Saturday, 15 December 2018 15:20

ሰሜን ቅርንጫፍ

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(6 votes)


     ስለዚህ የባንክ ቤት ሹም ለመናገር ብዙ አይከብደንም፡፡ ምክንያቱም አሳምረን ስለምናውቀው ነው፡፡ ይህ የባንክ ቤት ሹም፤ ቀኑን በሙሉ የራሱ ያልሆነ ብር ሲቆጥር ይውላል፡፡ ደሞዙ ግን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ፣ ኑሮውን ለመግፋት እንኳን የማይበቃው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ሶስት ጓደኞች አሉት፡፡ አንደኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን ስጋ ይበላል፣ ጫት ይቅማል፣ መጠጥ አይጠጣም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የክርስትና እምነት ተከታይ ሲሆን መጠጥ ይጠጣል፣ ስጋ ይበላል፣ ጫት አይቅምም፡፡ ሦስተኛው፤ የቡድሂዝም እምነት ተከታይ ሲሆን መጠጥ ይጠጣል፣ ጫት ይቅማል፣ ስጋ አይበላም፡፡ እሱ ግን በአንድ ፈጣሪ ብቻ የሚያምን፤ የምንም እምነት ተከታይ ያልሆነ---ሁሉንም ያደርጋል።
የዘወትር ጋባዦቹ እነሱ ሲሆኑ ላለበት የገንዘብ ችግር መፍትሔ ሲሰጡት በየራሳቸው እምነት አንፃር ነበር፡፡ ሙስሊሙ “መጠጥ ትተህ፣ ሶላት ብትሰግድ አላህ ይሰጥህ ነበር” ይለዋል፡፡ ክርስትያኑ ደግሞ “ጫቱን ትተህ፣ ብትፆም ብትፀልይ እግዚአብሔር ይሰጥሃል” ብሎታል፡፡ ቡድሂስቱ ደግሞ “ቤትህ ገብተህ አንድ ሻማ አብርተህ በተመስጦ ብትመሰጥ፣ እግዚአብሔር ያናግርሃል” አለው፡፡ ለሱ ይሄ የተሻለ ሃሳብ ሆኖ ታየው።
ቤቱ ገብቶ አንድ ሻማ አበራና፣በቡድሃ አቀማመጥ ተቀመጠ፡፡ ለብዙ ደቂቃዎች የሻማውን ብርሃን አተኩሮ ሲመለከት ቆየ፡፡ የሻማው ሰማያዊ ቢጫና ቀይ እሳት፣ ወደ አስራ ሶስት ቀለማት ተቀየረ፡፡ ወዲያው የአንድ ውብ የሆነ ህፃን ልጅ ምስል ቤቱን ዞረው፡፡ የባንክ ቤቱ የሂሳብ ሹም ደንብሮ ተነሳና፤ “ማነህ?” ሲል ጠየቀ፡፡
“እኔ ፈጣሪ ነኝ”
“እንዴት አንተ ህፃን የሰማይና የምድር ፈጣሪ ትሆናለህ?”
“እናንተ ሰዎች እስከ መቼም አይገባችሁ፤እኔን ማንም ማየት አይችልም፤ቅዱስና ንፁህ በሆነ ነገር ላይ እገለፃለሁ እንጂ”  
የባንክ ቤቱ የሂሳብ ሹም ሲርበተበት ቆየና፤ “እንካያስ ፈጣሪ ከሆንክ ለምን ደሃ አደረከኝ?”
“ሳትበላ አድረህ ታውቃለህ?”
“ገንዘብ አይበቃኝም”
“ምን ያህል ትፈልጋለህ?”
“በቀን ሃምሳ ሺህ ብር”
“ምን ያደርግልሃል?”
“እፈልጋለሁ”
“ይሰጥሃል ግን--”
“ምንድነው ከሰጠኸኝ በኋላ-- ግን ማለት?”
“በኔ ህግ መሰረት ነው፡፡ ራስህ ህጉን ሁሌ እንደምታፈርስ ባውቅም፣ ሌላ ሰው ግን በሰጠሁህ ገንዘብ ህጉን እንዲያፈርስ ማድረግ አትችልም፡፡ ስለዚህ መጠጥ አትጋብዝም፣ ጫት አታስቅምም፤ ለዝሙት አትተባበርም፡፡ ለራስህ ግን እንደፈለግህ ማድረግ ትችላለህ፡፡ ገንዘቡ የተሰጠህ ለቀን ወጭህ ስለሆነ፣ አንድም ሳንቲም ሳታሳድር ጨርሰህ ማደር አለብህ። ገንዘቡ የሚሰጥህ ለቀን ወጪህ ብቻ ስለሆነ ንብረት ማፍራት አትችልም፡፡ ሳትጨርስ ያሳደርከው ገንዘብ እዳ ይሆናል፤ሃምሳ ሺህ ብር ሲሞላ የእኔና የአንተ ውል ይቋረጣል” አለውና፤የህፃኑ ምስል ከቤቱ ጠፋ፡፡
የባንክ ቤቱ የሂሳብ ሹም እንቅልፉን ሳይጠግብ አድሮ ጠዋት ነቃ፡፡ እንደተለመደው ቁርስ ለማድረግ መስሪያ ቤቱ አጠገብ ወዳለው ቁርስ ቤት ጐራ ማለት ነበረበት። ፉል ዘመናዊ ከሻይ ጋር- ሙበሺት አቅርቦለት፣ አንድ ሁለት እንደ ጐረሰ፣ አንድ ገብስማ ፀጉር ያላቸው አዛውንት ወደሱ ተጠጉና፤ “አንተ የወዳጄ የአቶ እገሌ ልጅ አይደለህም?!” ሲሉት በመገረም አፍጦ አያቸው፡፡ “እገሌ” የሚለውን ቃል መጠቀም የፈለግነው፣ ሚስጥር ለመጠበቅ እንደሆነ ልንገልጽ እንፈልጋለን፡፡
“አዎን በርግጥ” አለ፤የባንክ ቤቱ የሂሳብ ሹም፡፡
“አባትህ መልካም ወዳጄ ነበር፡፡ ድሮ ከመሞቱ በፊት ሃምሳ ሺህ ብር አበድሮኝ ነበር፡፡ ያንን ዕዳ ለመክፈል ሳልችል ህይወቱ አለፈች፡፡ እንኳን አገኘሁህ። ወራሹ አንተ ስለሆንክ እንካ ተቀበለኝ፡፡” አሉና ቼክ አውጥተው፣ አሃዝና ቁጥር ከፃፉበት በኋላ፣ፈርመው ሰጡት፡፡
ቼኩን አፍጥጦ ሲመለከት ቆየና፣ ቀና ሲል ሰውየው የሉም፡፡
ወዲያው ወደ ባንክ ገብቶ፣ በጥሬ ገንዘብ ብሩን ተቀበለ፡፡ በህጉ መሰረት ብሩ ማለቅ አለበት፡፡ ዛሬውኑ። መጀመሪያ ያቀናው ወደ ሂልተን ሆቴል ነበር፡፡ ፀጉሩን ተከርክሞ፣ ፂሙን ከተላጨ በኋላ ሁለት ደብል ኮርቫይዘር ኮኛክ በስፕሬስ ቡና የተፈላ ጠጣ፡፡ እስከ ረፋድ ድረስ ዋና ሲዋኝ አረፈደና፣ ትንሽ ጀርባውን ለማፍታታት ማሳጅ አደረገ፡፡ ለምሳ የተገኘው ኢምግሬሽን ጐን ካለው የጣልያን ምግብ ቤት ነበር፡፡
አንድ ግማሽ ዶሮ አሮስቶ ከሩዝና ከተፈጨ ድንች በልቶ፣ አራት ዋንጫ፣ የፈረንሳይ ወይን ጠጅ ጠጣ፡፡ ሞቅ ሲለው ሞቅታውን ለማጥፋት፣ ወደ ሳዲቅ ጫት ቤት መሄድ ነበረበት፡፡ የሁለት ሺህ ብር ሚስማር ጫት ይዞ፣ ወደ አልበረካ ጫት መቃምያ አመራ፡፡ ሶስቱን ጓደኞቹን መጥራት ግን አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ህጉ ስለማይፈቅድ፡፡ ማታ እግረ መንገዱን ለማያጨሱ፣ ለማይጠጡና ለማይቅሙ አምስት የኔ ብጤዎች፣ ለማይሳደቡም ጭምር አንድ አንድ ሺህ ብር ሰጠ፡፡
ጭንቅላቱ ዞሮ ስለዋለ ማታ መጠጣት አልቻለም። ወደ ሆቴል አምርቶ ክፍል ለመያዝና ለመተኛት ቢያስብም ወቅቱ የስብሰባ ስለነበረ፣ያልተያዘ ክፍል ማግኘት አልቻለም፡፡ እቤቱ ሲገባ፣ ኪሱ ውስጥ ያለውን ብር ቆጠረ፡፡ ሃያ ሺህ ብር አድሯል፡፡ በሚቀጥለው ቀን አርፍዶ ስራ ገባ፡፡ አንድ ቡና ጠጥቶ፣ ጥቂት ስራዎችን ካነካካ በኋላ አንዲት በደንብ የለበሰች ሴት መጣችና ፊት ለፊቱ ቆመች፡፡ በደንብ አስተውሎ ሲመለከታት፣ ከስድስት ወራት በፊት አክሲዮን ልትገዛ ፈልጋ፣ ያገናኛት ሴት እንደሆነች አስታወሰ፡፡
“ኮሚሽኑን አልወሰድክም፤ቢደወልልህ ስልክ አታነሳም ነበር፤ እንካ” አለችና፤ የተፈረመበት ቼክ ሰጠችው፡፡ ቼኩን አፍጥጦ ሲመለከት፤ ሃምሳ ሺህ ብር። ቀና ብሎ ሲያይ፣ ቢሮው ውስጥ የለችም፡፡
በጭንቀት ተዋጠ፡፡ እሺ አሁን እንዴት ነው፣ ይህን ብር ጨርሼ የማድረው፡፡ ምን አይነት መከራ ነው ሲል ብቻውን አልጐመጐመ፡፡ ቼኩን በጥላቻ አፍጥጦ ሲመለከት ቆየና እያቃሰተ ተነሳ፡፡
ያለው ብቸኛ እድል ወደ ሂልተን መሄድ ነው። ቁርስ አደረገ፡፡ አርባ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ብር ቀረው። ወደ ሸራተን አመራ፡፡ አራት ጊዮርጊስ ቢራ ተጐነጨ። የምሳ ሰአት እስኪደርስ ዞር ዞር እያለ፣ የኔ ቢጤ ፍለጋ ጀመረ፡፡ ወቅቱ የስብሰባ ጊዜ ስለነበር፣ መንግስት የኔ ቢጤዎቹን ሁሉ ጠራርጐ የት እንዳስገባቸው አይታወቅም፡፡ አንድ ሁለት ቦርኮዎች አግኝቶ ነበር፡፡ እነሱም የጫት ገራባና ሲጋራ የያዙ ነበሩ፡፡ በመጨረሻ አንዲት መበለት አጋጣሙት፡፡ በደስታ ፈንድቆ፣ አስር ሺህ ብር ሰጣቸው፡፡ ሴትየዋ ያዩትን ማመን አልቻሉም፡፡
ምሳውን ሸራተን በላ፡፡ በዞረ ድምር ጭንቅላቱ ስለዞረ፣ መጠጡን ሲቀምሰው ወደ ላይ አለው፡፡ ሰላሳ አምስት ሺህ ብር ኪሱ ውስጥ አለ፡፡ እራቱን ጊዮን ሆቴል በልቶ፣ ዝም ብሎ ቆዝሞ አመሸ፡፡ ያለው እድል፣ ይህን ቀሪ ብር ለአንድ የኔ ብጤ ሰጥቶ፣ ኮንትራቱ እንዲቋረጥ ማድረግ ነው፡፡ ለማን መስጠት እንዳለበት ሲያስብ፣ ብርሃኑ የተባለው የሰፈሩ እብድ ትዝ አለው፡፡ ይህ እብድ በቁምጣ ብቻ ከወገቡ በላይ እራቁቱን ሆኖ ዝም ብሎ መንገድ ለመንገድ የሚዞር ነው፡፡ ምንም ሱስ የለበትም፡፡ ሱሱ መንጐራደድ ብቻ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ሁሌ ምግብ ለምትሰጠው ኮረዳ ሰርግ ላይ፣ ሸሚዝም ከረባትም ሳይለብስ፣ አዲስ ኮት ደርቦ ተገኝቷል፡፡ ኪሱን ፈተሸ፡፡ ሰላሳ አንድ ሺህ ብር አለ። በርገሩን ከበርገር ቤት ገዛና፣ የኮንትራት ታክሲ ይዞ፣ ወደ ሰፈሩ አመራ፡፡ ብርሃኑ የተለመደው ቦታው ላይ እንዲገኝ ይፀልያል፡፡ በጉዞው ላይ ድንገት ስልኩ ጠራ፡፡
“የባንክ ቁጥር 2030 ባለቤት እርስዎ ነዎት?”
“አዎ!”
“በሂሳብዎ የገባ ሃምሳ ሺህ ብር ፤ነገ ጠዋት ይምጡና ይውሰዱ”
“ከየት ነው?”
ስልኩ ተዘግቷል፡፡ እንደ ደረሰ ለታክሲ ነጂው ሶስት መቶ ብር ሲሰጥ፣ የቀረው ሰላሳ ሺህ በር ነበር፡፡ በርገሩን እየገመጠ ብሩን ይዞ፣ ወደ ብርሃኑ ማደሪያ፣ የፕላስቲክ ዛኒጋባ አመራ፡፡ ብርሃኑ በጀርባው ተኝቶ ሰማዩን ይመለከታል፡፡ በደስታ ፈንጥዞ ሰላሳ ሺህ ብሩን “እንካ” አለና እጁን ዘረጋ፡፡ ብርሃኑም እጁን ዘረጋ፡፡ የወሰደው ግን ብሩን ሳይሆን በርገሩን ነበር፡፡ ወዲያው ፊቱን አዙሮ በርገሩን መግመጥ ጀመረ፡፡ ያለው እድል ወደ ቤት መግባት ነው፡፡ እንደገባ ኮሞዲናው ላይ ትላንት ያሳደረው ሃያ ሺህ ብር ተቀምጧል፡፡ ሰላሳ ሺውን እላዩ ላይ ደረበበት፡፡ ተጠቅልሎ ተኛ፡፡ ጠዋት አርፍዶ ነበር ስራ የገባው፡፡ 2030 የሂሳብ ቁጥሩን ከፍቶ ተመለከተ። ሃምሳ ብር ብቻ ነው ያለው፡፡ ትላንት የተደወለውን ስልክ መታ፤ “አቤት”
 “በ2030 የሂሳብ ቁጥሬ ውስጥ ሃምሳ ሺህ ብሩ የለም!”
“በደንብ ይመልከቱት”
“አየሁት እኮ”
“ምን ቅርንጫፍ ነው የርሶ?”
“ምስራቅ”
“አይ ይቅርታ፤ የሰሜን ቅርንጫፍ ነው የተባለው፤ ይቅርታ”
“ኧ - ግን-”
ስልኩ ተዘግቷል፡፡
አገጩን በእጁ አስደግፎ፣ በሃምሳ ሺህ ብር ምን አይነት ስራ መስራት እንዳለበት ማሰብ ጀመረ፡፡

Read 2702 times