Print this page
Monday, 10 December 2018 00:00

አሐዱ ዌብ አዲስ የጨረታ አፕሊኬሽን መጀመሩን አስታወቀ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

 የዌብሳይት ዲዛይን ልማት ኩባንያ የሆነው አሀዱ ዌብ፤ ላለፉት 7 ዓመታት ኢትዮ ሰርችና በዌብ ሆስቲንግ ሲሠራ ቆይቶ ባለፈው ዓመት የጨረታ መከታተያ አፕሊኬሽን መጀመሩንና በቅርቡ ደግሞ ተጠቃሚዎች የጨረታ ሰነድ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ (Bid on Line) ይፋ ማድረጉን የኩባንያው መሥራችና ባለቤት አቶ አብረሃም አሰፋ ገልፀዋል፡፡
በወረቀት፣ በጋዜጣ፣ በማስታወቂያ ሰሌዳ፣…የሚወጡ ጨረታዎችን ተደራሽነት ለማስፋት፣ ቀላል የሆነ የሞባይል አፕሊኬሽን ፈጥረው “ሞብቴንዳር ዶት ኮም” የተባለ አዲስ የጨረታ መከታተያ አፕሊኬሽን የዛሬ ዓመት ይፋ ማድረጋቸውን የጠቀሱት አቶ አብረሃም፤ ከማንኛውም የጨረታ ምንጭ የተገኙ ሁሉንም ዓይነት ጨረታዎች፣ ማንኛውም ሰው ባለበት ስፍራ ሆኖ በእጁ ሞባይል መከታተል የሚችልበት ዘዴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  የፈጠሩት ሞብቴንደር ዶት ኮም አፕሊኬሽን፣ ጨረታ የሚያወጡ ድርጅቶችንና ጨረታ ገዢዎችን የሚያገናኝ ቀላል ዘዴ ነው ያሉት ባለቤቱ፤ ተደራሽነቱን በተመለከተ ሲያስረዱ፡- ጐግል ላይ የቻይና፣ የሕንድ፣ የደቡብ አፍሪካ ዕቃ አቅራቢዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የወጡ ጨረታዎችን መጠቀማቸው፣ የትኛውም ሰው የትም ሆኖ ጨረታዎችን እንዲከታተል ቀላል መንገድ ፈጥረናል ማለት ነው ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ያለው የኢንተርኔት ግንኙነት ደካማነት ለማስወገድ “ቱ ቢ ኢንተርኔት ኮኔክሽን” በመጠቀም ጨረታውን ማግኘት ይችላሉ ያሉት አቶ አብረሃም፤ ለኢንተርኔት ብዙ እንዳይከፍሉ ዳታውን በሞባይላቸው አፕሊኬሽን ካወረዱ በኋላ ከኢንተርኔት ሂሳብ (ገንዘብ) ቆጠራ ውጭ ዳታውን ሳይከፍቱ (ኦፍ ላይን) ሆነው ጨረታው መች እንደወጣ፣ መች እንደሚዘጋ፣ ዝርዝር መስፈርቶቹ ምን እንደሆኑ፣ ምን ያህል ቀኖች እንደቀሩት፣ ሁሉንም መረጃ ማግኘት፣ ጨረታ አውጪ ድርጅቶችም፣ የራሳቸውን ዌብሳይት በመጠቀም ጨረታውን ማውጣት ይችላሉ ብለዋል፡፡
ጨረታው ስህተት ቢኖረው ወይም ተጨማሪ ነገር ለማከል ቢፈለግ በጋዜጣ ከሆነ ለማረም የሚቀጥለውን ሳምንት መጠበቅ አለበት። ሞብቴንደር ከሆነ ግን ወዲያው ስህተቱን ማስተካከል ይቻላል ያሉት የአሀዱ መስራችና ባለቤት፤ በእኛ አፕሊኬሽን መጠቀም በርካታ ሰዎች ስለሚያዩትና የተሻለ ተደራሽነት ስላለው ከብዙ ተወዳዳሪዎች መካከል የተሻለና ብቃት ያለውን፣ አሳማኝ ዋጋ ያቀረበውን አቅራቢ መምረጥ ያስችላል፤ ሙስናንም መከላከል ያስችላል በማለት አስረድተዋል፡፡
በቴንደር ዶት ኮም መጠቀም ያለውን ጥቅም ሲያስረዱም፡- ገንዘብ መቆጠብ ያስችላል፣ ኢኮኖሚውን ያነቃቃል፤ ሙስናን ይከላከላል፣ ምርታማነትን ያሳድጋል፣ ጊዜን ይቆጥባል፣ ከባቢ አየርን ከብክለት ይከላከላል ያሉት አቶ አብርሃም፤ አገራችን ለጨረታ ኅትመት፣ ለአስተዳደርና ለትራንስፖርት በዓመት ከ745 ሚሊዮን ብር በላይ እንደምታወጣ፣ 85 በመቶ የቢዝነስ ኩባንያዎች በኤሌክትሮኒክስ መንገድ እንደሚጠቀሙ፣ ሰባቱንም ቀናት 24 ሰዓት መገልገል እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
ሦስት ዓይነት አከፋፈሎች እንዳሉ የገለጹት አቶ አብርሃም፤ የ3 ወር፣ የ6 ወርና የዓመት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የ3 ወር 15 በመቶ ቫትን ጨምሮ 400 ብር፣ የ6 ወር ቫትን አካቶ 600 ብር፣ የአንድ ዓመት 900 ብር መሆኑን ገልፀው፣ ከ8 ባንኮች ጋር ስለሚሠሩ (ንግድ ባንክ፣ አዋሽ፣ ዳሸን፣ አቢሲኒያ፣ ንብ…) ተጠቃሚዎች ወደተመቻቸው አንዱ ባንክ ሄደው ክፍያውን መፈጸም እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ደግሞ ጨረታ አውጪዎች የጨረታ ሰነዶችን ኦንላይን (Bid on line) ይፋ በማድረጋቸው ሰዎች የጨረታ ሰነድ ለመግዛት ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩበትን ጊዜ 64.4 በመቶ መቆጠብ ማስቻላቸውን፣ የጨረታ ሰነድ ሻጭና ገዢ ማገናኘታቸውን፣ ከ3000 ደንበኞች በላይ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

Read 3684 times