤርጢዮስ ዘ-ቫቲካን
Rate this item
(0 votes)

     ህዳር 15 ቀን 2011 ዓ.ም “ጥበብ” ዓምድ ላይ “ቃልም ሥጋ ሆነ” በሚል ርዕስ ተፅፎ ያነበብኩት የፍልስፍና መምህሩ፣ ብሩህ ዓለምነህ መጣጥፍ፤ የታላቁን መፅሐፍ ቃል ከፈላስፎቹ ቃል ጋር ያለ አግባብ እየቀየጠ ማቅረቡ ግር ቢለኝ ነው ለግብረ መልስ ብዕር ማንሳቴ። በመጽሐፉ ቃል ለሚያምኑ፣ ቃል ሥጋ የመሆኑ ጉዳይ እንዲያ ከዐውዱ ተፋቶና ተውሸልሽሎ የቀረበ ጊዜም አቀራረቡን “ኑፋቄ”፣ አቅራቢውን ደግሞ “መናፍቅ” ብሎ የመፈረጅ ዘመናትን ያስቆጠረ ሃይማኖታዊ ባህልም አለ፡፡ ይገባልም!
እንኳን ለጋዜጣ ፍጆታ ሲባል በለብ ለብ የቀረበ “ክርስቶስ ነክ” ፅሑፍ ቀርቶ፣ ጥንት እንደ አርዮስ እና ንስጥሮስ ያሉ የሥነ መለኮት ሊቃውንት፤ የመለኮትን ህልውና ዓይነተኝነት መነሻቸው አድርገው፣ ቃል ሥጋ ለሆነበት ሁኔታ ያቀረቡት ጥልቅ አስተንትኖና የሰጡት ብያኔም ውግዘት ገጥሞታል፡፡ ይልቁንም የፈላስፋውን ስፒኖዛ የመለኮት ግንዛቤ ከሐዋርያው ጳውሎስ የመለኮት ግንዛቤ ጋር ለማጋባት መሞከር፤ “እኔ፣ እኔ ነኝ” ብሎ ራሱን የገለጠውን የመጽሐፉን እግዚአብሔርና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እስከ ህይወት ፍጻሜው ሲሰብክ የኖረውን ጳውሎስ፤ በተቃራኒው እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ተነጠለ “እኔ” ባይ ህልውና እንደሌለው ከሚያስበው የስፒኖዛ ፍልስፍና ጋር መቀየጥ ከሚገባው በላይ ውጉዝ ነው፡፡
የፍልስፍና መምህሩ ብሩህ ዓለምነህ መጣጥፍ ጭብጥ የሆነው የስፒኖዛ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ያለው ግንኙነት እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች መስሎ መቅረቡ “ለመጽሐፉ ሰዎች” ፍፁም ዕንግዳ ከመሆኑም በላይ “የብዝሃ አማልክት”ን ፅንሰ ሃሳብ በመሸከሙ በክርስትና ሃይማኖት መሰረት ላይ የመቆም ህጋዊነት የለውም። የፍልስፍና መምህሩ ፅሁፍ፣ ስለ ስፒኖዛ በቅጡ ያልተተነተነ እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ከዘርዓያዕቆብም፣ ከአርስቶትልም፣ ከሄግልም፣ ከኬርኪጋርድም አባባሎችን እየቀነጨበ ያቀርባል። ሁሉም ስለ እግዚአብሔር ያሰቡት ሃሳብ ትክክል እንደሆነም ያረጋግጣል፡፡ “እገሌም፣ እገሌም ያሉት ትክክል ነው!” የሚል ብይን ይሰጣል፡፡ አቀራረቡ ከምሁራዊነት ይልቅ የሰባኪ ዘዬና ቃና አለው። “ሁሉም ትክክል ናቸው” ባይነቱም የፀሀፊውን የፖስት ሞደርኒዝም አስተሳሰብ አቀንቃኝነት ያሳብቃል፡፡
የፍልስፍና መምህሩ መጣጥፍ፤ “ቃልም ሥጋ ሆነ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መነሻው ያድርግ እንጂ ሃሳቡን የሚተረጉመውም ሆነ የሚተነትነው ቃሉ በተፃፈበት ዐውድ ዓይደለም፡፡ ይልቁንም እዚህ ውስጥ ተፈጥሯዊ እምነት፣ ብዝሃ አምላክነት፣ ፍልስፍናዊ እሳቤዎችና የወንጌል ትርክቶች አንድ ላይ ተቀይደው ስለቀረቡ፣ አንዱን ከሌላው መለየት በጣም ይከብዳል። የፅሁፉ አደረጃጀት በአንድ የፍልስፍና መምህር የተዋቀረ አይመስልም፡፡ “ይህ የእኔ ዕይታ ነው” ከማለት ይልቅ፤ “ነው!” ብሎ መደምደም ይበዛዋል፡፡
“ቃል አንድ ነው፤ ፍጥረታትን ግን በየወገናቸው አድርጎ በእነርሱ ውስጥ ብዙ መሰለ” የሚሉት የፍልስፍና መምህሩ፤ ስፒኖዛ፡- “እግዚአብሔርና ተፈጥሮ ሁለት የተለያዩ ነገሮች አይደሉም፣ እግዚአብሔር የተፈጥሮ ክስተቶች አንቀሳቃሽ ኃይል ነው” የማለቱን ትክክለኛነት ለማፅናት የተጠቀመበት አገላለፅ ነው፡፡ ይሁንና የስፒኖዛ የተፈጥሮ ክስተቶች አንቀሳቃሹ ዲዳ ኃይል በመጽሐፍ፤ አምሳያ የሌለው የሚናገር፣ የሚሰማ፣ የሚጠራ ሆኖ ከተገለጠው “ያህዌ” ጋር በፍፁም ስለማይገጥም ስፒኖዛ የሥጋ ዘመዶቹ በሆኑት አይሁድ ዘንድ የተወገዘ ነበር፡፡ የስፒኖዛ እግዚአብሔር እንደ ወገኖቹ አይሁድ ከፍጥረቱ ፍፁም የተለየ “ነጠላ” ህላዌ ሳይሆን፤ ሁሉም ፍጥረት፣ ዛፉም ቅጠሉም፣ እንስሳውም ሰውም የመለኮት ባህርይ ተካፋይነት አለው፡፡ የፍልስፍና መምህሩ፤ “እሱ አንድ ነው፣ መልኩ ግን ብዙ ነው፣ መገለጫውም እልፍ አእላፍ” የማለታቸው መነሻም ይኸው እንጂ “ቃልም ሥጋ ሆነ” የሚለው የመጽሐፉ ቃል ትርጉም በፍፁም ከዚህ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡
“‹እግዚአብሔር› ዓለሙን ከራሱ አመንጭቶ፣ በዓለሙ ኩነቶች በኩል ይገለፃል፡፡ ሁሉም ስሜቶች፣ ሁሉም አዕምሮዎች፣ ሁሉም ዓይኖች፣ ሁሉም ጆሮዎች፣ ሁሉም ወቅቶችና ሁሉም ክስተቶች ሆኖ ይገለፃል” የሚለው የፍልስፍና መምህሩ፣ ብሩህ ዓለምነህ ገለፃም ቢሆን፣ እግዚአብሔር የፍጥረቱ አስገኚ ታላቅ አዕምሮ ከመሆኑ ይልቅ በውስጣቸው አድሮ የሚያንቀሳቅሳቸው ግዑዝ ኃይል መስሎ እንዲሰማን ያደርጋል፡፡ እግዚአብሔር በፈጠረው ፍጥረት መላ አካል ውስጥ የመሸገ ሌላ ፍጥረታዊ አካል ይሆንብናል። የብሩህ ዓለምነህ መናፍቃዊ ገዢ ሃሳብም ይኸው ነው ማለት ይቻላል፡፡
“ቃልም ሥጋ ሆነ” የሚለውን የወንጌል ቃል ጠቅሶ፣ “እግዚአብሔር የሆነ ብቻ ሳይሆን የሚሆን ነው” የሚል እሳቤን የመዘዘው የፍልስፍና መምህሩ መጣጥፍ፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ ማን ኖሮ ነው፣ በኋላ ምን የሆነው? የሚለውን የወንጌል እውነት በአግባቡ ስለማይመልስ እርሳቸው በሳቱበት መንገድ ብዙዎች እንዲስቱ በር ይከፍታል፡፡ ቃል ሥጋ የሆነበት እውነታ ግን እንኳን የፍልስፍና እሳቤዎችን ከእውነቱ በላይ አግዝፈው ለሚመለከቱት ብሩህ ዓለምነህ ቀርቶ መላ ሕይወታቸውን “ሥግው” ለሆነው ቃል አሳልፈው ለሰጡት የሥነ መለኮት ልሂቃንም የነገረ - ክርስቶስ ጉዳይ ከሰው አእምሮ በላይ የላቀና የረቀቀ ነው፡፡
ቃል ሥጋ የመሆኑ ኩነት በእርግጥም በገጣሚው ሰለሞን ደሬሳ አባባል፤ አሥር ጊዜ ተጠይቆ፣ አሥር ጊዜ መልስ አግኘንቶ፣ እንደገና አሥር ጊዜ የሚጠየቅ መለኮታዊ ምሥጢር ነው። ቃል ሥጋ የሆነበት መንገድ አንዱ ከሌላው ጋር መቀላቀልም ሆነ መጠፋፋት በሌለበት ሁኔታ የተከናወነ መሆኑን መቀበል ግን የክርስትና ሃይማኖት ዶግማና ቀኖና ነው፡፡ የቃልና ሥጋ እንዲህ ያለው ተዋህዶም ለክርስቶስ ብቻ የሆነ እንጂ የፍልስፍና መምህሩ ብሩህ ዓለምነህ እንደሚሉት፤ ቃል ከሁሉም ፍጥረታት ጋር ተመሳሳይ ተዋህዶ አላደረገም።
በቅዱስ መጽሐፍ መረጃ መሰረት፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ሰውነትና አምላክነት (ቃል እና ሥጋ) በአንድ አካል ተዋህደዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አበው እንዳብራሩትም፤ ሁለቱ ባህርያት ሳይቀላቀሉ ደግሞም ሳይነጣጠሉ፤ አንዱ ሌላውን ውጦ ሳይሆን፤ አንዱ ሌላውን የራሱ ገንዘብ አድርጎ፣ በአንድ አካል፣ ፍፁም አንድ ማንነት ይዞ ይኖራል፡፡ ቃል ሥጋ የመሆኑ ፍቺም ይኸው ብቻና ብቻ ነው፡፡ እኔን ጨምሮ ክርስቲያኖች ሁሉ “ክርስቶስ ጌታችን” ብለው የተቀበሉትና በእምነት የሚከተሉት እርሱን ነው፡፡
ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት በቀራኒዮ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተው፣ መሞት ብቻ ሳይሆን መቃብር ፈንቅሎ የተነሳው ሥግው ቃል ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡
ከዚህ የተለየ የፍጥረትና የመለኮት ተዋህዶም የለም። በእርሱ (በክርስቶስ) የሚያምኑቱ የሰው ልጆች፤ “ቃልም ሥጋ ሆነ” ተብሎ ከተነገረለት የእግዚአብሔር ልጅ የሚካፈሉት ጸጋ ቢኖርም፣ ቁርጥ እርሱን ለመሆን የሚችሉበት አሳቻ መንገድ ግን የለም፡፡
በፍልስፍና መምህሩ መጣጥፍ ውስጥ ግን ፍፁም ከዚህ ተቃራኒ ብቻ ሳይሆን ፍፁም ግራ አጋቢ ሃሳብ ሰፍሯል፡፡ ቃል ሥጋ በሆነ ጊዜ፣ ረቂቅ መንፈስ የነበረው ኃይል አካላዊ ህልውና እንደተቀዳጀ፤ መንፈስ የነበረው ያ “አዕምሮ ቢስ” ኃይል ራሱን ወደማወቅ ንቃተ ህሊና እንደደረሰ ተተርኳል፡፡ በብሩህ ዓለምነህ መጣጥፍ “እኔታውን”  የተቀማው እግዜር፤ ራሱን አሟልቶ መግለፅ የቻለው በሰው ልጅ ከፍተኛ ንቃተ ህሊና ሲሆን፤ በክርስቶስ በኩል ከፍተኛ ንቃተ ህሊና ላይ ከመድረሱ በፊት ራሱን አያውቅም ነበር፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ግን የክርስቲያኑ የስነ መለኮት ሰውና ፈላስፋ ኬርኪጋርድ የቃል ሥጋ መሆን አገላለፅ፤ ለዚህ ሃሳባቸው ማነጻጸሪያ ሆኖ መቅረቡ ነው። ብሩህ ዓለምነህ ፍልስፍናን በሚያስተምሩበት ዩኒቨርሲቲ እንዲህ ያለውን መንገድ የሚከተሉ ከሆነም “ፍልስፍና” አዲዮስ! ቃል ሥጋ በሆነ ጊዜ “እግዚአብሔር” ከረቂቅ ባህርይው ወደተጨባጭ ነባራዊ እውነትነት እንደተቀየረ የሚገልፁት ብሩህ ዓለምነህ፤ ይህ ኩነት ለክርስቶስ ብቻ የሚሰራ ሳይሆን፤ ግልጠቱ በመሐመድም፣ በቡድሃም በኩል ተጨባጭ እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ “ቃልም ሥጋ ሆነ፣ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” የሚለው የወንጌል ቃል፣ ከክርስቶስ እኩል ለመሃመድና ለቡድሃ እንደሚሰራ ያወጉናል፡፡
መገለጡና ተጨባጭነቱ በእነዚህ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነም ፍንጭ ይሰጡናል፡፡ ለእኔ ግና ይህ የፍልስፍና ሃሳብ ሳይሆን መሬት ላይ ያለ ዕንግዳ ሃይማኖት ነው፡፡ መጣጥፉ ፍልስፍና ሃቲቶችን በምሁራዊ መንገድ ያንፀባረቀ ሳይሆን በዛሬው ዘመን አትሮኖስ ላይ ያለ የሃሰተኛ አስተማሪዎች ስብከት ነው። የበርካታ ስሁት እውቀቶችና ሃይማኖቶች መፈልፈያስ ውሉን የሳተ ሥነ - ፍታቴ ዓይደል!      

Read 1604 times