Monday, 10 December 2018 00:00

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(0 votes)

ክፍል- ፩ ስያሜውና ሥልጣኔው የቆመባቸው ሦስቱ መሰረቶች
               
   ከዚህ ቀደም በሐምሌና ነሐሴ 2010 ዓ.ም ‹‹ብህትውናና ዘመናዊነት›› በሚል ሰፊ ርዕስ፣ ሰባት የተለያዩ መጣጥፎችን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ማስነበቤ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ መጣጥፎች መካከል ‹‹ከአክሱም ቁዘማ ኢትዮጵያ ተወለደች››፣ ‹‹የኢየሱስ የመጨረሻዎቹ ቀናትና የኢትዮጵያ ሙዚቃ››፣ ‹‹ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድን በተአምራዊነት ተረክ›› እና ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር የመፍጠር ፕሮጀክትና የአማራነት ንቃተ ህሊና መደብዘዝ›› የሚሉት ይገኙበታል። ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ›› የሚለው ርዕስም ከእነዚያ መጣጥፎች ጋር በጣም ተዛማጅ ሲሆን፣ በዚህ ርዕስ ሥርም ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ተከታታይ ፅሁፎችን አቀርባለሁ፡፡
በበርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ የታሪክ ባለሙያዎች ዘንድ ‹‹የኢትዮጵያ ሥልጣኔ›› የሚለውን ቃል የሚያያይዙት ከጥንታዊ አክሱም ጋር እንጂ ‹‹ያሬድ›› ከሚለው ስም ጋር አይደለም። የእነዚህን የታሪክ ባለሙያዎችን አስተምህሮ ተከትሎም አብዛኛው ህዝብ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ ተብሎ ሲጠራ ወዲያው ወደ አእምሮው የሚመጣው ጥንታዊው አክሱም ነው፡፡
የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሥልጣኔ ከአክሱም ጋር ‹‹ብቻ›› የሚያያይዘውን ይሄንን ልማድ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበሩት በንጉሱ ዘመን የፍልስፍና መምህር የነበሩት ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ናቸው፡፡ እጓለ ከአብዮቱ በፊት በ1953 ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት የትምህርት ፍልስፍና መፅሐፍ ውስጥ ‹‹ያሬዳዊ ሥልጣኔ›› የሚል ሁለት ምዕራፎች አሏቸው፡፡
ዶ/ር እጓለ በእነዚህ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ስለ ኢትዮጵያዊው ሥልጣኔ ሦስት አዳዲስ ሐሳቦችን ያስተዋውቁናል፡፡ የመጀመሪያው፣ ‹‹ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ›› የሚለው አገላለፅ ጥንታዊ የአክሱም ሥልጣኔን ብቻ የሚገልፅ መሆን እንደሌለበት ያሳዩበት ነው፡፡ በርግጥ ገናናው የአክሱም ሥልጣኔ ክርስትና ሃይማኖትን ከመቀበላችን በፊት የተገነባ ከጥንታዊ ግሪክ፣ ፐርሺያና ቻይና ሥልጣኔዎች ጋር የሚስተካከል ሥልጣኔ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን፣ የአክሱም ሥልጣኔን ተክቶ ስለመጣው ክርስቲያናዊው ሥልጣኔ በርካታ የታሪክ ባለሙያዎች የሃይማኖትነት ደረጃን ከመስጠት ባሻገር እንደ ሥልጣኔ ቆጥረውት አያውቁም። በዶ/ር እጓለ አስተያየት ይሄ ስህተት ነው፡፡
ዶ/ር እጓለ፤ ይሄንን ስህተት ለማረም በመጀመሪያ የሄዱበት መንገድ ‹‹ሥልጣኔ ምንድን ነው?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት ነው፡፡ ሥልጣኔን ሲተረጉሙትም፤ ‹‹የእሴቶች ህብር (Compositum of Values)›› ይሉታል፡፡ እነዚህም እሴቶች በሥነ ምግባር፣ በሥነ ውበት፣ በቅድስናና በተጠቃሚነት የተዋቀሩ ናቸው፡፡ አንድ ሥልጣኔ የተሟላ ነው የሚያስብለውም፤ በእነዚህ አራት እሴቶች  ልህቀት (Excellence) ላይ ሲደርስ ነው፡፡
ዶ/ር እጓለ፤ የሥልጣኔን መስፈርት በዚህ መልኩ ካስቀመጡ በኋላ፣ የአክሱምን ሥልጣኔ ተክቶ የመጣውን ክርስትያናዊውን ማህበረሰብ በእነዚህ መስፈርቶች ይመዝኑታል፤ በዚህም አንድ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡ በዶ/ር እጓለ ድምዳሜ መሰረት፤ ክርስትያናዊው ማህበረሰብ ‹‹ከተጠቃሚነት እሴት›› በስተቀር ሌሎቹን ሦስት የሥልጣኔ እሴቶች፣ ማለትም በሥነ ምግባር፣ በሥነ ውበትና በቅድስና ረገድ ታላላቅ ሥራዎችን ሰርቷል፤ ሥርዓተ ትምህርትን፣ ሥነ ፅሁፍን፣ ዜማን፣ ኪነ ህንፃንና መንፈሳዊ ህይወትን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመሆኑም፣ ‹‹ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ›› ሲባል አክሱምን ብቻ ሳይሆን ክርስትያናዊውን ሥልጣኔም ማካተት አለበት፡፡  
ዶ/ር እጓለ በመፅሐፋቸው ያሳዩን ሁለተኛው አዲስ ነገር ደግሞ ‹‹ያሬዳዊ›› ስለሚለው ስያሜ አመጣጥና ተገቢነት  ነው፡፡ የሥልጣኔ ስያሜ ‹‹ጥቅል›› ከሚሆን ይልቅ በሥልጣኔው ውስጥ እንደ ፈርጥ ሆነው ሲታዩ በነበሩ ግለሰቦች ስም ቢጠራ የበለጠ ገላጭ ነው፡፡
አውሮፓውያን ጥንታዊ ሥልጣኔያቸውን ‹‹ፋውስትያን›› ብለው የጠሩበት ምክንያት ለዶ/ር እጓለ ተገቢና አሳማኝ ነው፡፡ ‹‹ፋውስት›› በ16ኛው ክ/ዘ በዘመነ ትንሳኤ (Renaissance) የኖረ ጀርመናዊ ሲሆን፣ ሁልጊዜ ለአዲስ እውቀት ባለው ጥማት የተነሳ በዘመኑ በምድር ላይ ያሉትን እውቀቶች ሁሉ የሰበሰበ፣ ሆኖም ግን ባገኘው እውቀት መርካት ያልቻለ አውሮፓዊ ነው። ይሄ ገደብ የለሽ የእውቀት ጥማቱ ፋውስትን ጠንቋይ ቤት እስከ መሄድ ድረስ ያደረሰው ሲሆን፣ አዲስ እውቀት ለማግኘት ሲልም ነፍሱን አስይዞ ከሰይጣን ጋር እስከ መደራደር ደርሷል። በፋውስት በኩል የተገለፀው ይህ ገደብ የለሽ የእውቀት ጥማት የመላው አውሮፓዊ ባህሪ መገለጫ ነው። ስለዚህም አውሮፓውያን ሥልጣኔያቸውን በፋውስት ስም ሰይመውታል፡፡
ዶ/ር እጓለ፤ ‹‹በሀገራችን ክርስትያናዊው ሥልጣኔ ውስጥ የፋውስት ዓይነት ተመሳሳይ ወኪል ይኖር ይሆን?›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ለዚህ ጥያቄያቸውም ‹‹ለብዙ የሃገራችን ሊቃውንት እንደ አርዓያ በመሆን በክርስትያናዊው የሥልጣኔ ዘመናት ሁሉ በዜማና በድርሰት ሥራዎቹ ጀማሪና እንደ አብሪ ኮኮብ ሆኖ ሲታይ የኖረው ያሬድ ነው›› በማለት ቅዱስ ያሬድን የክርስትያናዊው ሥልጣኔ ወኪል ያደርጉታል፤ ክርስትያናዊውን ሥልጣኔም በያሬድ ስም ይጠሩታል - ‹‹ያሬዳዊ ሥልጣኔ›› በማለት፡፡
ሌሎች ምሁራን ደግሞ፣ ክርስትያናዊውን ሥልጣኔ በሌሎች ተለዋጭ ስሞች ይጠሩታል። ለምሳሌ፣ ዶ/ር ተሻለ ጥበቡ ‹‹The Making of Modern Ethiopia›› በተባለው የዶክትሬት ማሟያ መፅሐፋቸው ውስጥ ‹‹የግዕዝ ሥልጣኔ›› ብለው ሲጠሩት (1974: 3)፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ደግሞ ‹‹ላሊበላዊ ሥልጣኔ›› የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡
ዶ/ር እጓለ በመፅሐፋቸው ያሳዩን ሦስተኛው አዲስ ነገር ደግሞ፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ያለበትን ጉድለት ነው፡፡ ምንም እንኳ ከላይ የጠቀስናቸው ሦስቱ ምሁራን ጥንታዊውን የአክሱም ሥልጣኔ በመተካት የመጣውን ሥልጣኔ በተለያዩ ስሞች ቢጠሩትም፣ ሦስቱም ስያሜዎች የሚያወሩት ግን ስለ አንድ ጉዳይ ነው - ከ6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ማበብ ስለጀመረው ስለ ክርስትያናዊው ሥልጣኔ!! ምሁራኑ የክርስትያናዊው ሥልጣኔ ‹‹መገለጫ ባህሪያት›› በማለት ያስቀመጧቸውም ነገሮች እንዲሁ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ዶ/ር እጓለ፤ ይሄንን መገለጫ ከአውሮፓውያኑ ጋር በማነፃፀር፣ ‹‹ፋውስታዊው ሥልጣኔ ‹‹ሰውን›› ማዕከል ያደረገ ሲሆን፤ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ግን ‹‹እግዚአብሔርን›› ማዕከል ያደረገ ነው›› ይሉታል፡፡ ይሄንን አባባል ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያምም ‹‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?›› (1986) በሚለው መፅሐፋቸው ውስጥ ተጋርተውታል፡፡
እጓለ፤ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተጠቃሚነት እሴት ይጎድለዋል›› የሚሉትም ነገር መነሻው ክርስትያናዊው ሥልጣኔ ምድራዊ ጥቅምን በመናቅ ‹‹እግዚአብሔርን ብቻ›› ማዕከል ያደረገ የሥነ ምግባር፣ የሥነ ውበትና የቅድስና እሴቶችን ስላዳበረ ነው፡፡ ይሄንን ሲሉን ዶ/ር እጓለ በተዘዋዋሪ ‹‹ብህትውና›› የያሬዳዊው ሥልጣኔ መሰረት እንደሆነ እየነገሩን ነው፡፡ ምንም እንኳ፣ እጓለ ‹‹ብህትውና የያሬዳዊው ሥልጣኔ መሰረት ነው›› ያሉት ነገር ትክክል ቢሆንም፣ የሥልጣኔው መሰረት ግን ብህትውና ብቻ አይደለም፤ ይልቅስ ሌሎች ኪነ ጥበባዊ (ሥነ ውበታዊ) እና ዲበ አካላዊ መሰረቶችም አሉት እንጂ፡፡
ባጠቃላይ፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ሦስት መሰረቶች - ዲበ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና ኪነ ጥበባዊ መሰረቶች - ላይ የቆመ ነው፡፡ ዲበ አካላዊው (Metaphysical) መሰረት ተአምራዊነት (Mysticism) ሲሆን፣ ሥነ ምግባራዊው መሰረት (Moral foundation) ደግሞ ብህትውና ነው፤ የያሬዳዊው ሥልጣኔ ኪነ ጥበባዊ መሰረት (Aesthetic foundation) ደግሞ ሰሞነ ሕማማት ነው፡፡ ሦስቱም መሰረቶች ታዲያ የመፅሐፍ ቅዱስ አስተምህሮን መነሻ አድርገው የተተከሉ ናቸው፡፡ እኛ ግን የፍልስፍና አፍቃሪያን ስለሆንን በዚህ መልስ አንረካም፤ ‹‹በእርግጥ እነዚህ ሦስቱ መሰረቶች መፅሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት አላቸው ወይ?›› ብለን እንጠይቃለን። በመሆኑም፣ በክፍል ፪ ፅሁፌ፤ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከቆመባቸው ሦስቱ አምዶች ውስጥ አንዱን (ብህትውናን) መዝዘን በማውጣት፣ ‹‹በእርግጥ ብህትውና መፅሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት አለው ወይ?›› የሚለውን ጥያቄ እንመለከታለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 2173 times