Saturday, 15 December 2018 14:31

የሰብአዊ መብት ጥሰት ለተፈፀመባቸው ካሣ ሊጠየቅ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ባለፉት 27 ዓመታት በመንግሥት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለተፈፀመባቸው ዜጎች ካሳ የሚጠይቅ የህግ ባለሙያዎች ማህበር እየተቋቋመ ሲሆን የሰብአዊ መብት በተፈፀመባቸው ወገኖች ላይ ጥናት እየተካሄደ መሆኑም ታውቋል፡፡
በዜጎች ላይ ለተፈፀመ የሰብአዊ መብት ጥሰት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ተጠርጣሪዎችን ወደ ህግ እያቀረበ መሆኑን ያደነቁት የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን፤ “መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች እስካሁን ግማሽ መንገድ ነው የሄድነው፤ ቀሪ ለህግ መቅረብ ያለባቸው ተጠርጣሪዎችና ጉዳዮች አሉ” ብለዋል፡፡
መንግሥት ለተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እውቅና መስጠቱና ፈፃሚ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ማቅረብ መጀመሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ አመሃ፤ “አካላቸውን ለተጎዱ፣ አካላቸውን ላጡ፣ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው፣ እንዲሁም ኑሮአቸውና ቤተሰባቸው ለተበተነባቸው ተገቢው ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል” ብለዋል፡፡
ለተፈፀመ ጉዳት ሁሉ ካሳ በህግ መሰጠት አለበት የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ ይህን ካሳ ለማሰጠትም በመመስረት ላይ ያለው “የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብት  ማህበር” በጥናት ተደግፎ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ተጎጂዎች ወደ መደበኛ ህይወታቸው የሚመለሱበት  በቂ ህክምና የሚያገኙበት፣ የስነ ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ በቋሚነት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ በካሳ ጥያቄው እንደሚካተትም አቶ አመሃ ጠቁመዋል፡፡
የእያንዳንዱ ተጎጂ የጉዳት አይነትና መጠን በመንግስት ተጠንቶ ካሳው ሊከፈል እንደሚገባ የገለፁት አቶ አመሃ፤ እየተቋቋመ ያለው “የህግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብት ማህበር” በራሱ መንገድ የተጎጂዎችን ሁኔታ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አይነትና የተጎጂዎችን ብዛት እንዲሁም ተጎጂዎች በፍትሃብሔር ክስ ካሳ የሚያገኙበትን የህግ አካሄድ እያጠና መሆኑን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ተጐጂዎችን በተመለከተም የጉዳታቸው መጠን ምንያህል ነው? እንዴት ነው ህክምና ማግኘት የሚችሉት? እንዴት ነው ወደ መደበኛ ህይወት መመለስ የሚችሉት? በሚለው ላይ ማህበሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ5ኛ ዓመት የህግ ተማሪዎችን በማሳተፍ ጥናት እያካሄደ መሆኑን አቶ አመሃ ገልፀዋል፡፡
ጥናቱ በቅርቡ ተጠናቆ ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት እንደሚያመራ ያብራሩት የህግ ባለሙያው፤ ተጎጂዎች ካሳ እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ የህግ ስርአቱም እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ተቀብሎ እንዴት ያስተናግዳል የሚለውን ለመፈተሽም ይረዳል ብለዋል - እንደዚህ አይነት ክስ ለፍ/ቤት እስካሁን ቀርቦ እንደማያውቅ በማስታወስ፡፡
“የህግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብት ማህበር ምስረታም ተጠናቆ የመንግሥት ፍቃድ እየተጠበቀ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አመሃ፤ ማህበሩ በዋናነት በሰብአዊ መብት ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ሰሞኑን በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢዎች፣ “የፍትህ ሰቆቃ” በሚል ርዕስ በተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ላይ ከተሳተፉ ተጎጂዎች መካከል ሁለት እግሩ ተጎድቶ በድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ወጣት ዮናስ ጋሻው፤ ዘጋቢ ፊልሙ ላይ የደረሰበትን ጉዳት መግለፁን ተከትሎ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሰበት እንዲሁም ከተከራየበት ቤት እንዲወጣ መደረጉን አስታውቋል፡፡           

Read 6158 times