Saturday, 22 December 2018 13:10

“የህዝብ ትግል ከማይቀለበስበት ደረጃ ደርሷል” ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  • አንድ የውጭ ሚዲያ፣ ሪፎርሙን የሚያጥላላ ዘገባ እንዲሠራ የ200 ሺ ዶላር ክፍያ ቀርቦለት ነበር
   • እርስበርስ ለመጠፋፋት መነሳታችን ለኦሮሞ ህዝብ አይጠቅምም - ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ
   • ለአለም ጭምር አዲስ የሆነ ርዕዮተ አለም ለማስተዋወቅ ዝግጅቱ ተጠናቋል ተባለ
     
    የህዝብ ትግል ከማይለቀስበት ደረጃ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሣ፤ ”የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከየት ወዴት” በሚል ርዕስ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደ ስብሰባ ላይ አስታወቁ፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ ከመላ ኦሮሚያ የተለያዩ ወረዳዎችና ዞኖች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ምሁራን የተሳተፉበት ሲሆን ከተሣታፊዎች በየቦታው ጥቃት ያለመቆሙ፣ የዜጐች መፈናቀልና የመንግስት የህግ የበላይነትን ያለማስከበር ጉዳይ በስፋት ተነስተዋል፡፡
ለጥያቄዎቹ ማብራሪያና ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትሩ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት፤ የለውጡ ጉዞ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም አሁንም የመላውን ህዝብ ድጋፍ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ በቤኒሻንጉልና በምዕራብ ወለጋ አዋሣኝ የተፈጠረውን ግጭት በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት ለማ መገርሣ፤ በአካባቢው ህግን ለማስከበር የተደረገውን እልህ አስጨራሽ ትግል አብራርተዋል፡፡  
“በቤኒሻንጉልና በምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ የተፈጠረው ችግር፣ በደምቢዶሎ 30 የመንግስት አመራሮች የተገደሉበት፣ 1ሺህ የክልሉ ሚሊሻ አባላት በታጠቁ ሃይሎች መሣሪያ በሃይል እንዲፈቱ የተደረጉበት ነው ያሉት አቶ ለማ፤ ይሄን መንግስት በትዕግስት የተመለከተው በአካባቢው የበለጠ እልቂት እንዳይፈጠር በማሰብ እንጂ እርምጃ መውሰድ አቅቶት አይደለም ብለዋል፡፡ አሁንም አካባቢው አለመረጋጋቱንና ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ትዕግስት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡  
ግጭቱ በተፈጠረ ወቅት መንግስት ሰላማዊውን ህዝብ አልታደገም በሚል ለቀረበው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፤ ”ወደ ቤኒሻንጉል የሚያልፈው መንገድ ሙሉ ለሙሉ በመዘጋቱ፣ መንግስት ሊፈጠር የሚችለውን እልቂት በማሰብ፣ በዶ/ር ዐቢይ ውሣኔ፣ በሌሊት ወታደሮችን በአንቶኖቭ አውሮፕላን በማጓጓዝ፣ ህዝቡን ከጥቃት መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡   
በሌሎች ግጭቶች ለተፈናቀሉ ዜጐችም የክልሉና የፌደራል መንግስት ያለውን እርዳታና ድጋፍ ያለመቆጠብ እያቀረበ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ለማ፤ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሱ ዜጐችን በተለያዩ ከተሞች እንዲሰፍሩ መደረጉን አውስተዋል፡፡
አሁንም በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ያለው ችግር አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ጉዳይ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ተመካክረው መልካም አቅጣጫ ማስያዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል - ፕሬዚዳንቱ። “ችግራችንን በትዕግስትና በውይይት መጨረስ አለብን።” ሲሉም መክረዋል፡፡
“የፖለቲካ ሃይሎች ትናንት ቃል የተገባባነውን ጉዳይ መዘንጋት የለብንም፤ እርስ በእርሳችን ለመጠፋፋት መነሳታችን ለኦሮሞ ህዝብ አይጠቅምም” ያሉት አቶ ለማ፤ የሀገር ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብተው ለዚህ ጉዳይ  የመፍትሔ አካል እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ምንድን ነው ዛሬ እርስ በእርስ የሚያዋጋን?” ሲሉ የጠየቁት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት  ፕሬዚዳንት፤ ”ይሄን በውይይት መመለስ አለብን” ብለዋል፡፡
“ከዚህ በኋላ የኦሮሞ ህዝብ ችግር በጦር ይፈታል የሚል እምነት የለንም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “የኛ ትግል የሚመራው በጽናትና በቁርጠኝነት ነው፤ ምንም መሣሪያ ተኩሰን አይደለም ወደ ለውጥ የመጣነው” ብለዋል፡፡ በእውቀት የተመራ ትግል አድርገን ነው እዚህ የደረስነው ሲሉም አክለዋል፡፡ “ነገም የጽናት፣ የእውቀት ትግል ብቻ ነው ውጤታማ የሚያደርገን” ሲሉ ለስብሰባው ታዳሚዎች አስገንዝበዋል፡፡
“አሁንም እኛ ህዝባችንን ተስፋ አድርገን ነው ከለውጥ አደናቃፊ ሃይሎች ጋር የምንጋፈጠው እንጂ የጦር ሃይል ይዘን አይደለም” ሲሉም፤ የለውጥ ሃይሎች በጋራ እንዲቀናጁና ከእርስበርስ መጠላለፍ ወጥተው፣ ለውጡን ወደፊት በጽናት እንዲያስቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
አሁንም ለውጡን ማን አመጣው በሚለው ላይ ንትርክ ውስጥ መገባቱን ያነሱት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ “ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ፤ አይ እሱ ነው ከሚለው ውዝግብ መውጣት አለብን፤ ድሉ የህዝብ ነው፤ ድሉን ማንም ከህዝቡ ወደ ራሱ ሊጐትት አይገባም፤ በዚህ ጉዳይ ተማምነን ስንጓዝ ብቻ ነው ከምንፈልገው ግብ መድረስ የምንችለው” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ለውጡ ከላይ እንጂ ከስር አልደረሰም ተብለው ለተጠየቁት ጠ/ሚኒስትሩ ሲመልሱ፤ ”ለውጡ አሁን ወደ ስር እየደረሰ ነው፤ ለውጡን የበለጠ የማጥለቅ ስራም እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡
የሀገሪቱን እያንዳንዱን ችግር በጥናት እየተፈተሹ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዐቢይ፤ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ስጋት ዳርጓት የነበረው የቻይና የብድር እዳ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር እልህ አስጨራሽ ውይይት በማድረግ፣ የብድር መመለሻ ጊዜው የተራዘመ እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል። “ለአዲስ አበባ ጅቡቲ ባቡር ፕሮጀክት ሀገሪቱ ከቻይና የተበደረችውን ብድር፣ በየአመቱ 400 ሚሊዮን ዶላር፣ በ10 አመት እንድትከፍል ተደርጐ የነበረውን ስምምነት በማስቀየር፣ አሁን በ33 አመት ጊዜ ውስጥ የእዳ ክፍያው እንዲጠናቀቅ፣ በየአመቱ ይከፈል የነበረው 400 ሚሊዮን ዶላር፣ ወደ 98 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ እንዲል አስችለናል” ብለዋል - ይሄ ትልቅ ለውጥ መሆኑን በመጠቆም፡፡  
“ብዙ ችግሮችን በእውቀትና ጽናትን በሚጠይቅ ትግል እየተሻገርን ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ”ከዚህ በኋላ አንድም እንቅፋት ለውጡን አያደናቅፍም፤ በጽናት ታግለን እንደምንሻገር በሙሉ የልብ መተማመን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡
የተለያዩ አደናቃፊ ሁኔታዎች ቢኖሩም የህዝብ ትግል በጽናት መሻገሩ አይቀርም፤ በማለትም ለለውጥ የሚደረገውን ትግል፣ ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብጽ የፈርኦን ባርነት ነፃ ያወጣበትን መንገድ በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡
ሙሴ ፈርኦንን “ህዝቤን ልቀቅ” ብሎ ጠይቆ፣ በመጨረሻም ፈርኦን ህዝቡን ለቆ፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ወታደሮቹን ልኮ፣ ከኋላ ሊያጠቃቸው የተከተላቸው ፈርኦን፣ የደረሰበትን ኪሣራ ያስረዱት ጠ/ሚኒስትሩ ”እኛም ጥያቄያችን ህዝባችንን ልቀቁ ነው፤ አይ አንለቅም የሚሉ ከሆነ የፈርኦን ወታደሮች እጣ ፈንታ ነው የሚደርሳቸው፤ የሚቀበሩበትን ጉድጓድ ነው የሚቆፍሩት” ብለዋል፡፡
ከመሬቱ የሚፈናቀለውን አርሶአደር ተጠቃሚ ለማድረግ ምን ታስቧል በሚል ለቀረበው ጥያቄም ጠ/ሚኒስትሩ ሲመልሱ፤ ”ከእንግዲህ ከቀዬው የሚፈናቀል አርሶ አደር አይኖርም፤ መሬቱ ለኢንቨስትመንት ሲፈለግ ቦታውን የፈለገው ባለሀብት ለገበሬው የ2 በመቶ ይሁን፣ የ5 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው የማድረግ ግዴታ ውስጥ ይገባል” ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ አምቦን በተለየ ሁኔታ አንስተዋል፡፡ “አምቦ ለኔ ኒው ዮርክ ነች፤ ኒው ዮርክ ላይ የነፃነት ሃውልት (Statue liberty) ቆሟል፤ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ሃውልት አምቦ ውስጥ ነው ያለው” ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ያለውን ለውጥ ጥላሸት ለመቀባትና “የሀሰት ነው፣ ለውጥ የለም” እንዲባል፣ ትላልቅ ሚዲያዎችን እንደ መሣሪያ ለመጠቀም ጥረት መደረጉን የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አንድ ታዋቂ የውጭ ሚዲያ ሪፎርሙን የሚያጥላላ ዘገባ እንዲሠራ የ200 ሺህ ዶላር ክፍያ ቀርቦለት አልቀበልም ብሎ መመለሱን የሚዲያው አመራሮች ነግረውኛል” ብለዋል፡፡
እነዚህ ሃይሎች ሁሉንም የማደናቀፊያ መንገዶች እየተጠቀሙ ነው ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ከሁለትና ሶስት ወር በኋላ ኦሮሚያ ውስጥ ህዝቡን በሃይማኖት ከፋፍሎ ለማጫረስ ውጥን መያዙን፣ ለዚህም ገንዘብ ተዘጋጅቶ ሰዎች እየተመለመሉ መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል፡፡ ህዝቡ ይሄን አውቆ አንድነቱን በዚህ ሊንዱ ከሚፈልጉ ሃይሎች ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በመጨረሻም ከውይይት አጀንዳው ወጣ ብለው፣ የፖለቲካ ርዕዮት አለምን በተመለከተ አስገራሚ ጉዳይ ለውይይቱ ተሳታፊ አጋርተዋል፡፡    
በ1971 እና 72 ዓ.ም ደርግ፤ ዛሬ ኢህአዴግ የሚመራበትን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ አለም እያዘጋጀ እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎች ከሰነዶች ላይ መመልከታቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ዐቢይ፤ ጅማ ላይ በተደረገው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጉባኤ ቃል በተገባው መሠረት፣ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለአለምም ጭምር አዲስ የሆነ ርዕዮተ አለም ለማስተዋወቅ ዝግጅት መጠናቀቁን ይፋ አድርገዋል፡፡ ሁሉም በጉጉት የሚጠብቀው ነው፡፡  

Read 1506 times