Sunday, 23 December 2018 00:00

በቻይና ሁዋዌ ሞባይል የሚጠቀሙ እየተሸለሙ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ የፋይናንስ ዘርፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዋንዙ ሜንግ በቅርቡ በአሜሪካ መንግስት ግፊት በካናዳ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተቃወሙና ቻይናውያን ለአገራቸው ምርት ቅድሚያ እንዲሰጡ ለማበረታታት በማሰብ፣ የተለያዩ የአገሪቱ ኩባንያዎች ለሁዋዌ ሞባይል ተጠቃሚዎች ሽልማት እየሰጡ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከቻይና ስመጥር የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ሼኖንግ ማውንቴን ሲኒክ ፓርክ፤ የሁዋዌ ሞባይል ለሚጠቀሙ ጎብኝዎቹ 9.4 ዶላር የሚያወጣውን የመግቢያ ትኬት እየሸለመ እንደሆነ ያስታወቀ ሲሆን በቤጂንግ የሚገኝ አንድ ባር በበኩሉ፤ ለባለ ሁዋዌ ሞባይል ደንበኞቹ የ20 በመቶ ቅናሽ እያደረገ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ሜንፓድ የተባለው ሌላ የቻይና የቴክኖሎጂ አምራች ኩባንያ ደግሞ ሁዋዌ ሞባይል ለሚገዙ ሰራተኞቹ የዋጋ ድጎማ እንደሚያደርግና  በአንጻሩ ደግሞ የአፕል ምርቶችን የሚገዙ ሰራተኞቹን እንደሚቀጣ መዛቱ ተነግሯል፡፡
በአለማችን ሁለተኛው ግዙፍ የስማርት ፎን አምራች ኩባንያ የሆነው የቻይናው ሁዋዌ የፋይናንስ ዋና ሃላፊ ዋንዙ ሜንግ፤ አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን የንግድ ማዕቀብ ጥሰዋል በሚል ከሳምንታት በፊት በአሜሪካ ባለስልጣናት ጥያቄ በካናዳ በቁጥጥር ስር መዋላቸውና ጉዳዩ ሁለቱን አገራት ወደ ከፋ ነገር ሊያመራቸው እንደሚችል ሲነገር መሰንበቱ ይታወሳል፡፡

Read 1435 times Last modified on Saturday, 22 December 2018 13:10