Saturday, 15 December 2018 14:29

መቄዶንያ በ1 ወር ውስጥ ከ164 ሚ. ብር በላይ ድጋፍ አገኘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 የመንግሥት ተቋማት አመራሮች ማዕከሉን እየጎበኙ ነው

     ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን መጎብኘታቸውን ተከትሎ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከ164 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን የመጠለያ ህንፃዎች ለመገንባት ቃል ገብተዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ፤ ከህብረተሰቡ በአጭር የ8151 መልዕክት ሲሰበስብ የቆየውን 74,718,165 (ሰባ አራት ሚሊዮን ሰባት መቶ አስራ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ስልሳ አምስት) ብር አስረክቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማዕከሉ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ ዜጎች በአጭር መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ፣ ተቋማት ደግሞ ማዕከሉን እየጎበኙ ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ሲሆን ለዚህ ፈጣን ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ሰራተኞች አዋጥተው ከሰጡት 10 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ አንድ ባለ 5 ፎቅ ህንፃ ገንብቶ ለማስረከብ ቃል ገብቷል፡፡ 100 ነፃ የደርሶ መልስ ቲኬቶችን ጨምሮ የተለያዩ የዓይነት ድጋፎችንም እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የ15 ሚሊዮን ብር ልገሳና አንድ የህንፃ ወለል በ56 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ለማስረከብ ቃል ገብቷል፡፡ የካውያ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ የስጋ መፍጫ ማሽኖች፣ የቴሌቪዥንና ሌሎች የቁሳቄስ ድጋፎችንም አድርጓል፡፡
5 ሚሊዮን ብር እና ሁለት አምቡላንሶችን ያበረከተው የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በበኩሉ፤ ለሚገነባው የማዕከሉ ህንፃ፣ እንዲሁም ለሰራተኞችና ለአረጋዊያኑ ዋስትና ለመግባት ቃል ገብቷል፡፡
አንድ የህንፃ ወለል ለመገንባትም ድርጅቱ ፍላጎቱን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በበኩሉ የ1 ሚሊዮን ብር እና የ2 መቶ ኩንታል ስኳር ድጋፍ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ፤ የ5 ሚሊዮን ብር እና ብርድልብሶችን ጨምሮ የተለያዩ የዓይነት ድጋፎችን አድርጓል፡፡ እንዲሁም የህንፃ ግንባታ ኮንቴነሮችንና ፌሮ ብረቶችን ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክም፤ የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ሃይለየሱስ በቀለ፤ በእሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም የ10 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡ 1 የህንፃ ወለል በ56 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ለማስረከብም ቃል ገብቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬት፤የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲሁም በቀጣይ በ10 የአዲስ አበባ ክ/ከተሞች ለሚገነቡ የማዕከሉ ህንፃዎች፣ የውሃ ቁፋሮና መስመር ዝርጋታ ለማከናወንና ሌሎች የአይነት ድፋፎችን ለማበርከት ቃል ገብቷል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ባፉት 3 ዓመታት ከህብረተሰቡ በ8151 አጭር የፅሁፍ መልዕክት የተሰባሰበውን ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አስረክቧል፡፡ በተጨማሪም የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲሁም የተለያዩ የነፃ አገልግሎቶችን ለማዕከሉ ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡ በቀጣይም እስከ ጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የተለያዩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፤ ቅዳሜና እሁድ፤ አረጋውያኑን እየጎበኙና ምሳ እያበሉ፣ የተለያዩ እገዛዎችን ለማድረግ፣ ወደ ማዕከሉ እንደሚያቀኑ ከተያዘላቸው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎም፣ኢትዮ ቴሌኮም ከህዝብ ያሰባሰበውን ጨምሮ ከ238 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማዕከሉ ተደርጓል፡፡ በርካታ ተቋማት በህንፃ ግንባታዎች ላይ ተሳትፎ ለማድረግም ቃል ገብተዋል፡፡ 

Read 5359 times