Saturday, 15 December 2018 15:55

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

“ጊዜ የማያዳላ ዳኛ ነው!”
                 
    አንድ ሰውዬ ነበር፡፡ በአካል፣ በመንፈስ የፈረጠመ፡፡…የሚያመልከውን አምላክ ምስል በትልቅ የመስታወት ፍሬም አድርጎ ከቤቱ ግድግዳ ላይ ሰቅሎታል፡፡ “አባቴ አየ” እያለ ይጠራዋል፡፡ … ያነጋግረዋል፡፡ “አየ” ግን ቃል አይወጣውም፡፡ ሆኖም ሰውየው በቀን ተቀን ውሎው የሚስተውን የእምነት ህግ ልክ እንደ ኮምፒውተርና ስክሪን መስታወቱ በመፃፍ ያሳየዋል፡፡ ለምሳሌ ሰውየው በቀን ውሎው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ዋሽቶ ከነበር … “መዋሸት ሐጢአት መሆኑን ዘነጋኸውን?” ወይም ከሰው ጋር ተጣልቶ ከነበር “ቀኝህን ሲመቱህ ግራህን መስጠት እንዳለብህ ተሳነህን?” የሚል ፅሁፍ ብቅ ይላል፡፡ ሰውየውም ስህተቱን አይደጋግምም፡፡
“አየ” የሚለውን ስም ያወጣለት “አለህምም፣ የለህምም” ለማለት ነው፡፡… ሁለቱን ቃላት እርስ በርስ በማጣፋት…አለህምም÷የለህምም = አየ፡፡
ሰውየው ባዳበረው ሰብዕና መሠረት፤ሌሎችን ሰዎች ይወዳቸዋል፣ ያከብራቸዋል፣ ያግዛቸዋል፡፡ ነገር ግን አብሯቸው አይውልም፣ አብሯቸው አይዋሽም፣ አብሯቸው አያማም (Loving but too detached ዓይነት)፡፡ … ይኸ ባህሪው አልተወደደለትም፡፡ “እሱ ማነው? … ከኛ በምን ይለያል?... ልክ እናስገባዋለን” በማለት አሴሩ፡፡ ምቀኛ አታሳጣኝ እንዲሉ፡፡ ሁለት ወንበዴዎችን ገዝተው አሰማሩበት፡፡ ወንበዴዎቹ ከጭለማ ስፍራ ሸምቀው ተናነቁት፡፡ አልቻሉትም፡፡ … በገዛ መሳሪያቸው አስቀራቸው፡፡ ነገር ግን አዘነ፡፡ “የፈለጉትን ቢያደርጉኝም መቀበል ነበረብኝ” ሲል ተፀፀተ፡፡ ወደ ቤት ለመግባት ፈራ፡፡ አየ፤ “የገነት በር ተደረገመ” ብሎ ሲፅፍበት ታየው። … እንዳሰበውም አልቀረም፡፡ በሩን ከመክፈቱ መስታወቱ ቦግ አለ፡፡ … ፅሁፉ ግን የለም፡፡
***
ካልቀበጡ አይዘሉ፣ ካልዘለሉ አይወድቁ፣ ካልወደቁ አይሰበሩ እንደምንለው፣ አውሮፓውያኑ “Rough play will end in tears” ይላሉ፡፡ በህግና ስርዓት የማይመራ ጨዋታ፣ መጨረሻው አያምርም እንደ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በእግር ኳስ ህግ፣ከተፎካካሪህ የበለጠ እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ጨዋታ ብትጫወትም፣ተፎካካሪህ የበለጠ ጎል ካገባ አሸናፊው እሱ ነው፡፡ ነጥብ የሚያዝልህ በምታስቆጥረው ጎል እንጂ ጥሩ በመጫወትህ አይደለም። ተሳስተህ ራስህ ግብ ላይ ብታገባ እንኳ የሚቆጠረው ለሱ ነው፡፡ የምትዳኘው ወደህና ፈቅደህ በመረጥከው ህግ (Rule of the game) ስለሆነ ቅር ሊልህ አይገባም። ድርድር የለውማ!!
ሕገ መንግሥትና ዝርዝር ድንጋጌዎች በማን አለብኝነት ጥሰህ፣ በዜጎች ላይ ለፈፀምካቸው ወንጀሎችና በደሎች “ለምን እጠየቃለሁ?” የምትል ከሆነ፣ “አንተ ማነህ?” ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ በስልጣን መዝረፍ፣ በጉልበት ማስገደድ፣ በቀልና ማስፈራራት---ዘላቂነት እንደማይኖራቸው አስቀድመህ ማወቅ ነበረብህ። በጉዞህ መጨረሻ ቲኬቶቹ ተቀደው፣ወደ ቆሻሻ መጣያ መወርወራቸው፣አለማሰብህ ዋናው ጥፋትህ ነው - ፍቅርና ወዳጅነት፣ ዝናም ቢሆን አላፊ ጠፊ፣ እንደ ስጋህ ረጋፊ መሆኑን፡፡
“Money, Position, fame, love, revenge are all of little consequences, and when the tickets are collected at the end of the ride, they are tossed in the bin marked FAILER.”
በማለት የፃፈልህ ጀምስ ሚሽነር ነው፡፡
ወዳጄ፡-“ከሃሳቦች ሁሉ እሚከፋው ማሰብ አለመፈለግ ነው” ይላሉ ሊቃውንት፤የሃሳብ የመጨረሻ ድርጊት፣ የምርጫ መጀመሪያም ሃሳብ ስለሆነ፡፡ ቅን ሃሳብ ወደ ገነት ሲያሳፍረን፣ተንኮላችን ወደ ተቃራኒው ያስጉዘናል፡፡ ሃሳብ አእምሮን ይገዛል፣ ልብን ይመራል፣ ባህሪን ያንፃል፣ ሩህሩህነትና ሰብዓዊነትንም ያጎናጽፋል፡፡ ለዚህ ነው The most wit thought is refusal to think” እንዲሉ ማለታቸው፡፡ (ያላወቁ አለቁ!)
ወዳጄ፡- እኔ እንደሚመስለኝ፤ለአስተሳሰብ ድህነትና ለሞራል ዝቅጠት የዳረገን ሥርዓቱና የስርዓቱ መሪዎች፣ ትውልድን ለማዳከም አመቻችተው ያደራጇቸውና ሲጠቀሙባቸው የነበሩት በዋናነት እንደ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ቤተ ክህነት፣ ሚዲያና መሰል ተቋማት ናቸው። … የተለያዩ የፖለቲካ አደረጃጀቶች፣ በደህንነት ስም የሚንቀሳቀሱ የአፈናና የውንብድና ተቋማት እንዳሉ ሆነው፡፡
ወዳጄ፡- አገራችን በወደቀችበት ጭለማ ውስጥ ቀደም ብለው ያለፉና ዛሬ ሰማይ ሊነካ የተቃረበ ስልጣኔ ላይ የደረሱ አገራት አያሌ ናቸው፡፡ የሚገርመው ያኔ፣ ስልጣኔ ኋላቀር በነበረበት .. የጤና፣ ትራንስፖርት፣ ምግብና መጠለያ ልማት ባልነበረበት፣ የኮምፒውተርና የሞባይል ስልክ ቴክኖሎጂ ባልታሰበበት ጊዜ ነበር፡፡ የኛ ደግሞ ዓለም በጠበበችበትና በያንዳንዱ ሰው መዳፍ ላይ መቀመጥ በቻለችበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1518 የደች ካቶሎካዊ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ የነበረው ኤራስመስ፤ (ከ1471-84) የሮማ ጳጳስ ለነበሩት፣ የሲስቲን ቻፕልን በብዙ ገንዘብ አስገንብተው በስማቸው እንዲሰየም ያደረጉት፣ አባ ሲክፀስ አራተኛ፣ ከ1492-1503 በወንበሩ የነበሩት ፓፕ አሌክስንዳር አምስተኛና ከ1503-13 እሳቸውን ተክተው በመንበሩ የተሰየሙት የእህታቸው ልጅ ጁሊየስ ሁለተኛን “አላማዊ ጳጳሳት” በማለት አጋልጧቸዋል፡፡ ጳጳሳቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ለእህት ወንድሞቸው ልጆችና ለዘመዶቻቸው ልጆች መበልፀጊያ እንዳዋሉት፣ የካህን አክሊላቸው የጣለባቸውን አደራ ችላ ብለው በፖለቲካ፣ አንዳንዴም በጥበብ ጉዳዮች ተጠምደው እንደነበር “The shamelessness of the Roman wria has reached its climax” በሚለው መፅሃፍ ዘርዝሮታል፡፡
ወዳጄ፡- የቤተ ክህነት ሰዎች መካሪና አስተማሪ መሆን ግዴታቸው ሆኖ ሳለ፣ ቤተሰብዓዊ ትስስሮሽ ባለው የፖለቲካና የሙስና ቅሌቶች መቆሸሻቸው፣ እግዜርን የመግደል ያህል ይቆጠራል የሚሉ ሊቃውንት ጥቂት አይደሉም፡፡ የታሪክና የፍልስፍና ሊቅ የሆነው ታላቁ ዊል ዱረንት፤“የስልጣኔ ታሪክ (History of civilization) በሚለው መጽሃፉ፡ … “ብዙዎቹ ካህናትና የግዜር መልዕክተኛ ተብዬዎች፣ገንዘብ ከመሰብሰብ በስተቀር ፍሬ በሚሰጥ መንፈሳዊ ስራ አልተሰማሩም” ይልና በመቀጠል፤
“…ለክርስትና ገንዘብ፣ ለጋብቻ ገንዘብ፣ ኑዛዜ ለመቀበል ገንዘብ፣ ለፍታት ገንዘብ፣ ለቀብር ገንዘብ።… ያለ ገንዘብ ደወል አይደውልም፡፡ የመንግሥተ ሰማያት በር የሚከፈተው ገንዘብ መክፈል ለሚችሉ ብቻ ይመስለኛል።” በማለት ያብራራዋል፡፡… “ቤተ መቅደሴን መሸቀጫ አደረጋችኋት!”
***
ወደ ጭውውታችን እንመለስ፡- ወንበዴዎቹ ሰውየውን እንዳነቁት፣ በደመ ነፍስ እንደታገላቸውና በገዛ መሳሪያቸው ጭጭ እንዳሰኛቸው፣ የመጣውን መቀበል ነበረብኝ ብሎ መጸጸቱን፣ የ“አየ”ን ፊት ለማየት እንደፈራና የሚፅፍለትን እንደገመተ ተጨዋውተናል፡፡ ነገሩ እንደጠበቀው አልሆነም፡፡ በሩን እንደከፈተ፤ ቤቱ በታላቅ ብርሃን ነበር የተሞላው፡፡ እየተርበተበተ ይቅርታ ለመጠየቅ፤ “አባቴ አየ” ብሎ ቀና ሲል … መኖሪያው፤”ብራቮ! ብራቮ! ብራቮ!” በሚል የድምፅ ማዕበል ተናወጠ!!
ወዳጄ፡- ፍትሃዊ ስትሆን እንኳን ሰው፣ እግዜር ያጨበጭብልሃል፡፡ በነገራችን ላይ ጊዜ የማያዳላ ዳኛ ነው፤ (Time is the very best arbiter!) በማለት የፃፈልንን ታስታውሳለህ? … ዶስቶቪስኪ ካልከኝ፣ ፅዋን አንስቻለሁ።
ሠላም!!
ከአዘጋጁ፡- ባለፈው ሳምንት በዚሁ ዓምድ፤ “ሂትለር” ከሚለው ቀጥሎ “እንደሚያስበው አይደለም” የሚለው ቃል በስህተት የተዘለለ ሲሆን “ሂትለር እንደሚያስበው አይደለም” ተብሎ እንዲነበብ ከይቅርታ ጋር  እንጠይቃለን።   

Read 758 times