Monday, 17 December 2018 00:00

1.55 ሚ. ሶርያውያን ስደተኞች ወደመኖሪያቸው ተመልሰዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ሞቃዲሾ ብዙ ህዝብ ተጨናንቆ የሚኖርባት የአፍሪካ ከተማ ሆናለች

    የእርስ በእርስ ግጭትን በመሸሽ ከመኖሪያቸው ከተፈናቀሉ ሶርያውያን ስደተኞች መካከል ከ1.55 ሚሊዮን በለይ የሚሆኑት ወደመኖሪያቸው መመለሳቸውን ዥንዋ ዘግቧል፡፡
ወደመኖሪያቸው ከተመለሱት ስደተኞች መካከል 1.26 ሚሊዮን የሚሆኑት በአገር ውስጥ ተፈናቅለው የነበሩ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ከ290 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ወደተለያዩ ጎረቤት አገራት ተሰድደው የነበሩ እንደሆኑ አመልክቷል፡፡
በጦርነት በፈራረሰቺዋ ሶርያ ስደተኞችን መልሶ ለማስፈር የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና 1.5 ሚሊዮን ያህል ዜጎችን መልሶ ለማስፈር የሚያስችል ስራ መሰራቱንም ዘገባው ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ብዙ ህዝብ በተጣበበ ሁኔታ ተጨናንቆ የሚኖርባት ቀዳሚዋ የአፍሪካ ከተማ መሆኗን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ግጭት፣ ጦርነትና የተፈጥሮ አደጋዎችን በመሸሽ ከገጠር አካባቢዎች ወደ መዲናዋ ሞቃዲሾ የሚሰደዱ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን የጠቆመው ኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የተባለ ተቋም፣ በ2018 አመት የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ340 ሺህ በላይ ሶማሊያውያን ወደ ሞቃዲሾ መግባታቸውን አስታውቋል፡፡ የሞቃዲሾ ነዋሪዎች ቁጥር 2.6 ሚሊዮን ያህል መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ በከተማዋ በአንድ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ ከ28 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚኖሩና ይህም ከተማዋን ከባንግላዴሽዋ ዳካ ቀጥሎ ነዋሪዎች በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩባት ሁለተኛዋ የአለማችን ከተማ ያደርጋታል ብሏል፡፡

Read 4114 times