Monday, 17 December 2018 00:00

የዓለም መንግስታትን ቀልብ የገፈፈ የፈረንሳይ ተቃውሞና ረብሻ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


    ዜጎች የወር መጨረሻ ላይ ለመድረስ ይጨነቃሉ። የዓለም መንግስታት፣ ከመቶ ዓመታት በኋላ የዓለም ሙቀት ሊጨምር ይችላል ብለው ለመደስኮር ይገባበዛሉ። ነዳጅንና መኪናን በማንቋሸሽ ይቀናጣሉ፤ የነዳጅ ታክስ በመጨመር ይወዳደሳሉ። የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ በማፍረስና የኤሌክትሪክ ዋጋ በማናር... ይሞጋገሳሉ። ይሄንን እንደ ስኬት የሚቆጥሩ መንግስታት፣... በእርግጥም ከእውኑ ዓለም ውጭ ተነጥለው ሌላ ምናባዊ ዓለም ውስጥ የገቡ ነው የሚመስሉት።
በርካታዎቹ የዓለም መንግስታትና ባለስልጣናት፣ ከተጨባጩ የሰዎች ኑሮ ጋር ተራርቀዋል። ከእውኑ የሰው ኑሮ በእጅጉ ከመራራቃቸው የተነሳም፣ እውነተኛና አሳሳቢ የኑሮ ጉዳይ ብዙም ትዝ አይላቸውም። አዲስ የነዳጅ ታክስ ሲታወጅ፣ በአድናቆት የሚያስጨበጭብ ስኬት እንጂ ኑሮን የሚነካና ለተቃውሞ የሚጋብዝ ችግር ሆኖ አይታያቸውም። ቢታያቸውም ከቁምነገር አይቆጥሩትም።
ለዚህም ነው፣ ለወገኞቹ የዓለም መንግስታትና ቢሮክራቶች፣ የፈረንሳዩ ተቃውሞና ረብሻ፣ ድንገተኛና አስደንጋጭ የሆነባቸው - “የነዳጅ ታክስ ላይ እንዴት ሰዎች ተቃውሞ ያሰማሉ? ለዚያውም፣ በሊትር 15 ሳንቲም በማይሞላ ታክስ፣ አገር በተቃውሞ ይረበሻል?” በሚል ስሜት አስገርሟቸዋል።
“የአካባቢ ጥበቃ” እና “የአየር ንብረት ለውጥ” ዲስኩር በሰፊው የሚደገስበት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ያሰፈሰፉት የዓለም መንግስታትና ባለስልጣናት፣ የተለመደው የሆይሆይታ ሳምንት ለመፍጠር ቢመኙም አልተሳካላቸውም። በእርግጥ አምናም ያን ያህል አልቀናቸውም። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ “የአካባቢ ጥበቃ” እና “የአየር ንብረት ለውጥ” ከሚለው ዓለማቀፍ የጥፋት ዘመቻ ውስጥ አሜሪካ እንደምትወጣ በመግለፃቸው ሳቢያ፣ ዓመታዊው ጉባኤ መቅኖ አጥቷል። ዘንድሮ ደግሞ፣ በፓሪሱ ተቃውሞ ሳቢያ፣ የዓለም መንግስታትና ባለስልጣናት፣ ቀልባቸው ተገፎ፣ ድምፃቸው ጠፍቶ፣ ዓመታዊው ጉባኤ የከሰረ ድግስ፣ የጨረባ ተዝካር መስሎ ተጠናቋል።

የ15 ሳንቲም አመፅ

ፈረንሳይን ሲያምሳት የሰነበተው አመፅ፣ በአዲስ የናፍጣ ታክስ ሳቢያ የተለኮሰ ነው። “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “የአየር ንብረት ለውጥ”፣ “የአለም ሙቀት”፣ “የካርቦን ልቅቀት”፣ “ሥነምህዳር”... ምናምን የሚሉ የለመዱ መፈክሮች በተስተጋቡበት የዩኤን አመታዊ ስብሰባ ላይ፣ የፈረንሳይ የነዳጅ ታክስ፣ የአድናቆት ውዳሴና የድጋፍ ጭብጨባ እንደሚቸረው ነበር የተገመተው። ለፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም፣ የዲስኩር ማሳመሪያ እንዲሆንላቸውና እንዲሞገሱበት።
አዲሱ የናፍታ ታክስ፣... በሚቀጥለው ወርም ተጨምሮበት፣ ለአንድ ሊትር ናፍታ፣ በዩሮ 14 ሳንቲም ይሆናል ተብሎ ነው የታቀደው። ታክሱ፣ ከብዙ ፈረንሳዊያን ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ ፕ/ት ማክሮን፣ ከቁብ አልቆጠሩትም - “የተምታታበት ትርጉም የለሽ ተቃውሞ ነው” በሚል ስሜት አጣጥለውታል።
ለሁለት ሳምንት የዘለቀው ተቃውሞ ተባብሶ ባለፈው ቅዳሜ በተለይ የፓሪስ ዙሪያ ሲረበሽ፣ ማክሮን አርጀንቲና ውስጥ በ”G20” ስብሰባ ላይ ነበሩ። አዲሱ የናፍታ ታክስ እንደማይሰረዝ የተናገሩት ፕ/ር ማክሮን፣ ጨርሶ መታሰብም የለበትም ብለዋል። እንዲያውም ታክሱ ዘግይቷ ባይ ናቸው።
“ሰኞ እለት የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ፣ ማክሰኞ እለት የነዳጅ አፍቃሪ መሆን አንችልም”... በማለት ተቃውሞውን ያጣጣሉት ማክሮን፣ በ”G20” ስብሰባ ላይም ሌላ ወሬ አልነበራቸውም። የአካባቢ ጥበቃ ፊታውራሪ፣ የስነምህዳር (የኤኮሎጂ) አስተማሪ፣ የፀረ-ነዳጅ ዘመቻ አውራ መሪ ሆነው፣...  ዲስኩራቸውን እያቀረቡ ነበር - አርጀንቲና ውስጥ። አገራቸው ፈረንሳይ ግን፣ ለግማሽ ምዕተዓመት ታይቶ በማይታወቅ ተቃውሞና ረብሻ እየታመሰ። ከዚያ በኋላም፣ በፖላንድ አለማቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ላይ በተመሳሳይ ዲስኩር የሞቀ ሙገሳ ይጠብቃቸዋል - ሰኞና ማክሰኞ። እንደታሰበው አልሆነም።
ሲያቃልሉትና ሲያብጠለጥሉት የነበረው የታክስ ተቃውሞ፣ አገርን የሚረብሽ እሳት ሆኖ አረፈው። ፓሪስ ታመሰች። ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው በረብሻው 3 ሰዎች ሞተዋል። % የሚቆጠሩ ተጎድተዋል። የዚያኑ ያህልም ታስረዋል።
ወደ ፈረንሳይ ተመልሰው፣ በረብሻ የደረሰውን ጉዳት ፓሪስ ውስጥ ዞር ዞር ብለው የተመለከቱት ማክሮን ግን፣... አሁንም፣ የናፍታ ታክስ ጨርሶ የማይቀር ጉዳይ ነው አሉ። “ተቃውሞዎችንና ቅሬታዎችን ለማድመጥ ዝግጁ ነኝ፤ የታክሱ ውሳኔ ግን አይቀየርም” አሉ ፕሬዚዳንቱ። የነዳጅ ታክስ እየጨመረ ይሄዳል እንጂ አይቀንስም! ለምን?
የነዳጅ ታክስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር የሚደረገውማ፣ “የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ፣ በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖችን ከገበያ ለማስወጣት፣... ከ150 ዓመታት በፊት ከነበረው የዓለማችን ሙቀት ጋር ሲነፃፀር፣ ወደፊት ከ100 ዓመት በኋላ የሚኖረው የዓለም ሙቀት ከ2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዳይበልጥ ለመከላከል፣... ኢኮሎጂን፣... ስነምህዳርን... አካባቢን ለመጠበቅ፣”... እንዲህ እንዲህ አይነቱ በተለምዶ በጭብጨባ የሚያስወድስ ዲስኩራቸውን ደገሙት - ፕሬዚዳንት ማክሮን።
የፕሬዚዳንቱ ምላሽና ንግግር አልፈየደም። እንዲያውም፣ ጉዳዩን ለማስረዳትና ለማረጋጋት የሚጠቅም ሳይሆን፣ ብዙዎችን በማናደድ ነገሩን የሚያባብስና የሚያጋግል እንደሆነ ኒውዮርክ ታይምስ አመልክቷል። በርካታ ዜጎች በፕ/ር ማክሮን ዲስኩር መብገናቸውን ጋዜጣው ለማሳየት፣ ያሰፈረው አስተያየት እንዲህ ይላል፤ “ዜጎች ታክስ እንዲቀነስልን ነው የጠየቅናቸው፤ እነሱ ሆዬ ኢኮሎጂ ይሉልናል”።
ነዳጅንና መኪናን ብቻ ሳይሆን ከግድብ ወይም ከኒኩሌር የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ሃይል መጠቀምም እንደ ብክለትና እንደ ጥፋት የሚቆጠርበት ዘመን አይደል? ፕ/ር ማክሮን፣ ከአዲስ የነዳጅ ታክስ ጋር ብዙ መኪኖችን ከአገልግሎት የሚያግድ አዲስ ምርመራ እንደሚያስጀምሩም ገልፀዋል። የኒኩሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ከመዝጋት ጋር፣ አዲስ የኤሌክትሪክ ዋጋ ጭማሪ ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዳቸውንም ጋዜጣው ዘግቧል። ጋዜጣው ይህንን የሚዘረዝረው፣ ፕ/ት ማክሮንን በመተቸት ሳይሆን በማሞገስ ነው። የፕሬዚዳንቱ አላማ፣ ፈረንሳይ ወደ ተሻለ ፅዱ የሃይል ምንጭ እንድትሸጋገር ነው በማለት ያወድሳቸዋል። በ250 ዓመታት ልዩነት፣ የዓለም ሙቀት በ2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዳይጨመር ለመከላከል መሆኑ ነው?
ተቃውሞ አቅራቢ ዜጎች ግን፣ በፕሬዚዳንቱ እቅዶች ይበግናሉ። የፕሬዚዳንቱ ትኩረት ሌላ፣ በእውን የሚታየው የዜጎች የኑሮ ጭንቀት ሌላ።
ፕሬዚዳንቱ ስለ ዓለማችን የሩቅ ዘመን መጨረሻ ያሰላስላሉ። ዜጎች ግን የወር መጨረሻ ላይ ለመድረስ ይጨነቃሉ - ሲል ዘግቧል ኒውዮርክ ታይምስ። (“...Mr. Macron is concerned about the end of the world, while they are worried about the end of the month.”)
ዘገባው፣ የመንግስታት ትኩረትና የዜጎች ኑሮ መራራቃቸውን የሚጠቁሙ ሌሎች ምሳሌዎችንም ጠቅሷል።
...working people need cars to get to jobs and conduct their daily lives...  The French president has until now tried to sail above the discontent, deploying lofty abstractions and determined to discourage the French from using cars.
በስራ የሚተዳደሩ ሰዎች ስራ ውለው ለመግባትና የእለት ተእለት ኑሯቸውን ለማከናወን መኪና ያስፈልጋቸዋል። ፕሬዚዳንቱ ግን፣ እስካሁን ቅሬታዎችን አሻግረው ሰማይ ለሰማይ የሚቀዝፉና የሚያንዣብቡ ሃሳቦችን እየለቀቁ፣ ፈረንሳዊያን መኪናን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ለመገፋፋት በፅናት ሲጥሩ ቆይተዋል...
ይሄ በሐሙስ እለት እትሙ ነው። በማክሰኞ እትሙ ደግሞ፣ ፈረንሳይ ከየትኛውም አገር በላይ ዜጎችን የምትደጉም አገር መሆኗን በመጥቀስ፣ የተቃውሞውን ትርጉም ለማቅለል ይሞክራል። 75 % ያህል ፈረንሳዊያን ተቃውሞው ተገቢ ነው ብለው እንደሚያምኑ ዘገባው ይጠቅሳል። ይሁንና ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ አንድ ሶስተኛው ያህል በመንግስት በኩል ለተለያዩ ድጎማዎች እንደሚውል ጋዜጣው ገልፆ፣ በዚህም ምክንያት የጥርጣሬ ጥያቄዎች እየናኙ ናቸው ይላል - ተቃውሞውን የሚያጣጥሉ ጥያቄዎችን በማስከተል።  ይሄ ሁሉ ድጎማ እየተሰጠ፣ ተቃውሞ አቅራቢዎቹ የምር በችግር ተጎድተው ነው ለተቃውሞ ወደ አደባባይ የሚወጡት? ምን ያህሉስ ተቃውሞ፣ ለምዕተዓመታት ከዘለቀው አመል የመነጨ፣ ለውጥን ከመቃወም አመል የመጣ ይሆን?
France protects citizens with one of the most generous social safety nets in the world, with over one-third of its economic output spent on welfare protection, more than any other country in Europe. ... While polls show that the Yellow Vests have the backing of three-quarters of the population, questions have swirled about how much pain the protesters are really experiencing - or how much of the outpouring can be chalked up to a centuries-old culture of demonstrating against change.
ኒውዮርክ ታይምስ አልያም ፕሬዚዳንት ማክሮንና በርካታ የዓለም መንግስታት፣ የዜጎችን ኑሮ ቸል ብለው በምናባዊ “ስነምህዳር” ወይም በ”አየር ንብረት ለውጥ ዲስኩር” ውስጥ እየተቀናጡ ለመቀጠል ቢሞክሩም እንኳ፣ ሙከራቸው ብዙም ሊያዛልቅ አይችልም። እንደማያዛልቅም እየታየ ነው።
በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ዙሪያ እንደምናየው፣ የኑሮ ጉዳይ ለጊዜው ቸል ቢባልም፣ ዞሮ ዞሮ የኑሮ ጉዳይ ነው - ማምለጫ የለውም። ኑሮ ቀልድ አይደለም፣ ኢኮኖሚ የሕይወት ጉዳይ ነው - በፈረንሳይም በሌሎችም አገራት።
በእርግጥ፣ ኒውዮርክ ታይምስ እንዳለው፣ የፈረንሳይ መንግስት ድጎማን በማስፋፋት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። ችግሩም ይሄው ነው። የድጎማ መንግስት፣ ውሎ አድሮ ውድቀትን የሚደግስ መንግስት ይሆናል።  
ድጎማዎችን በሰፊው የሚያከፋፍል መንግስት፣ በዚያው መጠን የዜጎችን ኪስ የሚያራቁት፣ ኢንቨስትመንትን የሚያሰናክል፣ የስራ እድል ፈጠራን የሚሸረሽር፣ ስራ ፈትነትን የሚያበረታታ፣ ተመፅዋችነትን የሚያበራክት፣ ኢኮኖሚን የሚያዳክም፣ እዳ ውስጥ የሚዘፈቅ መንግስት ማለት ነው።

የድጎማ መንግስት፣ የውድቀት መንግስት

ከዓለም ኢኮኖሚ ግማሹን ያህል የሚያመርቱ 9 አገራትን እንመልከት። ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ስፔንን፣ አውስትራሊያና ጃፓንን እንዲሁም ካናዳና አሜሪካን። አምና ከጠቅላላው የዓለም 80 ትሪሊዮን ዶላር የዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ፣ የእነዚህ አገራት ድርሻ 40 ትሪሊዮን ዶላር እንደነበረ ሲታይ፣ በእርግጥም የብልፅግናና የግስጋሴ አርአያነታቸው አያጠራጥርም። ነገር ግን፣ ከጥቂት አመታት ወዲህ ከአርአያነት እየራቁ፣ ከግስጋሴም እየወጡ፣ ስኬታቸው “ድሮ የቀረ ታሪክ” ወደመሆን ተቃርቧል። እንዴትና ለምን?
የዘጠኙ አገራት የመንግስት በጀት፣ ምን ያህል እንደነበርና ዛሬ የት እንደደረሰ በማየት እንጀምር - አስደናቂውን የግስጋሴ ስኬትና አሳዛኙን የውድቀት ቁልቁለት ለመቃኘት ፍንጭ ይሰጠናል። ለጊዜው አብረው የሚሄዱ የሚመስሉት፣ “የመንግስት ባጀት” እና “የኢኮኖሚ እድገት”... ዓመት አልፎ ዓመት በተቆጠረ ቁጥር ግን፣ ተቃራኒነታቸው ምንኛ ገንኖ እንደሚታይ ለመገንዘብም ይረዳናል።
የዛሬ መቶ ዓመት፣ የጣሊያንና የፈረንሳይ መንግስታት በጀት፣ ከዓመታዊ የዜጎች ምርት ውስጥ 15% ያህሉን የሚወስድ እንደነበር የአይኤምኤፍ ታሪካዊ መረጃ ያስረዳል። የአሜሪካ መንግስት ወጪ ደግሞ 7.5%።
በድምር፣ የዘጠኙን አገራት አማካይ የመንግስታት በጀት 13% % ገደማ ነበር - በ1910። በቀጥታ በታክስም ይሁን በሌላ ተዘዋዋሪ መንገድ፣ የመንግስት እጅ ከዜጎች ኪስ ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚወስድ የሚጠቁም ቁጥር ነው (ከመቶ ዶላር የዜጎች ገቢ ላይ፣ 13 ዶላሩን መንግስት ይወስዳል)።
በ1960ስ?
የመንግስታት ወጪ በፍጥነት ጨምሯል። እናም፣ የዜጎች ምርት 30% ያህሉን በመንግስት ይወሰዳል (በቀጥታ አልያም በተዘዋዋሪ)።
በ2010ስ?
የመንግስታት ወጪ፣ ይበልጥ እያበጠ እየባሰበት ሄደ እንጂ፣ አንዳች አደብ የሚያስገዛ መፍትሄ አልተገኘም።
የመንግስታት ወጪ፣ ከዜጎች ዓመታዊ ምርት ውስጥ 45% % ያህሉን የሚወስድ ሆኗል (ያው እንደተለመደው፣ በቀጥታና በዘወርዋራ፣... በአጣዳፊ እያዋከበና በዝግታ እያዘናጋ፣ ለዓመታት በሚጓተትና ቀልጦ በሚቀር ብድር፣ አልያም በዋጋ ንረት ኑሮን በሚሸረሽር የገንዘብ ሕትመት አማካኝነት... መንግስታት የዜጎችን የስራ ፍሬ በየዓመቱ ይወስዳሉ።)
“የመንግስታትን ወጪ የሚያሳብጡ” መዓት ወገኛ ሰበቦች በየጊዜው የመፈልፈላቸው ያህል፣ የመንግስትን ወጪ ለመቀነስ የሚጠቅም ደህና መፍትሄ ከአውሮፓ ምድር ጠፍቷል ማለት ይቻላል።
ዛሬ ዛሬ፣ ለጤና ድጎማ፣... ለማህበራዊ ዋስትና፣... ለትምህርት ድጎማ፣... ያለማቋረጥ መዓት የድጎማ አይነቶችና ሰበቦች እየተፈበረኩ፣... እነዚህን ሁሉ ወጪዎች ለመሸፈን በየጊዜው እየተደራረቡ በሚደረቱ የታክስ አይነቶችና የገንዘብ መሰብሰቢያ ሾላካ ዘዴዎች አማካኝነት፣ አብዛኞቹ የአውሮፓ መንግስታት፣... በሰው ኪስ ላይ፣ እኩል ተካፋይ ሆነዋል። ሰው ኑሮውን ለማሻሻል ሰርቶ በሚያፈራው ምርትና ገቢ ላይ፣ መንግስት እኩል ባለድርሻ ልሁን የሚለው “በፀባይ” አይደለም። አምራች ዜጎችን የሚሳደብ፣ “ስግብግቦች፣ አጭበርባሪዎች፣ ራስወዳዶች” እያለ የሚወነጅል፣ ለማሰር የሚዝትና የመቅጣት የሚጣደፍ ቁጡ ጉልበተኛ ነው - 50% ያህል የሰዎችን የጥረት ፍሬ አፍሶ የሚወስድ፣ የሰዎችን ምርት የሚነጥቅና ኪሳቸውን የሚያራቁት አዛዥ ናዛዥ ሆኗል ቢባል ይሻላል።
ለማንኛውም፣ በዜጎች ምርት ላይ መንግስት ቢሮክራሲ እኩል በላተኛ፣ በዜጎች ኪስ ውስጥ የመንግስት እጅ እኩል ቤተኛ ሲሆን፣... የመንግስት ወጪ በሰበብ አስባቡ ሲያብጥ፣ በጀቱ በየዓመቱ ሲለጠጥ፣... ጥፋቱና ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ነው።
በአንድ በኩል፣ የታታሪ፣ የምርታማና የስራ ፈጣሪ ዜጎች ኪስ በመንግስት የታክስ እጆች እያራቆተ፣... የሚያቅዱትን ኢንቨስትመንት እያሰናከለ፣ የሚከፍትቱን የስራ እድል እያመናመነ፣ የጥረታቸውን ፍሬ ያበላሻል፤ እያከሰረ ከስራና ከገበያ እያስወጣም፣ የአገራቸውን ኢኮኖሚ ያዳክማል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ድሃ አገራትም ሆነ በበለፀጉ የአውሮፓ አገራት፣ መንግስት እጅ ውስጥ የገባ ገንዘብ፣ ከመተሳሳይ አሳዛኝ እጣፈንታ አያመልጥም። ብዙ ገንዘብ የብክነትና የኪሳራ ሲሳይ ይሆናል። ይህም ብቻ አይደለም። አብዛኛው ሰው የመንግስት ተመፅዋችና ጥገኛ እንዲሆን የሚገፋፉ የድጎማ አይነቶችን እየፈለፈለ፣ ስንፍናንና ስራ ፈትነትን እያበረታታ ያበራክታል።
ከብክነቱና ከኪሳራው፣... ከድጎማው አይነትና መጠን ጋር የመንግስት ወጪ ይጨምራል። ወጪውን ለመሸፈን፣... እንደገና ምርታማና ስራ ፈጣሪ ዜጎች ይበልጥን የሚያዳክምና የሚያከስር፣ ቁጥራቸውን የሚያመናምንና እድገትን የሚሸረሽር ተጨማሪ የታክስ ጫና ያመጣባቸዋል።
መጨረሻው የማያምር አዙሪት ነው - በአንድ በኩል የእድገት ምንጭ የሆኑ ዜጎችን እያዳከመና እያመናመነ፣... በሌላ በኩል ደግሞ የድጎማ ጥገኛና የመንግስት ተመፅዋች ዜጎችን የሚያበራክት፣... የቁልቁለት አዙሪት።
የመንግስታት ድጎማና ወጪ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ፣ የአገሮቹ የኢኮኖሚ እድገት ቁልቁል እየወረደ ሲመጣ ማየት ይቻላል።
ከ1960 እስከ 1980 ድረስ የዘጠኙ አገራት አማካይ የኢኮኖሚ እድገት ከ3 % በላይ ነበር።
ከ1990 ዎቹ አጋማሽ በኋላ፣ የኢኮኖሚ እድገታቸው፣ ወደ 2.5 % ወርዷል።
ከ2000 ወዲህ ደግሞ ወደ 2 % አሽቆልቁሏል።
ከ2008 እስከ 2018 ድረስ ባሉት ዓመታትስ? 1.5 % ብቻ!

Read 3114 times