Saturday, 15 December 2018 14:26

የ“አብን” አመራሮች ከጠ/ሚ ጋር ተወያዩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)


     ሰሞኑን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና የተሰጠው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮች፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በአማራ ህዝብና በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲሁም በህግ የበላይነት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
የአብን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ስለውይይቱ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ አመራሮቹን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቢሮአቸው ጠርተው ለሰአታት የቆየ ውይይት ማካሄዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ በዋናነት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው ፍትህን የማስፈን ጉዳይ፣ በየአካባቢው እየተነሱ ስላሉ ግጭቶች እንዲሁም የሀገር አንድነትንና በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት አስጠብቆ ወደፊት መጓዝ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን አቶ ክርስቲያን አስታውቀዋል፡፡
በአብን በኩል በዋናነት የአማራ ህዝብ የማንነት፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የህልውና ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች መቅረባቸውን ያወሱት ኃላፊው፤ ጠ/ሚኒስትሩም እነዚህን ጉዳዮች በአግባቡ እንደሚረዱ ገልፀው፣ ነገር ግን ችግሮቹ በሰከነ መልኩ ዘላቂ በሆነ መንገድ መፍታት እንደሚገባ መግለፃቸውን ጠቁመዋል፡፡
እርቅ፣ ህገ መንግስት መቀየር፣ የህዝብ ቆጠራ ጉዳዮችም በውይይቱ ላይ ተነስተዋል፡፡
ህገመንግስቱን ማሻሻል እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱን ነገር ግን ም/ቤቶች በሙሉ በገዥው ፓርቲ ስለተያዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር መግባት እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለፃቸውን ያስታወሱት አቶ ክርስቲያን፤ ፓርቲያቸው በተለይ ቀጣዩን ምርጫ ለማድረግ የህገ መንግስቱ መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ማንሳቱን አስታውቀዋል፡፡ በሂደት ሁሉም ፓርቲዎች ተወያይተው በጉዳዩ ላይ አቋም እንደሚይዙም መግባባታቸውን ለማወቅ ተችሏል። በዚህ ውይይት ላይ የተነሳው ሌላው ጉዳይ፤ የህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ክርስቲያን ባለፈው ቆጠራ የተሠራው ስህተት ድጋሚ እንዳይሠራ ማስገንዘባቸውን አውስተዋል፡፡
ባለፈው ቆጠራ ከ3.3 እስከ 6 ሚሊዮን የሚደርስ አማራ መጥፋቱን ማስረዳታቸውንና ለዚህ በደል ህዝቡ ካሣ ሊከፈለው እንደሚገባና በመንግስት ደረጃም በዚህ ጉዳይ ግልጽ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት ፓርቲያቸው መጠየቁን፤ እርቅን በተመለከተም በቅድሚያ ባለፉት 27 አመታት ለተፈፀሙ ወንጀሎች የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ተቋቁሞና ጉዳዩ ተጠንቶ፣ ወደ እርቅ መገባት እንዳለበት ማስገንዘቡን አስታውቀዋል፡፡
በሀገሪቱ የተጀመረውን ፍትህን የማስከበር ሂደት ለመደገፍና በመሰል ጉዳዮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጐን ለመቆም “አብን” መወሰኑን አቶ ክርስቲያን አስታውቀዋል፡፡
“ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገው ውይይት እጅግ ውጤታማ ነበር” ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአማራ የቆመ ድርጅት አለ ብለው እኛን ለመስማት ፍቃደኛ ሆነው ማነጋገራቸው በበጐ የሚታይ  ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በጐንደር ከቅማንት ጉዳይ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ግርግር አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ከግርግሩ ጀርባ ህወኃት እንዳለበት በመግለጽ “ህወኃት አሸባሪ ድርጅት ነው፤ እንደ ፓርቲ ተመዝግቦ በሀገሪቱ ሊንቀሳቀስ አይገባውም” ብሏል፡፡
ህወኃትን በዘር ማጥፋት፣ በስልጣን መባለግና በሰብአዊ መብት ጥሰት የኮነነው “አብን” ከህወኃት ጋር አብረው የሚሠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ግንኙነታቸውን በድጋሚ እንዲያጤኑም ጠይቋል፡፡  

Read 5650 times