Saturday, 15 December 2018 15:53

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

 ክፍል-፪ ለመሆኑ መፅሐፍ ቅዱስ ብህትውናን ይደግፋል?

     “--የሀገራችንም ሰዎች በእርሻው፣ በንግዱ፣ በትዳሩ … ባጠቃላይ በኑሮው አልሳካላቸው ሲል ለዘመናት ይቺን ጥቅስ ሲጠቀሙባት ኖረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አርቲስቶቻችንና ዘፋኞችም ይሄንኑ መንገድ ሲከተሉ ታይተዋል፡፡ --”
       

     በክፍል አንድ ፅሁፌ ስለ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ስያሜና ሥልጣኔው ስለቆመባቸው ሦስቱ አምዶች - ማለትም ተአምራዊነት፣ ብህትውናና ሰሞነ ህማማት - አውርተናል፡፡ ከእነዚህ አምዶች ውስጥ የያሬዳዊው ሥልጣኔ የሥነ ምግባር መሰረት (Moral Foundation) ብህትውና መሆኑን በመጥቀስ፣ ስለ ብህትውና መፅሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል በክፍል ሁለት እንደምንመለከት ቀጠሮ ይዘን ነበር የተለያየነው፡፡
ምንም እንኳ ብህትውና የያሬዳዊው ሥልጣኔ አንደኛው ምሰሶ ቢሆንም፣ አስተሳሰቡ ግን በጥንት ኢትዮጵያውያን ምሁራን የፈለቀ አስተምህሮ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅስ አስተምህሮው ቀደም ብሎ ከአይሁዳውያን እምነት ጋር፣ በመቀጠልም ከዘጠኙ ቅዱሳን ጋር አብሮ ወደ ጥንታዊት አክሱም የገባ አስተምህሮ ነው፡፡
ለመሆኑ፣ እነዚህስ ሁለት እምነቶች፤(የአይሁድ እምነትና ክርስትና) ይሄንን አስተምህሮ ከየት አመጡት? ለዚህ ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው፤ እሱም ‹‹ከመፅሐፍ ቅዱስ›› የሚል ነው፡፡ በዚህ መልስ ላይ ግን የማይስማሙ ምሁራን አሉ፡፡ በመሆኑም፣ የመልሱን ሁለቱንም ጫፎች ይዘን ‹‹በእርግጥ መፅሐፍ ቅዱስ ብህትውናን ይደግፋል ወይ?›› ለሚለው ጥያቄ መልሱ ሁለት ነው - አዎም! - አይደለምም! ሁለቱም መልሶች ግን መፅሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አላቸው፡፡ እስቲ በየተራ እንመልከታቸው፡፡
መፅሐፍ ቅዱስ ብህትውናን ይደግፋል!!
‹‹ብህትውና መፅሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አለው›› ብለው የሚከራከሩ ምሁራን፣ እንደ ማስረጃ የሚጠቀሙበት ጥቅስ፤ የማቴዎስ ወንጌልን ነው፡፡ እንግዲህ ‹‹ብህትውና›› ስንል የዚህ ዓለም የሆኑ ነገሮችን ሁሉ (ለምሳሌ - አካልና ስሜቶቹን፣ ምድራዊ ሐብትን፣ ደስታንና ፖለቲካዊ ሥልጣንን፣ የአመክንዮን ኃይል ወዘተ…) የሚመለከት ነው፡፡ እነዚህ ምድራዊ የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ ሐዋርያው ማቴዎስ በወንጌሉ ምዕራፍ 19፤ ከቁጥር 16 ጀምሮ እንዲህ ይላል፡-
‹‹እነሆም፣ አንድ ሰው ወደ እየሱስ ቀርቦ፣ መምህር ሆይ ፍፁም እሆን ዘንድ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው፡፡ እየሱስም፣ ፍፁም ልትሆን ብትወድ፣ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፡፡ … ስለ ስሜም ቤቱን ወይም ቤተሰቡን ወይም እርሻውን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለም ህይወትንም ይወርሳል፡፡››
ይህ ጥቅስ ትንታኔ አያስፈልገውም፤ በመንፈሳዊ ህይወት ፍፅምና ላይ መድረስ የፈለገ ሰው፤ ምንና ምን ነገሮቹን መተው እንዳለበት በግልፅ ተቀምጧል። ጥቅሱ በምዕራብና በምስራቅ አብያተ ክርስትያናት ማህበረሰቦች ላይ ሁለት ውጤቶችን አስከትሏል፡፡
የመጀመሪያው፣ ለሥርዓተ ምንኩስና መነሻ ሆኗል። በ4ኛው ክ/ዘ የአሌክሳንደሪያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ አትናቲዎስ፤ የአባ እንጦስን የህይወት ታሪክ በፃፉበት The Life of St. Anthony መፅሐፋቸው ውስጥ እንደጠቀሱት፤ የሥርዓተ ምንኩስና መስራች የሆኑትና ከባላባት ቤተሰብ የተወለዱት አባ እንጦንስ፣ ሁሉን ነገር ትተው ወደ ብህትውና ህይወት እንዲገቡ ያደረጋቸው ከላይ የጠቀስነው የማቴዎስ ወንጌል እንደሆነ ፅፈዋል፡፡
የሀገራችንም ሰዎች በእርሻው፣ በንግዱ፣ በትዳሩ … ባጠቃላይ በኑሮው አልሳካላቸው ሲል ለዘመናት ይቺን ጥቅስ ሲጠቀሙባት ኖረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አርቲስቶቻችንና ዘፋኞችም ይሄንኑ መንገድ ሲከተሉ ታይተዋል፡፡ እናም በኢትዮጵያውያን ስነ ልቦና ውስጥ ብህትውና እስከ አሁን ዘመን ድረስ እንደ አንድ የህይወት አማራጭ ይታሰባል፡፡ ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሐንስም፤ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› መፅሐፋቸው ውስጥ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተጠቃሚነት እሴት ይጎድለዋል›› ያሉት ለዚህ ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወትም፣ ብህትውናን እንደ አንድ የህይወት አማራጭ የሚያስበውን ኢትዮጵያዊ ህሊና ክፉኛ የተቹት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከመንፈሳዊነቱ በተጨማሪ ‹‹የተጠቃሚነት እሴትንም›› ታሳቢ ማድረግ እንዳለበት መክረዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፣ ጥቅሱ ይሄንን ዓለምና ምድራዊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለመንፈሳዊ ህይወት እንቅፋት እንደሆኑ አድርጎ እንዲታሰብ ማድረጉ ነው፡፡ ይሄም በተራው፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ይሄንን ጥቅስ አጉልተው በሚጠቀሙ ማህበረሰቦችና የሀገራት የሀብት ክምችት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲኖረው አድርጓል፡፡
ባጠቃላይ፣ ‹‹ብህትውና መፅሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አለው›› በማለት የሚከራከሩ ሰዎች ትክክል ናቸው፡፡
መፅሐፍ ቅዱስ ብህትውናን አይደግፍም!!
በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ‹‹ብህትውና መፅሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ የለውም›› ብለው የሚከራከሩ ምሁራንም ትክክል መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ምሁራን እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የማርቆስ ወንጌል 2፡18-28 እና ቅዱስ ጳውሎስ በቆላሳይስ 2፡20-23 ላይ የፃፈውን ነው፡፡ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ከዓለማዊ ከመጀመሪያው ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት አትያዝ፣ አትቅመስ፣ አትንካ ለሚሉት ትዕዛዝ ስለ ምን ትገዛላችሁ? ይህ ትዕዛዝ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትህትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፤ ሆኖም ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም፡፡››
ምሁራኑ ይሄንን ጥቅስ ሲተረጉሙ፣ መፅሐፍ ቅዱስ የሚያዘው፣ ‹‹ራስን መግዛትን›› እንጂ ብህትውናን አይደለም፤ ምክንያቱም መፅሐፉ በሌላ ቦታ ላይ አካልን እንደ ስህተት ከማየት ይልቅ እንድንንከባከበውና ‹‹እግዚአብሔርንም እንድናከብርበት›› (1 ቆረ 6፡ 19) ያዛልና፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች መሰረት፤ ብህትውና የግል ፍላጎት እንጂ የእግዚአብሔር ፍላጎት አይደለም፡፡
ምንም እንኳን፣ ቆላሳይስን አጉልተው በሚፅፉ ምሁራን ዘንድ ‹‹ብህትውናን›› በጥብቅ ሥነ ምግባር በመተካት ‹‹ብህትውና መፅሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ የለውም›› በማለት ቢከራከሩም፣ ጀርመናዊው የሥነ ማህበረሰብ ተመራማሪ ማክስ ቬበር ግን፣ በዓለም ውስጥ ሆኖ ‹‹ራስን በመግዛት›› ላይ የተመሰረተውን ጥብቅ ሥነ ምግባር ሳይቀር ‹‹ዓለማዊ ብህትውና›› ይለዋል፡፡
በመሆኑም፣ እንደ ቬበር ያሉ የሥነ ማህበረሰብ ምሁራን፤ ብህትውናን ለሁለት ይከፍሉታል፣ ገዳማዊ ብህትውናና ዓለማዊ ብህትውና (Other-Worldly and Inner-Worldly (Secular) Asceticism) በማለት፡፡ በዚህ ትርጓሜ መሰረት፤ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 19፡16 ‹‹የገዳማዊ ብህትውና›› መነሻ ሲሆን፣ ማር 2፡ 18-28 እና ቆላሳይስ 2፡20 ደግሞ ‹‹የዓለማዊ ብህትውና›› መነሻ ነው፡፡
ዓለማዊው ብህትውና፤ ይሄንን ዓለም ጥሩም - መጥፎም ያልሆነ (Value-neutral) አድርጎ ያስበዋል፤ የሚያተኩረውም የሰው ምኞት (intention) ላይ ነው፡፡ አካልን፣ ዓለምንና ገንዘብን ጥሩም ሆነ መጥፎ የሚያደርጋቸው የሰው ሐሳብና ምኞት ነው። በመሆኑም፣ ከገዳማዊው ብህትውና በተቃራኒ፣ ዓለማዊው ብህትውና አካልን፣ ዓለምንና ሐብት ማከማቸትን አይቃወምም፡፡
መፅሐፍ ቅዱስ፤ ‹‹ብህትውና መፅሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አለውም - የለውምም›› ብለው ለሚከራከሩ ሰዎች በውስጡ እንደዚህ ዓይነት መከራከሪያ ጥቅሶችን መያዙ፣ ስለ ክርስትና ሦስት ነገሮችን እንድንደመድም ያደርገናል፡፡ የመጀመሪያው፣ ሃይማኖቱ በየዘመኑ ከሚነሱ ተለዋዋጭ የማህበረ-ኢኮኖሚ ክስተቶች ጋር ራሱን እያስማማ እንዲኖር አድርጎታል፡፡
ምንም እንኳ፣ የማቴዎስ ወንጌል 19፡16፤ በመካከለኛው ዘመን ለነበረው ፊውዳላዊ የማህበረ-ኢኮኖሚ ሁኔታ መንፈሳዊ መሰረትን የሰጠ ቢሆንም፣ ይህ ጥቅስ ግን ሐብት በማከማቸት ለተመሰረተው ካፒታሊዝም አይስማማም፡፡ በመሆኑም፣ የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ሲለወጥ፣ ማር 2፡ 18-28 እና ቆላሳይስ 2፡20 የማቴዎስ ወንጌል 19፡16ን በመተካት፣ ለአዲሱ የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መንፈሳዊ መሰረት መሆን ችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ክርስትና በፊውዳሊዝምም ሆነ በካፒታሊዝም ውስጥ ተቀባይና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ መቀጠል ችሏል፡፡
ሁለተኛው ደግው፣ ምንም እንኳ፣ ከላይ በጠቀስነው ምክንያት የተነሳ ክርስትና በየዘመኑ ከሚነሱ ተለዋዋጭ የማህበረ-ኢኮኖሚ ክስተቶች ጋር ራሱን እያስማማ መኖር ቢችልም፣ ይህ ችሎታ የመጣው ግን ሃይማኖቱ ራሱን ከመከፋፈል ነው፡፡ የወንጌላውያን ክርስትና በ16ኛው ክ/ዘ ከካቶሊኩ የተገነጠለው ለአዲሱ ካፒታሊስታዊ የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መንፈሳዊ መሰረት ለመስጠት ነው፡፡ በመሆኑም፣ የሰው ልጅ ነባራዊ ሁኔታዎች በተቀየሩ ቁጥር ክርስትናም ይበልጥ እየተከፋፈለ ይሄዳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የክርስትና ዓይነቶች ሊፈጠሩ የቻሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ሦስተኛው መደምደሚያ ደግሞ፣ መፅሐፍ ቅዱስ እንደ ብህትውና ባሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩና እርስበርስ የሚጣረሱ ጥቅሶችን የያዘ ከሆነ፣ ከሁለቱ ጥቅሶች ውስጥ አንደኛውን እንድንመርጥ የሚያደርገን ምንድን ነው? ወደሚለው ጥያቄ ያመራናል፡፡ የዚህ ጥያቄ መልሱ ‹‹ተርጓሚው የሚኖርበት የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ነው›› የሚል ነው፡፡ አባ እንጦንስ፤ ከቆላሳይስ 2፡20 ይልቅ፣ ማቴዎስ 19፡16ን እንዲመርጡ ያደረጋቸው፣ ወይም ደግሞ ማርቲን ሉተር፤ከማቴዎስ 19፡16 ይልቅ ቆላሳይስ 2፡20ን እንዲመርጥ ያደረገው ሁለቱም የነበሩበት የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው ነው። በመሆኑም፣ በተርጓሚዎቹ ውስጥ የሚንፀባረቀው መፅሐፉ የተሸከመው ሐሳብ ሳይሆን፣ ተርጓሚዎቹ የሚኖሩበት የማህበረ-ኢኮኖሚያዊው ፍላጎት ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ብሩህ ዓለምነህ፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን የኢትዮጵያ ፍልስፍና ደራሲ ነው፡፡ በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1202 times