Print this page
Saturday, 15 December 2018 15:07

“ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ!!”

Written by  ከበቀለ ዘሪሁን፤ (የኤልፎራ ሠራተኛ)
Rate this item
(0 votes)

 “ጥልቅ ተሐድሶ በሚድሮክ መንደር” በሚል ርዕስ ሰሞኑን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የቅዳሜ ህዳር 22 ቀን ዕትም ላይ በኤልፎራ ኩባንያና ግለሰቦች ላይ ላይ ያነጣጠረውን  ወቅታዊ ጽሑፍ በአንክሮ አንብቤዋለሁ። ሐሳብን የመግለጽ መብት እየዳበረ የመሄዱ ምልክቶች በመታየታቸው፣ የእድሉ ተጠቃሚ መሆን በፈለጉ ግለሰብ የተደረገ ጥረት አድርጌም እመለከተዋለሁ፡፡ነገር ግን “የጽሑፉ ይዘት የሚያንፀባርቀው የጸሐፊውን ብቻ ነው” ከማለት በስተቀር፣ የብእር ስምነቱ በማያጠራጥር ሁኔታ፣ ”ኩርኩራ ዋፎ” የሚል ስም የተጠቀሙትን ጸሐፊ ማንነት በይፋ አውቆ ቢያንስ የኢሜይል አድራሻ አግኝቶ፣ በቀጥታ ለማወያየት አልቻልኩም። ከዚህም በላይ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የኤልፎራ ኩባንያ እንደ ጠበቅሁት ሳይሆን ዝምታን በመምረጡ፣ ይልቁንም የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር፣ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ስለ ጽሁፉ ይዘት አስተያየት ሳይሰጡ ለማለፍ ባልቻሉበት፣ የሠራተኞች ወርኃዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስብሰባ ላይ ለጸሐፊውና ለጥረቱ አድናቆታቸውን በመግለጽ በአካል መጥቶ ቢያወያያቸው ይመርጡ እንደነበር በማውሳትና እውነታውን አሳውቀው የጋዜጣው ጽሑፍ ተባዝቶ በየመሥሪያ ቤቱ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ እንዲለጠፍ በማድረግ፣ ለተለየ ሐሳብ መንሸራሸር ያላቸውን እምነት እንደገና ከማረጋገጥ ያለፈ ምንም እርምጃ እንደማይወስዱ በመረዳቴ፤ የመስሪያ ቤታችን ባልደረባ መሆናቸውን ያመንኩት እኚህ ጸሐፊ ያነሷቸው ገንቢ ሐሳቦች ተበረታተው፣ በርካታ ሊስተካከሉ የሚገባቸው አሳሳች መረጃዎችና መታረም የሚገባቸው የአመለካከት ጽንፎች ተለይተው፣ምንም እንኳን ጸሐፊው “በእጄ ብዙ ማስረጃዎች አሉ” እያሉ ለማስፈራራት በሞመከራቸው ጭምር ምናልባት፣ ለአንዳንዶች እውነት መስለው የሚታዩ ግን ሐሰተኛ የሆኑ ጉዳዮች መታረም ስላለባቸው፣ ጽሁፉን ያነበቡ ሁሉ፣ እኔ የማውቀውን እንዲያውቁ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተገድጃለሁ፡፡
ጽሑፉ በአጠቃላይ መንፈሱ መጥፎ ተብሎ በጥቅል የሚወገዝ ባይሆንም በሶስት ደረጃዎች ከፍሎ በማየት፣ ብርታትና ጥንካሬውን ማቅረብ ይቻላል፡፡ እነዚህም ስለ ሥራ መሪያችን ስለ ዶ/ር አረጋ ይርዳው አስተዋጽኦና ችሎታ የመሰከሩትን በሚመለከት፤ የኤልፎራና የዶ/ር አረጋ ድክመቶችና መሻሻል አለባቸው ስለሚሏቸውና ማብራሪያ ስለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች፣ እንዲሁም የጽሑፉ ዋነኛ ዓላማና መነሻ ስለሆነው አንድ ግለሰብ ስላሰፈሯቸውና በብዙ ስህተቶች ስለታጨቁት አስተያየቶች የሚቀርቡ ክፍሎች ናቸው፡፡
በመሠረቱ ግለሰቡ ባበረከቱት ጽሑፍ፣ ስለ ድርጅቶቻችን የሥራ አመራር፣ ስለ ሥራ መሪያችን ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሥራ ተሞክሮና ማንነት፣ የዕውቀት ክህሎትና ታታሪነት ከተዘረዘሩት በላይ ብዙ ሊባል ቢቻልም፣ ጸሐፊው በጠቀሱት መጠን በጥሩ ንጽጽራዊ ቋንቋ በብእራቸው የመሰከሩት እውነታ በመሆኑ አልመለስበትም፡፡ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎችንና ማኔጅመንቱን በስመ ሚድሮክ በጀምላ ከመውቀስ መቆጠብ እንደሚያሻ የሰነዘሩት አስተያየትና ውድቀት የታየባቸው አንዳንድ ሁኔታዎችም  የባለሀብቱ ድከመት የወለደው ውድቀት አለመሆናቸውን ያመላከቱበት አገላለጽም እንዲሁ አክብሮት ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ዶ/ር አረጋ እንዳሉት፤ ”በጥቅል አስተማሪነቱ እንውሰደው” ብሎ ከማለፍ መብራራት የሚገባቸውና እውነት መስለው ሊያሳስቱ የሚችሉት ተለይተው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡  
የሥራ መሪያችን የዶ/ር አረጋን የሥራ አመራር ትግበራን አስመልክቶ ጸሐፊው፤ “Double Standard” በማለት የሰነዘሩትን ወቀሳ የቅድሚያ ትኩረት አድርጌዋለሁ፡፡ ”Double Standard” በሚል የተሰነዘረው ይህ ኃሳብ፤ የዕውቀት ሽግግርንና የውጭ ዜጋን በኢትዮጵዊ ባለሙያ የመተካትን ድርጅታዊ ተግባር በሚገባ ካልተረዳ ሰው የተሰነዘረ ሐሳብ በመሆኑ፣ የቃሉ አጠቃቀም ጭምር የተሳሳተ አተረጓጎም ይዟል፡፡ ጸሐፊው በጽሑፋቸው እንዳረጋገጡት፤ በ35 ፈረንጆች የተወረረ ይመስል በነበረው ግዙፍ ኩባንያ፣ በሚድሮክ ወርቅ የውጭ ዜጎችን፣ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ለመተካት፣የሥራ መሪያችን መቻላቸው፣ እውነት ነው፡፡ ይህ ተግባር እንዲያው በዘፈቀደ የተከናወነ ሳይሆን በኩባንያው ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ ከታች ተጥለው የነበሩትን ሠራተኞች ማንነት ሳይቀር አጥንቶ፣ 10 ዓመታት በፈጀ ሒደት ኢትዮጵያውያኑን ለአመራር ብቁ በማድረግ፣ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የሚመራ፣ ዘመናዊ የወርቅ አምራች ኩባንያ የመገንባት ተግባር ተከናውኗል፡፡ ይህ የሥራ መሪያችን አቋም የሚለዋወጥ ሳይሆን በየትም ሆነ የት ተገቢውን ጥናት በማድረግ መከናወኑ የሚቀጥል ሆኗል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስፈላጊነቱ በሚታመንበት ወቅትና ሥራውን ለማከናውን በቂ ባለሙያ በሀገር ውስጥ ባይገኝ፣ “ፈረንጅ” የተባለ ሀገራችን ዝር አይልም ማለት አይደለም፡፡ በጊዜ ልዩነትና በአካባቢ ሁኔታዎች የሚፈጠሩትን ተግዳሮቶች ከግምት ውስጥ  ሳያስገቡ፣ በአንድ አንገት ሁለት ምላስ በሚመስል አባባል፣ ትችት መሰንዘር ግን ከአላዋቂነትም በላይ ተራ ጥላቻ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የሥራ መሪያችን፣ በየትኛውም መመዘኛ፣ ፈረንጅ በማምጣት አባዜ የሚወቀሱ አይደሉምና ነው፡፡
ይህንን የሥራ አመራር ብቃትና ክህሎት፣ በአሁኑ ወቅት በኤልፎራ ኩባንያ ውስጥ ከተጀመረው የሥራ ሒደት ጋር ስንመለከተው ነገሩ የበለጠ ግልጽ ይሆናል፡፡ በዘመናዊ የእርሻ ትምህርት አንቱ የሚያሰኝ የትምህርት ማስረጃ ይዞ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ለቀናትም ያህል ወጣ ለማለት የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ባለበት ድርጅትና አልፎ ተርፎም ችሎታ ያለው ዜጋ በሚታጣበት አጋጣሚ፣ ረጃጅም ጫማዎችን አጥልቆ በክረምት የማጥ ጭቃ እየተራመደ፣ ገጠሩን ለማልማት ዕውቀቱንና ጉልበቱን በቆራጥነት ለመሽጥ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣን  ባለሙያ፣ በፈረንጅነቱ ብቻ የማግለል አባዜም ሊኖረን አይገባም፡፡ በኤልፎራ ኩባንያ ውስጥ የተደረገውም እንደ ዘበት፤ “ባለሙያ እያለ ለምን ፈረንጅ?” ተብሎ የሚተች አይደለም፡፡
የኤልፎራ ፈረንጅ ሠራተኞች ወደ ድርጅቱ የመጡት ምናልባትም በዓይነቱ በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው አዲስና ዘመናዊ የመስኖ አደረጃጀትና እጅግ ዘመናዊ የዶሮ እርባታ ተተቋም ግንባታ፣ በኩባንያው ሕይወት ውስጥ ስለተፈጠሩና እነዚህን የአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች በተሻለ ልምድና ዕውቀት ሥራ ለማስጀመር መሆኑን ጸሐፊው በሚገባ ያውቁታል። 850 ሚሊዮን ብር ድረስ የወጣባቸውን የዘመናዊ ዶሮ እርባታ  መሣሪያዎች ተከላ በጨፋ ለማከናወንና ምርታማነትን ለማዘመን የመሣሪያዎቹ ስሪት ሀገር ከሆነቺው ኢጣሊያ ባለሙያ መምጣታቸው፣ ወይም ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የፈሰሰበትን ዘመናዊ የነትሌ የመስኖ እርሻ ሥራ ለምርታማነትና ግብይት ለማብቃት፣ የደቡብ አፍሪካና የስፔይን ተወላጆች በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠራቸው በሀገሪቱ የሰው ኃይል ፖሊሲ በተደገፈ አሰራር፣ ተፈላጊዎቹ ባለሙያዎች ሀገር ውስጥ አለመኖራቸው ታውቆና፣ የውጭ ባለሙያዎቹ አስፈላጊነት በመንግሥት ጭምር ታምኖበት የተከናወነ ተግባር ነው፡፡ ባለሙያዎቹ፤ የመኖሪያና ሥራ ፍቃድ ተሰጥቷቸው፣ በኤልፎራ ሠራተኝነት ሲቀጠሩ፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጁ ሽግግርን ከማፋጠን እሳቤ እንጂ ብቃትና ችሎታ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን፣ የሥራ እድል ለማሳጣት አለመሆኑን፣ መንግሥትም ሆነ የኩባንያው ሠራተኞች በሙሉ የተረዱት የሥራ አመራር ሒደት ውጤት ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ የሚፈልጋቸው የውጭ ዜጎች፤ የሀገሪቷ የሰው ኃይል ፖሊሲ በሚፈቅደው መሠረት ተጋብዘውና ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ ተቀብለው፣ የድርጅቱ ባልደረቦች ሲሆኑ የሚከፈላቸው ደመወዝ ዓለም አቀፋዊ ሚዛን  ያለውና በውጭው ዓለም የኑሮ ደረጀ ክፍያ ስሌት እንጂ በኩባንያው ስኬል መሠረት አለመሆኑን ጸሐፊውም እንደሚያውቁት አልጠራጠርም፡፡ ነገርን ለማሳመር ብሎ ብቻ የሚቀጠሩትን የውጭ ዜጎች ደመወዝ በሀገራችን ስኬል መሰረት ከሚከፈለው ሰራተኛ ደመወዝ ጋር ማነጻጸር ወይ አላዋቂነት አለበለዚያም ውዥንብር ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራ ብቻ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚሁ ፈረንጆች የሥነ ምግባር ጉደለት ሲያሳዩ ደግሞ የስራ መሪያችን፣ ቁርጠኛ ውሳኔ በመስጠት፣ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸውንም፣ ጸሐፊው አይዘነጉትም፡፡ በመሆኑም የሥራ መሪያችን ባደረጓቸው ጥረቶች፣ የዘመናዊው የንግድ ሥራ እንቅስቃሴና የገበያ ትስስር፣ የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ እንዲሉ በተቻለ መጠን  በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ብቻ እንዲሰሩ የሚጥሩ፣ በኢትዮጵያ ቤተ ሙከራነት (ላቦራቶሪ )፣ ኢትዮጵያዊ  መድኃኒት ለኢትዮጵያ ችግር ብለው በማመን፣ በሻኪሶ ሆነ በነትሌ፣ በመተከል ሆነ በጨፋ፣ በሚድሮክ ጐልድ ሆነ በኤልፎራ ተመሳሳይ አመራር የሰጡ እንጂ ፀሐፊው እንዳሉት፤ የ”Double Standard” ተግባሪ አይደሉም፡፡ አማራጭ ፍለጋ የማዕድን ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በነፃ ትምህርት አሰልጥነው፣ በማዕድን ዘርፍ ያሰማሩ የሥራ መሪ፤ በፈረንጅ አባዜ አይታሙም፡፡
ኤልፎራ ኩባንያ በሚያከናውነው የአግሮ ኢንዱስትሪ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የሚለፋበትን ያህል የማያስገኝ  የመሆኑ ምክንያት በየጊዜው በማኔጅመንቱ መፈተሽ እንደሚገባው ታምኖበት ጸሐፊው ጭምር የተሳተፉባቸው ስብሰባዎች በየጊዜው ተካሒደዋል። የሥራ መሪያችን በሕዋውም ዓለም ሳይንስ እጅግ የተራመዱ ናቸውና፣ በአንደኛው ስብሰባ ላይ  በጠፈር ውስጥ ብርሃን የሌለበት ግን ሕልውናው ባከተመ የሕዋው አካል ላይ ግዙፍ የስበት ኃይል የሚፈጥረውን ሽንቁር፤ የጥቁር ጉድጓድ (Black hole) ምሳሌያቸው አድርገው አስተምረውበታል፡፡ ጸሐፊው በስብሰባው ያደመጡትንና የኤልፎራን ሕይወት ያመለከተውን “ብር መቋጠር የማይችል ጥቁር ቀዳዳ ከረጢት (Black hole)” ጉዳይ ከፈረንጆች የደለበ ደመወዝ ጋር አዛምደው ሊተቹ ቃቷቸዋል፡፡ ያ ቀዳዳ በፈረንጆቹ ደመወዝ ምክንያት የተፈጠረው ሳይሆን በእኛው በውስጥ ሠራተኞች ግዴለሽነት፣ ውጤት ተኮር ባልሆነ የንግድ እንቅስቃሴና በግላዊ ጥቅም ላይ ብቻ በተደረገ ትኩረት በገጠመን አውዳሚ የገበያ ስሪት፣ ስበት ግፊት የተፈጠረ ቀዳዳ ነው፡፡ ለዚህም በመፍትሔ ፍለጋ ሂደት ውስጥ በአማራጭነት የታየው ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን በድርጅታዊ መዋቅር፣ ወደ ታች በማውረድና በማዝለቅ፣ ራሳቸውን የቻሉ፣ ”Semi Authonomous” ክፍሎች በኩባንያው ውስጥ መፍጠር መሆኑ ታምኖበታል፡፡
በዚህም አናት ላይ ያለውን የማናጅመንት ሸክም ወይም በሥራ መሪያችን የአንድ ወቅት ትምህርታዊ ጽሑፍ እንደተብራራው፤ በፒራሚዱ ጫፍ ላይ ያለውን ሸክም እስከ ታች እንዲዘልቅ በማድረግ የተፈጠረውን የከረጢት ጥቁር ቀዳዳ መድፈን የሚያስችል ስልት ተቀይሷል፡፡ በዚህም መሰረት፤ የዶሮ እርባታንና ቄራውን የያዘውን ክፍል፣ በአንድ ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ የጥራጥሬና አትክልት እርሻዎችን አሰባስቦ በሌላ ተመሳሳይ ደረጃ ባለው ኃላፊ እንዲመራና የሪል ስቴት ተግባራትም በተመሳሳይ ተደራጅተው፣ በበቂ ባለሙያ ስር ተልዕኮአቸውን እንዲወጡ ሲታቀድ፣ በሚዘረጋው አዲስ መዋቅር ማርኬቲንግን የመሳሰሉትና አናት ላይ ሸክም ያበዙት መታጠፋቸው ስለማይቀር፣ “መነካቴ አይቀርም” ብለው የሰጉት ጸሐፊ፤ የብእር ችሎታቸውን ለአጓጉል ትችት ተጠቀሙበት፡፡ የድርጅቱን ከረጢት ጥቁር ቀዳዳ ለመድፈን፣ ዘመናዊው የአመራር ስርዓት ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ፣ ድርጅታዊ ከህሎትን በተመጣጠነ የሰው ኃይል ቁጥር መዘመን፣በሥራ መሪያችን አገላለጽም፤ “Right Sizing” ወሳኝነት ስለሚኖረው፣ ለዚሁ የተመጣጠነ የሰው ኃይል አደረጃጀትን በመከተል ወደ ታች ዝቅ ብለውና በቀጥተኛ የማምረት ተግባር ላይ ለመሠማራት ሲመደቡ፣ ብቃትና ችሎታ የሌላቸው ጸሐፊውን የመሳሰሉ ሰዎች “ሳልቀደም ልቅደም” ዐይነት ትችት ቢሰነዝሩ ብዙም አያስደንቅም፡፡
ትርፋማነትን በሚመለከት ተያይዞ በተሰነዘረውም ትችት፤ ወጪና ገቢን ያገናዘበ የንግድ እንቅስቃሴ በወጪዎቹ ላይ ትኩረቱን ማሳረፍ እንዳለበት ለማመልከት የተደረገው ጥረት፣ የሥራ መሪያችን በተደጋጋሚ እንደሚጠቅሱት፤ “common sense”  የሚያረጋግጥልን የሕሊና ዕውቀት ፍርድ፣ ሀቅ በመሆኑ ምሁርነትን ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ጥቅስ በመጥቀስ የሚገለጽ ዲግሪ ያለው የኢኮኖሚስት ባለሙያ ትንታኔ  የሚፈልግ አይደለም፡፡ ትርፋማ ለመሆን “Cost Control” ብቻ ሳይሆን ምርትን በትክክለኛ ዋጋ ለመሸጥ የሚያስችል ገበያን ፈጥሮ የሁለቱንም ሚዛናዊነት መጠበቅ እንደሚያሻ ኢኮኖሚስቶችም የሚያምኑበት በመሆኑ በዚህ ሒደት ወጪ እንዳይዝረከረክና የተባለውም ጥቁር ቀዳዳ(Black hole) ከመፈጠር እንዲያመልጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ የማርኬቲንግ ሰዎች ከደምበኞች ጋር ጤናማ ያልሆነ ጉድኝት ፈጥረው Cost ያለአግባብ እንዳይንርና ኩባንያ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። የኩባንያ ዓላማ ይህንን ሚዛን የመጠበቅ ስልት ስለሚያሻው፣ ደምበኛው ማንም ይሁን ማን፣ የታወቀና ያልታወቀ በሚል መለኪያ የገበያ ትስስርን ማስተዳደር አይቻልም። በመሆኑም ጸሐፊው እንደዚህ ያለ ድርጅት በማለት የትልቅ ደምበኛ ስም ጠቅሰው ያሰፈሩት አግባብነት ያለው አይደለም፡፡ ትርፋማና ውጤት ተኮር የሆነ የገበያ ትስስር ለማዳበር፣ ከደንበኛው ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በየጊዜው መቃኘት እንደሚገባ ዘንግቶ መተቸት፣ ኩባንያን ሳይሆን  የራስን ጥቅምና ትውውቅ ከማጎልበት ያለፈ ተልዕኮ ሊኖረው አይችልም፡፡    
ወደ ዋነኛው የጸሐፊው ጽሑፍ ዓላማ ስንመጣ ግን ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶችና መዋቅራዊ አስፈላጊነት፤ የኤልፎራን ምስራቃዊ ሪጅን እንዲመሩ የተመረጡት ሰው ላይ የተሰነዘሩትን ትችቶች እናገኛለን። በመሰረቱ በመሪዎች ሕይወትና የአመራር ሚና ውስጥ ተከታዩችን የማፍራት ብቃትና ችሎታ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሠራተኞቻቸውን ተፈጥሮአዊ ዝንባሌና እምቅ ችሎታ ፈልፍሎ የማውጣት፣ የመገንባትና የመጠቀም ከህሎት ለአንድ ድርጅትም ሆነ ለአንድ ሀገር ያለው ጠቀሜታ ጉልህ ነው፡፡ በዚህ መርህ ሊመዘን በሚገባ አመራር የኤልፎራን ሕይወት እንዲለውጡ በቅርቡ ከተመደቡት የሥራ ኃላፊዎች አንዱ የሆኑትና በጸሐፊው የተተቹትን ታታሪና ብልህ ሠራተኛ በሚመለከት የተሰነዘሩት ትችቶች፣ በአንድ ድርጅት ውስጥ በጋራ ለመስራት ከተሰማራ ባልደረባ የማይጠበቅና በግለሰብ ደረጃ በጥላቻ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነቀፋ በመሆኑ እጅግ አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡ ለአንባቢ ግንዛቤና ጠቀሜታ ሲባልም እውነታውን በዝርዝር ማቅረብ የግድ ነው፡፡
ለተጠቀሰው ኃላፊነት የተመረጡት ሠራተኛ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከተቋቋመ አንስቶ በግሩፑ ሠራተኝነት የነበሩ ሲሆን ሲቀጠሩ ዲግሪ ይዘው አልተቀጠሩም፡፡ ሆኖም በተለያዩ ኩባንያዎችና የተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ተመድበው አገልግለዋል፡፡ በኮርፖሬት ማኔጅመንቱ ውስጥ በጠቅላላ አገልግሎት ዘርፍ፣ የትራንስፖርት ስምሪትን በዘመናዊ እቅድ ከማደራጀት ጀምረው፣ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት እርከኖች ዕውቀትና ልምድ ሲያካብቱ የቆዩት እኚህ ትጉህ ሠራተኛ፤ በአንድ በኩል የሥራ መሪያችንን የሠራተኞችን ዕምቅ ችሎታ ፈልፍሎ የማውጣትና የማጐልበት ችሎታን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሠራተኛን መማር የሚችል ብሩህ አእምሮና አስተዋይ ልቦና የሚኖረውን ጠቀሜታ በግልጽ ለማስተማር፣ ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ፤ የሥራ ቦታ ብቻ ሳይሆን መማሪያና የባለሙያ ማፍርያ ተቋማት ስብስብ መሆኑንም የሚያረግጥ ነው፡፡ ለዚህም የሥራ ባልደረባችን ያስመዘገቧቸውን ተከታታይ የሥራ ውጤቶች በመመዘን መረዳት ስለሚቻል፣ ለአብነት ብቻ ጥቂቶቹን የሥራ ውጤቶቻቸውን እጠቅሳለሁ፡፡
የዩኒቲ ዩኒቨርስቲን የደሴ ቅርንጫፍና ካምፓስ ማስፋፊያ ሥራ በመምራትና አደረጃጀቱን ለማዘመን የተደረገውን ጥረት በማገዝ አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል፤
በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ የአዲስ አበባ የገርጂ ካምፓሰ ካከናወኗቸው በርካታ ተግባራት በተጨማሪ በቡራዩ የገፈርሳ ካምፓስ፣ ሕንጻዎችን በአነስተኛ ወጪና በተፈላጊ ጥራት አሰርተው አስረክበዋል፤
በቢሾፍቱ ከተማ በ100 ሚሊዮን ብር የተገዛውን የብሉ ናይል ሁለተኛ ፋብሪካን ዘመናዊ ለማድረግ በተሰጣቸው ሙሉ ኃላፊነት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራቸውን አጠናቀው ለፋብሪካው የዛሬ እይታ አብቅተዋል፤
በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የዶሮ እርባታ መንደር፣ በአካባቢ ዐየር ብክለት ችግር ሲገጥመውና ሰፊ ትችት ሲሰነዘርበት፣ በተሰጣቸው ኃላፊነት፣ ዘመናዊ ኬጅ በማሰራት፣ መጥፎ ሽታን የመሳሰሉትን ችግሮችን በማስወገድና በማስረከብ፣ በተደላደለ ሁኔታ ችግሮቹን ለመፍታት አስችለዋል፤
በዚሁ ከተማ ውስጥ ለኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች የተሰጡ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጁ 121 መኖሪያ ቤቶችን በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ አስገንብተው አስረክበዋል -- ወዘተ፡፡
እነዚህና ሌሎችም የባልደረባችን ስኬታማ ስራዎች የሚያረጋግጡት የሥራ ልምድ፣ ትምህርትና ሥራ ሲጣመሩ፣ ሰውን ሙሉ እንደሚያደርጉና ኢንዱስትሪያዊ ስኬትም የሚለካው፣ በዩኒቨርስቲ  ፊደል በመቁጠር  ሳይሆን በተሰጠ የሥራ ድርሻ ወጤትን በማስመዝገብ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት በአንድ የሙያ ዘርፍ ብቃትን ለማረጋገጥ የሚኖረው የምስክርነት ሚና ዝቅ ተደርጎ ሊታይ የማይገባውና አስፈላጊነቱም የማያጠራጥር ቢሆንም፣ብሩህ አእምሮና አስተዋይ ልቦና ያላቸውና ዲግሪ የሌላቸው፣ (በምሁራን እየተመሩ ጭምር) የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ መካድ አይቻልም፡፡    
ሌላው አሳዛኝ የትችት አቅጣጫ የታክሲ አሽከርካሪነትንና “የሥራ መሪያችን ሾፌርነትን” በማዛመድ ያቀረቡት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተቺውን የ“Intellectual Arrogance” ሰብዕና ያመለክታል፡፡ እንደ ማንኛውም ቢዝነስ፤ የታክሲ ንግድ ሥራ በጣም አስፈላጊና በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን ጸሐፊው አያውቁት ይሆናል እንጂ በውጭውም ዓለም የሚከበር የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ የታክሲ ንግድ ሙያ የትናንሽ ኩባንያዎች ምልክት እንጂ በጸሐፊው እንደተዘለፈው የዝቅተኛ ሥራ ምልክት አይደለም፡፡ የታክሲ አሽከርካሪዎች ከእነረዳቶቻቸው በሀገራችን የትራንስፖርት ሕይወት ውስጥ እየተጫወቱ ያለውን ሚና ማስተዋል ይጠቅማል። በውጭው ዓለም ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሰዎች ጭምር፣ የሚሰማሩበት የሥራ መስክ በመሆኑ፣ በንግድ ዓለም ያልነበረና በፖለቲካውም ዓለም ያልተሳከለት ሰው እንደሚለው፣ ሰውን ዝቅ የማድረግያ የሥራ መስክ አይደለም፡፡ መስተዋት ቤት የሚኖር ድንጋይ አይወረውርም እንዲሉ፣ የራስን ብቃት በተመደቡበት የስራ ዘርፍ ብቻ መፈተኑ ይጠቅማል፡፡
ሾፌራቸውንና እሺ ባይ ሎሌዎችን እንደሚቀጥሩ በጸሀፊው የታሙት የሥራ መሪያችን፤ “ሾፌር”፣ “ተላላኪ” ወዘተ የሚሰኙ ስያሜዎች፣ የዝቅተኛ ሥራ መለያ እንዳይሆኑ “ቪኸክል ኦፕሬተር”፣ “የቢሮ አቴንዳንት” ወዘተ እየተባሉ እንዲጠሩ ከማስተማር አልፈው፣ በመመሪያ ጭምር አስገዳጅ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጸሐፊው ራሳቸው እንደሚያውቁት፤እራሳቸው ከማሽከርከር ተገትተው፣ በቪኽክል ኦፕሬተር ሲጠቀሙ ታይተው የማያውቁ የሥራ መሪ ናቸው፡፡ የሀገርህን እወቅ የመሳሰሉ በሺህ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ርዝመት ያለው መንገድ፣ እስከ 3 ቀናት ጭምር፣ ያለ እረፍት ሠራተኞቻቸውን ይዘው ሲጓዙ፣ ወልድያና ሻኪሶ በዓመት ከአራት ጊዜ በላይ እየተመላለሱ፣ የኩባንያዎቻቸውን የምርት ሒደት ሲከታተሉ፣ እንደ ወልድያ ስታድዮም ግንባታ ዓይነት ፐሮጀክቶችን በቅርብ እየተገኙ ሲመሩ፣መኪናቸውን ራሳቸው ከማሽከርከር አልፈው በሌላ ቪኽክል ኦፕሬተር ተጠቅመው እንደማያውቁ፣ ጸሐፊው ጭምር የማይዘነጉትና በብዙ ሰዎች የተደነቀ ተግባራቸው ነው፡፡ እኔና የሥራ ባልደረቦቼ እንደሰማነው በአሜሪካ በቆዩባቸው 20 ዓመታትም ሆነ ቀደም ሲል ለ10 ዓመታት በሰሩበት የአየር መንገድ መስሪያ ቤት በቆዩባቸው ዓመታት ጭምር፣ የራሳቸውን መኪና ራሳቸው እንጂ የሚያሽከረክርላቸው ሹፌር  አልነበራቸውም፡፡ ጸሐፊው ነገር ለማሳመርና ተጠቃሹን የኤልፎራ የስራ ኃላፊ ዝቅ ለማድረግ ካለ ዓላማ ብቻ ተነስተው፣ ትዝብት ላይ የጣላቸውን ትችት አስነብበውናል፡፡ ሌላ ቦታ የሚታየውን እዚህ በማዛመድ፣ “እሳቸውም ባለሹፌር ናቸው” ለማስባል የተደረገ የአፍ ማዳለጥ መሆኑን እገምታለሁ፡፡
ሎሌነት ያሉትም በየትኛውም እይታ፣ ገጽታው የተለያየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለፖሊሲዎችና ስራ አፈጻጸም መመሪያዎች ሎሌ መሆን፣ በንግዱ ዓለም እጅግ ተፈላጊ የሆነ ችሎታ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ውስጥ ሎሌ መሆን የሚጠበቅ ነው፡፡ ጸሐፊው ማለት የፈለጉትን ሎሌነት በሚመለከት ግን የሥራ መሪያችን አጥብቀው የሚያወግዙትና የበታች አለቆችም ሎሌ ሠራተኛ እንዳይፈጥሩ የሚከላከሉት መጥፎ ድርጊት ነው፡፡ ሠራተኛውን ከአለቆች የጌትነትና የበላይነት ስሜት ለመከላከል የሥራ መሪያችን ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ የሠራተኛ ከስራ መባረርን ወይም መቀነስን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የዘረጉት ስልት ነው፡፡ ሠራተኛን ለዚህ የሚያበቃ ሁኔታ ቢፈጠር የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት ከሰጡበት በኋላ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጡትና በደብዳቤውም ላይ የሚፈርሙት እሳቸው ብቻ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ኃላፊነቱን ራሳቸው ይወስዳሉ፡፡ በተመሳሳይም ሠራተኞች የሚያጠራቅሙት የፕሮቪደንት ፈንድ ተቀማጭ ሒሳብ፤ ለጡረታቸውና በፖሊሲ ለተደገፈ ወጪዎች ብቻ እንዲለቀቅ፣ በሠራተኛው ፍላጎት ጭምር ሲጠየቅ፣ ገንዘቡን የመልቀቅ ስልጣን ያላቸው እሳቸው ብቻ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ ይህም የበታች ሥራ ኃላፊዎች፤ ሠራተኞቻቸውን ሎሌ እንዳያደርጓቸው ለመከላከል ማቀዳቸውን ቢያረጋግጥ እንጂ መወቀሻቸው ሊሆን አይችልም፡፡ የሥራ መሪያችን የሚያደርጉት ይህን መሰል ሙሉ ቁጥጥርና በወሳኝነት የደብዳቤዎቹ ፈራሚ መሆን፤ የሠራተኞችን ሙሉ መብት ለመጠበቅ እንጂ የሥራ ኃላፊዎች ብቃት ጉድለት ወይም የእሳቸው ጣልቃ ገብነት ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይገባ፣ ራሳቸው ጸሐፊው ከልባቸው ይቀበሉታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ጸሐፊው ስለመተካካት ባነሷቸው ሐሳቦችም የሚያውቁትንም እንደማያውቁ ሆነው ተችተዋል፡፡ እያንዳንዱ ኩባንያ የራሱ አሰራርና የራሱ ድርጅታዊ መዋቅር ያለው ሲሆን በአብዛኛው የቴክኖሎጂ ግሩፑ ተሞክሮ፣ በተመሳሳይ ደረጃ ከተደረጉ ዝውውሮች በስተቀር የሥራ ኃላፊዎች ምደባ፣ ከታች ወደ ላይ በሚደረግ እድገት የተከናወነ ነው፡፡ ለሥራ አስኪያጆች ምክትል ሥራ አስኪያጆች እየተመደቡም፣ ተከታዩን የኃላፊነት እርከን እንዲለማመዱ ይደረጋል፡፡ የቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር የሥራ ድርሻም ተተኪ እንዳያጣ፣ በኩባንያ ሥራ አስኪያጅነት አመራር ሲሰጡ የቆዩ ሰዎች በፕሪንሲፓል ኦፕሬሽን ኦፊሰርነት ማዕረግ፣ የዋናው ሥራ መሪያችን ምክትሎች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጸሐፊው እንደሚሉት ሳይሆን የቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰራችን ምክትሎችም ሆኑ የኩባንያዎቻችን ሥራ አስኪያጆች፣ በእድሜና በጾታ ስብጥር፣
በአርአያነት የሚታይ ቡድን አባላት ሆነው፣ በዲግሪ የተመረቁና አንዳንዶቹም ሥራ አስኪያጆች ሁለተኛ ማስተርስ ዲግሪዎቻቸውን ጭምር የያዙ ባለሙዋሎች መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህም ለሥራ መሪያችን የመተካካት ፖሊሲ፤ የቀደመ ውጥን ጥርጊያ መንገድን ያመቻቸ፣ የመልካም አመራር ተግባር መሆኑ ለጸሐፊው እንዴት ሊታያቸው እንዳልቻለ የሚገርም ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ቢሆን በተስተካከለው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሲስተም  ውስጥ ጠንካራና ጎበዙ ወደ ላይኛው እርከን እየወጣ፣ የተዘረጋው የጠንካራ አመራር ስልት ይጎለብታል እንጂ በአንድ ሰው አለመኖር የድርጅቶች ሕልፈተ-ሕይወት አይመጣም፡፡ ስለዚህም የሥራ መሪያችን ምክትሎች፣ ከዘመናዊ ትምህርት ዕውቀታቸው ባሻገር ኩባንያ ከመምራት ጀምሮ ኃላፊነታቸውን ለመሸከም የሥራ ልምድ ያደበሩ፣ በጾታና በእድሜ ክልል ስብጥር ተመጣጣኝ የሆነ ቡድን ለመመስረት ያስቻሉ መሪዎች በመሆናቸው፣ “ዋናው የሥራ መሪ ባይኖሩ” ወይም “አሳቸው ሲሄዱ” የሚል አገላለጽ፣ የተሳሳተ እይታ ከመፍጠር ያለፈ እርባና የለውም፡፡
ግልጽነትንና ተደራሽነትን በሚመለከትም ጸሐፊው ከእውነታው የራቀ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ በእርግጥ የሥራ መሪያችን የሚከተሉት የአመራር ስልት፣ እንደ ባለሙያነታቸው ለየት ያለ የራሱ የሆነ መንገድ እንዳለው ይስተዋላል፡፡ “ወደ መሠረቱ እየወረዱ የማይሰሩ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከላይ ቢሮአቸው ተቀምጠው በማዘዝ ብቻ መምራት ከፈለጉ፣ የድርጅታዊ ቁመናው ፒራሚድ፣ ጫፉን መሸከም ተስኖት ይወድቃል” በሚል ብሂል፣ ተሞከሮአቸውን ለሁሉም እያሳዩ ነው። ይህ የአመራር ስልታቸው፤ ከየትኛውም ሠራተኛ ቀድሞ የሥራ ቦታ በመገኘት፣ ለዘመናዊ አስተዳደር፣ በአርአያነቱ የሚጠቀስና የሥራ መሪን በሁሉም ሥፍራ፣ ለሁሉም ሠራተኛ ተደራሽ የሚያደርግ፣ ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ክህሎትን የሚያመላክት  እንጂ “ሌሎች ስለሚያቅታቸው እኔ ታች ወርጄ ልሥራ” የሚል ተሞክሮ አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን ኖሮ፣ ጸሐፊው ራሳቸው እንደሚያውቁት፤ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ የገበያ ንግድ  የሚያንቀሳቅሱና ከ7 ሺህ በላይ የሆኑ ሠራተኞች ያሏቸውን 26 ኩባንያዎች፣ በአንድ ሰው መምራት እንዴት ይቻላል? ጸሐፊው ራሳቸውም ሆኑ ማንኛውም ሠራተኛ፣ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰራችንን ማግኘት ቢፈልግ፣ የትኛውም ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ዘንድ ባልተለመደ የ”Open Door” ፖሊሲያቸው ተግባራዊነት፣ ያለምንም ቀጠሮ፣ ወደ መቻሬ ግቢ ጎራ ብሎ ማግኘትና ማነጋገር እንደሚችል፣ የትኛውም ሠራተኛ፣ የሥራ ኃላፊና የሠራተኛ ማህበራት መሪዎች  በሚገባ የሚመሰክሩት ነው፡፡ በየትኛውም የሥራ ኃላፊ ዘንድ ባልተለመደ ሁኔታ በየማለዳው ሳይታክቱ ለሠራተኞቻቸው በቀጥታ ተደራሽ ሆነው፣ ችግሮቻቸውን የሚያደምጡበትና መፍትሔም የሚሰጡበት አካሄድና የዓመታት ተሞክሮ፣ የአመራር ስልት፣ በአርአያነት ሊወሰድ የሚገባው እንጂ የሥራ አስኪያጆች ቡራኬ መቀበያ መድረክ አድርጎ መዝለፍ ተገቢ አይመስለንም፡፡
ኩባንያዎች ሊያተርፉ፣ ሊከስሩ ወይም የውድቀትም ሆነ የእድገት አመላካች አኃዝ ሳያስመዘግቡ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ጸሐፊው እንደሚያውቁት፤ በቴክኖሎጂ ግሩፑ የ19 ዓመታት ልምድ  እንደታየውና ጸሐፊውም በሚገባ እንደሚያውቁት፣ በየዓመቱ ኩባንያዎችም ሆኑ የሥራ አመራሮች ያሳለፉትን የሥራ አፈጻጸም ውጤት በመመልከትና ገጠመኞቹን ከእነምክንያታቸው በማጤን፣ ውይይት የሚደረግባቸው ዓመታዊ ስብሰባዎች ይካሔዳሉ፡፡ የዚህም ዓላማ የተዳከመው ብርታት አግኝቶ፣ የጠነከረው ለበለጠ ስኬት አልሞ፣ የኩባንያዎቻችን ድርጅታዊ ሕልውና እንዲቀጥል ጥረት ለማድረግ ነው፡፡ የሁሉም ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎችና የሠራተኛ ማሕበራት መሪዎች በሚገኙበት ያለማቋረጥ በየዓመቱ የሚደረገው ይህ ስብሰባ፤ የዘመናዊ አመራር አኩሪ ጉዞ መሆኑን ራሳቸው ጸሐፊው ጭምር፣ በስብሰባዎቹ ተሳታፊ የነበሩ በመሆናቸው፣ በሌሎች ዘንድ በአርአያነቱ የሚወደስ ነው፡፡ እነዚህ መሰል ስብሰባዎችም ሆኑ ሌሎች የውይይት መድረኮች አጀንዳ ተቀርጾላቸው ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው ሠራተኞች ብቻ እንዲገኙ ተጋብዘው ይከናወናሉ፣ ተከታይ ስልቶች ይነደፋሉ፤ ድርጅታዊ መዋቅሮችም ይሻሻላሉ። በዚህ ወቅትም ሆነ በማንኛውም የሥራ ግንኙነቶች፤ ማንኛውም ተሳታፊ አማራጭንና የተሻለ የአሰራር ሒደት ሐሳቦችን ይዞ ከመምጣት ይልቅ ላለፉት ድክመቶች ወይም ለተሰሩት ስህተቶች ምክንያቶችን የመደርደር አቀራረብ ይዞ ቢመጣ፣ የሥራ መሪያችን በጥሞና የማዳመጥ ትዕግስት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ “I manage Options Not Excuses” እያሉ ያለማቋረጥ የሚያስተምሩትም ለዚሁ ነው፡፡ አማራጮችንና መፍትሔዎችን ከማቅረብ ይልቅ ለተፈጸሙ ስህተቶች ምክንያትን በመደርደር የሚጀምሩ ሥራ አስኪያጆችን፤ “ወደ አያት ለመሔድ ወይም ለመምጣት አማራጭ መንገድ ፈልግ እንጂ ለሥራ መዘግየት የመንገድ መጨናነቅን በምክንያት አታስረዳኝ” በማለት የሥራ መሪያችን ተከታዮቻቸውን ቢገስጹ ጠቀሙ እንጂ አልጎዷቸውም፡፡ በአመራር ተሞክሮአቸውም ሆነ በትምህርት አሰጣጣቸው ምንጊዜም “Think Different!”  የሚሉት የሥራ መሪያችን፤ የተለየና ገንቢ ሓሳብ ይዘን ብንቀርባቸው የሚገፋተሩ መሪ አይደሉም፡፡
በመጨረሻም፤ ጸሐፊው ከጠቀሷቸው እውነታዎች ውስጥ አንደኛው፣ በባለሀብቱ እምነትና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት እቅድ ኩባንያዎቻችን በአፈጣጠራቸው ትርፍ ለማጋበስ ተብለው የተፈጠሩ አለመሆናቸው ነው። ኩባንያዎቹ የመከስር ሂደት ሲገጥማቸውም ቢሆን አንድም ሰራተኛ ሳይባረር፣ የሥራ አጡ ቁጥር እንዳይበዛ በሚደረገው ብሄራዊ ጥረት ውስጥ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ የመቆየቱ ምስጢር፣ ይኸው የአፈጣጠር ታሪክና የባለሀብቱ ልዩ ችሮታ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ስለ ኩባንያዎች የባንክ ብድር ጸሐፊው ያነሷቸው ጉዳዮች አልፎ አልፎ ከሚታዩና ተመላሽ ከተደረጉ ውስን ብድሮች የዘለለ በእዳነት የሚጠቀስ ታሪከ ያላቸው ኩባንያዎች በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ውስጥ ስለሌሉ፣ መረጃው አሳሳች ነውና መታረም ይገባዋል፡፡ በእርግጥም በአሁኑ ወቅት ኤልፎራን ጨምሮ አንዳንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ የስራና ምርታማነት ተግዳሮት ክፉኛ ሲፈታተናቸውና በሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር ወጪ በየወሩ እየወጣ፣ የሠራተኞች የሥራ ዋስትና እንደቀጠለ መሆኑ ሌላው ሊጤን የሚገባው ጉዳይ ቢሆንም የአመራሩን ቆራጥነትነትና መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ መሆንን የሚያሳይ ነው፡፡ ቸር ይግጠመን!!
ከአዘጋጁ፡- ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከላይ በቀረቡት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ፣ የሁለት ጸሃፊዎችን ለየቅል የሆኑ  አስተያየቶች ማቅረባችን የሚታወስ ሲሆን፣ሁልጊዜም አስተያየቶች በግለሰቦች (ግለሰባዊ) ጉዳይ ላይ ሳይሆን በሃሳብ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህም  መሰረት፤ ይሄ ጽሁፍ መጠነኛ አርትኦት ተደርጎበት የቀረበ መሆኑን ልንገልጽ  እንወዳለን፡፡      

Read 1363 times