Saturday, 15 December 2018 16:08

ቀታሪ ግጥም ( ቁጥር፡-2)

Written by  አንለይ ጥላሁን ምትኩ (ከሳውዝ ዌስት አካዳሚ)
Rate this item
(4 votes)

  ግጥም ነፍስን የሚኮረኩር የደደረ ስሜትና  ሀሳብ በምጡቅምናብ ተከሽኖ የሚቀርብበት የጥበብ ውጤት ነው፡፡ ህመምና እርካታ፣ ብሶትና ደስታ እኩል የሚሞሸሩበት ...የተንተከተከ የስሜት ማግ ነው፡፡ገጣሚ የሚተክለው የእውነት ምሰሶ ነው፤ ህይወት የተሸከመ፡፡ ይህ ደግሞ በግለሰቡ መጠበ ብልክ ይወሰናል፡፡ ለዚህ መሠለኝ ሠለሞን ደሬሳ፤ "የግጥም ፈንታ የሰውን ልጅ ግላዊ መፍጨርጨር ከዚህ ዓለም ችላ ባይነት ጋር አያይዞ ማብላላት ይመስለኛል። ማብላላት፣ ማፋጨት፡፡ እያፋጩ ተቃራኒዎችን ማጣመድ፣ ተመሣሣዮችን ማለያየት፡፡ ከግጭታቸው ለአንዳፍታ እንደ በራሪ ኮከብ የሚታይ ግልጥ መፍትሄ ማዋለድ፡፡" ነው የሚለን፡፡ ለጥበቡ አንዳች  ተግባራዊ ፋይዳ በመስጠት የኑሮ ብልሀት ያሸክመዋል፡፡ ልክ እንደ ደበበ ሰይፉ "ጊዜ በረርክ በረርክ" አይነት፡፡
ጊዜ በረርክ በረርክ
ጊዜ በረርክ በረርክ
ግና ምን አተረፍክ
ግና ምን አጎደልክ?
 ሞትን አላሸነፍክ
 ሕይወትን አልገደልክ፡፡
***
1982
(ደበበ ሰይፉ÷ ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ(የብርሃን ፍቅር)÷ቅፅ ፪÷1992÷ ገፅ 96)
ደበበ የጊዜን የመኖር ፋይዳ አሠላስሎ ቢያመው፣ ቢከነክነው በፌዝ ተሳለቀበት፡፡ የጊዜን መረብ በጣጠሰው፡፡ በሞትና በህይወት መሀል አቁሞ ባይተዋር አደረገው፤ጊዜን፡፡ምንጊዜንብቻ! እኛንም ባይተዋር አድርጎ አስደመመን እንጂ፡፡ ሩሲያዊያን፤ "ግጥም ነገሩን በነገር በመንቀፍ (በመገልበጥ) ባይተዋር ሲያደርግ ነው--የግጥም ተግባር"  የሚሉት ለዚህ ሳይሆን ይቀራል?!
[ቀታሪ÷ ስሩ ቀተረ ነው፡፡ ቀተረ÷ እኩል ለመሆን ተከታተለ÷ ተቀታተረ÷ ተመለካከተ÷ ተወዳደረ÷ ተተካከለ ÷ ተመዛዘነ÷ ተፈካከረ÷ ተፈላለገ (አስ) ከባለ ቀትር አትቀታተር፡፡ (ከሣቴ ብርሃን ተሠማ÷ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት÷ ገፅ፫፻፹፬÷2008 ዓ.ም) ግጥም ምንጬ ህይወት ነውና (ቋንቋው (መንገዱ) አዕምሮን፣ ስሜቱ ልብንና መልዕክቱ ልቦናን ይቀትራል፡፡) አዕምሮን፣ ልቦናንና ልብን የቀተረ ከምናብ የሚፈለቀቅ የፀነነ የጥበብ ውጤት ነው፡፡መቀተሩ ከልማድ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው፡፡ ፈጠራ ደግሞ ልማድን መሻገር ይጠይቃል፡፡ ከልማድ ያልተሻገረ ግጥም ነፃ አያወጣም። አይታኘክም-የተመጠጠነውና፡፡]
* * *
ዘላለማቸው
አንተም የዘላለሙ!
እንዳ'ማኒው --- እንደ እምነቱ÷
አዛዡ --- ለየሕይወቱ ÷
ለግቡ --- ወይለውድቀቱ÷
አንተነህሲሉ --- ያማሉ÷
ሰዎች --- ሁሉ፡፡
ካለህታዲያ --- ጸጥ አትበል÷
እሳት የለውም --- ከሰል፤
ጸጥታው፡፡
ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ነው ውጊያ÷
የእሰጥ አገባ --- ፍልሚያ÷
ሰው መሆን የማያምረው÷
ማን ይገኛል? ካለስማነው ?
በጎዳና ላይ ትርምሱ ---
በ'ሰጥአገባው --- ያለፋይዳ÷
አምሮታቸው --- ሳይጎዳ÷
በሰዉ መሆን --- ምኞታቸው÷
"ወዴቱ" --- ለጠፋባቸው÷
 እባክህ --- አሳያቸው፡፡
ለየአማኒው --- እንደምነታቸው÷
 እባክህ --- ንገራቸው÷
 ዘላለሙ --- ዘላለማቸው፡፡
***
  26--6--82
(ወንድዬ አሊ፣ ወፌ ቆመች፣ ገፅ 38፣ ፲፱፻፹፬ዓ.ም)
"እውነት የክት ልብሷን ለብሳ ስትታይ ግጥም ትባላለች" ይላሉ፤ ፈረንሳዮች፡፡ የህይወትን ሀቅ በእውነት ሀሩር አዝላ ለአደባባይ፣ ለዘመን ቃፊር መብቃቷን ስለታዘቡ፡፡
ወንድዬ አሊ፤ በ"ዘላለማቸው"  ግጥም ያደረገው ይኸው ነው፡፡
ካለህ ታዲያ --- ጸጥ አትበል÷
እሳት የለውም --- ከሰል፤
ጸጥታው፡፡
በማለት አስረግጦ ያሳስባል-- ተራኪው፤ የሰው ልጅ የኑሮ፣ የህልውና፣ የዘላለማዊነት ምልከታ ጥያቄ ውስጥ ስለወደቀበት፡፡ ይህ ማህበራዊም ሆነ፣ ግለሰባዊ ባይተዋርነት መሠረቱ ጥልቅ ትዝብት ነው፡፡"ካለህ ታዲያ---ጸጥ አትበል" ፍርድ የናፈቀ፣ የተብሰከሰከ ስሜት፣ ባይተዋርነት ያጠለሸው፣ የተቀታተረ ምልከታ  (ህመም) ነው፡፡ የለህማ ከመንበሩ'ን-- ያስታውሰናል፡፡እግዜርን ሳይጨምር የቆጠረ፣ ሁልጊዜ ሲቆጥር ይኖራል ---- እንደ ማለት ነው፡፡ በአንድ ወቅት የወሎ ገበሬ (በሰፈራ ምክንያት) የደረሰበትን በደል፣ምሬት፤
"ቀና ብዬ ባየው  ሰማዩ ቀለለኝ፣
አንተንም እንደኛ ሰፈራ ወሰዱህ መሰለኝ"
በማለትየእውነት ( የሀቅ) ምንነትን ይሞግታል። ጉዳዩ ''መኖር ወይ ስአለመኖር" --ይመስላል፡፡ፍርድ፣ፍትህ የጎደላቸው ነፍሶች ጩኸት ነው፡፡ምሬቱ የሚፈጥረው የስሜት ረመጥ፣ የህልውናን ጉዳይ ትርጉም አሳጥቶ፣የአምላካቸውን (የፈጣሪን)ህልው መልክ ይፈታተናል፡፡ይቀትራል፡፡ተራኪው --
"አንተነህ ሲሉ -- ያማሉ÷
ሰዎች -- ሁሉ ::"    በማለት ተጠያቂ  ያደርገዋል-"የዘላለሙ"ን፡፡ ከባለ ቀትር አትቀታተር--እዚህ ላይ አይሰራም፡፡ ተጠያቂነቱም የሚመነጨው ከመጀመሪያዎቹ ሦስት ስንኞች ነው፡፡   
"እንዳ'ማኒው-- እንደ እምነቱ ÷
አዛዡ-- ለየሕይወቱ ÷
ለግቡ--ወይ ለውድቀቱ ÷"  በማለት፡፡
በረቀቀ መንገድ የተገለፀ ነው፤ በምፀት፡፡ እንደ ሰው ልጅ ሁሉ ለፈፀመው ተግባር ሀላፊነት በመስጠት ተጠያቂ ያደርገዋል --ተራኪው -- ምንጭ በመጥቀስ /ሰዎች ---ሁሉ'ን/፡፡በርግጥ ፈጣሪን በተለያዩ ሰዋዊ ጉዳዮች ተጠያቂ ማድረግ በባህላችን የተለመደ ተግባር ነው፡፡
ለምሳሌ አንዲት ሴት ቀትሮ የያዛትን የሀዘን ስሜት
"ስትታመም ታማ ስትሞት ተቀበረች፣
አንተስ ትነሳ የኔና ትየታለች"  በማለት በፈጣሪና በሰው መካከል ያለው ግንኙነት ፋይዳው ጠልሽቶ አልታይሽ ቢላት፤ የእናቷን ህመም፣ መከራ፣ ሞት፣ ከንቱነት... ከእየሱስ (ከአብ ልጅ) ሞቶ ከመቀበሩ ጋር አነፃፀረችው፡፡ ትካዜ፣ ቁጣና ምፀት የተቀላቀለበት ነው። ምናልባትም "ሞቶ የመነሳቱ"  ጉዳይ ህልው የሆነው በእኛ እንጂ  እጣቸው አንድ ነው --ያለች ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሄር የማይሞት ሰው ነው፤ ሰው ደግሞ የሚሞት ፈጣሪ /አምላክ/ ነው -- ያለች ያክል ይሰማናል፡፡ ልክ፡- "ለየአማኒው -- እንደምነታቸው÷
እባክህ --- ንገራቸው ÷
ዘላለሙ --- ዘላለማቸው" በማለት ተራኪው እንደተሳለቀው ሁሉ፡፡ "ግጥም በሌለበት አለም መኖር አልፈልግም" ነበር ያለው፤ ገጣሚ ደረጀ በላይነህ። የግጥም ሀቅ ነፍስን ሰቅዞ ይይዛል፡፡ አያፈናፍንም፡፡ ቀታሪ ነው፡፡
በሰው መሆን -- ምኞታቸው÷
"ወዴቱ" ---  ለጠፋባቸው ÷
እባክህ --- አሳያቸው፡፡
በፊት ለፊቱ የተራኪውን ህመም፣ ልምምጥ ዘወር ስንል ሰውነት (ሰው መሆን) ተብትቦ ለያዛቸው ምስኪን ፍጥረታት የዘረጋኸውን ወጥመድ አንሳላቸው --አሽሙር የተሸከመ አርኬ ነው። ገጣሚ ክፍሌ አቦቸር፤ " ለኪነ-ጥበብ የሰገደል ብበምናባዊ ስርሰራ ጥልቀት በውስጡ ጠፍቶ ይሰነብታል" እንዳለው ሁሉ - ገጣሚ ወንድዬ አሊ፤ በ"ዘላለማቸው" ግጥም ዘላለማዊነትንና ከንቱነትን በፈጣሪ ጥላ ከልሎ፣ ጊዜን ተሻግሮ ከስረ መሰረቱ ላይ የህልውና ጥያቄ ያነሳል፡፡ አንዳች ረብ ያለው መልስ ይፈልጋል፡፡ በርግጥ ተራኪው ዳር ቆሞ የሚታዘብ እንጂ ውስጥ ገብቶ የሚብሰከሰክ አይደለም፡፡ ባየው፣ በሰማው የሚታመም፣ የሚብሰለሰልነው -- መልዓክ ይመስላል። የሰዎችን ስሜትም ሆነ ምኞት በጥልቀት ይረዳል፡፡ በራሱ የቆመ በመሆኑ በ"ዘላለማቸው" ስራ ይሳለቃል፡፡ ምላሽ ባለማግኘታቸው ይታመማል። የራዕያቸው ተጋሪ ይሆናል፡፡ ስለሆነም የሁሉ ነገር ምንጩ "ዘላለማቸው" ነው-- ባይ ነው፡፡ ራሳቸው ለራሳቸው  ኖረው አያውቁም፤ ያለ ይመስለኛል። ዓላማቸውን ተነጥቀዋል እንደማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ታምራት ጠባቂ አድርጓቸዋል፤ ደካሞች፡፡
ግጥሙ በቀላል ቋንቋ የተሰናኘ ቢሆንም የስንኞቹ አደራደር፣ የሀሳቡ ምጥቀት ልብ ይገዛል፡፡ የገዘፈ ሰዋዊ ጉዳይ የተሸከመ ነው፡፡ በሚነበብበት ወቅት የተወሰኑ ስንኞች ላይ የሚያንገዳግድ ቢመስልም ምጣኔው የተስተካከለ ነው፡፡ ዜማው ቀልብ ይይዛል።
የግጥሙ አሰነኛኘት ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮም ምሉዕነት ያላብሳል፡፡ እንቡጥ አመልማሎ ነው --  እያደር ይፈካል፡፡ ካጀማመሩ "አንተም የዘላለሙ!" በማለት "ዘላለማቸው"ን ይመክራል። ይገስፃል፡፡ መላ ይጠቁማል፡፡ እግር ሲደርስ፣ እግት ይመለስ--  ሆነ ነገሩ፡፡ ምናቡ እጅግ ዕሩቅ ነው፡፡ በአራት አንጓና በሰባት አርኬ የተማገረ ግጥም ነው። ሰለሞን ደሬሳ እንደሚለው፤ ግላዊ መፍጨርጨሩ አንዳች በራሪ ኮከብ ላይ ያደርሰናል፡፡ ሰላም፣ ሀሴት ያጎናፅፈናል፡፡ ኸረ ያቁነጠንጠናል ማለት ይቀላል፡፡ ቸር እንሰንብት!!
ከአዘጋጁ፡-ጸሐፊው በሳውዝ ዌስት አካዳሚ፣ የቋንቋ መምህር ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡-
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1721 times