Sunday, 23 December 2018 00:00

ከከረረ ሙግትና ተቃውሞ በኋላ በአብላጫ ድምጽ የፀደቀው አዋጅ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(8 votes)



- “አዋጁን ማጽደቅ ልንወጣ የማንችለው አደገኛ ችግር ውስጥ ያስገባናል”
- “ህገመንግስቱን ሽፋን አድርገን ስንሰራ የኖርነውን ሃጢያት የምንታጠብበት አዋጅ ነው”
- አዋጁ በ33 የተቃውሞ ድምፅ፣ በአራት ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ ድጋፍ ፀድቋል
• የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱን ያወዛገበው የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በአብላጫ
ድምጽ ፀደቀ፡፡ 33 የምክር ቤቱ አባላት የአዋጁንመጽደቅ የተቃወሙት ሲሆን አራቱ ደግሞ ድምጽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከትላንት በስቲያ ሃሙስ ባካሄደው ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ቀርቦ የነበረውን የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ መርቶት ነበር፡፡
ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር ካጠኑና ለሣምንታት ከተወያዩ በኋላ ማሟላት ይገባዋል ብለው ያመኑባቸውን ጉዳዮች በማካተት ለምክር ቤቱ የውሣኔ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ለውሣኔ በቀረበው በዚህ የማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ውዝግብና ክርክር አካሂደውበታል፡፡
የትግራይ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ “የማቋቋሚያ አዋጁ ህገ መንግስቱን የጣሰ፣ የህዝቦችን ልዕልና የሚያሳንስ፤ የህዝቦችን የስልጣን ባለቤትነት የሚነፍግ በመሆኑ ሊፀድቅ አይገባም” በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ ይህንን የኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ማጽደቅ ማለት አገሪቱን ልትወጣው ወደማትችለው አስቸጋሪ ሁኔታ መጨመር ነው” ያሉት ከትግራይ ክልል  የምክር ቤት አባል አቶ አፅብአ ግርማይ፤ አዋጁ በመጽደቁ ሳቢያ ሊመጣ የሚችለውን ችግር ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው፤ የክልሎች ፍላጐት መሆኑ ባልተጤነበትና ክልሎች ባልተሳተፉበት ሁኔታ ተወያይቶ ይህንን አይነት አዋጅ ማጽደቁ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው፤ “አዋጁን ካፀደቁ በኋላ ምነው ባላደረኩት ኖሮ ከሚል ፀፀት ለመጠበቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
“አዋጁን ማጽደቁ ቀላል ሊሆን ይችላል የሚያመጣው መዘዝ ግን በቀላሉ የምንላቀቀው አይሆንም፡፡ እኛ የምክር ቤት አባል ሆነን በህዝብ ተመርጠን ስንመጣ ህገ መንግስቱን የመጠበቅና የማስከበር ኃላፊነት ተቀብለናል፡፡ ህገ መንግስቱ ሲፈርስ ቆመን የምናይበት ሁኔታ የለም፤ የአዋጁን መጽደቅ አጥብቀን እንቃወማለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዋጁ ሊፀድቅ አይገባም የሚለውን ሃሳብ የሚደግፉ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት የመቃወሚያ ሃሳባቸውን ለም/ቤቱ በማቅረብ የአዋጁ መጽደቅ የሚያስከትለው መዘዝ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል። “ከዚህ አዋጅ ጀርባ አንድ ነገር አለ፡፡ የትኛውም ክልል ጥያቄ ባላነሳበትና አጥኑልኝ ብሎ ባልጠየቀበት ሁኔታ፣ አጥኚ ኮሚቴ እናቋቁማለን ብሎ ማቋቋሚያ አዋጅ ማጽደቁ፣ ከጀርባው የታሰበ ሌላ ነገር መኖሩን የሚያመለክት ነው፣ ይህ እንዲሆን ደግሞ መፍቀድ የለብንም” ብለዋል፡፡
የትግራይ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑ 10 የምክር ቤቱ አባላት “አዋጁ መጽደቅ የለበትም፣፤አዋጁ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው፤ የሚያስከትለው ጦስም ቀላል አይደለም” የሚል ሃሳብ የያዘ የምክር ቤቱ አባላት የተፈራረሙበት ባለ 23 ገጽ አስተያየት ቀደም ብለው ለም/ቤቱ አቅርበው ነበር፡፡
የማቋቋሚያ አዋጁ አሁን አገሪቷ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ በመሆኑ ጊዜ ሳይሰጠው ሊፀድቅ ይገባል በሚል ሃሳብ የተከራከሩ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፤ ከየትኛውም ወገን የሚመጣ ዛቻና ማስፈራሪያ ሳይበግረንና ሳንዘናጋ አዋጁን ማጽደቅ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
“ምክር ቤቱ በዚህ መጠንና ሁኔታ አንድ አዋጅ መጽደቅ የለበትም ብሎ የተከራከረበት አጋጣሚ የለም” ያሉት አንድ የምክር ቤት አባል፤ “ከዚህ ቀደም የህዝቦችን መብት የሚጥሱ አዋጆች በተደጋጋሚ ሲፀድቁ በአስቸኳይ ይፀደቅ እያለ ሲያሳልፍ ኖሯል። ይህ የህዝቦችን መብት የሚያስከብር አዋጅ ለማውጣት ግን ይህን ያህል ችግር የሆነበት ምክንያት አልገባንም” ብለዋል፡፡ “ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ሰዎች ሲኮላሹ፣ ሲገረፉና ሲሰቃዩ እያየ ዝም ከማለት በስተቀር ህገ መንግስቱ ተጣሰ ያለበት አጋጣሚ አልነበረም” ያሉት እኚሁ አባል፤ “የህዝቡን ችግርና የሰላም ማጣቱን መንስኤ አጣርቶ የመፍትሔ ሃሳብ የሚያቀርብ ኮሚሽን ይቋቋም ሲባል ይህን ያህል ተቃውሞ ማሰማቱ ያስተዛዝበናል” ብለዋል፡፡
ይህ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ለመካስ የመጣና በህገ መንግስቱ ላይ የተሰጣቸው መብቶች መከበራቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ አዋጅ ነው ያሉት ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል፤ “ህገመንግስቱን ሽፋን አድርገን ስንሰራ የኖርነውን ሃጢያት፣ የምንታጠብበት፣ ራሳችንን ወደ ትክክለኛው መስመር የምናስገባበት አዋጅ ነው” ብለዋል፡፡
የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በቀረቡት የድጋፍና የተቃውሞ ሃሳቦች ላይ በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደተናገሩት፤ የሚወጡ አዋጆች ሁሉንም ወገኖች በእኩል ያስደስታሉ የሚል ሃሳብ እንደሌላቸው ጠቅሰው፤ የሚወጡ አዋጆች በአንድ አካባቢ ወይም በአንድ ክልል ተቀባይነት አላገኘም ተብለው ውድቅ እንዲሆኑ የሚደረግበት ምክንያት የለም ብለዋል፡፡ አያይዘውም፤ “ይህ ፓርላማ ምን ሲሰራ፣ ምን አይነት ህጐችን ሲያፀድቅ እንደኖረ የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ አንድን ሰው ብቻ ትኩረት አድርጐ፣ ያንን ሰው ለመያዝና ለማሰር የሚያስችሉ የፕሬዚዳንቱን መብትና ጥቅም የሚያስቀሩ ህጐች ሁሉ ወጥተው የፀደቁት በዚህ ምክር ቤት ነው፡፡ ሁላችንም ምን ስንሰራ እንደኖርን ወደ ኋላ መለስ ብለን ማሰብና ማስታወስ ይገባናል” ብለዋል - አቶ ተስፋዬ፡፡
“እኔ እንደውም ይህ ፓርላማ በይፋ ህዝቡን ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብዬ ነው የማምነው፤ የምንሰራውንና የምንናገረውን ሁሉ እያሰብንበትና ራሳችንን ከታሪክ ወቀሳ እያፀዳን ቢሆን ጥሩ ነው” ያሉት ሰብሳቢው፤ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነን በዚህ ምክር ቤት ወንበር ላይ ስንቀመጥ የምንወክለው የኢትዮጵያን ህዝብ እንጂ የመጣንበትን ክልል ህዝብ ብቻ አይደለም፤ ይህ ከሆነማ ውክልናችን በዚያው በክልል ምክር ቤት ውስጥ ተገድቦ መቅረት ነበረበት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሚቋቋመው የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሾሙ መሆኑንና ኮሚሽኑ በብዙ ክልሎች በስፋት እየታዩ የመጡትን ግጭቶች ለመፍታት የችግሮችን ምንጭ የመለየትና የማጥናት እንዲሁም ለሠላም መስፈን የሚያግዙ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማቅረብ ይሰራሉ ተብሏል፡፡  



Read 9310 times