Saturday, 22 December 2018 08:09

አይካ አዲስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ስራ አቆመ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

በቱርካውያን ባለሃብቶች በሠበታ ከተማ የተቋቋመው አይካ አዲስ የጨርታ ጨርቅ ፋብሪካ ከትናንት ጀምሮ ሥራ ማቆሙን ለሠራተኞቹ አስታወቀ፡፡
4000 (አራት ሺ) የሚሆኑ የፋብሪካው ሠራተኞች ከረብዕ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ላይ የሠነበቱ ሲሆን አርብ ጠዋት ወደ ፋብሪካው ሲመለሱ በማስታወቂያ ቦርድ ላይ “ሳይሰራ የሚከፈል ደሞዝ ስለሌለ፣ ፋብሪካው ለጊዜው ስራ አቁሟል” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎ፣ ሠራተኛው እንዲመለስ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፋብሪካው ባለቤት ቱሪካዊው ዩሱፍ ሃይዲኒ ፋብሪካውን ጥለው ከተሠወሩ ከ6 ወር በላይ መሆኑን የገለፁት ሠራተኞች፤ “ፋብሪካውን የሚያስተዳድረው” ልማት ባንክ ነው የሚል መረጃ እንደደረሳቸው፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ፋብሪካውን የሚያስተዳድረው አካል በውል እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡
ሠራተኛው የስራ ማቆም አድማ ላይ የሰነበተውም “የፋብሪካው የወደፊት እጣ ፈንታና የስራ ዋስትናችን ይረጋገጥልን” በሚል ጥያቄ እንደነበር የገለፁት ሠራተኞቹ፤ ከአርብ ጀምሮ ግን ፋብሪካው ላልተወሰነ ጊዜ ስራ ማቆሙ በማስታወቂያ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል፡፡
ላለፉት 6 ወራት የፋብሪካው መደበኛ ስራ ተቀዛቅዞ መቆየቱን የጠቆሙት ሠራተኞቹ፤ ይሁን እንጂ ሠራተኛው የሚያገኘው ወርሃዊ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም አልተቋረጠም ነበር ብለዋል፡፡

Read 12063 times