Saturday, 15 December 2018 14:32

የትግራይ ሰልፎችና የፖለቲከኞች ስጋት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

   “መገንጠል የትግራይ ህዝብ አጀንዳ አይደለም”

     መቀሌን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች ከሰሞኑ ለሁለተኛ ጊዜ “ህገ መንግስቱ ይከበር፣ የማንነት የድንበር ኮሚሽን ሊቋቋም አይገባም፤ ዘርን ለይቶ የሚያጠቃ የህግ ማስከበር ሂደት ተቀባይነት የለውም” የሚሉ መፈክሮች ተንፀባርቀዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል “የትግራይ ወጣቶች በቀጣይ ለማንኛውም ነገር እንዲዘጋጁ አበክረው ያሳሰቡ ሲሆን፤ የህዝቡ ድምጽ ሊደመጥ እንደሚገባውም ተናግረዋል - በሰልፎቹ፡፡
ሠላማዊ ሰልፉ አስፈላጊ እንደሆነ የሚገልፀው የአረና ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ፤ በተለይ “ህገመንግስቱ ይከበር” የሚለው መርህ የምስማማበት ጉዳይ ነው ይላል፡፡ ከዚህ ቀደም በትግራይ ህገ መንግስት ይከበር ብሎ ሠልፍ መውጣት እንደ ሃጢያት ይቆጠር እንደነበር ያስታወሰው አብርሃ፤ “አሁን ህወሓት በራሱ ደርሶ ሲያየው ያደረገው ቢሆንም የምደግፈው ጉዳይ ነው” ብሏል፡፡
“ሠልፍ በዋናነት ትክክለኛ ጥያቄ የያዘ ቢሆንም ልክ ህወሓትን የሚደግፍ ተደርጐ መቆጠር የለበትም” ያለው ሊቀመንበሩ፤ የትግራይ ህዝብ አጥፊዎችን ከህግ ለመከላከል ያደረገው ሠልፍ ተደርጐ መውሰድም እንደሌለበት ይገልፃል፡፡ የህወኃት ባለስልጣናት ህዝቡ ከጐናቸው የተሠለፈ በማስመሰል ከፌደራል መንግስት ጋር ለመደራደሪያነት ሊጠቀሙበት ይፈልጉ ይሆናል ያለው አቶ አብርሃ፤ ይህ ግን ፈጽሞ ይሳካላቸዋል የሚል እምነት የለኝም” ብሏል፡፡
“የመድረክ” እና “የአረና” ሊቀመንበር አቶ ጐይቶም ፀጋዬ በሠልፉ አንድምታ ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው፤ ነገር ግን ህወሓት ሠልፉን እንዳዘጋጀው አልጠራጠርም ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀድሞ አረና ተመሳሳይ ሠልፍ ለማድረግ ሞክሮ መከልከሉን በማስረጃነት በመጠቆም፡፡
“በሠልፎቹ የሚነሱት ጥያቄዎች ትክክለኛ ቢሆኑም ሠልፎቹ የተደረጉበት ወቅት ግን የህወሓት አመራሮች መሸሸጊያ በሚፈልጉበት ሰዓት መሆኑ በሌላው ህዝብ ዘንድ በበጐ እንዳይታይ አድርጐታል” የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ጐይቶም ገልፀዋል፡፡
ሠላማዊ ሠልፉ በህዝቡ ሙሉ ፍላጐት የተደረገ ነው? አይደለም? የሚለውን ለማወቅ በመጀመሪያ ህዝቡ ነፃ ሊወጣ ይገባው ነበር የሚሉትም ሊቀመንበሩ፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሠላማዊ ሠልፉ በህዝቡ ፍላጐት ብቻ ነው የተደረገው ማለትም አይቻልም” ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ኢ/ር ይልቃል ግን የተለየ ሃሳብ ያንፀባርቃሉ፡፡ “ሰልፉ በትክክልም የህዝቡ ስሜት የተንፀባረቀበት ነው፤ ይህም የሆነው ላለፉት 27 አመታት የተገነባው ብሔር ላይ የተመሠረተ ስርአት ሁሉንም ነገር በብሐር ቋት ውስጥ እንዲታሰብ በማስቻሉ ነው” ባይ ናቸው፡፡  
“የኛ ልጆች ለምን ይነካሉ? ከሚል መነሻ የተደረገ ሠልፍ ነው” ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት  ኢ/ር ይልቃል፤ “ሠልፉ ራስን የመከላከል ነው” ይላሉ፡፡
ሠልፉ የሚያመላክተው ሃገሪቱ ምን ያህል በጐሣና በብሔር መከፋፈሏንና የባዕድነት ስሜት መበልፀጉን የሚያሳይ ነው ብዬ አምናለሁ ብለዋል - ኢንጂነሩ፡፡ የሠማያዊ ፓርቲ አመራሩ አቶ አበበ አካሉ ደግሞ ደግሞ የዜጐች ህገመንግስታዊ መብት መከበር በጀመረበት በአሁኑ ወቅት ህገመንግስቱ ይከበር ብሎ ሠላማዊ ሠልፍ መውጣት አስገራሚ ነው ይላሉ፡፡ ሠልፉም የትግራይን ህዝብ ሃሳብ ይወክላል የሚል እምነት እንደሌላቸው አቶ አበበ ይናገራሉ፡፡
የትግራይ ህዝብ ለህግ ማስከበሩ ቀና መሆን አለበት የሚሉት አመራሩ፤ ህገመንግስቱ ይከበር ሲባል በወንጀል የሚፈለግን ሰው አንድ ክልል ለፌደራል መንግስቱ አሳልፎ የመስጠት ህገመንግስታዊ ግዴታ እንዳለበት መገንዘብ ይገባል፤ ህገመንግስቱ ሊጣስ አይገባውም” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
“የሰልፎቹ ባህሪ በህዝብ የመነገድና ህዝብን በአስተሳሰብ የማሸፈት አደገኛ ተግባር ነው” ይላሉ አቶ አበበ፡፡
በሠልፉ ላይ “የገነባናት ሀገር የማታከብረን ከሆነ የምታከብረንን ሃገር ለመፍጠር እንገደዳለን” የሚል መፈክር መሠማቱ ይታወሳል፡፡ በሠላማዊ ሰልፍ ከተንፀባረቁ መፈክሮች አንዱ ነበር፡፡ በእርግጥ ትግራይ በፌደራል መንግስቱ እርምጃዎች የተነሳ ልትገነጠል ትችል ይሆን? “ይሄ የማይሞከር ነው” ይላሉ - የትግራይ ፖለቲከኞች፡፡
ፖለቲከኛና የማህበራዊ ድረ ገጽ ጦማሪው አቶ አምዶም ገ/ስላሴ፤ መገንጠል የሚል ጉዳይ ለትግራይ ህዝብ አይሠራም ይላሉ - የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን ለድርድር እንኳ እንደማያቀርብ በመጠቆም፡፡ “የህወሓት ባለስልጣኖች አጀንዳውን እንደ አንድ የፖለቲካ መጫወቻ ሊጠቀሙበት ይችላሉ” የሚሉት ጦማሪው “ህዝቡ ግን በምንም ተአምር የመገንጠል ሃሳብ የለውም የህወሓት ሰዎች እንገንጠል ካሉም መጀመሪያ የሚታገላቸው የትግራይ ህዝብ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም” ይላል፡፡ በህወሓት ውስጥ በጣም ተስፋ የቆረጠው ቡድን አጀንዳውን እንደማስፈራሪያ ሊጠቀምበት ይሞክራል እንጂ በህዝቡ ውስጥ የመገንጠል ሃሳብ ፈጽሞ የለም” ሲል አስረግጦ ይናገራል አቶ አምዶም፡፡
አቶ አብርሃም ሆነ አቶ ጐይቶም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ “የመገንጠል ጉዳይ የትግራይ ህዝብ አጀንዳ አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም፤ መፈክሩና አጀንዳው የህወሓት ነው” ብሏል - አቶ አብርሃ፡፡
“የትግራይ ህዝብ ተለይቶ ጥቃትና አድልኦ እንዲፈፀምበት ስለማይፈልግ መሠረታዊ ጥያቄው በእኩል ልታይ ይገባል የሚል እንጂ የመገንጠል ጉዳይ አይደለም” ብለዋል ፖለቲከኞቹ፡፡
ተጠያቂነት ያለባቸው ሰዎች በየትኛውም ደረጃ በህግ የመጠየቃቸው ጉዳይ ለድርድር ሊቀርብ እንደማይገባ የሚያስገነዝቡት የሰማያዊው አቶ አበበ፤ የትግራይ ህዝብ ጥቂቶች የህግ ተጠያቂነት ያለባቸውን ሰዎች ለመከላከል ብሎ ከቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ይጣላል የሚል እምነት የለኝም፤ ጉዳዩን በአግባቡ ሲረዳ ወደ እነሱ መዞሩ አይቀርም ብለዋል፡፡ እስካሁን ባለውም የትግራይ ህዝብ አምኖበት በሠልፉ የተሳተፈ አይመስለኝም፤ ይህ በመሆኑም የከፋ ችግር ይፈጠራል የሚል ስጋት የለኝም” ይላሉ አቶ አበበ፡፡
ጉዳዩ በአግባቡ መያዝ አለበት” የሚሉት ኢ/ር ይልቃል በበኩላቸው፤ “በአግባቡ ካልተያዘ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ሊያመራ ይችላል፤ ተስፋ የቆረጠ አካል ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡
በሌሎች ሀገራት የተፈጠሩ የእርስ በእርስ ጦርነቶችም መነሻቸው እንዲህ ያለው አካሄድ መሆኑን የጠቀሱት ኢ/ር ይልቃል፤ “የውጭ ሃይሎችም በጉዳዩ እጃቸውን ሊያስገቡ የሚችሉበት እድል መፈጠር የለበትም” ብለዋል፡፡
የፌደራል መንግስቱ የትግራይን ህዝብ ፍላጐት በሚገባ የተረዳው አይመስለኝም የሚሉት አቶ አምዶም፤ ጉዳዩ በጥንቃቄ መታየትና ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አቶ ጐይቶም በበኩላቸው፤ የህዝቡ የልብ ትርታ በሚገባ የሚደመጥ ከሆነ፣ የከፋ ችግር ይኖራል የሚል ስጋት እንደሌላቸው አውስተዋል፡፡ አቶ አብርሃ በበኩላቸው፤ በፌደራሉና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል የጐላ ፀብ እንደሌለ ይገልፃሉ፡፡
መፍትሔው ምንድነው?
የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የሚመጥን መፍትሔ ያስፈልጋል የሚሉት ኢ/ር ይልቃል በቋሚነት የፌደራል ስርአት አወቃቀሩን በድጋሚ መፈተሽና ሀገሪቱ ወዴት መሄድ እንዳለባት ግልጽ መስመር አውጥቶ መወያየት ነው ይላሉ፡፡ ይሄን ሃሳብ የሚያጠናክሩት አቶ አበበም፤ ሁለም ሰው ሃላፊነት ተሰምቶት ነገሮችን ከማራገብ መቆጠብ ያስፈልጋል፤ የፌደራል መንግስቱና የክልሉ አስተዳደር ህዝብን ወደ ማይሆን አቅጣጫ ከመምራት ተቆጥበው፤ ችግሩን በውይይት መፍታት እንዳለባቸው ያሳሰቡት አቶ አበበ፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ሀገሪቱ በቀጣይ ወደ አለመረጋጋት አዞሪት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
ረገብ ብሎ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ጐይቶም በበኩላቸው፤ “ግፋ በለው ከሚል ቅስቀሳ መውጣት አለብን፤ ይህ ካልሆነ ግን ሀገሪቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት የምትገባበት እድል ሰፊ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡


Read 8695 times