Saturday, 15 December 2018 16:11

የእጅጋየሁ ሽባባው ‹‹ናፈቀኝ››

Written by  ደረጀ ኅብስቱ
Rate this item
(8 votes)

“-ጂጂ ዘማሪ እንጂ ዘፋኝ አትመስልም፤ ነገረ ስራዋ ሁሉ ወደ ውስጥ፣ ወደ ነፍስ ያደላል፡፡ በእርሷ ዘፈን ዝለል ዝለል የሚል ስሜት አይመጣልህም፤ ይልቁንም ጥልቅ ተመስጦ ይዞህ እብስ ይላል፡፡--”
   


    ጂጂ እያልን የምንጠራት የጎጃሟ ጉብል እጅጋየሁ ሽባባው፤ በርከት ያሉ መሳጭ ዘፈኖችን ጀባ ብላን፣ ለዓመታት ተሰውራብናለች፡፡ ‹‹ናፈቀኝ›› የሚለውን ዘፈኗን በየአጋጣሚው በሰማሁት ቁጥር እራሷ ጂጂ ትናፍቀኛለች፡፡ ምናልባት ናፍቆቷ ይቀልልኝ እንደሆነ ብዬ ‹‹ናፈቀኝ››ን እያንጎራጎርኩ ነው፡፡
‹‹ናፈቀኝ የኛ ቤት ጨዋታ፤
ቁርሱ ምሳ እራት የእምዬ ፈገግታ፤
የዘመድ አዝማዱ ጨዋታ ካካታ›› ትላለች ጂጂ፡፡
ኢትዮጵያዊ እሴት ከምንላቸው ነገሮች አንድ ተሰባስቦ፣ ተጠራርቶና ተጠባብቆ፣ በአንድነት ሞሰብ ሰርቶ ለማዕድ መቀመጥ ነው፤ እጅግ ግለኝነት በተጠናወተው የፈረንጆች ዓለም ያለችው ጂጂ፤ ከቤተሰብ ጋር ተሰባስቦ መመገብ ይናፍቃታል፤ የመመገብ ስርዓታችን ውስጥ ያለው ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› የምንለው በፈገግታ ታጅቦ መገባበዙና መጎራረሱም ይናፍቃል፡፡
‹‹የጠጁ ቤት ሌላ፤
የጠላው ቤት ሌላ፤
ፋሲካው አያልፍም ሰው ጠግቦ ሳይበላ፤
የመጣው እንግዳ ስክሮ ሳይጣላ›› የአመጋገብ ስርዓታችን ብቻ ሳይሆን የምግብ ማዘጋጃውና ከተመገቡ በኋላ ያለው ገቢርም ይናፍቃታል፡፡ ሰፋ ያለ ድግስ የሚደግስ ቤተሰብ ወይም የዘመድ አዝማዱ ቁጥር ብዙ የሆነበት ቤተሰብ፤ የጠላ ማጀት፣ የጠጅ ማጀት፣ የእንጀራ ማጀት ወዘተ-- በክፍል ከፋፍሎ ያዘጋጃል፡፡ ‹‹የጠላው ቤት ሌላ፤ የጠጁ ቤት ሌላ›› ትለናለች፡፡  ቤተሰቡም የተጠራውም ተጋባዥ እንብርቱ እስኪ ወጠር የመብላት የመጠጣት መብት አለው፤ በአገር ቤቱ ድግስ፤ ታዲያ ሆድ ያባውን ጌሾ ያወጣዋል እንደሚባለው ሁሉ፣ ለጸብ የሚዳርጉ ጥቃቅን ርእሶች አይጠፉም፡፡ ዛሬም ቢሆን ባህርዳር ከተማ የሚገኘው ድብ አንበሳ ሆቴላቸው የሚጥለው ጠጅ፤ እንኳን ጠጥተውት ልምድ የሌለውን ሰው፣ በሽታውም ያሰክራል፡፡ ምናልባትጂጂ፤ የልጅነት ትዝታዋ ጽኑ ሆኖባት ነው ለጠጁና ለጠላው፤ ለጸቡም ጭምር  በፍቅር የምታዜምለት፡፡
‹‹ናፈቀኝ ዛሬ በሰው ሃገር፣ ትዝታው ገደለኝ፤
የሰው ከብት እያየሁ፣ እያንገበገበኝ፤
ወሃ ጃሪ ወሃ ኮሉ፣ ያባቴን በሬዎች፣ የናቴን መሰሉኝ››
ለጂጂ ሁሉም ያገር ቤቱ ነገር ይናፍቃታል፣ ትዝታው ያንገበግባታል እናም ትዝታዋንና ናፍቆቷን ለመወጣት አካባቢዋን ስትቃኝ፣ በፈረንጅ ሃገር ሰው ሰው የሚሸት ለዛ ታጣለች፤ እናም የሰው ከብት እያየሁ እያንገበገበኝ  ትለናለች፡፡
ከአያቱ ጋር የሚያድግ ያገር ቤት ልጅ  ምሽት ላይ ከምድጃው ዳር ዳር ተኮልኩሎ፣ ተረት እየኮመኮመ ነውና የሚያድግ፣ ጂጂም የልጅነት ተረቶች ሁሉ ይናፍቋታል፡፡ ዘመድ አዝማዱ ሁሉ የራሱን ፍቅር ለመግለጽ እምዬዋ፣ አካላቴ፣ ጎኔ፣ ሽታዬ ወዘተ እያለ የተለያየ ስም ለአንድ ልጅ በመስጠት፣ ጽኑ ፍቅር እንዳለው ያሳውቃል፡፡ ስም የበዛለት ልጅም ያ ሁሉ ሰው ስለሚወደው መሆኑን ስለሚያውቅ፣ ፍንደቃና ቡረቃው አያሌ ነው፤ ለጂጂ ታዲያ ይሄም ይናፍቃታል። እጅጋየሁ ብሎ ለመጥራት በሚከብደው ማህበረሰብ ውስጥ መሆኗም፣ ስሟን አሳጥራ ጁጂ እንድትል አስገድዷታል፡፡  
‹‹ስም የለኝም፣ ስም የለኝም በቤቴ፤
አንዱ እምዬዋ ሲለኝ፣ አንዱ ሲለኝ አካላቴ፤
ጎኔ ሽታዬዋ ሲሉኝ፣
 በፍቅራቸው ሲጠሩኝ›› -- እያለች ታንጎራጉራለች።
‹‹ናፈቀኝ ጎረቤቱ፤
ናፈቀኝ ጨዋታው፤
ናፈቀኝ እህት ወንድሞቼ፤
አይጠፋም ትዝታው›› እንዲህ እያለች ስታንጎራጉር፣ በሌሊት ጨረቃዋ ያንቡሌ ትደንሳለች፤ ከዋክብት ተሰባስበውና ተሰልፈው፣ ሰለሜ ሰለሜ ሲደንሱ ልታዩ ትችላላችሁ፤ ምነው ቢሉ-- የጂጂ እንጉርጉሮ ስጋና ደምን ዘልቆ፣ የአጥንት መቅኖ ያንሸራሽረዋልና ነው፡፡ ጂጂ ዘማሪ እንጂ ዘፋኝ አትመስልም፤ ነገረ ስራዋ ሁሉ ወደ ውስጥ፣ ወደ ነፍስ ያደላል፡፡ በእርሷ ዘፈን ዝለል ዝለል የሚል ስሜት አይመጣልህም፤ ይልቁንም ጥልቅ ተመስጦ ይዞህ እብስ ይላል፡፡ ፀሐይ የጨነቀለት እያለች ስታቅራራ፣ ሰማዩና ደመናው ደግሞ አለምዬ ሶራ ሶራ እያሉ ሲደልቁ ልታይ ትችላለህ፡፡
የጂጂን ዘፈን ግጥሞች፣ ከእነዜማው ልብ እያሉ ካደመጡና ትንሽም ቢሆን ያገር ቤት ትዝታ ካለዎት፣ ነፍስና ስጋዎ እስኪላቀቁ ድረስ፣ መመሰጥዎ አይቀርም። የበሬዎችና  የላሞች ቁመና ከእነ ማቆላመጫ ስማቸው ይታወስዎታል፤ ያገር ቤቱ ሰው ኮልባ፣ ኮሉ፣ ጃሪ፣ ጎዶ ወዘተ-- እያለ የሚጠራቸውና በእንጉርጉሮ የሚያዜምላቸው ከብቶች ሁሉ ትዝ ይልዎታል። በባዕድ ሃገር፣ በስደት እየተንከራተቱ ከሆነ ደግሞ እጅግ ሲበዛ ስሜትዎትን ሊያጦዘው ይችላል፡፡ የጂጂ ናፈቀኝ፤ የራሱን አምሳል የሆነውን ሰው፣ በስደተኝነቱ ምክንያት የማያከብር፣ ሰው መሳይ ከብት ቢበዛባት ይመስለኛል--ጂጂም የሰው ከብት እያየሁ እያንገበገበኝ  የምትለን (ካገሩ የወጣ ሃገሩ እስኪመለስ፤ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ  እንድትል፤ አስቴር አወቀ)፡፡
‹‹ናፈቀኝ ደገኛው ቄስ ሞገስ፣
በፈረስ በበቅሎ ተጉዞ ሲመጣ፤
ለአመት በዓል ጨዋታ››
ደገኛው፣ ደጉ፣ ከደጎች ሃገር የሚኖረው ቄስ ሞገስ ይናፍቃታል ለጂጂ፡፡ ቆለኛ ከብቱን አስብቶ ጎትቶ፣ ከገበያ አምጥቶ ይሸጣል፤ ደገኛ ደግሞ ገዝቶ፣ አርዶ፣ በብልት በብልት አወራርዶ፣ ለምግብነት ያዘጋጀዋል፤ ይላሉ አባቶቻችን ስለ ደገኛ ሲያወሩ፡፡  ልክ እንደዚህ ሁሉ፤ ወንጌላዊያን ወንጌልን ቢጽፏትም፣ በምሳሌ በአንድምታ አብራርተው ያስፋፏት ደገኞች ናቸው። የጂጂ ቄስ ሞገስ፤ በፈረስ በበቅሎ ተጉዞ ነው፣ እነርሱ ቤት ላመትባል የሚመጣው፤ ከእንስሳት ሁሉ ጣዕምን በመለየት ፈረስን የሚያክለው የለም ይላሉ፤ አባቶች። ምነው ቢሉ-- አፈርና ገብስ ቀላቅለው ቢሰጡት፣ በከንፈሩ በምላሱ እየለየ ገብሰ ገብሱን ብቻ እየለየ ይመገባልና  ይሉናል፡፡ ‹‹ሰው ሁሉ እልል እያለ ሲቀበል በእምቢልታ›› ትለናለች፤ጂጂ- ለቄስ ሞገስ አገሬው የሚሰጠውን ክብርና አቀባበል እየናፈቀች፤ ለታላቅ ለካህን የአገሬው ሰው ያለውን አክብሮት በኪነቷ ውስጥ አስውባ፣ ለትውልድ እያስተላለፈች፡፡
ለማሳያ ያህል ዛሬ ‹‹ናፈቀኝን›› አነሳነው እንጂ የጂጂ ስራዎች በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ፣ ኢትዮጵያዊ እሴቶችንና ለዛዎችን ነው፣ በኪነት አስውባ - የከወነችልን፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች፤ ኪነት ስለ ኪን ብቻ ነው የሚመለከታት፤ የምን እሴት፣ የምን ትውልድ፣ የምን ትምህርት ነው? ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ኪነት አላማ ሊኖረው ይገባል፤ አገርን፣ ትውልድን፣ እሴትን ማቀፍ ይኖርበታል፤ የሚል እምነት አላቸው። የሁለቱንም ወገን ባስታረቀ መልኩ፣ የጂጂ ኪናዊ ስራዎች ተውበው የተሰሩ ናቸው፡፡ ‹‹ካህኔ›› የሚለው ስራዋን ብንመለከተው፣ ምናልባት አሁን ለማሳያነት ከመረጥኩት ‹‹ናፈቀኝ›› እጅግ ልቆ የተሰራ መሆኑን ለመረዳት ትንሽ ማዳመጥ ብቻ ይበቃናል፡፡ ለዛሬ ግን ራሷ ጂጂ ስለናፈቀችኝ፣ ትንሽ በናፈቀኝ ልቆዝም፡፡ በስዊዘርላንድ የሚገኘው Springer Nature የተሰኘው የምርምና ህትመት ተቋም ስለ ፍልስፍናና  ኪን እንዲህ ይለናል፡-
In the art world, the permanent drive for renewal has urged more and more artists to turn to philosophy to support their concepts of art. Artists have sometimes taken this approach to such extremes as to identify thinking about art with art itself, as has happened in conceptual art.  
ጂጂ ፍልስፍና ስለ መማሯ በእርግጠኝነት ደፍሮ ለመናገር ባልችልም፣ አንዳች የፍልስፍና መንፈስ በነፍስያዋ ወስጥ እንዳለ ግን በአስር ጣቴ እፈርማለሁ፤ ምነው ቢባል-- የጂጂ ዘፈን፤ እጅግ ተውቦ ባህልንም፣ የተለምዶ ጉዳዮችንም፣ አሊያም አንዳች የጥንት ነገር በግድ እንድናስበው ያደርገንና፣ በውስጣችንም በውስጡም ተመስጠን እንድንጠፋ ያደርገናል፡፡ ለኢትዮጵያ እንግዳ የሆነ ሰው እንኳ ቢሆን፣ ከጂጂ ዘፈኖች ጋር ለመዋሃድ እምብዛም እንደማይቸገር፣ የብዙ ጊዜ ትዝብታችን ነው፤ በተለይ ከሃገር ከወጣች በኋላ ሙዚቃዋን የከወነችው ከውጭ ሃገር ሰዎች ጋር ስለሆነ እነርሱ ምን ያህል ተመስጠው፣ አብረዋት እየከወኑ እንደሆነ ፣በቀላሉ መገንዘብ  ይቻላል፡፡
‹‹አንተየ በገና ጨዋታ፣ አይቆጡም ጌታ፤
ያገሩ ገነኛ ሆ! እያለ ሲመጣ
አባዬ ናፈቀኝ የከብቶቹ ጌታ
ሲባርክ ሲመርቅ የቤቱን ጨዋታ›› ትለናለች -- የለመድነውን ዓመት በአላዊ ጨዋታ በሚስረቀረቅ ዜማና ድምጽ አስውባ ስታስጨፍረን፡፡ በአገር ቤት ባህል እየጨፈሩ የሚገቡበት፣ የቤት ባለቤት፣ በልጆቹ ስም በከብቶቹ ስም፣ እያሞካሹ፣ የእነቡሬ ጌታ፣ የእነጎዶ ጌታ፣ የእነ ኮልባ ጌታ-- እያሉ መጨፈር ልማድ ነውና አባቷን፣ የከብቶቹ ጌታ ትለዋለች- ባለሃብት መሆኑን በገደምዳሜ ለመመስከር፡፡ ለእናቷም ቢሆን ሞቅ ያለ ምስጋና ትቸራቸዋለች፤ እንዲህ እያለች፡- ‹‹እምዬ እናት ዓለም፣ ጉልበትሽ ችሎታሽ፤ ይበልጣል ከሺህ ሰው፣ ያንን ሰው ሁሉ አጠገበው››
ዜማውን ለወጥ አድርጋ ጥልቅ ትዝታ ውስጥ በሚከት እንጉርጉሮ ያዜመችው ደግሞ ለታላቅ ወንድም ወይም መከታ ለሚሆን አጎት በሚለገስ ሙገሳ አይነት እንዲህ ትላለች፡- ‹‹የሽመል አጓራ አይችልም ገላዬ፤ የኔሆድ አኔዋ ናቁም ከኋላዬ፤ አያና ደማሙ አያና ደማሙ፤ አያና ደማሙ አያና ደማሙ›› የሽመል ምክቶሽ ጨዋታ ለልጅ እጅግ ያስፈራል፤ አንዱ ወደ ሌላኛው አናት ወዝ የጠገበ ዱላ ሲሰነዝር ፣ያኛውም በበኩሉ፤ አናቱን ለመከላከል የያዘውን እብድ የሚያክል ሽመል በሁለት እጁ ይዞ፣ ወደ ላይ ከፍ ሲያደርግ፤ አገር ቀውጢ ሲሆን አቧራው ሲድቆነቆን ለሚታዘብ፤ሰዎቹ አውሬ ይመስሉታል፡፡ ታዛቢው ልጅ ከሆነ ደግሞ ይርዳል፤ ይንቀጠቀጣል፤ እናም ታላቅ ወንድም ወይም አጎት ካለው፣ መሸሸጊያ ከለላ እንዲሆነው ሄዶ ይወሸቃል፤ እናም ጂጂ አይችልም ገላየ ና ቁም ከኋላዬ -ትላለች፡፡
‹‹አባይ ወዲያ ማዶ ትንሽ ግራር በቅላ፤
ልቤን ወሰደችው ከነስሩ ነቅላ›› -- ትለናለች ጂጂ፤የኛንም ልብ በችሎታዋ ከእነስሩ ነቅላ እየወሰደች- ይህቺ የአባይ ጉብል፡፡ ግራሯ ትንሽ ብትመስልም፣ የበቀለችበት ከወንዝ ማዶ ቢሆንም፣ ልብን ነቅላ የመውሰድ ችሎታ አላት፡፡ የአገር ቤት ጎረምሳ በኮረዳ ፍቅር ልቡ ሲነሆልልበት፣ እርሻው አልታረስ፣ ከብቶች አልጠበቅ ሲሉት፣ የሚያንጎራጉራት የህዝብ ግጥም ትመስለኛለች- ጂጃችን አስውባ የምታዜምልን፡፡ አስማተኛዋ አቀንቃኝ  ወዴት ነው ያለሽው? ባለሽበት ቦታ ሁሉ የኢትዮጵያ አምላክ አለሁ ይበልሽ!!

Read 2747 times