Saturday, 22 December 2018 09:23

ኤችአይቪን በሚመለከት ሁሉም ጤንነቱን ይወቅ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)


    <Know Your Status> የዘንድሮው ማለትም የሰላሳኛው የአለም ኤይድስ ቀን መሪ ቃል ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጠር ህዳር 22/2011/ በውጭው አቆጣጣር ደግሞ ዲሴምበር 1/2018 አለምአቀፉ የኢችአይቪ ቀን ዘንድሮ ለ30/ኛ ጊዜ በተለያየ መንገድ ታስቦ ውሎአል። UNAIDS እንደዘገበው በአለማችን ከ9.4/ሚሊዮን በላይ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለ ሰዎች እስከዛሬ ያሉበትን ሁኔታ አያውቁም፡፡    
በውጭው አቆጣጠር ከ1988 ጀምሮ ኤችአይቪ ኤይድስን በሚመለከት የተለያዩ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በጅምሩ ላይ የነበረውን ሰቆቃ ለማስቀረትም ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የነበረውን ሞት ለመቀነስ የተቻለበት ሁኔታ አለ፡፡ በመሆኑም ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በአለም ላይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ቢኖርም በጤንነት ሕይወታቸውን የሚመሩበት እድል አግኝተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በሕክምና ባለሙያዎች የምክር አገልግሎትና በሚሰጣቸው ሕክምና ላይ በመን ተራስ ቤተሰብ መስርተው ማንኛውም ሰው የሚመራውን ሕይወት በጤናማነት መምራት መቻላቸው በአለም ላይ በተሰሩ የተለያዩ ስራዎችና በተደረገ ጥረት መሆኑ እሙን ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ በአለም ላይ ዛሬም ገና ብዙ መሰራት አለበት የሚያሰኝ እውነታ እየታየ ነው፡፡ እንደ UNAIDS ሪፖርት በተለይም ሰዎች የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ይኑር አይኑር ለማወቅ ጥረት አለማድረጋቸው እና ከአወቁም በሁዋላ የሚያ ሳዩት ቸልተኝነት ትልቁ ችግር ነው፡፡ እራስን ለኤችአይቪ ምርመራ አዘጋጅቶ ቫይረሱ በደም ውስጥ መኖር አለመኖሩን አስቀድሞ ማወቅ ካወቁም በሁዋላ ተገቢውን ማድረግ በአለም ላይ የሚታቀዱ የልማት ግቦች እንዲሳኩ አጋዥ እንደሚሆን እና በቫይረሱ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ በመከላከል ሌሎችንም የቤተሰብ አባላት መከላከል እንደሚቻል UNAIDS ያስረዳል፡፡
ዛሬም አሳሳቢው አድሎ እና መገለል ሰዎች እራሳቸውን ለማወቅ ጥረት እንዳያደርጉ እንደሚያደርግ UNAIDS ያምናል፡፡ ሰዎች በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን እውቀት የማጎልበትና እራሳቸው እንዲያውቁ የማድረግ ጥረት የሳሳ መሆኑን እና ሰዎች ስለ ጤንነታቸው ምርመራ የሚያደርጉት ሲታመሙ ወይንም በአንድ ምክንያት የጤና ምርመራ ውጤታቸው ሲፈለግ መሆኑ በአለም እየታየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቫይረሱ መኖሩ በታወቀበት ጊዜ ማለትም ከ30/ አመታት በፊት የነበረ ልምድ ነው፡፡ ይህ ልምድ ቫይረሱን በሚመለከት ለሚሰሩ ስራዎች ውጤት እንዳይኖር ማድረግ እና ለሕክምናውም ይሁን ለመከላከሉ ተግባር እውክታን መፍጠሩ አልቀረም፡፡
በወደፊቱ አሰራር በአለም ላይ ያሉ ሰዎች ብዙ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ለእራስ ከመመርመር ጀምሮ ሕብረተሰብ ቤተሰብን እንዲሁም ህብረተሰቡን ለፕሮግራሙ ዝግጁ ማድረግ እና የኤችአይቪ ቫይረስ በደም ውስጥ መኖር አለመኖሩን አስቀድሞ ማወቅ እንዲሁም ለህክም ናው እና ለምክር አገልግሎቱ ዝግጁ መሆን የሁሉም ኃላፊነት ነው ብሎአል UNAIDS.
የአለም የጤና ድርጅት እንዳወጣው መረጃ እስከ 2016/መጨረሻ ድረስ በአለም ላይ ከ70/ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኤችአይቪ ኤይድስ ቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 35/ ሚሊዮን የሚሆኑት በኤችአይቪ ኤይድስና ተያያዥ ምክንያቶች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ወደ /36.7/ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይህም በአለም ላይ አስከፊው ገጽታ ነው፡፡
በኢትዮጵያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ወደ 1.18%ማለትም /718.550/ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን ይህ ደግሞ በአገሪቱ ኤችአይቪ አሁንም ክትትል የሚያስፈልገው የጤና ሁኔታ መሆኑን ይጠቁማል።
በኢትዮጵያ የተሰራው Demographic Health Survey (DHS)  እንደሚያሳየው በቅኝቱ ከተካተቱት ወደ 56% የሚሆኑ ሴቶች እና 55 % የሚሆኑ ወንዶች ስለ ኤችአይቪ ምንም አይነት ምርመራ አድርገው እንደማያውቁ የሚያሳይ ሲሆን ምናልባትም መላው ህዝብ ተመርምሮ እራሱን ቢያውቅ ቫይረሱ በደማቸው አለ የሚባሉት ሰዎች ቁጥር ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ይሆናል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ምርመራ አድርገው ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው መኖሩን ካወቁት ውስጥ 72% የሚሆኑት ለጤንነታቸው ማድረግ የሚገባ ቸውን በባለሙያዎች የምክር እገዛ እና ሕክምና የቀጠሉ ሲሆን ወደ 28% የሚሆኑት ግን ቫይረሱ በደማቸው መኖሩ ከተነገራቸው በሁዋላም ችላ ያሉ መሆናቸው ታውቆአል፡፡
በነአለም አቀፍ ደረጃ በ2020/ እንደውጭው አቆጣጠር ኤችአይቪ ኤይድስ ስርጭቱ በቁጥጥር ስር እንዲውል የአለም ሀገራት በተስማሙት መሰረት ኢትዮጵያም የእራስዋን የድርጊት መርሀ ግብር ቀርጻ በእንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡
በኢትዮጵያ ኤፕሪል 21/2017 ይፋ የሆነው አገር አቀፍ ፕላን እንዳወጣው መረጃ በአሁኑ ወቅት ኤችአይቪ በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሆነ ትኩረት ያለው… ስርጭቱም ከቦታ ቦታ በተለያየ ደረጃ ያልተቋረጥ ወይንም ዝቅተኛ የማይባል እና እራስን ከቫይረሱ የመከላከል ሁኔታ ውም የተዘናጋ ይመስላል፡፡ PEPFAR የተሰኘው ድርጅት እንደውጭው አቆጣጠር በ2017/ ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ በ2016/ የነበረው መረጃ እንደሚያሳየው በቫይረሱ የተያዙ ትላልቅ ሰዎች 1.1/% ሲሆኑ ይህም በመስተዳድሮች ተለይቶ ሲታይ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
(ጋምቤላ 6.6%፤ በአዲስ አበባ 5.0%፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች 0.7%)
የኤችአይቪ ስርጭት በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማም ልዩነት አለው፡፡ ለምሳሌም (5.1%) የሚሆኑት በትላልቅ ከተሞች የሚገኙ ሲሆን ወደ 3.1% የሚሆኑት ደግሞ በትናንሽ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ 0.6 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በገጠር አካባቢ በተለይም ለዋና መንገዶች ወይንም የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ለሚያርፉ ለሚነሱባቸው ቦታዎች ቅርብ በሆኑ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ለዋና መንገድ እስከ 5/ኪሎ ሜትር ቅርብ የሆኑ የገጠር ነዋሪዎች በርቀት ከሚገኙት ይልቅ 4/ጊዜ እጥፍ ወይንም ይበልጥ ለኤችአይቪ ቫይረስ ተጋላጭ ናቸው፡፡  ሌላው በኢትዮጵያ ለኤችአይቪ ቫይረስ ስርጭት እንደምክንያት የሚቆጠመ  ረው የእናቶች የእርግ ዝና ክትትል በትክክለኛው ጊዜ አለመጀመር ወይንም በሕክምናው ባለሙያዎች የሚነገረውን መመሪያ በትክክል እና በአፋጣኝ አለመተግበር እንዲሁም ጭርሱንም ክትትል አለማድረግን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ድርጊት በተለይም ከ2005/እንደውጭው አቆጣጠር በፊት በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ወደ 60% ይደርሱ የነበረ ሲሆን በምእተ አመቱ የኤችአይቪ ኤይድስ እንቅስቃሴ ግን ውጤታማ የሆነ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሎአል፡፡
በኤችአይቪ ቫይረስ የሚያዙ አዲስ ሰዎች ምክንያታቸው ምን ሊሆን ይችላል?
በቅድሚያ ለቫይረሱ የመጋለጥ ምክንያቶች ተብለው ከሚወሰዱት ውስጥ ሁለት አይነት የወሲብ ግንኙነቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ይኼውም አንዱ ጋብቻ ከመፈጸም በፊት ኃላፊነት በጎደለው መልኩ እና እራስን ከመከላከል ውጭ የሚደረግ የወሲብ ግንኙነት ሲሆን ሌላው ደግሞ ጋብቻ ከፈጸሙም በሁዋላ በአንድ ከመወሰን ይልቅ ከሌሎችም ጋር ልቅ የወሲብ ግንኙነት በመፈጸም ምክንያት የሚተላለፍበት መንገድ ነው፡፡
ተጋቢዎች የሕክምና ምርመራ ውጤታቸው የተለያየ ወይንም አንዱ ቫይረሱ በደም ውስጥ ሲገኝ ሌላው ነጻ የመሆኑ ነገር ወደ 65% የሚደርስ ሲሆን  የቫይረሱ ስርጭት በአብዛኛው ጋብቻ በፈጸሙት ዘንድ የሚታይ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ጋብቻቸው በፍቺ ወይንም በሞት የተቋረጠ ወንዶችና ሴቶች በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው ከሌሎች ከፍ ብሎ ይታያል፡፡
የልጅነት ጋብቻ፤ የትዳር ጉዋደኛ ጥቃት ማድረስ፤ የጾታ እኩልነት አለመኖር የመሳሰሉትም ፍቺን ለመፈጸም ከፍተኛ ምክንያት ተብለው የሚወሰዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ኤችአይቪን ከመከ ላከል አንጻር ተዘጋጅቶ እንደውጭው አቆጣጠር በ2017/ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ የጋብቻ ፍቺ በቫይረሱ ለመያዝ እንደ አንድ ምክንያት የሚወሰድ ነው፡፡

Read 2201 times