Saturday, 15 December 2018 15:38

ሾተልን ወደ አፎት፤ ቁጣን ወደ ትዕግስት

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

 አንድ ሰው በአልጀዚራ ቀርቦ ሲናገር ሰማሁት፤ እንዲህ ሲል፤ ‹‹በቻይና ፓርቲን መለወጥ አይቻልም። ፖሊሲን መለወጥ ግን ይቻላል፡፡ በአሜሪካ ደግሞ ፓርቲን መለወጥ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ፖሊሲን መለወጥ አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል፤ በቻይና ፖለቲካው በኢኮኖሚው ላይ ሥልጣን አለው፡፡ በአሜሪካ ደግሞ ኢኮኖሚው በፖለቲካው ላይ ሥልጣን አለው፡፡ በቻይና ፖሊት ቢሮው (ፖለቲካው) ካፒታልን ያዘዋል። በአሜሪካ ደግሞ ካፒታል ፖለቲካውን ይዘውረዋል፡፡ ለዚህ ነው፤ ስርዓቱ ካፒታሊዝም መሰኘቱ፡፡››
የኢትዮጵያ ነገር የተለየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፓርቲንም ሆነ ፖሊሲን ማፍረስ እንጂ መቀየር አይቻልም። አሁን ፍፁም ግራ አጋቢ ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡ እንደ ቻይና ፖለቲካው ኢኮኖሚውን አያዘውም፡፡ እንደ አሜሪካም ኢኮኖሚው ፖለቲካውን አይዘውረውም፡፡ ስለዚህ የምንከተለው ስርዓት ካፒታሊዝም አይደለም። አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መሆኑምን መመስከር አይቻልም፡፡ በዚህ የለውጥ ማዕበል ውስጥ ሆነን ለማለት የምንችለው፤ ገና የጠራ ነገር የለም ብቻ ነው፡፡
‹‹ሰዎች ከጠላቶቻቸው አንደበት የሚሰሙትን እውነት መቀበል አይችሉም፡፡ አሳዛኙ ነገር፤ ብዙውን ጊዜ ከወዳጆቻቸው አንደበት እውነት አያገኙም›› ይባላል፡፡ለኢትዮጵያ ወዳጅ ወይም ጠላት ሊባል የማይችል፤ ሬኔ ለፎርት የተባለ የሐገረ ፈረንሳይ ሰው፤ በተለያየ ጊዜ ስለ ወቅታዊ የሐገራችን ሁኔታ ግምገማ ያቀርባል፡፡ የእኛን ምሁራን በሚያሳፍር ደረጃ ትንተና እያቀረበ አቅጣጫ ያመለክታል፡፡
ይህ ፀሐፊ፤ የዶ/ር ዐቢይንበኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ መምጣት በአዎንታ ያየዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ከሲዖል በር እንድትርቅ አድርጓታል›› ብሎ ያስባል። ነገር ግን ዶ/ር ዐቢይ አንዳንድ ስህተቶችን መፈጸማቸውን ያምናል፡፡ እናም ስለሐገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲህ ይላል፤
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ለብዙ ዘመናት በኢትዮጵያ የሚታወቀውን ሁሉንም ነባር የመንግስት አሰራር ዘይቤዎችንበአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ ነቃቅለው በመጣል በታሪክ ጎዳና ጉዟቸውን ጀምረዋል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ  የወሰዷቸው ሊበራላዊ ለውጦች እና ቀዳሚ እርምጃዎች፤ የብዙሃኑን የኢትዮጵያ ህዝብ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ በዚህም እያደር በሚጨምር ጉልበት ሐገሪቱን ወደ አዘቅት እየገፋ ቁልቁል ሲያወርዳት የነበረው ኃይል እንዲገታ ማድረግ ችለዋል የሚለው ለፎርት፤ ዶ/ር ዐቢይ ሦስት ትላልቅ ስትራተጂያዊ ስህተቶችን ፈፅመዋል ይላል፡፡
የመጀመሪያው ስህተታቸው፤ ዶ/ር ዐቢይ በካሪዝማቸው፤ በጠንካራ ዝናቸው እና እንደ ‹‹ቲምለማ›› ባሉ ጥቂት የቁርጥ ቀን ታማኞቻቸው በመደገፍ አጀንዳዬን ከግብ ለማድረስ እችላለሁ ብለው ማመናቸው (ወይም እንደዚህ እያሰቡ የሚንቀሳቀሱ መምሰላቸው) ነው፡፡ በአጭሩ፤ ዶ/ር ዐቢይ አመራራቸውን ከተቋማዊ አሰራር እንዲወጣ አደርገው (de-institutionalize) መምራት እንደሚችሉ የሚያስቡ ይመስለኛል ይላል፡፡ከተቋማዊ አሰራር የተነጠለ (de-institutionalize) አመራር መፍጠር እንዲችሉ ያስባሉ የሚላቸው ዶ/ር ዐቢይ፤ የመንግስት ስርዓቱን ፕሬዚዳንታዊ ለማድረግ እንደሚያስቡበሰፊው ይነገር እንደነበርና፤ ይህምሐሳባቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከተለመደው ‹‹የትልቅ ሰው››የአመራርዘይቤ ጋር የሚገጣጠም፤ ያንንምካባ ለመደረብ የሚያስችል ዘመናዊ ስልት ነው ይላል፡፡ በሌላ አገላለፅ፤ ዶ/ር ዐቢይ ከፍተኛውን የሥልጣን ኃይል የሚዘውር አነስተኛመዋቅርን በመጠቀም፤ ሥራቸውን እንዳሻቸው ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ይችሉ ዘንድ፤ኢህአዴግን እና የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን (በተለይም ካቢኔውን፤ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶችንና ፓርላማውን)አልፈውለመሄድ ያስባሉ፡፡
ሁለተኛው ስትራቴጅክ ስህተት፤ ዶ/ር ዐቢይ በማከታተል የወሰዷቸው የለውጥ እርምጃዎች በበርካታ ዜጎች ዘንድ በአወንታዊ ስሜት የታዩና  የልባቸውን መሻት የሞሉ እርምጃዎችቢሆኑም፤ እርምጃዎቹን ሲወስዱ ያለ በቂ ዝግጅትና ለውጡ ሊያስከትል የሚችለውን አወንታዊ ወይም አሉታዊተጽዕኖ በወጉ በማሰብ ባለመሆኑ፤የተወሰዱት እርምጃዎች በመጨረሻ ሊያመጡ የሚችሉትን ውጤት ለመቆጣጠር የሚያስችል ብቃትየሌላቸው መሆኑ ነው።
ዶ/ር ዐቢይ ትንፋሽ በሚያሳጥር ጥድፊያ ከወሰዷቸው እርምጃዎች ውስጥ ጎላ ያሉትና ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግሩ ውሳኔዎች የሚሆኑት፤ እንደ ኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር -ኦነግ እና እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ግንቦት 7 ያሉ ነፍጥ አንስተው ሲታገሉ የቆዩ እና ህገ ወጥ በሚል የተፈርጀው የቆዩ ተቃዋሚ ኃይሎችን መጋበዛቸው እና ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የተወሰደው እርምጃ ነው፡፡ እነዚህ በጥንቃቄ በተዛጀ የሁነት ዝግጅት ለህዝብ ይፋ የተደረጉት እርምጃዎች፤ ከተጨባጭ ፋይዳቸውይልቅ ተምሣሌትነታቸው ይበልጥ ጉልህ ነው፡፡ የእነዚህ እርምጃዎች ቀዳሚ ግብ የዶ/ር ዐቢይ ተቀናቃኞች ሁሉ ነገሩያበቃለት መሆኑን አምነው ለውጡን እንዲቀበሉ የማድረግ ግብ ነው፡፡
ሦስተኛ፤ ዶ/ር ዐቢይን ወደ ሥልጣን ያመጣቸው፤ በህወሓት ላይ የተፈጠረው የተቃውሞ ማዕበልና ድርጅታቸው ከብአዴን ጋር የመሠረተው ታክቲካዊ ህብረት ነው፡፡ ይህም ህብረት መደላድል ያገኘው፤ በህዝቡ ዘንድ ያለው እውነተኛ የፌዴራሊዝም አስተዳደርን የመተግበር  ፍላጎትና የትግራይ ልሂቃን የበላይነት እንዲያበቃ ከመሻት ነው፡፡ መፈክሩም ‹‹ወያኔ ይውደም›› የሚል ነበር፡፡
ይህ የህዝብ የተቃውሞ ስሜት ሊያስገኝ የሚችለውን የፖለቲካ ፋይዳ ይበልጥ ለማጠንከርና ለማጎልበት፤ ዶ/ር ዐቢይ የተቃውሞ ስሜቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረጉን ቀጥለውበታል፡፡ ይህን ዓላማ ለማሳካትም፤ የፌዴራሉ ስርዓት (ስለዚህም የህወሓት) ደመኛ ጠላቶች የሚጠቀሙበትን ፖለቲካዊና ታሪካዊ ሬቶሪክ እስከማሽሞንሞን ተጉዘዋል፡፡ ከግንቦት 7 ጀምሮ የደርግ መውደቅ እስከሚያብከነክናቸው ወገኖች ድረስ በሐቲት ዝምድና ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል በሚል የሚከሰው ረኔ ለፎርት፤ እነዚህም ወገኖች፤ ታላቋ፣ ዘላለማዊቷና በአንድነቷ ጸንታ የኖረችው ኢትዮጵያ እንድትንበረከክ ያደረጋት የሁሉም ክፉ ነገሮች ምንጭየፌዴራል ስርዓቱ ነው ብለው የሚያምኑ ኃይሎች መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡
‹‹የአራት የብሔር ድርጅቶች ጥምረት ውጤት የሆነው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ተደርጎ ሚታይ አይደለም፡፡ መንግስትና ሐገረመንግስት ለዘመናት ተቆላልፈው በኖሩባት በኢትዮጵያ፤ ነባሩ የፖለቲካ ባህል አሁን ድረስ መዝለቅ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ ተጠናክሮ ይታያል፡፡ በሕግም ባይሆን በነባር ወግ ድጋፍ፤ ፓርቲው የሐገረ- መንግስቱን፤ ከዚያም ባሻገር ህዝቡንና ህዝብ - ቀመስ (parapublic) የኢኮኖሚ ዘርፉን እንዳሻው ለማድረግ የሚችል ኃይል ያለው ነው›› ይላል፡፡
አንድ የመንግስት ሠራተኛ፤ ‹‹እንደ አንድ የመንግስት ሠራተኛ የተጣለብህ ኃላፊነት ምንድነው?›› በሚል ለሚቀርብለት ጥያቄ እውነተኛ ምላሽ ለመስጠት ድፍረት ካገኘ፤ ሊሰጠን የሚችለው መልስ ‹‹የፓርቲውን ትዕዛዝ ማስፈጸም›› ከሚል የተለየ ሊሆን አይችልም የሚለው ፀሐፊው፤ መንግስታዊማሽኑ የራሱ የሆነዲናሞ አለው ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር እንደማይቻል ጠቅሷል። በዚህ ሁኔታ ለመንግስት መዋቅሩ መንቀሳቀሻ ኃይል እና አቅጣጫ ሊሰጠው የሚችለው፤ የተረጋገጠ እና የተጨበጠ ራዕይ ያለው ጠንካራው የኢህአዴግ  አመራር ብቻ ነው የሚለው ለፎርት፤ ህወሐት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የፖለቲካ ስልጣን ይዞ መቆየት በመቻሉ፤ የፓርቲው ብቻ ሳይሆንየመንግስቱም የጀርባ አጥንት ሆኖ ለመውጣት የሚያስችል ከበቂ በላይ የሆነ ጊዜ አግኝቷል ብሏል፡፡
የመንግስት መዋቅሩን ወቅታዊ ቁመና ሲገልጽ፤ በገጠር የወረዳ መስተዳድር የሚሰራ አንድ የመንግስት ሠራተኛ፤ ‹‹በወሩ መጨረሻ ደመወዛችን እንዳይቀርብን በማሰብ ብቻ፤ በጧት ወደ ቢሮ ገብተን፤ ምንም ሥራ ሳንሰራ እንቆይና አመሻሹ ላይ ከመሥሪያ ቤት እንወጣለን …… ከበላይ አመራሩ ምንም ዓይነት የሥራ መመሪያ አንቀበልም፤ እኛም ምንም ዓይነት መመሪያ ለበታች አመራሩ አንልክም፡፡ ማንም ሰው ምንም ዓይነት ውሳኔ አይወስድም፡፡ አብዛኛዎቻችን ለተመደብንበት ሥራ ብቃት የሌለን እና በፓርቲ ምደባ ቦታውን የያዝን ሰዎች በመሆናችን፤ በማናቸውም ጊዜ ከሥራ ልንሰናበት እና ከኃላፊነት ልንሻር እንደምንችል እናውቃለን›› ሲል መናገሩን ለፎርት ጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም፤ የአካባቢ መስተዳድሮች ከውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭም በኩል ፈርሰው ይታያሉ። ቀደም ሲል በፈፀሙት ያልተቋረጠ ግፍ የተነሳ፤ የታችኛው የመንግስት መዋቅር ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ የተቃውሞ ማዕበል እያስተናገደ መሆኑንና፤ ህዝቡም ህጋዊ ሥልጣን ያላቸው አካላት አድርጎ እንደማይመለከታቸው ገልጧል፡፡ አንድ ቁልፍ የመንግስት ባለሥልጣንም ‹‹በአሁኑ ሰዓት መንግስት ፈርሷል፡፡ የላይኛው መዋቅርከታችኛው መዋቅር የሚያገናኘው የዕዝ ሰንሰለት በቦታው የለም፡፡ መከባበር ወይም ፍርሃት የለም፡፡ የተፈጠረው የሥልጣን ገዋ (ቫክዩም) ማህለቅት የለሽ ነው›› እንዳሉት ጠቅሷል፡፡
የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባዔም ‹‹አሁን በሐገሪቱ እየተመለከትን ያለነው ሥርዐተ አልበኝነት ነው›› ማለቱን ያስታወሰው ለፎርት፤ ከዚህ አንጻር ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሄደው የነበሩትን ወታደሮች ድርጊት አንስቷል፡፡ በአብዛኛው የሐገሪቱ አካባቢ በአንጻራዊ ሚዛን ሰላማዊ የዕለት ተዕለት ህይወት እንደ ቀጠለ መሆኑንም ጠቅሶ፤ ‹‹የበታች መዋቅሩ ሥልጣን በየአካባቢው ሰው እጅ የገባ ይመስላል›› ብሏል። እንደ ዝርፊያና ስርቆት ያሉ ተራ ወንጀሎችም እንደ ሰደድ እሳት መስፋፋታቸውን አንስቷል፡፡ አያይዞም፤ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የተጠናከረ መሆኑን የሚያወሳው ለፎርት፤ ቀኑ ዘንበል ያለ እንደሆን ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚያስቡና አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ የለም ብለው የሚያስቡ ሰዎች መሣሪያ እየገዙ መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡
ከሁሉም በላይ አሳሳቢ ሆኖ የታየው፤ ለፎርት ‹‹የዘር ማጽዳት›› ሲል የገለጸው ክስተት ነው፡፡ የሁከት ክስተቶችና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ቁጥር መጨመሩንም የገለጸው ለፎርት፤ ‹‹ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በነበሩት 6 ወራት የተከሰቱት የሞት አደጋዎችና እርሳቸው ጠ/ሚ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ባሉት 6 ወራቶች ውስጥ የተከሰቱት የሞት አደጋዎች በንጽጽር ሲታዩየ48 በመቶ ዕድገት ይታያል፡፡ ከሚያዚያ ወር 2010 እስከ ጥቅምት 2011 ባሉት 6 ወራት 954 የሞት አደጋ ተከስቷል፡፡ የህዝብ መፈናቀል ችግርም ተስፋፍቷል። ዛሬ በኢትዮጵያ ከየመንና ከሶርያ የበለጠ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
የጸጥታ ኃይሎች እና ፖሊስ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከልና ሲከሰቱም እርምጃ ወስዶ ጸጥታን ማስከበር አለመቻሉንም ያነሳል፡፡ጠ/ሚ ዐቢይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደዱ መሆናቸውን ደጋግመው ቢገልፁም፤ እስካሁን የመጣ ለውጥ አለመኖሩን ጠቅሷል፡፡ አያይዞም፤ ሁሉም ታዛቢዎችአለመረጋጋቶቹ ሳይፈቱ በቆዩ ችግሮች ሳቢያ የሚከሰቱ መሆናቸውን እንደሚያምኑና፤ ችግሮቹም የተጽኖ አቅማቸውን የማሳየት ጉጉት ባላቸው የየአካባቢው ፖለቲከኞች የሚባባሱ ችግሮች መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ብዙዎች ችግሩን የዐቢይን የለውጥ እርምጃ ለማሰናከል ከሚፈልጉ፤ በሽምቅ ከሚሰሩ፤ ሁሉንም ቦታ ለመድረስ ከሚችሉ እና በመቀሌ ከመሸጉ ‹‹የጨለማ ኃይሎች›› ሻጥር ጋር አያይዘው ለማየት የሚፈልጉ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ ይህን ድምዳሜ የሚደግፍ አዳችም ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉን ያወሳው ለፎርት፤ በእርግጥም ‹‹የለውጥ አደናቃፊ›› ኃይሎች እዚህም እዚያም መንቀሳቀሳቸው የሚታበል ባይሆንም፤ የተፈጠረው የስልጣን ክፍተት ዋነኛ ባለድርሻ ራሱ መንግስት ነው ብሏል፡፡ የችግሩ ዋነኛ ምንጭ ከፀጥታ አካላት ጀምሮ በተለያዩ አካላት ዘንድ የሚታየው ‹‹እስኪ ነገሩ ይጥራ›› ከሚል እሳቤ የሚነሳ የመደንዘዝ ዝንባሌ (passivity) እንጂ ሻጥር አይደለም የሚለው ለፎርት፤ ችግሩ ጠንካራ የዕዝ ማዕከል ካለመኖሩ እና ለወትሮው የሚታወቀው ጥብቅ የሆነ ተዋረዳዊ የመንግስት አሰራር ስርዓት ከመፍረሱ ጋር የሚያያዝ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ታዲያ በዚህ ሂደት፤ አንድአሳሳቢ፤ በሰፊው የሚታይ እና እጅግ አደገኛ የሆነ ነገር እየተፈጠረ መሆኑን የጠቆመው ፀሐፊው፤ ይህም አሳሳቢ ችግር ጽንፈኛ የብሔር ማንነት እየጎለበተ መምጣቱ ነው ብሏል፡፡ በተለያዩ የብሔር ቡድኖች ዘንድ የሚታየው የማንነት እንቅስቃሴ የማይታረቅ መስሎ መታየት መጀመሩን የሚጠቅሱ አንዳንድ ምሁራን ብቅ ብቅ ማለታቸውን ጠቅሶ፤ እነዚህ ምሁራን ‹‹ራስን የመነጠል እርምጃ የማይቀር ሆኖ እየመጣ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲናገሩ›› መስማቱን ገልጧል፡፡ አሁን የሚታየው የክልል የማንነት እንደ ቀድሞው ራስን በአወንታ የመግለጽ ሳይሆን፤ ከመነጠል፣ ከበቀል እና ከመጤ ጠል ዝንባሌዎች ጋር የተሳሰረ መሆኑንም አመልክቷል።
የዚህ ሁሉ ችግር ማሰሪያው የህግ የበላይነትን ማስከበርነው የሚለው ረኔ ለፎርት፤ በዚህ ረገድ ባለፈው ጊዜ በሐዋሳ የተካሄደው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ የህግ የበላይነትን ማስከበር ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚል ውሳኔ ማሳለፉን አስታውሷል። ሁሉንም ከፋፋይ አጀንዳዎች በመተው የፓርቲውን አንድነት ከአደጋ ለመጠበቅ ጥረት አድርጓል በሚል የሚጠቅሰው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ፤ ሁለት ወሳኝ እርምጃዎችን መወሰዱንና እነዚህም ዶ/ር ዐቢይን በድጋሜ የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ የመምረጥ ውሳኔና ፓርቲውን ከመፍረስ ለማዳን ሲባል በአንድ አጀንዳ -ማለትም የህግ የበላይነት በማስከበር - ዙሪያ የመሰባሰብ ውሳኔ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ ባወጣው የአቋም መግለጫ፤‹‹የህግ የበላይነትን የሚጻረሩ ድርጊቶች መገታት አለባቸው›› የሚል ጠንከር ያለ ሐሳብ መስፈሩን የዘከረው ፀሐፊው፤ ‹‹ሆኖም ጥያቄው ይህን ለማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?››የሚል መሆኑን አስረድቷል፡፡
ሐተታውን በመቀጠል፤ ‹‹በአሁኑ ጊዜ የሽግግር የሚል ነገር አጀንዳ ሆኖ አይታይም›› የሚለው ለፎርት፤ አንዳንዶች (እንደ ጀዋር ያሉ ሰዎች) ‹‹አብዮቱን እና ሐገሪቱን ከጥፋት ለማዳን›› ያለው ብቸኛው መፍትሔ፤ ‹‹አጀንዳዎችን በቅደም ተከተል አስቀምጦ ድርድር መጀመርና ለምርጫ ዝግጅት ማድረግ ነው›› እንደሚሉ አስረድቷል፡፡ ‹‹ከሁለት ወራት በፊት እኔም ተመሳሳይ አቋም ነበረኝ›› ብሎ፤ ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ከተቻለ የተቃውሞ መንፈሱን በማርገብ ህዝቡን ወደ ግልጽና ወሳኝ ወደሆነ የጋራ ግብ ሊያመጣው ይችላል የሚል እምነት እንደነበረው እና አሁን ይህ አቋሙ መቀየሩን ያብራራል፡፡
አሁን በሐገሪቱ በሚታየው የፀጥታ መደፍረስና አለመረጋጋት ሁኔታ ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ቀርቶ፤ ምርጫ ሊባል የሚችል ነገር እንኳን ማከናወን እንደማያስችል ገልፆ፤ ‹‹አሁን በሚታየው የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ የሚካሄድ የምርጫ ዘመቻ፤ ያለውን ዕብደትና ኢ- ምክንያታዊነት ይበልጥ እንዲባባስ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም›› ብሏል፡፡ በመሆኑም፤ ከችግሩ መውጫ ወሳኙ መንገድ ህግ እና ሥርዓት ማስፈን መሆኑን ጠቁሞ፤ ይህም ሥራ ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ የተከሰተውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር በተወሰደው እርምጃ እንደታየው፤ በፀጥታ ኃይሎች ጥረት ብቻ ሊሳካ የሚችል አይደለም ብሏል፡፡
ህግ እና ስርዓትን የማስፈንምሥራ፤ ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆን ቁጥር ባለው እና ብዙውን ጊዜ የአካባቢው የፓርቲ መዋቅር ሊቀመንበር ሆኖ ለሚገኘው የቀበሌ ሊቀመንበር ታማኝነት በሚያሳየው የሚሊሻ ኃይል አማካኝነት ከዝቅተኛው እርከን ከቀበሌ መጀመር ይኖርበታል፡፡ የፓርቲና የመንግስት ሥልጣን የመጨረሻው የትስስር ነጥብ የሆነውም እርሱ ነው ብሏል፡፡
ስለዚህ የመንግስትና የፓርቲ የአሰራር ስርዓት ተመልሶ መቆም ይኖርበታል የሚለው ለፎርት፤ ይህን ለማድረግ፤ በትንሽ የአካታችነትና የትብብር መንፈስ የመገንባት ጥረት የህዝብ አመኔታ ሊያገኝ የሚችል አመራር መፍጠር ያስፈልጋል ብሏል፡፡
አክሎም፤ ‹‹ጎምቱው የፖለቲካ ሰው ሌንጮ ለታ እንዳሉት›› ያለው ለፎርት፤ ‹‹እኛ (የፖለቲካ ፓርቲዎች) በበርካታ መሠረታዊ ጉዳዮች እንለያያለን። ኢትዮጵያ ምንድነች፤ ምን ዓይነት የዴሞክራሲ ስርዓት ያስፈልገናል…..በሚሉ ጉዳዮች እንለያያለን፡፡ የተለያዩ አቋሞችበእንዲህ ያሉ ሸለቆዎች ተለያይተው ቆመዋል፡፡ ….. ነገር ግን እኛ ድርድር አድርገን ከአንድ መቻቻያ ነጥብ ከመድረስ በስተቀር ሌላ ምርጫ ያለን አይደለንም፡፡ ይህን ማድረግ ከተሳነን ከፊታችን የሚደቀነው ዕጣ ፈንታ ጠቅላላ የስርዓት መፍረስ አደጋ ነው›› ማለታቸውን ጠቅሷል፡፡
ከአንድ መቻቻያ ነጥብ የመድረስ ቀና ፍላጎት በሁሉም ወገኖች ዘንድ ቢኖርም፤ በምን አጀንዳ ዙሪያ እንነጋገር፤ በዚህ የምክክር መድረክ ተሳታፊ የሚሆኑትስ ወገኖች እነማን ይሁኑ የሚለውን ነገር አንጥሮ ማውጣት ያስፈልጋል ያለው ፀሐፊው፤ አነጋጋሪ አጀንዳዎች አድርጎ የወሰዳቸውን ጉዳዮች በማውጣት ትንታኔ አቅርቧል፡፡ ከነዚህ አጀንዳዎች መካከልም፤ ‹‹የፌዴሬሽን ስርዓቱ ምን መልክ ያለው ይሁን›› የሚለው ጥያቄ አንዱ መሆኑን ጠቅሶ፤ የአንዳንዶች ሐሳብ የቋንቋ ወይም የብሔር መስመር የተከተለ አከላለል እንዲኖር ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ አሁን ያለው አከላለል እንዳለ ሆኖ፤ ክልሎች ለኮንፌደሬሽ የቀረበ ነፃነት እንዲያገኙ የሚደረግበት ስርዓት ይኑር የሚሉ መሆናቸውን ያብራራል፡፡ እንዲህ ዓይነት የአመለካከት ልዩነት በኦዴፓ (የቀድሞው ኦህዴድ) ውስጥ መኖሩን የሚገልፀው ለፎርት፤ ዶ/ር ዐቢይ ጠንካራ ህብረት የሚፈጥር ፌዴሬሽን የሚፈልጉ መሆናቸውንና አክራሪ ኃይሎች ደግሞ ለኮንፌደሬሽን የቀረበ ሁኔታ የሚሹ መሆናቸውን ጠቅሶ በአሁኑ ሰዓት ‹‹ኦዴፓ አካል የሌለው ጭንቅላት ነው›› ይላል - አመራሩ የድርጅቱን የበታች ኃይል አመኔታ ለማግኘት ብዙ ሥራ የሚጠይቀው መሆኑን ለማመልከት፡፡
የታችኛው ኃይል ከዶ/ር ዐቢይ ይልቅ፤ ለኦነጉ መሪ ለአቶ ዳውድ ኢብሳ፤ ለኦፌኮ መሪዎች ለዶ/ር መረራ ጉዲና እና በቀለ ገርባ፤ ለኦዴግ አመራር ለሌንጮ ለታ፤ ለቄሮ እና ለጃዋር መሐመድ ቅርበት አላቸው ይላል። ከሃያ ሺህ በላይ ካድሬዎችን የበወዘው (ሳያባርር) ኦዴፓ፤ በታችኛው መዋቅር ብዙ አመኔታ ያለው ድርጅት አይደለም - አሁንም ዶ/ር ዐቢይ በኦሮሚያ ተወዳጅ መሪ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ስለዚህ ዶ/ር ዐቢይ ለኃላፊነታቸው የሚመጥን መዋቅር ተከል የፖለቲካ ሥልጣን የላቸውም ይላል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አቋም ጠንካራ ማዕከላዊነት ባለው እና ባልተማከለ የአስተዳደር ዘይቤ የሚዋልል እና ግልጽነት የሌለው መሆኑን የሚጠቅሰው ለፎርት፤ አንዳንዶች ይህን ታክቲክ ይሁነኝ ብለው እንደያዙት ያስባሉ ይላል፡፡
ፀሐፊው በዚሁ አግባብ ሌሎች የግንባሩን አባል ድርጅቶች ሁኔታ ይገመግማል፡፡ ለጊዜው የቀረበው ይበቃል፡፡ ሰክኖ መነጋገር ከተቻለ፤ በተለያዩ ችግሮች መናጣችን ባይቀርም፤ የከፋ ነገር እንዳይገጥመን ማድረግ እንችላለን፡፡ አያያዛችን ግን ይህን አያመለክትም፡፡ ስለዚህ ሾተልን ወደ አፎት፤ ቁጣን ወደ ትዕግስት በመመለስ መነጋገር ያስፈልገናል፡፡ ይህም ንግግር ከገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መጀመር አለበት፡፡

Read 1534 times