Saturday, 22 December 2018 13:11

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ስንብት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

  - 95ኛ ዓመት ልደታቸውን በአስመራ ለማክበር አቅደው ነበር
    - የዓይን ብሌናቸው በቃላቸው መሰረት ተለግሷል
        
    ከመስከረም 28 ቀን 1994 ዓ.ም እስከ መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ ይህቺን ዓለም የተሰናበቱት የዛሬ ሳምንት ነበር- አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ፤ ህይወታቸው ባለፈበት ዕለት በኢትዮ-ኤርትራ ቀጣይ የሰላም ጉዳዮች ላይ ለመምከር በሀርመኒ ሆቴል ቀጠሮ ነበራቸው፡፡ 95ኛ ዓመት ዕድሜያቸውን ለመድፈን የአስራ አራት ቀናት ዕድሜ ብቻ ሲቀራቸው ህይወታቸው ያለፈው መቶ አለቃ ግርማ፤ የልደት በዓላቸውን በሚወዷትና ሥራ በጀመሩባት የአሥመራ ከተማ ለማክበር ዕቅድ እንደነበራቸው ተነግሯል፡፡  
የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ ትውልድና ዕድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ አባታቸው የቄስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ብለው አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደሚገኙ አንድ ቄስ ዘንድ ልከዋቸው ነበረው፡፡ የታላቁ የጦር መሪ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) ረዳት የነበሩት የትንሹ ግርማ አባት፤ ወደ አልጋ ወራሽ አገልጋይነት ሲዛወሩ፣ኑሮአቸውን ከመሰረቱበት የሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ ተነስተው፣ከእነ ቤተሰቦቻቸው በጃንሜዳ አካባቢ መኖር ጀመሩ፡፡
ፕሬዚዳንት ግርማም ዘመናዊ ትምህርታቸውን ለመማር ወደ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት አቀኑ። ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲመለሱ በእጅጉ ከሚመሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል ዋንኛው በወቅቱ የአውሮፕላን ማሣረፊያ ከነበረው የጃንሜዳ አካባቢ የሚነሱ ድምፆችን መስማትና አውሮፕላኖች ሲነሱና ሲያርፉ ማየት ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ታዲያ ፕሬዚዳንቱ በእጅጉ ለሚታወቁበት የሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ መሰረት የጣለና እሳቸውም ለሙያው ጥልቅ ፍቅርና ፍላጐት እንዲያድርባቸው ያደረገ ነበር፡፡  
በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ፣ጣሊያን አገራችንን በመውረሩ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ፡፡ ለጥቂት ጊዜያትም ወደ ገጠር በመሄድ ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ቆዩ፡፡ በ1930 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በመምጣት “ዘ ስኳላ ፕሪንስፔ ፒዮሜንቴ” የተባለ የጣሊያን ት/ቤት ገቡ፡፡ በ1933 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች የሬዲዮ መገናኛ ክፍል ባልደረባ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በ1936 ዓ.ም ደግሞ ከሆለታ ገነት ጦር ት/ቤት በምክትል መቶ እልቅና ማዕረግ ተመርቀዋል፡፡
በ1938 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሲቋቋም፣ ወደ አየር ኃይል ት/ቤት በመግባት የተለያዩ አስተዳደራዊ ትምህርቶችን ተከታትለዋል፡፡ በ1940 ዓ.ም በአየር ኃይል ክፍል የአየር መቃወሚያና በረራ መቆጣጠሪያ ማዕከል ውስጥ ረዳት መምህር፣ በመቀጠልም የሲቪል አቪዬሽን ዋና ሥራ አሥኪያጅ በመሆን ከ10 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡
የመቶ አለቃ ግርማ የፖለቲካ ህይወት የጀመረውም ከዚህ በኋላ ነበር፡፡ በ1953 ዓ.ም በተደረገው የፓርላማ ምርጫ፣ በ36 ዓመት ዕድሜያቸው በህዝብ ተመርጠው ፓርላማ ገቡ፡፡
የንጉሱ ዘመን አልፎ ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣም፣ ፕሬዚዳንት ግርማ ከፖለቲካም ሆነ ከስልጣንና ከኃላፊነት አልተለዩም፡፡ ደርግ የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባቋቋመው ሸንጎ ውስጥ የአማካሪ ሸንጐው አባል አደረጋቸው። በመቀጠልም፤ የኤርትራ የሰላም ኮሚሽነር ሆነው እንዲሰሩ በደርግ መንግስት ተሹመው ወደ ኤርትራ ተላኩ፡፡ ለ21 ዓመታትም በኤርትራ ምድር ተልዕኮአቸውን ሲፈፅሙ ቆዩ፡፡
በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት ስልጣን ሲለቅና የኢህአዴግ መንግስት አገሪቱን ሲቆጣጠር፣ ኤርትራም ከኢትዮጵያ የመገንጠሏ ጉዳይ እውን ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት ግርማ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ አገራቸው ከገቡ በኋላም ለፓርላማ አባልነት ምርጫ፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በግል እጩ ተወዳዳሪነት ቀረቡ፡፡ ውድድሩ ቀላል አልነበረምና ተሸነፉ፡፡ ተስፋ ግን አልቆረጡም፡፡ ይልቁኑም የተሻለ ሃሳብና መንገድን እንዲፈልጉ አበረታቸው እንጂ፡፡ በድጋሚ ምርጫ ሲመጣ ጠብቀው፣ ወደ ቱሉቦሎ በመሄድ፣ በግል እጩ ተወዳዳሪነት ተመዘገቡና ለውድድር ቀረቡ፡፡ አሁን ተሳካላቸው፤ 57ሺ ድምፅ አግኝተው ፓርላማ ገቡ፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር መቶ አለቃ ግርማ፤ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በአንድ ወቅት ባደረግሁት ቃለ ምልልስ፤ ይህ የፕሬዚዳንትነት ምርጫ ከእሳቸው እውቅና ውጪ የተደረገ ቢሆንም፣ “ቦታውን ካገኘሁ በኋላ ግን ወድጄዋለሁ፤ የሚጠላ ቦታ አይደለም” ሲሉ አጫውተውኝ ነበር፡፡ በፕሬዚዳንትነትም ከመስከረም 28 ቀን 1994 ዓ.ም እስከ መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ዙሮች ማለትም ለ12 ዓመታት ያህል አገልግለዋል። ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ጋር በነበረኝ ቆይታ፤ “ለመሆኑ የቤተ መንግስት ህይወትዎ ምን ይመስል ነበር? የፈቀዱትን እንዲያደርጉ፣ የፈለጉትን እንዲናገሩ ይፈቀድልዎ ነበር?” የሚል ጥያቄ አቅርቤላቸው ነበር፡፡
የቤተመንግስት ህይወታቸው የተመቻቸ እንደነበር የገለፁልኝ የቀድሞው ፕሬዚዳንት፤ የፈለጉትን ከመነጋገርና ከማድረግ የሚከለክላቸው እንደሌለም አውግተውኛል፡፡ በወቅቱ እሳቸውን ከመንግስት ባለስልጣናቱ ጋር የሚያጋጫቸው ጉዳይ “ቤተ መንግስቱን የማንም መጫወቻ አደረግከው፤ ማንም እንደ ልቡ መውጣትና መግባት እንዲችል አደረከው” የሚል እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ “እኔ ለምን እደበቃለሁ፤ አልሰረቅኩ አልገደልኩ፤ ሊጠይቀኝ የሚመጣ ሁሉ እንደል ቡ ገብቶ ሊጠይቀኝ ይችላል” ባይ ነበሩ - የቀድሞው ፕሬዚዳንት፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ለባለስልጣናቱ አልተመቻቸውም፡፡ “አደብ ግዛ” ብለዋቸዋል - በተደጋጋሚ፡፡
መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ ለ12 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ፣ ደሞዛቸው ምን ያህል እንደ ነበር ጠይቄአቸው፤ “ደመወዝ አልነበረኝም፡፡ ዝም ብለው ለኪስ ገንዘብ እያሉ 10ሺ ብር በየወሩ ይሰጡኝ ነበር” ብለዋል፡፡ ከሳቸው በፊት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ደሞዝ 5ሺ ብር እንደነበር ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡   
የቀድሞው ፕሬዚዳንት በስልጣን ዘመናቸው አንድም የሞት ፍርድ እንዳላፀደቁ ይናገራሉ። ይልቁንም ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩትን 23 ሰዎች ጉዳይ በመያዝ፣ ጉዳያቸው በሰላም እንዲፈታ በማድረግ፣ ከሞት ፍርድ ነፃ እንዳደረጓቸው ገልጸውልኛል፡፡
መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ ከመንግስት ሥራ ውጪ በተለያዩ አገር አቀፍና አለም አቀፍ ድርጅቶችም ውስጥ በሃላፊነት ደረጃ ሰርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ንግድ ልዑክ ወኪል፣ የጊቤ እርሻ ልማት መስራችና ዳይሬክተር፣ የከፋ ቲምበር ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ መስራችና ዳይሬክተር፣ የቲ-ሻየር ሆም የቦርድ ፕሬዚዳንት፣ የሌፕረሲ መቆጣጠሪያ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቦርድ ዳይሬክተርና በዚሁ መ/ቤት በዓለም አቀፍ ሎጀስቲክ ዲፓርትመንት የበላይ ጠባቂ እንዲሁም የ“ለም ኢትዮጵያ” የቦርድ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡
አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ ጣሊያንኛና ትግርኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚናገሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ የካበተ የንባብ ልምድ የነበራቸው ሲሆን ደራሲና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር መስራችም ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው የኢፌድሪ ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዱ፤ “ቤተ መፃህፍት ነበሩ” ሲሉ የገለጿቸው- ባለፈው ረቡዕ በአስከሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት በተለያዩ የበጐ አድራጎት ተግባራት ላይም በግንባር ቀደምትነት ተሳታፊ ነበሩ። የኢትዮጵያ የዓይን ብሌን ባንክ መስራች እንደነበሩ የሚነገርላቸው መቶ አለቃ ግርማ፤ አርአያ ለመሆንም የዓይናቸውን ብሌን ለመለገስ ቃል የገቡ የመጀመሪያው ሰው እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በዚሁ መሰረትም ፕሬዚዳንቱ ህይወታቸው ባለፈበት ወቅት የዓይን ብሌን ባንክ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፤ አስከሬናቸው ባረፈበት ቦታ ተገኝተው፣ የዓይን ብሌናቸውን ተረክበዋል፡፡
የእኚህ አገራቸውን ወዳድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ የቀብር ስነስርዓት ባለፈው ረቡዕ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በፀባዎተ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዱ፣ የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፣ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነዳሶ ጊዳዳ፣ በቅርቡ ከሥልጣናቸው በፈቃዳቸው የለቀቁት አሁን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመና ሌሎች ባለስልጣናት፣ እንዲሁም ዲፕሎማቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶች ተገኝተው ነበር፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ይመኛል፡፡ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርላቸው!    

Read 766 times